| የአዲስ አበባ ውሃ! |
|
|
| Sunday, 11 May 2008 | |
|
በታደሰ ገብረማርያም
በአዲስ አበባ ከተማ በቧንቧ የሚሰራጨው የመጠጥ ውሃ ጥራት የጎደለው፣ በቆሻሻ ዝቃጭ የተበከለና ድፍርስ መሆኑን በየክፍለ ከተሞቹ የሚገኙ አንዳንድ የሕብረተሰብ ክፍሎች ገለፁ፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ የውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ኃላፊ ደግሞ ለመጠጥ የሚውለው ውሃ መቶ በመቶ ጥራቱን የጠበቀ መሆኑን አስታወቁ፡፡ በተለያዩ ቀበሌዎች የሚኖሩት የሕብረተሰብ ክፍሎች እንዳመለከቱት፣ የቧንቧ ውኃ የጥራት ጉድለት ብቻ ሳይሆን መጥፎ ጠረንም አለው፡፡ ብናኝ የመሳሰሉ ነገሮችም ሲንሳፈፉበት ይታያል፡፡ ይህ ዓይነቱ ሁኔታ አልፎ አልፎ ለትውከትና ለተቅማጥ ዳርጓቸዋል፡፡ ነዋሪዎቹ እንዳሉት ይህንን ለመከላከል እያፈሉ ወይም ከባክቴሪያ ነፃ መሆኑ የተረጋገጠ ውሃ እየገዙ መጠጣት የግድ ሆኖባቸዋል፡፡ በባልዲ ወይም በሌላ ማጠራቀሚያ ዕቃ የተቀመጠው የቧንቧ ውሃ ትንሽ ሲቆይ ከሥሩ ብዙ የቆሻሻ ዝቃጭ ተከማችቶ እንደሚያገኙ፣ በተለያየ ምክንያት ውሃው ጠፍቶ ለትንሽ ጊዜ ከቆየ በኋላ ድንገት ሲመጣ ጭቃና ድፍርስ ሆኖ እንደሚወርድ አስረድተዋል፡፡ ከአስተያየት ሰጪዎቹም መካከል በአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ለብዙ ዓመታት አገልግለው በአሁኑ ጊዜ የግል ሥራቸውን የሚያኪያሂዱ፣ ስማቸውና ምስላቸው እንዲገለጽባቸው ያልፈለጉ አንድ መሃንዲስ “የለገዳዲ ውሃ ማጠራቀሚያ (ሪዘርቭየር) ለማዳበሪያ ዝቃጭ የገፈርሳ ውሀ ማጠራቀሚያ ደግሞ ለባክቴሪያ የተጋለጡ ናቸው” ብለዋል፡፡ የለገዳዲ ውሃ ማጠራቀሚያ ለማዳበሪያ ዝቃጭ ሊጋለጥ የቻለው አካባቢው የሚገኙ ገበሬዎች ለምርት ማሳደጊያ የሚጠቀሙበት ማዳበሪያ በዝናብ ወቅት ወደ ማጠራቀሚያው እየገባ የመከማቸት አጋጣሚ ስለሚያገኝ ነው፡፡ ከዚህም ሌላ ከየቤቱ የሚወጣው ደረቅ ሆነ ፍሳሽ ቆሻሻ የሚወርደውም ወደ ማጠራቀሚያው ነው፡፡ የገፈርሳውም በባክቴሪያ ሊጋለጥ የቻለው በአቅራቢያውና በዙሪያው በርካታ ሰዎች በመስፈራቸው ነው፡፡ ሁለቱም ማጠራቀሚያዎች የያዙትን ውሃ ከባክቴሪያና ከሌላም ተውሳክ ለማፅዳት ሲባል ከተወሰነው መጠን (ዶዝ) በላይ ክሎሬን መጨመር የግድ መሆኑን አስተያየት ሰጪው ጠቁመው፣ ከመጠን በላይ የገባው ክሎሬን ደግሞ በጤና ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንደሚያሳድርና ውሃውም የክሎሪን ጠረኑን ይዞ ለብዙ ጊዜ እንደሚቆይ አስረድተዋል፡፡ በአዲስ ከተማ ክፍል ከተማ ቀበሌ 19/20 ነዋሪ የሆነችው ወጣት አሥረስ ዘሩ “ቤተሰቤ ውሃ የሚጠጣው በማሽን እያጣራ ነው፡፡ ውሃው ድፍርስና ቆሻሻ በመሆኑ የተነሳ ማሽኑ ሁልጊዜ በዝቃጩ ይደፈናል፡፡ ስለሆነም በየሁለት ወር እናስጠርገዋለን፡፡ በዚህም ወቅት የሚወጣው ዝቃጭ ሲታይ የአዲስ አበባን ውሃ እንኳንስ ለመጠጥ ለመታጠቢያም ለመገልገል አያስመኝም” ብላለች፡፡ በልደታ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 15/16 ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ጽጌ በቀለ በቧንቧ ውሃ የምናፈላው ሻይ፣ ቡና፣ ወጥ ወዘተ. የክሎሬን ጣዕም እየያዘ ተቸግረናል፡፡ ውሃው ድፍርስ ከመሆኑም ሌላ ዝቃጭ ይበዛበታል፡፡ ለንጽህና መጠበቂያ ካልሆነ በስተቀር የቧንቧን ውሃ መጠጣት ካቆምን ቆይተናል፡፡ በጣም የሚያሳዝነው ይህንን ጉዳይ ተከታትሎ የሚያስተካክል አካል አለመኖሩ ነው” በማለት ተናግረዋል፡፡ ኃላፊው አቶ ጌትነት ገሠሠ በበኩላቸው “የባለሥልጣኑ መሥሪያ ቤት ለከተማው ሕዝብ የሚውል የመጠጥ ውሃ የሚያሰራጨው የዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅት ያወጣውን የጥራት ደረጃ በሚገባ ማሟላቱን ካረጋገጠ በኋላ ነው፡፡ ለጥራት መለኪያ ያስቀመጠውንም መስፈርት 95 በመቶ ያህሉን ያሟላ ውሃ ለመጠጥ ይውላል ብሎ ዓለም አቀፉ ድርጅት አስቀምጧል፡፡ የአዲስ አበባ የመጠጥ ውሃ ግን ከዚህም በላይ መቶ በመቶ ጥራቱን የጠበቀ ነው” ብለዋል፡፡ የውሃው ጥራት የዓለም ጤና ድርጅት ያወጣውን ደረጃ ማሟላቱን የሚያረጋግጥበት በዘመናዊ መልክ የተደራጀ ላቦራቶሪ አለው፡፡ ላቦራቶሪው ከግድቦች፣ ከጉድጓዶችና ከማጠራቀሚያ ጣቢያዎች በየቀኑ የውሃ ናሙና እየወሰደ አስፈላጊውን ምርመራ ያካሂዳል፡፡ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ውሃን በዘመናዊ መልክ ማሰራጨት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የተቀበሩ የውሃ መስመሮች እንዳሉ፣ እነዚህም መስመሮች በዕድሜ ብዛትና በተቀበሩበት አፈር ፀባይ ምክንያት ካልተሰበሩ ወይም ካልበሰበሱና ሌላ ባዕድ ነገር ካልገባባቸው በስተቀር የሚያስከትሉት ጉዳት እንደሌለ አስረድተዋል፡፡ “ለአዲስ አበባ ሕዝብ የሚቀርበው የመጠጥ ውሃ ሳይፈላና ሌላም ነገር ሳይጨመርበት ለመጠጥ እንደሚውል በፍፁም እርግጠኞች ነን” ያሉት ኃላፊው ይህም ሲባል የብክለት አደጋ የለም፣ ሊያጋጥምም አይችልም ማለት እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡ መንገድ ሲሠራ የቧንቧ መስመሮች ይሰበራሉ፡፡ በዚህን ጊዜ አፈርና ቆሻሻ ሊገባ ይችላል፡፡ ለዚህም በቅድሚያ የሚወሰደው እርምጃ ውሃው ወደ ሕብረተሰቡ እንዳይሄድ መዝጋት ነው፡፡ ከዚያም በኋላ ብክለቱን ለማስወገድ ጥረት ይደረጋል፡፡ እንዲህ ዓይነት አደጋዎች የትም ያጋጥማሉ፡፡ ደንበኞች ለመጠጥ የሚጠቀሙበት ውሃ ቀለምና ሽታው ላይ ከተለመደው የተለየ ነገር ሲያጋጥማቸው ዝም ብለው ከመጠቀም ይልቅ ለባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ በስልክ ሊያሳውቁ እንደሚገባ በዚህም የተፈጠረ ችግር ካለ ወዲያውኑ የመፍትሄ እርምጃ ለመውሰድ እንደሚቻል አስረድተዋል፡፡ የቧንቧ መስመሮች በእርጅናና በዝገት ምክንያት የሚያስከትሉትን ጉዳት ለመከላከል ሥራ እየሠራ ነው፡፡ ይህም ማለት የብረት ቧንቧዎች በኘላስቲክ ቧንቧዎች በመቀየር ላይ ናቸው፡፡ ከብዙ ዘመን ጀምሮ የተቀበሩ የውሃ ቧንቧ መስመሮች የት አካባቢ እንኳን እንደተቀበሩ ለማወቅ የሚያስቸግርበት ሁኔታ ነበር፡፡ አሁን ግን ከዚህ ችግር ለመላቀቅ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ናቸው፡፡ በመከናወን ላይ ከሚገኙትም ጥረቶች መካከል በኮምፒውተር መረጃ በመመዝገብ እያንዳንዱ ቧንቧ መቼና የት እንደተቀበረ፣ ምን ያህል ስፋት እንዳለው ለማወቅ የሚያስችሉ እንቅስቃሴዎች እንደሚገኙበት አቶ ጌትነት ገልፀዋል፡፡ አቶ ዘለቀ ተፈሪ በባለሥልጣኑ መሥሪያ ቤት የውሃ ጥራት ቁጥጥር አገልግሎት ኃላፊ በበኩላቸው “የእኛ ሱፐርቪዥን ውሃው ከማጠራቀሚያው ወጥቶ በእያንዳንዱ ኔትወርክ ተሰራጭቶ ዋና ዋና ከባድ መስመር የምንላቸው ነገሮች ውስጥና ከዚያም ከእያንዳንዱ ደንበኛ ቤት እስከሚሄድ ደረስ ነው” ብለዋል፡፡ የቁጥጥሩም ሥራ የሚካሄደው የውሀ መስመር ሲስተሙን ይወክላሉ ተብለው በተመረጡ ከ15 እስከ 2ዐ ቦታዎች ላይ በየቀኑ ናሙና በመውሰድ ነው፡፡ በዚህ ዓይነቱ ቁጥጥር ላይ በመጀመሪያ የሚታየው ውሃው ክሎሪን አለው ወይ የሚለው ነው፡፡ ክሎሪን አለ ማለት ደግሞ ቆሻሻ አልገባበትም ማለት ነው፡፡ ቢገባም መከላከል ይችላል፡፡ ክሎሪን የለም ማለት ደግሞ ውሃው ለብክለት የተጋለጠ ነው ወይም ሊበከል ይችላል፡፡ ለዚህም ወዲያውኑ የመፍትሄ እርምጃ መውሰድ የግድ ይላል፡፡ የባለሥልጣኑ መሥሪያ ቤት ሠራተኞችም ይህ ዓይነቱን የመፍትሄ እርምጃ የመውሰድ ሙሉ ሥልጣን፣ መብትና ኃላፊነት አላቸው፡፡ ይህም ማለት መስመር የሚዘጉት ከበላይ ኃላፊ ወይም ከባለሥልጣን አስፈቅደው ሳይሆን ራሳቸው ናቸው እንዲዘጋ የሚያደርጉት፡፡ ማንኛውም ደንበኛ በውሃው መልክና ሽታ ላይ ለውጥ ማየቱን ለመሥሪያ ቤቱ ለማሳወቅ እንዲችል ያለክፍያ በነፃ የሚደውልባቸው ዘጠኝ የነፃ ስልኮች መዘጋጀታቸውን፣ አንዳንድ ደንበኞችም በዚህ ዓይነት አካሄድ በመጠቀም እንደሚያሳውቁና ወዲያውኑም አስፈላጊውን የመፍትሄ እርምጃ እንደሚካሄድ፣ እንዲህ ዓይነት ጥያቄ በአብዛኛው ከመርካቶ፣ ከሰሜን ሆቴልና ከሽሮ ሜዳ አካባቢ አልፎ አልፎም ከቂርቆስ እንደሚቀርብ ኃላፊው ገልፀዋል፡፡ ውሃው አልፎ አልፎ የክሎሪን ጣዕም አለው ብለው አንዳንድ ወገኖች ይናገሩ ነበር፡፡ መሥሪያ ቤቱ ለመጠጥ ውሃ አገልግሎት የሚጠቀመው የዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅት ባወጣው ደረጃ መሠረት ከዜሮ ነጥብ ሁለት እስከ ዜሮ ነጥብ ስምንት ድረስ ያለውን ክሎሬን ነው፡፡ ይህ ዓይነት መጠን ያለውን ክሎሪን በአፍም ሆነ በአፍንጫ ሴንስ ለማድረግ እንደማይቻል አቶ ዘለቀ አመልክተዋል፡፡ ዶክተር አቻምየለህ አለባቸው በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ የተላላፊ በሽታዎች መምሪያ ኃላፊ ይህንኑ አስመልክተው በሰጡት አስተያየት “የቧንቧና የሪዘርቫየር የውሃ ናሙና ወስደን በኢትዮጵያ የጤናና የሥነ ምግብ ምርምር ኢንስቲትዩት (ፓስተር) አስመርምረን እንዳየነው ከሆነ የንጽህና ችግር የለበትም፡፡ ወይም ለመጠጥ የሚበቃ አይደለም የሚያሰኝ አይደለም” ብለዋል፡፡ ከምንጮችና ከጉድጓዶች የሚገኘው ውሃ ግን የመበከል ሁኔታዎች የሚታዩበት አጋጣሚ እንዳለ፣ ወረርሽኝ ሲከሰትም እንደዚህ ዓይነት ውሃ በሚጠጡ ሰዎች ላይ የከፋ እንደሚሆን አስረድተዋል፡፡ አቶ ገብረ ሥላሴ ገብረ አምላክ በፌደራል አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን የአካባቢ ትምህርትና ግንዛቤ መምሪያ ኃላፊ በበኩላቸው፣ “ከውሃ ማጠራቀሚያ ግድቦች አካባቢ የፍሳሽ እንቅስቃሴ፣ የማዳበሪያና የኬሚካል አጠቃቀም ስለሚከናውኑ ውሀው ከእነዚህ ሁሉ ነፃ ነው ለማለት አያስደፍርም፡፡ ነገር ግን በግድቦቹ የተጠራቀመው ውሃ ደረጃውን የጠበቀና ለሰው ጤና ጉዳት የሌለው መሆኑን ከተረጋገጠና ከተጣራ በኋላ ስለሚሰራጭ ጉዳት አያመጣም” ብለዋል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |