|
አትሌቶቻችንን "ከአልባሽ መስሎ ገፋፊ" ይሰውራቸው |
|
|
|
Sunday, 11 May 2008 |
|
አፈወርቅ አባመርሳ
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስተናጋጅ የሆነበትና በአዲስ አበባ የተካሄደው ዝግጅት የአፍሪካ አትሌቲክስ (16ኛው) ሻምፒዮን የተሳካ መሆኑ በይፋ ተነግሮለታል፡፡ እንደዚህ ያሉ አህጉራዊ ዝግጅቶችን በብቃት በተሳካ ሁኔታ ማጠናቀቅ እንዲያውም ከቀድሞዎች የተሻለ፣ የሚል ሙገሳ ማግኘት በራሱ የመልካም ምግባር ውጤት ነው፡፡
አትሌቲክስ በተለይም የሩጫ ውድድሮች፣ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ተፈቃሪ እንደመሆናቸው፣ እንዲህ አይነቱን ዝግጅት ለማቅረብ የሕዝብ የድጋፍ ስሜት በብዙ ረገድ ያግዛል፡፡ አትሌቲክስ በተመልካቹ ዘንድ በኢትዮጵያ ተፈቃሪ እንዲሆን ያስቻለው፣ የውጤቱ ባለቤትነት ፀበል ለኛም በመርከፍከፉ ሳይሆን አይቀርም፡፡
ኢትዮጵያ ለ50 ዓመታት ያህል ስሟ በአሸናፊነት በተከታታይ የተጠራበት መስክ ቢኖር የሩጫው ስፖርት ነው፡፡ በእግር ኳሱ ስፖርት "መፈጠራችን እስኪረሳ" ያለመታወቃችንን ያህል፣ በሩጫው ስፖርት እንደወራጅ ውሃ ሳያቋርጥ የሚፈስ የድል አርማ ለማውለብለብ ችሏል፡፡ በኦሎምፒክ መድረክ ብቻ እንኳ ከአበበ ቢቂላ እስከ ቀነኒሳ ድረስ ሳያቋርጥ የድል ባለቤት ሆነናል፡፡
በተሰለፉበት ሙያ የሕዝባቸውን ክብርና ኩራት ለጠበቁ ድል አድራጊዎች ምን ጊዜም ክብርና ሞገስ ይገባቸዋል፡፡ እነሱን ለድል ለማብቃት የሙያቸውን ወዝ ላፈሰሱ አሰልጣኞችም ሞገስ ይገባቸዋል፡፡ ለአመራሩም ጭምር፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብም እነዚህን ድል አድራጊዎች በሚችለው አቅሙ ያለውን ያህል ሰጥቷቸዋል፡፡ ልቡን ከፍቶ ስሜቱን አቀጣጥሎ አክብሮቱን ለግሷቸዋል፡፡ ይኸ የአትሌቶችና የሕዝብ ፍቅር ያቆራኘ ገመድ እንዳይበጠስ የመጠበቅ ሃላፊነት በራሳቸው በአትሌቶቹ ላይ ይወድቃል፡፡ ሕዝባቸው ለነሱ የሚሰጠውን አክብሮትና ፍቅር፣ አትሌቶቹ በሚያገኙት ገንዘብና በሚኖሩበት የተደላደለ ኑሮ ሊለውጡት ቀርቶ ሊያወዳድሩት አይችሉም፡፡ በማንኛውም የሙያ መስክ የተሰለፉ ባለሙያዎች ያገኙትን የሙያ ክብር በበቀሉበት ሃገር በመኖራቸው ሊደሰቱበት እንጂ በሃገራቸው በመኖራቸው እንደ ዕዳ ከፋይ ሊያደርጉት አይገባም፤ የሚል እምነት አለኝ፡፡
በሌላ ሃገር በመኖር ይገኛል ከሚባለው ጥቅም ይብዛም ይነስ በሃገር ውስጥ የሚገኘው ጥቅም ይሻላል፡፡ የጎደለም ነገር ቢኖር እንኳ የሕዝቡ ፍቅር ይሞላዋል፡፡ የሕዝቡ ውዴታ ያስተካክለዋል፡፡ ይኸን የተገነዘቡ ባለሙያዎች ያሉን ይመስለኛል፡፡
በዚያው ልክ ውጤታቸው የእውቅናውን አክሊል ከደፋላቸው በኋላ፣ በውስጣቸው የተመሳጠረውንና ለድላቸው ውጤት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ አስተዋፅኦ ያደረገውን የሕዝባቸውን ልባዊ ድጋፍና አክብሮት የሚያቀልሉ መኖራቸው አይቀርም፡፡ እንደዚህ አይነቶቹ ከሕዝባቸው ጋር ይቆራረጣሉ፡፡ አክብሮቱን ነፍጎ ቸልታውን ያሳያቸዋል፡፡ ፍቅሩን ትቶ ጥላቻውን በተለያየ መንገድ ይገልፅላቸዋል፡፡ በሕዝብ ዘንድ የታዋቂ ሰው አክብሮት ወሰን የሚያጣውን ያህል፣ ቅሬታውም መቀመቅ ድረስ ያወርዳል፡፡ ከራሱ አልፎ ለቤተሰቦቹ ይተርፋል፡፡ የሩጫው ስፖርት አሸናፊዎቻችንም ከዚሁ ማወዳደሪያ አያመልጡም፡፡
ባለፈው ሳምንት በተጠናቀቀው 16ኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮን ዝግጅት፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ማድረግ የሚገባውን ተግባር መፈፀሙ የሚያከራክር አይመስለኝም፡፡ የአፍሪካ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንም ጭምር የተመሰገነና የተደነቀ ዝግጅት እንደነበረ መስክሮለታል፡፡ በሥራ አፈፃፀሙ አመርቂነት የተነሳ ለተለያዩ የኢትዮጵያ ድርጅቶች ወደፊትም ዝግጅቱን እንዲመሩ በር ከፍቶላቸዋል፡፡ የአፍሪካ አትሌቲክስ ምስጋናውን የሰጠው ለፌዴሬሽኑ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ሕዝብም ነበር፡፡ የሕዝቡ የተዋበና ያማረ ድጋፍ፣ የራሱ ዜጎች የገቡበትንና ያሸነፉበትን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ጨዋታዎች በሙሉ ስሜት ማየቱ አፍሪካዊያኖችን አስደስቷቸዋል፡፡ ስለዚህ አድንቀዋል፡፡
ነገር ግን አጠቃላይ ውጤቱ እንደዚህ ያማረና የተወደደ ነው ቢባልም አንዳንድ ጥያቄ የሚያስነሱ ተግባሮች አልነበሩም ማለት አይደለም፡፡ ከነዚህም ውስጥ አንዱ የታዋቂው አትሌት የቀነኒሳ በቀለ በአንደኛው ውድድር ለመሳተፍ አለመፍቀድና በሌላው ውድድር ተሳትፎ ማሸነፍ ናቸው፡፡
ቀነኒሳ በቀለ ኢትዮጵያ ካፈራቻቸው ድንቅና ምርጥ አትሌቶች አንዱ መሆኑ ከአፅናፍ እስከ አፅናፍ የሚመሰከርለት ነው፡፡ በርካታ ሪኮርዶችን በእጁ ያስገባ፣ ከሱ በፊት የነበረው ኃይሌ ገ/ሥላሴ አስከብሮት የቆየውን ክብር የጠበቀ መሆኑም ርግጥ ነው፡፡
በዚህም የኢትዮጵያ ሕዝብ ይወደዋል፤ ያከብረዋል፤ ነገር ግን ውዴታና አክብሮት የሚመነጨውም ከውጤት ብቻ ሳይሆን ከሥነ ምግባር ጭምር መሆኑን መዘንጋት አያስፈልግም፡፡ ቀነኒሳ አሁን እያሳየ ያለው አቋም የቀድሞ አካሄዱን የተከተለ ነወይ? የሚል ጥያቄ እየተነሳ ነው፡፡ ስለዚህም ሁሉም ነገር ከመስመር ሳይወጣ ቀነኒሳን መምከር፣ መንከባከብ ያስፈልጋል፡፡ ነገ ብዙ ሃገራዊ ተልዕኮዎችን ሊፈፅም እንደመቻሉ፣ ስህተቱን ማረም፣ ስህተቶቹን በቅን መንፈስ መንገር፣ ያስፈልጋል፡፡ ይህም አስተያየቴ ከቅን መንፈስ የመነጨና፣ ቀነኒሳ ለታላቅ ክብር እንዲበቃ ከመፈለግ አኳያ መሆኑን መግለፅ እፈልጋለሁ፡፡ ቀነኒሳ እንዲያድግና ለበለጠ ክብር ሞገስ እንዲበቃ የተሳሳተበትን እንዲያርም መንገር ትተን በየግላችን እያወራን የምንደማደምበት ከሆነ ቅሬታው ወደ ጠለቀ የሕዝብ ስሜት ተቀላቅሎ መነቀፍን ያመጣበታል፡፡ ይኸም የሚያበሳጨው ይሆናል፡፡ ከተበሳጨ ደግሞ ለጥሩ ውጤት መብቃቱ ያጠራጥራል፡፡ ባለፈው ውድድርም ለመወዳደር አለመፈለጉ የተተረጎመበት መንገድ በቀነኒሳ ላይ አንዳንዶቹ ቅሬታ እንዲያድርባቸው ማደረጉ መደበቅ የለበትም፡፡
የአፍሪካ አትሌቲክስ አዲስ አበባ ውስጥ ሲዘጋጅ፣ የኛዎቹ አትሌቶች መሆን ያለባቸው አስተናጋጅ እንጅ ተጋባዥ አይደለም፡፡ ሊያጓጓቸው የሚገባው ማስተናገድ እንጂ ተስተናጋጅነት ሊሆን አይገባውም፡፡ ቄጤማ ጎዝጉዞ፣ ያለውን አዘጋጅቶ ታጥቆና አደግድጎ እቤቴ ግቡልኝ፣ እንደሚል ጨዋ ኢትዮጵያዊ፣ አፍሪካዊ ወንድሞቻቸውን ለመቀበል የተዘጋጁ መሆን አለባቸው፡፡ ፌዴሬሽኑንም "ምን እንርዳህ?" እያሉ መደገፍና መርዳት እንጂ እንዲጋብዛቸው ከመጠበቅ አልፈው የፕሮቶኮል አቀማመጣቸውን የሚያስቡ መሆን ያለባቸው አይመስለኝም፡፡ ቅድሚያ ለኢትዮጵያ ክብር መሆን አለበት፡፡
በሌላ በኩል፣ ምንም እንኳ ገንዘብ የማይገኝበትም ቢሆን፣ ለአንድ አፍሪካዊ አትሌት የአፍሪካን አትሌቲክስ ከማክበር በላይ አጀንዳ ሊኖረው አይገባም፡፡ ለአንድ ኢትዮጵያዊ አትሌት የኢትዮጵያን አትሌቲክስ ከማክበር በላይ ሌላ ጉዳይ ሊኖረው አይገባም፡፡ ቀነኒሳ ግን ይህን የሚያረጋግጥ ተግባር ባለማሳየቱ ትችቶች እየተሰነዘሩበት ቆይተዋል፡፡
የመጀመሪያው ችግር ቀነኒሳ በቅድሚያ ለምን አልተነገረኝም? በሚል ቅሬታ በሽልማት ሥነ ሥርዓቱ አለመገኘቱ ነው፡፡ እርሱ እንደሚለው በጊዜው ስላልተነገረውና ጥሪውን የሰማው ከልምምድ ቦታው ለመምጣት በሚያስችል ጊዜ ባለመሆኑ መቅረቱን ነው፡፡
ፌዴሬሽኑ ግን ቀደም ብሎ ማሳወቁን በስልክም ጭምር መጠቆሙን ይገልፃል፡፡ ለጊዜው የፌዴሬሽኑን አባባል ትተን የአትሌቱን ንግግር እንውሰድ ብንል እንኳ ለአፍሪካ አትሌቲክስ ዝግጅት ቀነኒሳ ራሱን ከፌዴሬሽኑ አስገልሎ መልዕክት ለመስማት እንኳ በሰው በኩል እስከማድረግ መድረሱን ያሳያል፡፡ አትሌቱ እንግዶች አዲስ አበባ በሚመጡበት ጊዜ ታዋቂው አፍሪካዊ አትሌት ፌዴሬሽኑ ማግኘት እስኪቸግረው ድረስ ርቆ መገኘቱ መልካም ግንኙነት መኖሩን አያሳይም፡፡
ሁለተኛ በሕዝቡ ፊት በራሱ ሃገር ውስጥ 10"000 ሜትር ለመወዳደር አለመፈለጉ የተለያየ ግምት እንዲሰጠው አድርጓል፡፡ ለምን ለመወዳደር አልፈገለም? ለሚለው ጥያቄ ብዙ መልሶች እያመነጨ ሁሉም የራሱን ትርጓሜ ሰጥቶበታል፡፡ እንደ አጋጣሚ ደግሞ ሁሉም ትርጉሞች ቀነኒሳን የሚጠቅሙ አይደለም፡፡ ሁሉም ትርጉሞች፣ ለሃገሩ ለአዘጋጅነት ለተመረጠችበት ሻምፒዮና አክብሮት እንደሌለው የሚያሳዩ ሆነው ተተርጉመዋል፡፡ ይኸንንም ስሜት 5"000 ሜትር ሮጦ እስከ አለሳለሰው ድረስ በሕዝቡ ዘንድ ሰር"ል፡፡ እንደ ተሰማው ከሆነ የፌዴሬሽኑ ትዕግሥቱ ስላለቀ ቀነኒሳ በ5"000 ሜትር እንዳይወዳደር ከወሰነ በኋላ ቀነኒሳ ባቀረበው የይቅርታና የምልጃ ተማፅኖ ሊወዳደር መቻሉ ነው፡፡
መወዳደሩ በሁለት መንገድ ጥሩ ነው፡፡ አንደኛው ለቀነኒሳ የሚጠቅመው፣ በሕዝቡ ፊት ለመወዳደር ያለመፈለጉ፣ የፈጠውን ቅሬታ እንዲለሰልስለት ረድቶታል፡፡ ሁለተኛም በቤጂንግ ኦሎምፒክ ለሚደረገው ውድድር የኢትዮጵያ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሊጥልበት የሚችለውን የእግድ ውሳኔ ያስቀርለታል፡፡
በሌላ በኩል ኢትዮጵያም ተጠቃሚ ሆናለች፡፡ ቀነኒሳ ከባድ ትግል አድርጎ ድል አስገኝቷል፡፡ በድሉም ሕዝብ ያደረበትን ቅሬታ እንዲያለዝብ ሲያደርግ ለሃገሪቱም ተጨማሪ ወርቅ አስገኝቷል፡፡
በዚያው መጠን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከፍተኛ ግምት ውስጥ የሚገባበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ዲሲፕሊንን የሚያየው እንዴት ነው? አንድ አትሌት በፈለገው ጊዜ ፌዴሬሽኑ ያወጣውን የመወዳደርና የሥልጠና ሥርዓት ሲያፋልስ የሚወስደው ርምጃ መኖር የለበትም ወይ? ርምጃው ታላቅና ታናሽ አትሌት በሚል የሚለያይ ከሆነ ፌዴሬሽኑን የተከበረ ያደርገዋል ወይ? የሚሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ መሰናዳት አለበት፡፡
እንደሰማነው ከሆነ ቀነኒሳ አልወዳደርም በማለቱ ሌላ ተወዳዳሪ አትሌት ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ ቀነኒሳ እወዳደራለሁ በማለቱ ብዜ ደክሞ የተዘጋጀበትን ውድድር? እንዲቀር ተደርጓል፡፡ ይህ እውነት ከሆነ ፍትህ ሊባል ይችላል ወይ?
ታዋቂነት፣ ከዲሲፒሊን ከመታነፅ ውጭ ሊያደርግ እንደማይችል ታዋቂ አትሌቶች ራሳቸው አምነው መቀበል ብቻ ሳይሆን አርአያ ሊሆኑ ይገባል፡፡ ካልሆኑ ፌዴሬሽኑ ሕግ አስከባሪ መሆኑ የግድ ነው፡፡ በዚህ ረገድ በቀነኒሳ ላይ የተሰጠው የፈቃድ ውሳኔ ትክክል መስሎ አይታይም፡፡ አሰልጣኞችም በዚህ ላይ አቋም አለመያዛቸውና በይሉኝታ ገመድ ተተብትበው ቀነኒሳ ከዲስፒሊን ውጭ ያሳየውን ስህተት አለመንቀፋቸው ነገ ችግሩ በራሳቸው ላይ መጠምጠሙን መርሳታቸውን ያሳያል፡፡ ለመሆኑ ብርሃኔ አደሬ በሷ ላይ የተወሰነውን ከአሁኑ ጋር አነፃፅራ ጥያቄ ብታቀርብ ፌዴሬሸኑ ምን ሊል ይሆን?
ከላይ የገለፅኳቸው ሁሉ የሚያሳዩት ቀነኒሳ በታዋቂነቱ ላይ በዲስፒሊን ክብ ውስጥ ሆኖ ቢሰራ ይከበርበታል እንጂ አይነቀፍበትም፡፡ ይጠቀምበታል እንጂ አይጎዳበትም፡፡ ታዋቂ መሆኑን ተገን አድርጎ፣ "ማን አለኝ ከልካይ" ካለ እንደማንኛውም አትሌት መመከር እንዲያም ሲል መቀጣት አለበት፡፡ ዲሲፒሊን ለምንም ሥራ መሰረት ነው፡፡ ዲሲፒሊን ከሌለ ምንም ነገር አስተማማኝ አይሆንም፡፡
ይሁንና አትሌቱ አሁን እያሳያቸው ላሉት ስህተቶች የራሱ ሃሳብ ነው ብዬ ማሰብ ያቅተኛል፡፡ ሲያዩትና ሲያነጋግሩት ቅንነቱ ከፊቱ ላይ የሚነበብት ቀነኒሳ፣ ከዚህ ጋር የማይገናኝ ተግባር ሲፈፅም ሲገኝ ለማለት የምችለው በአካባቢው ያሉ መካሮች ነን ባዮች የራሳቸውን ስሜት እየተከተሉ ሳያሳስቱት አይቀሩም ማለት ይቀለኛል፡፡ ለዚህም ምሳሌ የሚሆነው በቅርቡ ከአንድ የፊልም ባለሙያ ጋር ያነሳው ጭቅጭቅ ነው፡፡
በቀነኒሳ የቀድሞ እጮኛው ላይ ያጠነጠነ ፊልም ሥራው ከተጀመረ በኋላ ቀነኒሳ ሃሳቡን በመለወጡ አንጃ ግራንጃ ተፈጠረ፡፡ በአንጃ ግራንጃው ምክንያት መረጃ የማሰራጨት ሃላፊነቱን ለመወጣት ሁለቱንም ወገኖች አነጋግሮና ሚዛናዊ ዘገባ ለማቅረብ በተዘጋጀው የሪፖርተር ጋዜጣ ላይ ያሳየው ምግባር ከቀነኒሳ የመነጨ ነው ብሎ ማመን ያቅታል፡፡
አትሌቱ ቃለ ምልልሱን ወዶና ፈቅዶ ከሰጠ በኋላ እንዳይተላለፍ ሲፈልግ ይህንኑ ብቻ መንገር በቂው ሆኖ ሳለ፣ በአጃቢዎች ተከቦ ሦስት ራሱን ሁኖ በጋዜጣው ዝግጅት ክፍል ገብተው ከጋዜጠኞች ጋራ ከአታካራ በላይ ያለፈ የኃይል ቃለ ምልልስ ማድረጋቸው ታውቋል፡፡ እንዲህ አይነት ተግባሮቹ ልዩ ስም እያሰጡት እያስጠረጠሩት፣ እያስተቹት እያስመቱት እንደሆነ ያሰበበት አይመስለኝም፡፡ ማንም ቢሆን ተደፈርሁ ብሎ ላመነበት ጉዳይ አጃቢና ቁጣ እንደማያስፈራው አለመገንዘቡም ስህተት ይመስለኛል፡፡ ያን ጊዜ በብዙ ድካሙና ላቡን አፍስሶ የገነባው ስሙ ሲናድ፣ አሁን "ዘራፍ አካኪ" የሚሉለት አጠገቡ አይገኙም፡፡ ለመሆኑ የፊልም ሥራው በምን ምክንያት ቀረ?
ከላይ እንደገለፅሁት ይህን አስተያየት የፃፍሁት ቀነነኒሳን ታላቅ ሆኖ ለማየት ካለኝ ፍላጎት ብቻ ተነስቼ ነው፡፡ ጉድፎቹን በመንቀስ ንጹህ እንዲሆንና ከፍ ካለ የክብርና የዝና ሰገነት ላይ እንዲወጣ ካለኝ ምኞት ብቻ ነው፡፡ አጉል መካሮች እያሳሳቱት ከሱ ባህርይ ውጭ ወደ ሆነ ተግባር እንዳይተላለፍ አስቤ ነው፡፡ ከፌዴሬሽኑ ጋር ተስማምቶ የቤጅንግ ኦሎምፒክ ድልን እንዲያስጎነጨኝ ባለኝ ከፍተኛ ጉጉት ነው፡፡
ስለዚህ ቀነኒሳ ግራ ቀኙን አይቶ የሚታረመውን አርሞ መካሮቹን በሚገባ አውቋቸው፣ በአዲስ ውጤት እንዲራመድ እንመኝ"" "ከአልባሽ መስሎ ገፋፊ፣ ከደጋፊ መስሎ ገፊ" እንዲሰውረውም እንፀልይለት፡፡ |