| የዳቦ አምራቾች ድጎማ እንዲደረግላቸው... |
|
|
| Sunday, 11 May 2008 | |
|
የዳቦ አምራቾች ድጎማ እንዲደረግላቸው ጥያቄ ለማቅረብ ተስማሙ
በቤዛዊት ሥዩም የዳቦ አምራቾች የዱቄት ዋጋ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ በመሆኑ ዳቦን በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ ድጎማ እንዲደረግላቸው ለንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጥያቄ ሊያቀርቡ ተስማሙ፡፡ የዳቦ አምራቾች ከጥራትና ደረጃዎች ባለሥልጣን በጋር የዳቦ ደረጃን ወጥ በሆነ ሁኔታ ለማውጣትና እየጨመረ ለመጣው የዱቄት ዋጋ መፍትሄ ለመፈለግ በተቋቋመው ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ተስፋዬ በሪፖርተር ጋዜጣ እንደገለፁት፣ የስንዴ ዋጋ እየጨመረ በመምጣቱ በተመጣጣኝ ዋጋ ለሸማቹ ለማቅረብ እገዛ ያስፈልጋቸዋል፡፡ የዱቄት ዋጋ እየጨመረ በመምጣቱ ከጥራትና ደረጃዎች መዳቢ ባለሥልጣን ጋር በጋራ ባቋቋሙት ኮሚቴ ዳቦ አምራቾች በግብአትነት በሚጠቀሙበት ዱቄት ላይ የተለየ ድጎማ ወይም ዱቄትን ከአምራቾቹ በአነስተኛ ዋጋ በቀጥታ እንዲያገኙ የሚያስችላቸው ዕድል እንዲመቻችላቸው ጥያቄ እንደሚያቀርቡ ገልፀዋል፡፡ የዱቄት ዋጋ 820 ብር መድረሱን የገለፁት አቶ ተስፋዬ ዳቦ ቤቶች ያለባቸውን ወጪ በማስላት የዋጋ ማስተካከያ ማድረጋቸውን ጠቁመዋል፡፡ ባለፉት ጊዜያት 50 ግራም ዳቦ ከ30 እስከ 35 ሳንቲም ይሸጥ እንደነበር ጠቁመው አሁን ባለው ዋጋ እያንዳንዱ ዳቦ ቤት ወጪውን በማመዛዘን የራሱን የዋጋ ስሌት እንዲያወጣ መስማማታቸውን ተናግረዋል፡፡ በዚሁ መሠረትም የአንድ ዳቦ አነስተኛ መጠን 50 ግራም በማድረግ ከ50 እስከ 60 ሳንቲም በመሸጥ ላይ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ የዋጋ ቁጥጥር ለማድረግ የተቋቋመው ግብረ ኃይል ለዳቦ ግብአት የሚውሉ ምርቶችን ዋጋ ባለመረዳት 50 ግራም ዳቦ በ20 ሳንቲም ሽጡ ብሎ ያስገድድ እንደነበርና በዚህ መሠረት የተዘጉ ዳቦ ቤቶች እንደነበሩ የገለፁት አቶ ተስፋዬ ጠቁመው እያንዳንዱ ዳቦ ቤት በሚያዋጣውና ኅብረተሰቡን በማይጎዳ በኩል የሚሸጥበት ሁኔታ እንዲመቻች ጠይቀዋል፡፡ የዳቦ አምራቾች ማኅበር ለመመስረት ከተመረጡት 15 የኮሚቴ አባላት ከጥራትና ደረጃዎች መዳቢ ባለሥልጣን ጋር በጋራ በመሆን በአዲስ አበባ በሚገኙ ዳቦ ቤቶች ባደረጉት የመስክ ጥናት አብዛኛዎቹ ዳቦ ቤቶች በጥራትና ደረጃዎች አነስተኛ የዳቦ መጠን ተብሎ ከተቀመጠው 50 ግራም ያነሰ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ አብዛኛዎቹ ዳቦ ቤቶች ከ26.7 እስከ 49 ግራም ልዩነት የሚመዝን ዳቦ እንደሚያመርቱ በዳሰሳው የተገኘ ሲሆን ሁሉም ዳቦ ቤቶች ወጥ የሆነ ግራም እንዲኖራቸው ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ ያልሆኑ ደግሞ ፈቃዳቸውን ሊነጠቁ አንደሚችሉም ተገልጿል፡፡ የግብአቶች ዋጋ መቀነስ ካልታየ ወደፊት አብዛኛዎቹ ዳቦ ቤቶች ሊዘጉ እንደሚችሉ ስጋታቸውን ገልፀዋል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |