| እቴጌ ጣይቱ ተውኔት ታተመ |
|
|
| Sunday, 11 May 2008 | |
|
በሔኖክ ያሬድ
በጸሐፌ ተውኔት ጌትነት እንየው ተደርሶ ለአንድ ዓመት ተመንፈቅ በአዲስ አበባ ባህልና ቴአትር አዳራሽ ሲታይ የቆየው "እቴጌ ጣይቱ" ታሪካዊ ተውኔት በመጽሐፍ መልክ ታትሞ ለእይታ በቃ፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጻሕፍት ማደራጃ ክፍል (ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ) አማካይነት የታተመው መጽሐፍ ሚያዚያ 27 ቀን 2000 ዓ.ም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ተመርቋል፡፡ የዩኒቨርሲቲው ፕሬስ ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ማስረሻ ፈጠነ በአገሪቱ ለረዥም ጊዜ ተቋርጦ የቆየውን የቴአትር ስክሪፕት (ጽሑፍ) ኅትመት እንደገና በመጀመሩ ተቋማቸው ደስተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ከጸሐፌ ተውኔት ጸጋዬ ገብረ መድኅን "ሀሁ በስድስት ወር"፣ "እናት ዓለም ጠኑ" እና ረሀሁ ወይም ፐፑሪ በኋላ የተውኔት ድርሰት ኅትመት መቆሙን ያወሱት ዳይሬክተሩ የቴአትር ዘመን የሚሸጋገረው ሲታተም በመሆኑ ተቋሙ ጥረቱን እንደሚቀጥልና ሌሎችም በአገሪቱ ለመድረክ የሚበቁት ተውኔቶች ከዘመን ዘመን እንዲሸጋገሩ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ በምርቃው ሥነ ሥርዓት በተውኔቱ ድርሰት ላይ በዶ/ር ዮናስ አድማሱ ሐቲት (ዲስኮርስ) ሲቀርብ፣ የእቴጌ ጣይቱ ዐውደ ሕይወት በተለይ በነገሥታት ጋብቻ ትስስር፣ በኢትዮጵያውያን ንግሥታትና በአፍሪካ ሴት መሪዎች ላይ ያተኮረ ጥናትም ዶ/ር ኄራን ሠረቀ ብርሃን አቅርበዋል፡፡ የእቴጌ ጣይቱ ተውኔት እንዲጻፍ መነሻ የሆኑትና ያስተባበሩት ወ/ሮ ሰሎሜ ታደሰ "ዓድዋ የአፍሪካ ድል ከሆነ፣ እቴጌ ጣይቱ ደግሞ የአፍሪካ ንግሥት መባል ይገባቸዋል" የሚል አቋም እንዳላቸውና ቀደም ሲል 16 እውቅ ሴቶችን በማስተባበር ለእቴጌይቱ በቆረቆሯት አዲስ አበባ ሐውልት እንዲቆምላቸው ጥረት እያደረጉ መቆየታቸውን፣ ይሁን እንጂ በአሜሪካ የተቋቋመው "የጣይቱ ማዕከል" የይገባኛል ጥያቄ በማንሳቱ እስካሁን ምንም ማድረግ እንዳልተቻለ ገልፀዋል፡፡ ወደደፊት ሲኬድ ነባሩን ማስታወስ እንጂ ያለፈውን ማጥፋት አግባብ እንዳልሆነ የጠቆሙት ወ/ሮ ሰሎሜ፣ ባደረጉት ጥረት ተውኔቱ ለግብ መድረሱ እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል፡፡ በዓድዋ ድል 100ኛ ዓመት መታሰቢያ አጋጣሚ የተዘጋጀውና በእቴጌ ጣይቱ ሕይወትና ተጋድሎ ዙሪያ የሚያጠነጥነው "የሸዋ መርፌ" ዘጋቢ ፊልም (ዶክመንተሪ) ከፊል ገጽታ በቀረበበት መድረክ፣ ከተውኔቱ የተመረጡ ቅንጭቦች ለዕይታ በቅተዋል፡፡ 67ኛው የኢትዮጵያ ድል በዓል ምክንያት በማድረግም የዩኒቨርሲቲው ፕሬስ ያሳተመው የማይጨው ዘመቻንና የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ውሎን የሚዘክረው ዜና መዋዕልም ታትሞ መቅረቡ ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |