| ምክር ቤቱ ሕንፃውን ለመረከብ... |
|
|
| Sunday, 11 May 2008 | |
![]() ምክር ቤቱ ሕንፃውን ለመረከብ የሚኒስትሮች ም/ቤትን ውሣኔ እየጠበቀ ነውበዳዊት ታዬ የኢትዮጵያ ንግድ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ሜክሲኮ አደባባይ የሚገኘውንና በስሙ ተመዝግቦ የቆየውን ባለሰባት ፎቅ ሕንፃ ለመረከብ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሣኔ እየተጠበቀ መሆኑን አስታወቀ፡፡ ለንግድ ምክር ቤት ሕንፃ ግንባታ ተብሎ ከንጉሡ በተሰጠ 4000 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ በ1951 ዓ.ም የተገነባውን ሕንፃ መልሶ ለመረከብ የሚያስችል ደረጃ ላይ የተደረሰው የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሕንፃው ይመለስልን ለሚለው ለም/ቤቱ ጥያቄ ትኩረት ሰጥቶ ጥያቄውን ለሚኒስትሮች ም/ቤት ውሣኔ እንዲሰጥበት በማድረጉ መሆኑን የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ም/ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው አየነው አስረድተዋል፡፡ በደርግ ዘመን ትርፍ ቤትና ትርፍ ቦታን ለመውረስ በወጣው አዋጅ ቁጥር 148/70 መሠረት የአዲስ አበባና የኢትዮጵያ ንግድ ም/ቤት ከሚገለገሉባቸው አንደኛና ሁለተኛ ፎቅ በስተቀር ሌላው የሕንፃው አካል ተወርሷል፡፡ የሕንፃው ሕጋዊ ባለንብረት ም/ቤቱ መሆኑን በማሳወቅ ሕንፃው እንዲመለስለት ተደጋጋሚ ጥያቄ ለመንግሥት ቢያቀርብም አዎንታዊ መልስ ሳይገኝ መቅረቱ ይታወሳል፡፡ ፕሬዚዳንቱ እንዳሉት ከሆነ በአሁኑ ወቅት ሕንፃውን ለማስመለስ በአዲስ መልክ በተደረገ ጥረት ጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጠው በመደረጉ ተስፋ ሰጪ ደረጃ ላይ መደረሱንና የሚኒስትሮች ም/ቤት ውሣኔ እየተጠበቀ መሆኑ ተገልጿል፡፡ አዲሱ የም/ቤቱ አመራር የሕንፃው ባለቤት ንግድ ም/ቤቱ ስለመሆኑ የሚያረጋግጥ መረጃ አቅርቧል፡፡ የሕንፃው አለመመለስ ካስከተላቸው ችግሮች መካከል በም/ቤቱ ስር ያሉ የዘርፍ ማኅበራትና የንግድ ም/ቤቶች ቢሮ አልባ መሆናቸውና አብዛኛዎቹ በትውስትና በኪራይ እየተገለገሉ መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡ በሌላ በኩልም የአገሪቱን የንግድ ዘርፍ ለማጠናከርና ለማጐልበት ሁሉም የግሉ ዘርፍ ተወካዮች ከተበታተነ አሠራር ተላቅቀው በዚህ ሕንፃ ውስጥ ሆነው በጋራ ቢመሩ የግሉ ዘርፍ በተቀላጠፈ ሁኔታ እንዲሠራ የሚያስችል ይሆናል፡፡ ከ30 ዓመታት በላይ ከእጁ የወጣው ባለሰባት ፎቅ ሕንፃ ግንባታ ከተጠናቀቀ በኋላ የምድር ቤቱንና የመጀመሪያውን ፎቅ የአዲስ አበባ ንግድ ም/ቤት ሁለተኛውን ደግሞ የኢትዮጵያ ንግድ ም/ቤት እንዲገለገሉበት ተደርጐ ቀሪው የሕንፃው አካል እንዲከራይ ተደርጐ እንደነበር ያስታወሱት ፕሬዚዳንቱ፣ የደርግ አዋጅ ከታወጀ በኋላ ግን ሁለቱ ምክር ቤቶች የሚጠቀሙበት ሕንፃ አስቀርቶ ሌላው ትርፍ ነው በሚል ተወርሷል፡፡ ሁለቱም ንግድ ም/ቤቶች በያዙት ህንፃ ያለኪራይ እስካሁን ድረስ እየተጠቀሙበት መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በሌላ በኩልም ም/ቤቶቹ ከሚገለገሉበት ሕንፃ ውጪ ያለውና እንዲወረስ ከተደረገው አምስቱ ፎቅ ይገኝ የነበረው ኪራይ ከ1970 ዓ.ም ጀምሮ ለ18 ወራት የተወሰነ ለመንግሥት ቀሪው ደግሞ ለም/ቤት ይሰጥ የነበረ ቢሆንም ከ18 ወራት ቆይታ በኋላ ግን የኪራዩ ገቢ በሙሉ ለመንግሥት እንዲገባ መደረጉም ም/ቤቱ እንደ አንድ የገቢ ምንጭ ይጠቀምበት የነበረውን ገንዘብ እንዲያጣ ማድረጉ ተወስቷል፡፡ ይህ የም/ቤቱ ሕንፃ በወቅቱ የተገነባው በንግድ ም/ቤቱ አባላት መዋጮና በመንግሥት ፈቃድ ከውጭ ንግድ ምርቶች በቴምበር የተሰበሰበ ገንዘብ ለሕንፃው ግንባታ እንዲውል በመደረጉ ነው፡፡ በሌላ በኩል ም/ቤቱ የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ም/ቤት የአንደኛ ዓመት ምስረታ በዓልና የምክር ቤቱ የ60 ዓመት የሥራ ሂደት በአዲሱ የኢትዮጵያ የሚሌኒየም በሚል የሚያካሂደውን በዓል አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ፣ በዓሉ የንግድ ምክር ቤቶች ላለፉት 30 ዓመታት የንግዱን ማኅበረሰብ መብትና ጥቅም ለማስከበር ያደረጉትን እንቅስቃሴ፣ ንግድና ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ ያበረከቱትን አስተዋፅኦ የሚዘክር መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ የብሔራዊ ምክር ቤቱና የክልል ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ኃላፊዎች በጋራ በሰጡት በዚሁ ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የበዓሉ መሪ ቃል “የኢትዮጵያን ምርት ይግዙ” የሚል ሲሆን ምርቶቹ ኅብረተሰቡ እንዲጠቀምባቸው በአገር ምርት የመገልገል ባሕልን ለማዳበር ታስቦ እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡ ከግንቦት 1 እስከ 4 ቀን 2000 ዓ.ም በሚቆየው በዚሁ የበዓል አከባበር፣ በንግዱ ኅብረተሰብና በመንግሥት ኃላፊዎች መካከል የሚደረግ የፓናል ውይይትና የምክር ቤቱን የ60 ዓመታት ጉዞ የሚያስቃኝ የፎቶ ግራፍ ኤግዚቢሽን ተጠቃሽ ፕሮግራሞች ሲሆኑ “የኢትዮጵያን ይግዙ” የሚል የሩጫ ውድድርም ይካሄዳል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |