| በአዲስ አበባ 32 ድልድዮች ከ4ዐዐ... |
|
|
| Friday, 11 January 2008 | |
|
በአዲስ አበባ 32 ድልድዮች ከ4ዐዐ ሚሊዮን በላይ ወጪ እየተሠሩ ነው ከመስቀል አደባባይ ቃሊቲ ያለው መንገድ ግንባታ ተጀመረ በአዲስ አበባ ከተማ እየተገነቡ ካሉ የመንገድ ሥራዎች ጐን ለጐን ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የ32 ድልድዮች ግንባታ በመከናወን ላይ መሆኑ ተገለፀ፡፡ ከመስቀል አደባባይ ቃሊቲ ያለው መንገድ ግንባታም ተጀመረ፡፡ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍቃዱ ኃይሌ ለሪፖርተር ጋዜጣ እንደገለፁት በመገንባት ላይ ያሉት 32 ድልድዮች አዳዲስና ቀድሞ የነበሩትን ደረጃ የማሳደግ ሥራን ያጠቃልላል፡፡ የከተማውን እድገትና የትራፊክ ፍሰት ተከትሎ የድልድዮች ግንባታ ወሳኝ በመሆኑ አሁን ያለውና ወደፊት ሊኖር የሚችለውን የትራፊክ ፍሰት እና ብዙ ተሽከርካሪዎችን ለማስተናገድ የሚችሉ ድልድዮች በመገንባት ላይ ናቸው፡፡ አሁን እየተገነቡና ደረጃቸው እንዲያድግ እየተደረጉ ካሉት ጋር በጥቅሉ ከ29ዐ በላይ የሚሆኑ ድልድዮች መኖራቸውን የጠቆሙት አቶ ፍቃዱ፣ በቀጣይ ዓመታትም ከትራፊክ ፍሰቱ ጋር ተመጣጣኝ የሚሆኑ የድልድይ ግንባታዎች እንደሚከናወኑ አመልክተዋል፡፡ የድልድዮቹ ሥራ በአብዛኛው ለኮንትራክተሮች በተናጠል የሚሰጥ እንዳልሆነ ያመለከቱት አቶ ፍቃዱ፣ በተለያዩ የከተማው አካባቢዎች እየተገነቡ ካሉ መንገዶች ጋር በጥምረት የሚሠሩ ናቸው፡፡ በ2ዐዐዐ የበጀት ዓመት ባለሥልጣኑ ለመንገድ ጥገናና ለመሳሰሉት ሥራዎች ከተያዘለት ጠቅላላ በጀት 3ዐ በመቶው የድልድዮች ድርሻ ነው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ከቃሊቲ እስከ መስቀል አደባባይ ድረስ ያለውን መንገድ በአዲስ መልክ ለመገንባት ጨረታውን ያሸነፈው የቻይናው ኩባንያ ቁፋሮ መጀመሩ ታውቋል፡፡ ለዚህ መንገድ ሥራ በመንገዱ ግራና ቀኝ ያሉ ቤቶች በመፍረስ ላይ ያሉ ሲሆኑ እየፈረሱ ካሉት ቤቶች መካከልም አብዛኛዎቹ የንግድ ቤቶች ናቸው፡፡ በተለይ በደብረ ዘይት መንገድ ጠመንጃ ያዥ አካባቢ ያሉ ንግድ ቤቶች በተሰጣቸው አጭር ጊዜ ቤቶቻቸውን እያፈራረሱ ንግዳቸውን ወደ ሌሎች አካባቢ በማዘዋወር ላይ ናቸው፡፡ ይህ መንገድ እየተገነባ ካለው የጐተራ ተላላፊ ድልድይ ጋር ተገጣጥሞ የሚሠራ ሲሆን ጠቅላላ ወጪውም ከ390 ሚሊዮን ብር በላይ ይሆናል፡፡ በዳዊት ታዬ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |