Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Saturday
Jul 05th
Home arrow Sections arrow ዲያስፖራው ባለፉት ዘጠኝ ወራት
ዲያስፖራው ባለፉት ዘጠኝ ወራት Print E-mail
Sunday, 11 May 2008
በጋዜጣው ሪፖርተር

ዲያስፖራው ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከተንቀሳቀሰባቸው ዘርፎች መካከል ኢንቨስትመንት ዋናው ሲሆን በእውቀትና በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በአገር ገጽታ ግንባታና በቅስቀሳ ሲሳተፍ ቆይቷል፡፡
ባለፉት ዘጠኝ ወራት ዲያስፖራውን አስመልክቶ ሲደረጉ በነበሩ እንቅስቃሴዎች ዙሪያ አቶ ደመቀ አጥናፉ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጄነራል ተጠባባቂ ኃላፊ እንደገለፁት፣ ዲያስፖራው በተለያዩ የልማት ዘርፎች ላደረገጓቸው እንቅስቃሴዎች መረጃ ዋናው ቢሆንም በኢንቨስትመንት፣ ክልሎች በሚያወጧቸው የኢንቨስትመንት ማበረታቻዎች፣ እያንዳንዳቸው አስፈፃሚ መ/ቤቶች የሚያወጡዋቸው መመሪያዎችን፣ ደንቦችን፣ አዋጆችን ለማግኘት ዲያስፖራው ችግር ነበረበት፡፡

በመሆኑም በኢንቨስትመንትም ሆነ በሌሎች የልማት መስኮች ዲያስፖራው እንዲሳተፍ ለማድረግ ወቅታዊ፣ ተገቢና ትክክለኛ መረጃ ለመስጠት የተደረገው እንቅስቃሴ ያለፉት ዘጠኝ ወራት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በስፋት የሰራበት ወቅት ነበር፡፡

በዋናው መሥሪያ ቤትና በሚሲዮኖች፣ ከሚመለከታቸው የፌደራልና የክልል መሥሪያ ቤቶች በየጊዜው የሚወጡትን መመሪያዎችና ደንቦች፣ የተደረጉ ማሻሻያዎችን በማሰባሰብና በማደራጀት በሚሲዮኖች አማካይነት በውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እንዲደርስ ጥረት ተደርጓል፡፡

አብዛኛው ዲያስፖራ በሚኖርባቸው አገሮች ሚሲዮኖች የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት የአገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ፣ በኢንቨስትመንትና ሌሎች እንቅስቃሴዎችን በሚመለከት ወቅታዊ መረጃ እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡

በዘጠኙ ወራት 34 ውይይቶች በተለያዩ አገሮች ተደርገዋል፡፡ ትክክለኛ መረጃ ለማስተላለፍም የፌዴራል ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት በተለያዩ የሥራ አጋጣሚዎች ወደ ውጭ በሚሄዱበት አገር በአገሪቱ ስላሉ ሴክተር መ/ቤቶችና በተለይም ዲያስፖራው አስተዋጽኦ ሊያደርግ በሚችልበት ዘርፍ ገለፃና ማብራሪያ እንዲሰጡ ለማመቻቸት ጥረት ተደርጓል፡፡

የክልል መንግሥታት በብዛት የክልሉ ተወላጆች ወዳሉባቸው አገሮች በመሄድ ስለ ክልላቸውና በአገሪቱ እየተካሄደ ባለው የልማት እንቅስቃሴ ዙሪያ እንዲወያዩና ገለፃ እንዲሰጡ ተደርጓል፡፡ በመሆኑም ባለፉት 9 ወራት የኦሮሚያ ክልል ልዑካን ቡድን በአሜሪካና በጀርመን የሥራ ጉብኝት አካሂዷል፡፡

የትግራይ ክልል ልዑካን ቡድን በሳዑዲ አረቢያ ውይይት ያካሄደ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅትም የጋምቤላ ክልል ልዑካን ቡድን በአሜሪካ የክልሉ ተወላጆችን እያነጋገሩ ነው፡፡

አስፈፃሚ መ/ቤቶችም ሆኑ ክልሎች ድረ ገጽ እንዲከፍቱና መረጃ እንዲያሰራጩ ተደርጓል፡፡ ከድረገጽ መክፈቱ ጋር ተያይዞ ዲያስፖራው አገልግሎት የሚፈልግባቸው እንደ ባንክ፣ ማስታወቂያ ሚኒስቴር፣ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ኢንቨስትመንት ቢሮ የመሳሰሉ መ/ቤቶች ድረ ገጾች በውጪ በሚሲዮኖች አማካይነት ዲያስፖራው እንዲያገኝ መደረጉን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሚሌኒየም ሲከበር ወደ አገር ቤት ለመጣው ዲያስፖራ ኃላፊዎች በተገኙበት የውይይት መድረክ ተዘጋጅቷል፡፡

የተሰጠው መረጃ በልማት ብቻ ሳይሆን በሌሎች ዘርፎች ስለነበር ዲያስፖራው በኢንቨስትመንትና በሌሎች የልማት እንቅስቃሴዎች ሲያደርግ የነበረው እንቅስቃሴ እድገትና መሻሻል እያሳየ መጥቷል፡፡

ከኢንቨስትመንት፣ ከባንክ፣ ከሬሚታንስ ጋር ዲያስፖራው የሚያጋጥመውን ችግር ከፌደራል የአቅም ግንባታ ጋር ባለው የጋራ መድረክ በየወሩ በመሰብሰብ ዲያስፖራው በሚያነሳቸው ጥያቄዎች ላይ በመወያየት ለችግሩ መፍትሄ ለማግኘት ጥረት ሲደረግ ቆይቷል፡፡

ክልሎችም ባወጡት የእቅድ አፈፃፀም ዙሪያ በየሦስት ወሩ እየተገናኙ ለመገምገም ጥረት ሲደረግ ነበር፡፡ የዲያስፖራውን የልማት አጋርነት ይበልጥ ለማጠናከር በአሁኑ ሰዓት ደግሞ ጥናት እየተካሄደ ነው፡፡ ጥናቱም እስካሁን በመንግሥት የተወሰኑ የፖሊሲ እርምጃዎች፣ አሰራሮችና አደረጃጀቶችን ለመፈተሽ ዲያስፖራውን በአገር የልማት እንቅስቃሴ ለማሳተፍ ከፍተኛ ልምድና ተሞክሮ ያላቸውን አገሮች ከኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በማዛመድ ወጥ የሆነ የዲያስፖራ ፖሊሲ ለማዘጋጀት ጥናት ተጀምሯል፡፡

ዲያስፖራው በአገሩ መጥቶ በልማት እንዲሳተፍ ብቻ ሳይሆን በአገሪቱ በአጠቃላይ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካና በማኅበራዊ ዘርፎች ዙሪያ እየተካሄዱ ያሉ እንቅስቃሴዎችን አስመልክቶም መረጃዎች ሲሰጡ ቆይተዋል፡፡

በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በትግራይ፣ በደቡብና በአዲስ አበባ 671 ዲያስፖራዎች ባለፉት 9 ወራት በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለመሰማራት ፍቃድ ወስድዋል፡፡

ዲያስፖራው ከተወለደበት አካባቢ ያለውን ትስስር ለማጠናከር በቀዬው በሚደረግ የልማት እንቅስቃሴ እንዲሳተፍና ድጋፍ እንዲያደርግ በአካባቢ ልማት ማኅበር እንዲደራጅ፣  አባል ማኅበራትም እንዲጠናከሩ በሚሲዮኖች አማካይነት ሲሰራ ቆይቷል፡፡ በመሆኑም 12 የልማት እና ሰባት የንግድ አክሲዮን ማኅበራት ተቋቁመዋል፡፡ ዲያስፖራው ከትውልድ አካባቢው ትስስሩን እንዲያጠናክር ክልሎች የመኖሪያ ቤት ቦታ አሰጣጥ መመሪያ አዘጋጅተው እያስተናገዱ ነው፡፡

በተለያዩ ዘርፎች እውቀት ያላቸው ዲያስፖራዎች በእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲሳተፉ በተደረገው ጥረት በሙያቸው ቀጥታ ግንኙነት ካላቸው መ/ቤቶች ጋር በመገናኘት እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡ ከአሜሪካ 3 ፕሮፌሰሮች ከአዳማ ዩኒቨርሲቲ፣ አንድ ፕሮፌሰር፣ ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር ሠርተዋል፡፡ በዲያስፖራ የሕክምና ባለሙያዎች ማኅበር አባላትም በአገር ቤት ለመንቀሳቀስ ጥረት አድርገዋል፡፡

አቶ ደመቀ እንደሚሉት እንቅስቃሴዎቹ ቢደረጉም የተገኙት ውጤቶች በቂ አይደሉም፡፡ ከዲያስፖራው ብዛት አንፃር በአገር ውስጥ በልማት እንዲሳተፉ ለማድረግ በሚመለከታቸው አካላት በኩል ከፍተኛ ሥራ እንደሚያስፈልግ ያሳያል፡፡
 
< Prev   Next >