Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
Jul 20th
Home arrow Sections arrow “ዋጋው ባይረጋጋ እንኳን ነጋዴው...
“ዋጋው ባይረጋጋ እንኳን ነጋዴው... Print E-mail
Sunday, 11 May 2008
Image
አቶ ጌታቸው አየነው
“ዋጋው ባይረጋጋ እንኳን ነጋዴውመረጋጋት ይኖርበታል”

አቶ ጌታቸው አየነው
የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት

አቶ ጌታቸው አየነው የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአስመራ ዩኒቨርሲቲ ወስደዋል፡፡ ለ12 ዓመታት በተለያዩ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ በመምህራን ማሰልጠኛ ተቋምና በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡ ባለፉት አስር ዓመታት ደግሞ ወደ ንግድ ዓለም በመሸጋገር እየሠሩ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት በአዲስ መልክ እንዲመሰረት ሲደረግ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሆነው ተመርጠው በማገልገል ላይ ናቸው፡፡ በምክር ቤቱና በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ዳዊት ታዬ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በአዲሱ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ውስጥ ምን ያህል አባል ምክር ቤቶች አሉ?

አቶ ጌታቸው፡-
የኢትዮጵያ የንግድ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በአዋጅ ሲደራጅ አባል ምክር ቤቶቹ የክልል ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች ሁለት የከተማ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች (የአዲስ አበባና የድሬዳዋ”፣ ስድስት አገር አቀፍ የዘርፍ ማኅበራት፣ አንድ የኢትዮጵያ ዘርፍ ማኅበራት በድምሩ 18 ምክር ቤቶችን በአባልነት ይዟል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ሚያዚያ 1999 ሲቋቋም እያንዳንዱ ክልል የራሱን የከተማ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በማደራጀት የአባላቱ ቁጥር አስመዝግቦ ነው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተቋቋመው፡፡

ሪፖርተር፡- በቀድሞውና በአሁኑ ምክር ቤቶች መካከል ያለው ልዩነቱ ምንድነው?

አቶ ጌታቸው፡-
አደረጃጀቱ ነው፡፡ የቀድሞው የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ይባል የነበረው በአባልነት የያዛቸው 15 የከተማ ንግድ ምክር ቤቶችን ብቻ ነው፡፡ ከእነዚህ ሌላ የክልል ንግድ ዘርፍ ምክር ቤት የለም፡፡ በአሁኑ ሰዓት ግን የአገሪቱ የፌዴራል ሲስተም የተከተለ አወቃቀር በመሆኑ አምራች ነጋዴዎችና አገልግሎት ሰጪ ነጋዴዎች በከተማ ወይም በወረዳ ደረጃ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ተሰባስበው የክልል ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶችን ይመሰርታሉ፡፡ እነዚህ የክልል ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች ደግሞ አገር አቀፉን ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ም/ቤትን ይመሰርታሉ፡፡ በአሁኑ ሰዓት ባለን መረጃ ትላልቅ የምንላቸው አራቱን የክልል ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ብንወስድ እንኳ በትግራይ 15፣ በአማራ 40፣ በኦሮሚያ 20፣ በደቡብ 22 የሚደርሱ የከተማ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት አሉ፡፡ የአሁኑ አደረጃጀት በአገሪቷ ያለውን የንግድ ኅብረተሰብ መድረስ የሚችል ነው፡፡ ከዚህም የምንረዳው እያንዳንዱ የከተማ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ም/ቤት በአማካይ አንድ ሺህ አባል ነጋዴ እንዲይዝ ቢሠራ እያንዳንዱ ም/ቤት 20 ሺህ አባል ነጋዴ ማደራጀትና አክቲቭ ተሳታፊ ማድረግ ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- ከአዲስ አበባ ውጭ ያሉ ንግድ ምክር ቤቶች ጠንካራ አልነበሩም፡፡ የአሁኖቹስ ተጠናክረዋል?

አቶ ጌታቸው፡-
የንግድ ምክር ቤቶችን የበፊቱንም የአሁንም በክብ ቀለበት ችግር ውስጥ ናቸው፡፡ በከተማ በክልልና በአገር አቀፍ ደረጃ ላይ ያለውም ቢሆን እንደ ምክር ቤት ለአባሎቹ ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጥ ይጠበቃል፡፡ ተገቢውን አገልግሎት ለመስጠት ደግሞ ባለሙያዎችን መቅጠር ይኖርበታል፡፡ ለመቅጠር ደግሞ የመክፈል አቅም እንዲኖረው ይገባል፡፡ የመክፈል አቅም እንዲኖረው አባላት መምጣት አለባቸው፡፡ አባላት ለማምጣት ደግሞ ከምክር ቤቱ አገልግሎት ይጠብቃሉ፡፡  አንድ ቦታ ላይ ሰብሮ መግባት ያስፈልጋል፡፡ የበፊቱ ንግድ ምክር ቤት የነበረበት አንዱ ችግር ነው፡፡ አሁንም ያሉት ምክር ቤቶች ተመሳሳይ ችግር አለባቸው፡፡ አሁን ያለው ጥሩ አጋጣሚ ነጋዴው በማኅበሩ በመደራጀት ችግሩን በግለሰብ ደረጃ ሳይሆን በምክር ቤት ደረጃ ለሚመለከተው አካል በማቅረብ አፋጣኝ ምላሽ ማግኘት የሚችል መሆኑን ተረድቷል፡፡ ነጋዴው በምክር ቤት በመሰባሰቡ አዳዲስ መረጃዎችን ማግኘት እንደሚችሉ ተረድተዋል፡፡ በቅርብ ርቀት ንግድ ምክር ቤቶቹ ተጠናክረው የተሻለ ሥራ መሥራት እንዲችሉ የሚያስችል ደረጃ ላይ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ምክር ቤቱ በአዲስ መልክ ከተቋቋመ ከአንድ ዓመት ለአባላቱ ምን አደረገ?

አቶ ጌታቸው፡-
ታች ወርዶ ለግለሰብ ነጋዴ ብሔራዊ ምክር ቤቱ የሚያደርገው ነገር ላይኖር ይችላል፡፡ ግን ለምክር ቤቶቹ ያደረገውን ለመግለፅ ያህል በቅድሚያ አዲስ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሥራ ሲጀምር ቅድሚያ ትኩረት ሰጥቶ ወደ ሥራ የገባው ተቋማዊ አደረጃጀቱ የተጠናከረ እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡ አንድ ምክር ቤት እንደተቋም ግለሰቦች በመጡና በሄዱ ቁጥር መለዋወጥ የለበትም፡፡ እኛ በመጣን ጊዜ ዋና ፀሐፊው ከሥራ የለቀቀበት፣ መምሪያዎች ያልተደራጁበት ሙሉ በሙሉ ባይባልም ሃምሳ በመቶ የሰው ኃይል የሌለው ነበር፡፡ አዲሱ የዳይሬክተሮች ቦርድ ቅድሚያ የሰጠው ይህንን ተቋም ማደራጀት ነው፡፡ ልዩ ልዩ የሥራ መመሪያዎችን ማውጣት፣ አዲስ የሰው ኃይል መዋቅር ማዘጋጀት፣ መምሪያዎች በተገቢው የሰው ኃይል እንዲሸፈኑ የማድረግ ሥራ ረጅም ጊዜ ወስዶብናል፡፡ የ5 ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ የማውጣት ሥራም እንደዚሁ፡፡ ለአባል ምክር ቤቶች እናደርጋለን ያልነውን ሙሉ ለሙሉ ለመሸፈን ባንችልም በአገር አቀፍ ደረጃ የተደራጀ የቢዝነስ አጀንዳ ነበረና በአምስት ከተሞች የአገር ውስጥ ቢዝነስ አጀንዳ ተዘጋጅቷል፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ አንድ አገር አቀፍ ቢዝነስ አጀንዳ ተዘጋጅቷል፡፡ በዚህ አጀንዳ የክልል ምክር ቤቶች እንዲመክሩበት ተደርጓል፡፡  ለሚመለከታቸው የድርሻ አካላት ቢዝነስ አጀንዳው እንዲደርሳቸውና መድረክ እንዲመቻችልን ጠይቀናል፡፡ በተለይ ግብር ነክና ከቀረጥ ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለቅመን በማውጣት ከገቢዎች ሚኒስቴር ጋር ባለፈው ጥር ወር ላይ የግማሽ ቀን የፓናል ውይይት አድርገናል፡፡ ሚኒስትሩ በተገኙበት የተደረገ በመሆኑ መፍትሔ የምንላቸውንም አመላክተናል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በአገራችን የፐብሊክ ፕራይቬት ፓርትነር ሽፕ፣ የንግዱ ማኅበረሰብና የመንግሥት የምክክር መድረክ ከ1995 እስከ 1997 ድረስ ለስድስት ተከታታይ ጊዜያት መካሄዱ ይታወሳል፡፡ ይህ አካሄድ መልክ ያለው የተደራጀና ወጥነት ያለው ባለመሆኑ ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ ተቋርጧል፡፡ ይህ አደረጃጀት ተቋማዊ ይዘትና ሕጋዊ ሰውነት ኖሮት እንዲቀጥል ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጋር በተደጋጋሚ በመመካከር በተለይም የዓለም ባንክ አጥንቶ ያመጣውን ሰነድ በመፈተሽ ከሁለቱ ወገኖች የተውጣጡ ባለሙያዎች ረቂቅ ሰነድ አዘጋጅተዋል፡፡ በቅርቡም ይህ አደረጃጀት ተቋማዊ ይዘት ኖሮት ሕጋዊ ሰውነት አግኝቶ የምክክር መድረኩ ተግባራዊ ይሆናል ብለን እንጠብቃለን፡፡

ሪፖርተር፡- ምክር ቤቱ በአዲስ መልክ ከተቋቋመ ወዲህ ከአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ውጪ ዓመታዊ መዋጮውን ያስገባላችሁ ምክር ቤት አለ?

አቶ ጌታቸው፡-
በአዲሱ አደረጃጀት የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትን ጨምሮ ማንም የሚጠበቅበትን ዓመታዊ መዋጮ አላስገባም፡፡

ሪፖርተር፡- ለምን አላስገቡም?

አቶ ጌታቸው፡-
ይህ ነው ችግሩ፡፡ ደብዳቤዎችን ከመፃፍ ባሻገር ባገኘነው የምክክር መድረክ ሁሉ ጥያቄ እናቀርባለን፡፡ የክልል ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አደረጃጀታቸው ገና አዲስ ስለሆነ ጊዜ ስጡን የሚል ጥያቄ ነው ያላቸው፡፡ መክፈል እንዳለባቸው ግን ያምናሉ፡፡ እነሱ የሚሰበስቡት ከከተሞች ነው፡፡ ከከተሞች ሰብስበው አልጨረሱም፡፡ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ደግሞ እስከ ዛሬ በነበረው አካሄድ ክልሎች የማይከፍሉበት ሁኔታ እንዲኖር ስለማይፈልግ ለመክፈል ፈቃደኛ ነው፡፡ ያለበትንም ድርሻ ያውቃል፡፡ ነገር ግን ክልሎች ላይ ሊሠራ ይገባል የሚል እምነት ስላለው ነው፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ገቢ ያደርጋሉ ብዬ አምናለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- በአዲስ አበባና በኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት መካከል ያለመግባባት እንደነበር ይታወቃል፤

አቶ ጌታቸው፡-
በሁለቱ ምክር ቤቶች መካከል ያለው ችግር አሁን በአዲሱ አደረጃጀት የመጣ ሳይሆን ቀደም ብሎ በ1996/97 ዓ.ም የነበረ ነው፡፡ የችግሩ መንስዔ በአጭሩ በሥራ የሚፈጠር አለመግባባት ነው፡፡ በሥራ ምክንያት የነበረው አለመግባባት በመቀራረብ መፍታት ይገባል፡፡ እኛ በገባን ጊዜ በሁለቱ ምክር ቤቶች መካከል የነበረውን አለመግባባት ለመፍታት በቅድሚያ ለአለመግባባቱ መነሻ የሆኑትን ችግሮች ምንድናቸው ብለን ለይተን ለማውጣት ሞክረናል፡፡ በችግሮቹ ዙሪያ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ ሦስት ጊዜ በመደበኛ ስብሰባ ተወያይቶበታል፡፡ መፍትሔ ይሆናሉ ያላቸውን ሃሳቦች ጠቁሟል፡፡ ከአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አመራሮች በመነጋገር ለችግሮቹ አማራጮች ናቸው ያልናቸውን በማቅረብ 90 በመቶ ችግሩን ፈትተን መግባባት ላይ ደርሰናል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት 50ኛ ዓመቱን በሚያከብርበት ጊዜ ሁለቱን ንግድ ምክር ቤቶች በዓሉን ለየብቻ አክብረዋል፡፡ በ60ኛው ዓመት እንዳይደገም ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ምክር ቤቱ በአዲስ መልክ የተቋቋመበትን አንደኛ ዓመትና የተመሠረተበትን 60ኛ ዓመት በጋራ ለማክበር እየተዘጋጀን ነው፡፡ በሁለቱ ምክር ቤቶች መካከል ያለውን አለመግባባት ሙሉ ለሙሉ ፈተናል ማለት ባይቻልም በመደማመጥ፣ በመቀራረብና ሃሳብ ለሃሳብ በመለዋወጥ ለብዙዎቹ ችግሮች መፍትሔ ሰጥተናል፡፡

ሪፖርተር፡- ለንግዱ ኅብረተሰብ የውጪ ገበያን የማፈላለግ ሥራ እንድትሠሩ ይጠበቅባችኋልና ይህንን ተግባራችሁ ተወጣችሁን?

አቶ ጌታቸው፡-
በአዋጁም ላይ እንደተቀመጠው ንግድ ምክር ቤቶቹ የአባሎቻቸውን ምርት ያስተዋውቃሉ፡፡ የውጭና የውስጥ ገበያን ያፈላልጋሉ ነው የሚለው፡፡ በዚህ ዓመት ገበያ ለማፈላለግ ወደ ውጭ አገር አባሎቻችንን ይዘን በመሄድ የሠራነው ሥራ የለም፡፡ ነገር ግን የተለያዩ የንግድ ልኡካን ገበያ ለመፈለግ ከአዳዲስ ምርቶች ጋር ለመተዋወቅ ወደ አገራችን ይመጣሉ፡፡ እነዚህን በመቀበልና የመጡበትን የንግድ ዘርፍ በመለየት ተመሳሳይ የንግድ ዓይነት የሚያመርቱ አባሎቻችን ቀድመን ከአዲስ አበባና ከክልል በማፈላለግ የአቻ ለአቻ ውይይት እንዲያካሂዱ አድርገናል፡፡ በጋራ እንዲሠሩ የቴክኖሎጂ ልውውጥ እንዲኖርም ጥረናል፡፡

ሪፖርተር፡- የ5 ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ አዘጋጅታችኋል፡፡ ግቡ ምንድነው?

አቶ ጌታቸው፡-
የእቅዱ ዋና ዋና ተግባራት በቅድሚያ አገር አቀፍ አገልግሎት እንዲሰጥ አድርጐ ማደራጀት ነው፡፡ አባል ድርጅቶች አቅማቸው እንዲያድግና ቁጥራቸውም ለማሳደግ ነው፡፡ አሁን አለን የምንለው የአባላት ቁጥር 98 ሺህ ነው፡፡ ከአራትና አምስት ዓመት በኋላ ግን ሁለትና ሦስት እጥፍ አድጐ 400 ሺህና ከዚያም በላይ አባል እንዲኖረን መሥራት ትልቁ እቅዳችን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ብሔራዊ ምክር ቤቱ በ98 ሺህ አባል ብቻ እንዴት ይወሰናል? አዲስ አበባ ብቻ እኮ ከ200 ሺህ በላይ ነጋዴዎች አሉ፤ አባሎቻችሁ ደግሞ ብዙም አይደሉም፤

አቶ ጌታቸው፡-
እኛም የምንለው ይህን ነው፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ አሁን ያለው 98 ሺህ አክቲቭ አባል ነው የሚለውም ትልቅ ጥያቄ መሆን አለበት፡፡ ቁጥሩ አነሰ? አንድ ጥያቄ ነው፡፡ በስትራቴጂክ እቅዳችን መጀመሪያ ላይ ያስገባነው 98 ሺው አክቲቭ ተሳታፊ እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡ ይህም ዓመታዊ ክፍያውን እንዲከፍል፤ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆን ማስቻል ነው፡፡ ያለው ነጋዴ ቁጥር እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ብቻ ከ250 ሺህ በላይ ነጋዴዎች ይኖራሉ፡፡ ነገር ግን የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በአሁኑ ሰዓት በእጁ ላይ ያለው የአባላት ቁጥር ከ8 እስከ 10 ሺህ የሚደርስ ነው፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት የንግድ ምክር ቤቶች በክብ ቀለበት ችግር ውስጥ ስላሉ ነጋዴው አገልግሎት ይጠብቃል፡፡ ምን ይሠራልኛል ብሎ ይጠብቃል፡፡ ምክር ቤቶች ተጠናክረው ለአባሎቻቸው ብዙ ዓይነት አገልግሎት የሚሰጡ መሆናቸውን ማሳየት አለባቸው፡፡ ያኔ ነው ምክር ቤቱ የእኔ ነው ብሎ መምጣት የሚችለው፡፡

ሪፖርተር፡- የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበት ተከስቷል፡፡ በምክር ቤት ደረጃ ምን አድርጋችኋል?

አቶ ጌታቸው፡-
የዋጋ ንረቱ በአገራችንም ይሁን በዓለም አቀፍ ደረጃ ወቅታዊና አንገብጋቢ ችግር ነው፡፡ ብዙ አገሮች አጣብቂኝ ውስጥ የገቡበት ስለመሆኑ በየሚዲያው እየተዘገበ ነው፡፡ በእኛም አገር ከሌላው ጊዜ በተለየ ሁኔታ የዋጋ ንረት ከቀን ወደ ቀን፣ ከሣምንት እስከ ሣምንት እጨመረ ሁኔታ ነው፡፡ የዓለም አቀፉም ሆነ የአገራችን የዋጋ ንረት መንስኤው አንድ ነው ብለን አናምንም፡፡ ብዙ ባለሙያዎች እንደሚገልፁት ዘርፈ ብዙ የሆነ ችግር ነው፡፡ በአገራችን የተከሰተው የዋጋ ንረት ብዙ ምክንያቶች አሉት፡፡ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በቅድሚያ ሙያዎች ጊዜያቸውና ጉልበታቸውን መስዋዕት አድርገው ችግሩን በሚገባ ለይተው ሊነግሩን ይገባል፡፡  

ሪፖርተር፡- ለምን ሌሎችን ትጠብቃላችሁ? እናንተ ለማስጠናት አልሞከራችሁም?

አቶ ጌታቸው፡-
በዚህ ርእስ ላይ ምክር ቤታችን አባል ምክር ቤቶችን ጠርቶ የግማሽ ቀን ውይይት በማድረግ ወቅታዊ የክልሎች ሁኔታ ምን ይመስላል የሚለውን ለማየት የሚያስችል መረጃ አግኝተናል፡፡ በየክልሎቹ የዋጋ ንረቱ እስከምን ደረጃ ላይ ደርሷል? የዋጋ ንረቱ የንግዱን ኅብረተሰብም ይጎዳዋል፡፡ ኅብረተሰብ በሁለት በኩል ይጐዳል፡፡ በአንድ በኩል እንደማንኛውም ኅብረተሰብ ሸማች ስለሆነ ዋጋ በናረ ቁጥር እንደሸማች ይጐዳል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ አግባብነት የሌላቸው ነጋዴዎች የሚያደርሱት ችግር ጤናማውን ነጋዴ ይጐዳዋል፡፡ ወመንግሥት ባቋቋማቸው የክልልና የከተማ ዋጋ አረጋጊ ግብረ ኃይል ውስጥ የምክር ቤቱ አመራሮች እንዲገቡና የሚወሰደው እርምጃ ፍትሐዊ እንዲሆን እንዲሠሩ ውሳኔ አስተላልፈናል፡፡ በተወሰነ ክልሎች በአማራ፣ በኦሮሚያ በተወሰነ አካባቢ፣ በደቡብ በተወሰነ አካባቢ የንግድ ምክር ቤቶቹ በእነዚህ ግብረሃይሎች ውስጥ ገብተው የበኩላቸውን ድርሻ እየተወጡ ነው፡፡

የምንሻቸው መፍትሔዎች ጥናቱን በማሳየት ቋሚ መፍትሔ እንዲገኝ ማድረግ፣ እስከዚያው ድረስ ግን መንግሥት በጊዜያዊነት የወሰዳቸው እርምጃዎች በመደገፍ በሂደቱ ግን በአግባብ የሚነግዱ ነጋዴዎች እንዳይጐዱ አብሮ መሥራት፣ ያለአግባብ የሚነግዱትን ደግሞ ከመንግሥት በፊት ቀድሞ በመድረስ ትክክል እንዳልሆኑ መምከር፣ አስፈላጊ ከሆነም ወደ ሕግ ማቅረብ ተገቢ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በሕጋዊ መንገድ የሚነግዱ ነጋዴዎች እየተጐዳን ነው፣ ዋጋው በየቀኑ እየጨመረ በመሆኑ ዋጋ መለዋወጥ ግድ እየሆነብን ነው፡፡ አንዳንዶቹ መሥራተ አቅቷቸው እየዘጉም ነው፡፡ ለዚህ ምን አማራጭ መፍትሄ ታቀርባላችሁ?

አቶ ጌታቸው፡- ችግሩ በመንግሥትም ይሁን በምክር ቤታችን ሊፈታ የሚችል አይደለም፡፡ ለዚህ ነው ሁሉን አቀፍ ጥናት ያስፈልጋል የምንለው፡፡ ለአባሎቻችን የምንመክረው ለሙያቸው ታማኝ ሆነው ተገቢውን አገልግሎት መስጠት እንዳለባቸው ነው፡፡ የዋጋ ንረትን ምክንያት በማድረግ አስፈላጊ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት መሥራት የለባቸውም፡፡ ገና ለገና መንግሥት የዋጋ አረጋጊ ግብረሃይል አቋቁሟልና ያልተጠበቀ እርምጃ ይወስድብኛል የሚል ፍራቻ ሊያድርባቸውም አይገባም፡፡ ዋጋው ባይረጋጋ እንኳን ነጋዴው መረጋጋት ይኖርበታል፡፡

ሪፖርተር፡- ነጋዴው እንዲረጋጋ ምን አድርጋችኋል? ነጋዴዎች ሲታሠሩ እርምጃ ሲወሰድባቸው ምን አድርጋችኋል?

አቶ ጌታቸው፡-
ብሔራዊ ንግድ ምክር ቤቱ አደረጃጀቱ በቀጥታ ከክልሎች ጋር ነው የሚሆነው፡፡ ግለሰብ ነጋዴዎች ጋ ወርዶ የሚያደርገው ነገር አይደለም፡፡ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ከኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በጋራ መመካከር ለአባሎቹ ፎረም አዘጋጅቶ ተወያይቶበታል፡፡ የሚወሰደው እርምጃ አግባብ ያለው እንዲሆን መክሯል፡፡ ጥናትም ለማስጠናት እየሞከረ ነው፡፡   

ሪፖርተር፡- ም/ቤቱ በአዲስ መልክ ከተደራጀ ወዲህ ከተለያዩ አቅጣጫዎተ አመራሩ ለንግዱ ኅብረተሰብ ከመቆም ይልቅ ለመንግሥት ያደላ ነው እየተባለ የተለያዩ አስተያየቶች ይሰነዘራሉ፤

አቶ ጌታቸው፡-
ይህ አስተያየት ወሬ ብቻ ሳይሆን ተፅፎም አይተናል፡፡ እንዲያውም ለጋሽ ድርጅቶች የምንላቸው ባስጠኑት ጥናት ላይ (The new elected board of directors is governments dream of board) ብለዋል፡፡ ይሄ ያመናል፡፡ በአገራችን ያለው ትልቁ ችግር በፖለቲካውም ይሁን በማኅበራዊ ጉዳይ ላይ ገብተን ሳናየው ነው የምንፈርጀው፡፡ የአዲሱ ምክር ቤት አስራ አንዱ የቦርድ አባላት ለዚህኛው የፖለቲካ ድርጅት ወግነዋል ለማለት ምን የተጨበጠ ማስረጃ አለ? ይህንን ቦታ እንደያዝን ወዲያውኑ በመንግሥት ላይ የሆነ ያልሆነውን በመናገር ወቀሳ እንድናበዛ ተጠብቆ ከሆነ አግባብ አይደለም፡፡ እኛ የምናምነው መጀመሪያ ችግሩን ማወቁ ላይ ነው፡፡ ችግር ያመጣውን አካል ልንወቅሰው ይገባል፡፡ እንደገባን ችግር ሆኖ ያገኘነው የምክር ቤቱ ሕንፃ ተወርሶ ይህንን ያህል ጊዜ መቆየቱ ነው፡፡ በመጀመሪያው የቦርድ ስብሰባችን ሕንፃውን ማስመለስ አለብን ብለን ነው ኮሚቴ ያቋቋምነው፡፡ ሕንፃው እንዲመለስ በተደጋጋሚ ጥያቄ አቅርቧል፡፡ ወዲያውኑ ነው ለመንግሥት ያቀረብነው፡፡ አዲሱ ቦርድ የመንግሥት ወገናዊነት አለው የሚያሰኝ ምን አለ? የንግዱ ህብረተሰብ ቀርቦ ስላላየን ምን እየሠራን እንደሆነ ስላላወቀ ያላወቀውን አካል ደግሞ ወደ አንድ ጎን ነው የምትፈርጀው፡፡ ከዚህ ባሻገር ረጂ ድርጅቶችም አድሏዊ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ ምክንያቱም እነሱም ቢሆን ሳያውቁ የተለቃቀመ ወሬ በመያዝ ነው ፅሁፍ ያወጡት፡፡ ይህንን ባገኘነው አጋጣሚ ፊት ለፊት ቁጭ ብለን ተነጋግረን ያመኑበት ነው፡፡ እዚህ የተሰባሰብነው ነጋዴ በመሆናችን ነው፡፡ ነጋዴ ደግሞ የፖለቲካ ድርጅት አባል አይሁን የሚል ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ የለም፡፡ ከመካከላችን ያሉት የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት የአንድ ወገን የፖለቲካ ድርጅት ደጋፊ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እኔ እስከማውቀው ግን እንደዚህ ዓይነት መረጃ እጃችን ላይ የለም፡፡ ትልቁ ነገር በቦርዱ ውስጥ ያሉት ተመራጮች የየትኛው ፖለቲካ ድርጅት ደጋፊ ናቸው ሳይሆን መባል ያለባቸው ያን የሚወግኑትን የፖለቲካ ዓላማ ምክር ቤቱ ውስጥ ይዘው መጥተዋል ወይ የሚለው ነው፡፡ መፈተሽ ያለበትም ይህ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በቀጣዩ ዓመታት ነጋዴው ከእናንተ ምን ይጠብቅ?

አቶ ጌታቸው፡-
ምክር ቤቱ በአዲስ አደረጃጀት ከተመሠረተ አንድ ዓመት ነው፡፡ በአገራችን የንግድ ምክር ቤት ከተጀመረ 60ኛ ዓመቱ ነው፡፡ ስለዚህ በሚቀጥለው ዓመት በዚህ ዓመት ከተጓዝነው ፍጥነት በተሻለ ደረጃ በንግዱ ኅብረተሰብ ዘንድ አገራዊ መግባባት ኖሮ ንግዱ ጤናማ ውድድር እንዲካሄድበት ትልቅ ሥራ እንሠራለን፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በአገር ደቀፍ ደረጃ ያስጠናናቸው የቢዝነስ አጀንዳዎች ውስጥ የታዩ ችግሮችን በፐብሊክ ፓርትነር ሽፕ ፎረም አማካኝነት በቋሚነት እንዲመከርባቸው እናደርጋለን ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ በተለይ ይህ ያለንበት ሕንፃ በደርግ ተወርሶ አሁንም በመንግሥት ይዞታ ስር መሆን በጣም ትልቅ ጫና በምክር ቤቱ ላይ እንዳሳደረ መሆኑን ለመንግሥት ለማሳየት ሞክረናል፡፡ ስለዚህ ይህ ሕንፃ በሚቀጥለው ዓመት ተመልሶልን ሁሉም ምክር ቤቶች በአንድ ጥላ ስር ተሰብስበው ሕንፃው ሲሠራ ለነበረበት ዓላማ ይውላል ብለን እናምናለን፡፡
 
< Prev   Next >