| “ጦርነት የሚፈጠረው ተቃዋሚዎች... |
|
|
| Sunday, 11 May 2008 | |
![]() አቶ ኅሩይ ተድላ አቶ ኅሩይ ተድላ ባይሩ የኤርትራ ፓርቲ ኮንግረስ ሊቀመንበር በየማነ ናግሽ አቶ ኅሩይ ተድላ ባይሩ ይባላሉ፡፡ አባታቸው በኢትዮጵያና ኤርትራ ፌዴሬሽን ወቅት በመጀመርያው የኤርትራ ፕሬዚዳንት ነበሩ፡፡ አቶ ኅሩይ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል፡፡ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ኤም.ኤ ባስቶክሆልም ዩኒቨርሲቲ ሰርተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የዶክትሬት ዲግሪያቸውን እየሰሩ ነው፡፡ መቀመጫቸውን ስቶክሆልም /ሲዊድን አድርገዋል፡፡ አቶ ኅሩይ ሰባት ቋንቋዎች ትግርኛ፣ አማርኛ፣ ግዕዝ፣ ዓረብኛ፣ እንግሊዝኛ፣ ጣሊያንኛና ፈረንሳይኛ ይናገራሉ፡፡ የኤርትራ የ11 ተቃዋሚ ፓርቲዎች እናት ድርጅት የሆነው የኤርትራ ዴሞክራሲያዊ ኪዳን ጥምር ፓርቲ ጉባኤ በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ አቶ ኅሩይ ደግሞ ፓርቲያቸውን (ኤርትራን ፓርቲ ኮንግሬስ - ሰልፊ ጉባኤ ኤርትራ) ወክለው በታዛቢነት እየተሳተፉ ነው፡፡ በዚህና በኤርትራ ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ አነጋግረናቸዋል፡፡ ሪፖርተር፡- የሕይወት ታሪከዎን ባጭሩ ቢነግሩኝ? አቶ ህሩይ፡- የታጋይ ታሪክ ነው ያለኝ፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ በነበርኩበት “ማህበር ሸውዓተ” የኤርትራ ነፃነት ንቅናቄ (ELM) የሚባል የኤርትራ ተማሪዎች ኮሚቴ ሊቀመንበር ነበርኩ፡፡ እንዲሁም የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ (ESM) መስራቾች አንዱ ነበርኩ፡፡ በ1966/67 አውሮፓ ለከፍተኛ ትምህርት በሄድኩ ጊዜ የማህበሩ ሊቀመንበር ሆኜ አገልግያለሁ፡፡ ከኔ በኋላ ደግሞ ኃይሌ ፊዳ ነበር የመራው፡፡ ሪፖርተር፡- የአባትዎ የወቅቱ የፖለቲካ አመለካከት ምን ይመስላል? አቶ ህሩይ፡- አባቴ የማህበር አንድነት ዋና ፀሐፊ ነበር፡፡ የማህበር አንድነት ፕሮግራም “አንዲት ኢትዮጵያ ወይም ሞት” የሚል አላማ ይዞ ነበር የሚንቀሳቀሰው፡፡ ነገር ግን እንደታሰበው ባይቀናም ኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ በፌዴሬሽን ስትቀላቀል የኤርትራ የፖርላማ ሊቀመንበር ነበር፣ ቀጥሎም የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት ሆኖ ተመረጦ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ በሲዊድን የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነ ተመደበ፡፡ ንጉሰ ነገስቱ ፌዴሬሽኑን ካፈረሱት በኋላ ጉዳዩ እንደታሰበው አልተሳካም፡፡ አባቴም በ1967 ወደ ውጭ አገር ወጣና ያኔ “ሱፕሪም ካውንስል” ይባል የነበረው የጀብሃ (ELF) ምክትል ሊቀመንበር ሆነ፡፡ ብዙ አስተዋፅኦ ካደረገ በኋላ እ.ኤ.አ በ1982 ዓ.ም ዓረፈ፡፡ ሪፖርተር፡- እርስዎ ከአባትዎ ወረስኩት የሚሉት ነገር አለ? አቶ ህሩይ፡- ብዙ ሰው አፍንጫችሁ ይመሳሰላል ይለኛል፡፡ (ሳቅ) ሪፖርተር፡- የፖለቲካ አመለካከታችሁስ፣ አባትዎ አንዲት ኢትዮጵያ የሚል አቋም ነበራቸው፣ አቶ ህሩይ፡- በወቅቱ አንድነት ማለት “አንድ ንጉስ፣ አንድ ስልጣን” ማለት ነበር፡፡ ኤርትራ እንደሚታወቀው በቅኝ ግዛት ስር ስለነበረች ትንሽ በዴሞክራሲና ሌሎች የተወሰነ ዘመናዊነት ተጀምረዋል፡፡ በተቃራኒው በኢትዮጵያ ፈላጭ ቆራጭ ንጉስ ነበሩ፡፡ አሁን ግን የአንድነት ትርጉሙ ተቀይሯል፡፡ የአንድነት ትርጉም የአብሮ መኖርና የጥቅም ዝምድናን የማጠንከር ነው፡፡ በዚህ በአዲሱ የአንድነት ትርጉም እየተረዳዳን መኖሩ የጊዜው ጥያቄ ነው፡፡ መልስ ማግኘት አለበት፡፡ እንግዲህ በአባቴ ዘመን የነበረ የአንድነት ስሜት በአሁኑ ዘመን ሊኖር ከሚችለው የአንድነት ትርጉም አንፃር የሚታይ ይሆናል፡፡ ሪፖርተር፡- ነፃነትስ ለእርስዎ ምንድን ነው? ከኤርትራ አንፃር? አቶ ህሩይ፡- ኤርትራ ውስጥ አሁን ነፃነት የሚባል ነገር የለም፡፡ ኤርትራ ውስጥ ነፃነት ሳይሆን ባርነትና አምባገነንነት ነው ያለው፡፡ ሰላም የለም፡፡ የጦርነት መንፈስ ብቻ ነው ያለው፡፡ ሰላም ከሌለ ስለነፃነት ማውራት ይከብዳል፡፡ ከአጎራባች አገሮችም መልካም ጉርብትና የለም፡፡ ጦርነቱ ከተጠናቀቀ በኋላ እንደ ደንቡ ሁለቱም የኢትዮጵያና የኤርትራ መንግሥታት ቆም ብለው ቢነጋገሩ ወደፊት ሊያገለግል የሚችል አስተሳሰብ ይመነጭ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የአስመራው ፈላጭ ቆራጭ አልቀበልም ብለዋል፡፡ ይሄ ሁሉ እንግዲህ የሚያሳየው ኤርትራ ውስጥ ነፃነት እንደሌለ ነው፡፡ የምንታገለውም ለአዲሱ ነፃነት ነው፡፡ አዲሱ ነፃነት ደግሞ በቅድሚያ ሰላም እንዲፈጠር ማድረግ፣ በተለይ ከወንድሞቻችን ኢትዮጵያውያን በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ እሱ ከሌለ ብዙ ሌላ ችግር (ውጊያ፣ ችግር፣ ሞት ወዘተ) ሊያጋጥመን ይችላል፡፡ በአፍሪካ ቀንድ ድህነት ሳይወገድ ደግሞ የተሟላ ነፃነት ሊኖር አይችልም፡፡ የነፃነት እንቅፋት ድህነት ነው፡፡ የአቶ ኢሳይያስ የጦርነት መንፈስ ካልተቀየረ፣ ተቃዋሚዎቹ አሸንፈው ስልጣን በሚይዙበት ጊዜ ከጎረቤት አገሮች ጋር በመሆን ድህነት፣ በሽታ፣ ድንቁርናን አብረን ልንዋጋ እንችላለን፡፡ ነፃነታችንም ይረጋገጣል፡፡ ሪፖርተር፡- ኤርትራ ኢትዮጵያ ውስጥ በነበረችበት ወቅት በሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች ላይ ነበር ጭቆናው፣ አቶ ህሩይ፡- አዎ ትክክል ነው”“ ሪፖርተር፡- የኤርትራ ጥያቄ ከዚህ ተለይቶ ይታያል? አቶ ህሩይ፡- ምንም የሚለይበት ነገር የለም፡፡ ስለ ሰንደቅ ዓላማ ሁሉም ሰው በአጭር ግዜ አውቆና ተቀብሎ ይህ የእኛ ነው ሊል አይችለም፡፡ ለአንዱ ኢትዮጵያዊ የገባው ሰማንያ ሚሊዮን ኢትዮጵያዊ በአንዴ ይገባቸዋል ማለት አይደለም፡፡ ለኤርትራውያኖችም እንደዚሁ፡፡ አንድነት መገንባት ሰንደቆችን ማከማቸት አይደለም፡፡ ሰንደቆቹ አገር እንዲዳብር ለማነሳሳትና ለማነቃቃት ይረዱሃል እንጂ ጥሬ ሆነው የሚበሉ አይደሉም፡፡ ሪፖርተር፡- እንዲህ ከሆነ ኢትዮጵያ ውስጥ ሆነው መብታቸውን ያስከበሩ ብሄረሰቦች አሉ፣ አዲስ አገር ከመፍጠር የተገኘው የተለየ ጥቅም ምንድነው? አቶ ህሩይ፡- እንዲህ ዓይነት ክርክርና አስተሳሰብ ሁላችንንም ሊያስማማ ወደሚችል እንደምታ አያደርስም፡፡ እንደውም ሰክረን እስከምንወድቅ ሊያደርሰን ይችላል፡፡ አንድ ጊዜ ልጅትዋ ከተዳረችና ጎጆዋን ከመሰረተች በኋላ ባልሽን ፈትተሽ፣ ቤትሽን አፍርሰሽ ነይ እኛ ቤት ኑሪ ልንላት አንችልም፡፡ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ከግምት አስገብተን የአብሮ መኖር፣ አብሮ መበልፀግ ግንኙነቶችን ማጠናከር ይቻላል፡፡ ነፃነቱን ደግሞ ኤርትራ የእኔ ነፃነት ነው ሳትል ኢትዮጵያም የለም የኔ ነው ሳትል ለሁላችንም የሚያመች የጋራ ነፃነት በሁለቱም ሊፈጠር ይችላል፡፡ ሪፖርተር፡- የኤርትራ ተቃዋሚዎች ከጉባኤው እን”ወጡ የመከፋፈል አባዜ አላችው፣ አቶ ህሩይ፡- እስካሁን ከ1960ዎች ጀምሮ በርካታ የኤርትራ ተቃዋሚዎች ተመስርተው ተለያይተዋል፡፡ አንዳንድ አዋቂ ኤርትራውያን እንደሚሉት የመከፋፈል ፖለቲካ ኤርትራ ውስጥ የበቀለ ነው፡፡ ሪፖርተር፡- የመለያየታቸው ምሲጢር ምንድነው? አቶ ህሩይ፡- ለነፃነት በነበረው ትግል ጊዜ ሁሉም ሰው የቤቱን ልዩነቶች እንደ ሁለተኛ ደረጃ ስለሚቆጥረው የመቻቻል ሁኔታ ነበር፡፡ ከነፃነት በኋላ ግን እነዚያ ልዩነቶች ብቅ እያሉና የራሳችን የውስጣችን ጉዳይ የሃይማኖት፣ የብሄር የዴሞክራሲ ጥያቄዎች ይዞ መምጣት ጀመረ፡፡ አንዳንድ ጊዜ የመብት ጉዳይ ሌላ ጊዜ ደግሞ የስልጣን መቆናጠጫ ምክንያቶች ይሆናሉ፡፡ በኤርትራ ተቃዋሚዎች መካከል ያለውም ልዩነት ምንጩ ይሄው ነው፡፡ ሪፖርተር፡- ከዚህ በፊት ሁለት ተመሳሳይ ጉባኤዎች (በካርቱምና አዲስ አበባ) በኪዳን ስም ተካሂደዋል፡፡ አሁን ለሶስተኛ ጊዜ መሆኑ ነው፡፡ የመክፈቻ ንግግሩና የጉባኤው አጀማመር መንፈስ ምን ይመስላል? አቶ ህሩይ፡- መንፈሱ ቆንጆ ነበር፡፡ እርግጥ የማንኛውም ዓይነት ድግስ የመጀመሪያ ቀን ቆንጆ ነው፡፡ ማዕከላዊ ጥያቄዎች በሚነሱበት እንዴት እንደሚሆን አላውቅም፡፡ ረይሄ ቃለ መጠይቅ የተደረገው ባለፈው ሰኞ ነውሪ ሪፖርተር፡- ሊያወዛግቡ ይችላሉ የሚሉዋቸው መሰረታዊ ነጥቦች ምንድን ናቸው? አቶ ህሩይ፡- አንዱ “ቅዋም” (ሕገ ደንብ”፣ ሁለተኛ ደግሞ ቻርተሩ ነው፡፡ እነዚህ ጉዳዮች የተለያዩ ረቂቁ አስተሳሰቦች ሊፈጥሩ ይችላሉ፡፡ ረቂቁ ተዘጋጅቷል፤ ለውይይት ይቀርባል፡፡ ሪፖርተር፡- ይፀድቃል የሚል እምነት አለዎት? አቶ ህሩይ፡- ተቃዋሚዎቹ ይቺ ስብሰባ በድል ካልደመደሟት እየሳሳ ይሄዳል፡፡ ድሉም የአቶ ኢሳይያስ ይሆናል፡፡ ከዚያ በኋላ ደግሞ መጥፎ ጎረቤት ካለ ወደ ሌላ አቅጣጫ ሊወስድ ይችላል፡፡ ረቁቁን ከማፅደቅ ሌላ አማራጭ የለም፡፡ ሪፖርተር፡- የስደት መንግሥት የማቋቋም አጀንዳ አላችሁ ይባላል? አቶ ህሩይ፡- እሱ እንግዲህ ሁሉም ኤርትራውያን በደንብ ይወያዩበታል፡፡ በሃሳብ ደረጃ ሁሉም ይቀበሉታል፡፡ በኤርትራ ውስጥ ህጋዊነት ሕዝቡ አንድ ሆኖ ለነፃነት ስለታገለ ነው፡፡ የኢሳይያስ ስልጣን ደግሞ ሕጋዊ የሆነበት ምክንያት ድርጅቱ አሸናፊ ሆኖ አስመራ ስለገባ ነው፡፡ ያቋቋመውን ስልጣን ሌላ እስኪመጣ ድረስ ሕዝቡ ተቀብሎት ነበር፡፡ አሁን 17 ዓመቱ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ ከኢትዮጵያ ጨምሮ ከሁሉም አጎራባች አገሮች ጋር ግጭት ተፈጥሯል፡፡ ጦርነት ደግሞ ሕጋዊነትን ያፈራርሳል፡፡ ሕዝብህን ለመቀለብ ካልቻልክና ግማሹ ሕዝብ ሸሽቶ ከአገሩ ከወጣ ምን ያህል ህጋዊነት አለ፡፡ የአቶ ኢሳይያስ ህጋዊነት አልቆ በበትርና በዱላ የሚቀጥል ስልጣን ብቻ ነው ያለው፡፡ ዓመታት ለዴሞክራሲ ሲሉ የታገሉ የኤርትራ ሕዝቦች አንድ ሆነው መታገል ቢያስቸግራቸውም፣ በኤርትራ ሕዝብ ላይ የሰነዘሩት ጥቃት የለም፡፡ የስደት መንግሥት በሚፈጠርበት ጊዜ ሕጋዊነቱን ከአቶ ኢሳይያስ ይረከባሉ፡፡ የተቀረው ኤርትራ ውስጥ ያለው ሕዝብም ይህንን መንግሥት ነው የሚደግፈው፡፡ የውጭ ፖለቲካ ያየን እንደሆነ ደግሞ ለምሳሌ ጎረቤቶቻቸንና የሰንዓ ፎረም (የሱዳን፣ ኢትዮጵያና የመን) እውቅናና ድጋፍ ያደርጉለታል፡፡ እዚህ ያሉት ኤንባሲዎችም የስደት መንግሥቱን ለመደገፍ ዝግጁ መሆናቸው የታወቀ ነው፡፡ ይወዱታልም፡፡ ይህ ከሆነ በቀጥታ እንደ መንግሥት እንኳ ባይደግፉ በተለያዩ መንገዶች መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሊረዱ ይችላሉ፡፡ ይህ ሲሆን የኤርትራ ስደተኞች ጉዳይ በቀላሉ ሊፈታ ይችላል፡፡ ድሮ ኢሳይያስን ጠልቶ ከኤርትራ ይሸሽ የነበረም ይቀላቀላል፡፡ የስደት መንግሥቱ የጦር ኃይል ስለሚኖረው፣ በተናጠል ብቻ ሳይሆን መኮንኖችም እስከነ ትጥቃቸውና ሰራዊታቸው ይመጣሉ፡፡ ትንሽ ቆይተው የስደት መንግሥቱ አካሄድ በጎ ከሆነ እዛው ይሻለናል ብለው እስከ ብርጌድ ይዘው ሊገቡ ይችላሉ፡፡ ይህ ስትራቴጂ በጣም ትልቅ ነው፡፡ ሪፖርተር፡- አካሄዱን አስባችሁበታል? አቶ ህሩይ፡- አስበን ብዙ ነገር ጽፈንበታል፡፡ ጎረቤታችን ደግሞ ሃሳቡን ቢቀበሉም ደረጃ በደረጃ እዚያ እንዲደርስ ነው የፈለጉት፡፡ ሪፖርተር፡- እናንተስ ራሳችሁ ስልጣን ብትይዙ ዴሞክራሲያውያን ስለመሆናችሁ የኤርትራ ሕዝብ በምን ይተማመናል? አቶ ህሩይ፡- ዴሞክራሲ በግንባራችን የምንነቀሰው አይደለም፡፡ ሂደት ስለሆነ ሁሉ ጊዜ ፈተና እያለፍክ የምትገነባው ነው፡፡ ስለዚህ ዴሞክራሲያውያን ካልሆንን ሕዝቡ ብዙ ፈተናዎች እያሳለፈ ዴሞክራሲያዊ እንድንሆን ሊያስገድደን ይገባል፡፡ ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ መንግሥት ድጋፍ እየተደረገላችሁ ነው፡፡ ጉባኤው በአዲስ አበባ መሆኑ በኤርትራ ሕዝብ በኩል እምነት አያሳጣችሁም? ሌላ አገር ቢሆን አይሻልም ነበር? አቶ ህሩይ፡- በኢትዮጵያ መንግሥት ሊደረግ የሚችል ድጋፍ በጥቅምና በጊዜያዊ ስሜት የተገፋፋ ሳይሆን መርህን የተከተለ እንደሚሆን ተነግሮናል፡፡ ጉባኤው እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ በመሆኑ ጥርጣሬ ሊያሳድር ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ የትግርኛ ተናጋሪዎች የሚናገሩት አንድ አባባል አለ፡፡ ፍቺው “እቃ ይዤያለሁ ብለህ ሳትተኛ አታድርም” ነው፡፡ ስለዚህ ሃሜቱን መቀበል ነው፡፡ ይህንን ተቀብለን ቁም ነገር እናሳይ፡፡ ቁም ነገሩ ነው ነፃ የሚያወጣውን፡፡ ሪፖርተር፡- በቅርቡ በተለይ ከሚስስ ጃንዳይ ፍሬዘር (በአሜሪካ ረዳት የውጭ ጉዳይ ሚ/ር) ውይይት አድርጋችሁ ነበር፡፡ የውይይታችሁ ማዕከል ሊነግሩን ይችላሉ? አቶ ህሩይ፡- የተለመደ ምክክር ነው፡፡ የቀጣናው የደህንነት ሁኔታ በተመለከተ ነው፡፡ ሊበለፅግ የሚችል ነው፡፡ በተለይ የሁሉም ነገር መፍትሄ ልትሆን የምትችል የስደት መንግሥት የማቋቋም ጉዳይ አሜሪካኖች ይወዷታል፡፡ በእርግጥ ሰውየው ቢያስቸግራቸውም ራሳቸው ያሳደጉት ነው፡፡ ሪፖርተር፡- ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ በየቀኑ የሚነዙትን ፕሮፖጋንዳ ሕዝቡ ምን ያህል ይቀበለዋል? ከተቃዋሚዎች በኩልስ ይህንን ጥላቻ ለማስቀረት ምን አስተዋፅኦ አድርገዋል? አቶ ህሩይ፡- ለጊዜው ሊሆን ይችላል፡፡ ሆኖም ኢሳይያስ የሚፈጥረውን ጥላቻ ተቃዋሚዎች እያፈረሱት ነው፡፡ ሪፖርተር፡- እንዴት? አቶ ህሩይ፡- በፕሮፖጋንዳቸውና እዚህ በመቀመጣቸው፡፡ አቋማቸውን ሳይቀይሩ ስንት ዓመት ሆኗቸዋል? ይህንን ያዩ ኤርትራ ውስጥ ያሉት ዜጎችም፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ምን አደረገን? እያሉ ወደ ኢትዮጵያ እየጎረፉ ነው፡፡ በሕዝብ ግንኙነት በተቻለ መጠን ለሁለተኛ ጊዜ ጦርነት እንዳይፈጠር እነዚህ ሰዎች ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል፡፡ ጦርነት የሚፈጠረው ተቃዋሚዎች ሲሰንፉ ብቻ ነው፡፡ ተቃዋሚዎች ሃይለኞች በሚሆኑበት ጊዜ ጎረቤቶች ወደ ውጊያ ለመሄድ አይገደዱም፡፡ ስለዚህ የተቃዋሚዎች ሁኔታ የራሱ ተጽዕኖ አለው፡፡ በቅርቡ የስደት መንግሥቱ ከተመሰረተ ከኤርትራ ወታደር አንድ አራተኛው ይመጣል፡፡ ሪፖርተር፡- የድንበሩ ጉዳይስ? አቶ ህሩይ፡- በእኔ በኩል የድንበሩ መፍትሄ እውን የሚሆነው አቶ ኢሳይያስና ጠ/ሚ መለስ ቁጭ ብለው ሲነጋገሩ ብቻ ነው፡፡ አቶ ኢሳይያስ እምቢ ማለቱ አይገባኝም፡፡ የምትሰጠው መልስ ዲፕሎማቲክ ነው፡፡ በባህላችን “ተጋጊናእንዲና፣ ሰይጣን አስሓሒቱና ሞበር” (ሰይጣን አሳስቶናል) ብለው አይደለም የሚታረቁ የትግርኛ ተናጋሪዎች፡፡ ቁጭ ብሎ መነጋገር ለምን እንደሚፈሩ አይገባኝም፡፡ በመነጋገራቸው የድንበር ክልሉን ይቀይራል ማለት አይደለም፡፡ መግባባት ብቻ ነው የሚፈጥረው፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |