| የጉራጌ ኪነ ሕንፃ |
|
|
| Sunday, 11 May 2008 | |
|
በምሕረት ሞገስ
የጉራጌ ባህላዊ ቤት በገጠራማው አካባቢ የሚሰራው የኅብረተሰቡን ባህላዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሥነ ምሕዳራዊ ገፅታ በሚያሳይ መልኩ ነው፡፡ እንደየአካባቢው ሥነ ምሕዳራዊ ገፅታ በደጋውም ይሁን በወይናደጋው በአካባቢው የሚገኙ አስፈላጊ ተክሎች ለቤቱ ግንባታ ይውላሉ፡፡ ጽድ፣ ወይራ፣ የዘንባባ ቅጠልና ሳር መሠረታዊ የግንባታው አካሎች ሲሆኑ የእንሰት ውጤት የሆነውም ገመድም ለግንባታው ሚና አለው፡፡ ዶ/ር ፈቃዱ ገዳሙ የጉራጌ ቤትን በሚመለከት ያደረጉት ከፊል ጥናት እንደሚያመለክተው፣ በጉራጌ ባህል ያገባ ወንድ ደረጃውን የጠበቀ ቤት መገንባት ሲኖርበት ሴቲቱ ደግሞ የቤቱን እቃ ማሟላትና ማጋጌጥ ይጠበቅባታል፡፡ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ከጋብቻቸው በፊት በቤት ግንባታና አያያዝ ባለሙያ ሆነው መገኘታቸው ለጋብቻቸው እንደ አንድ መስፈርት የሚወሰድ ብቻ ሳይሆን በትዳር ውስጥ ላለው ቀሪው ጊዜያቸውም የሚመዘኑበት ነው፡፡ በጉራጌ ባህል ቤት ትልቅ ሥፍራ የሚሰጠው ሲሆን ለባለቤቱም የስሙ መጠሪያ ነው፡፡ የጉራጌ ቤት በየቀኑ ለሚከናወኑ ሁነቶች በበአላትና በተለያዩ ዝግጅቶች ወቅት የኅብረተሰቡ ባህላዊ ትስስር የሚገለፅበት ነው፡፡ እያንዳንዱ የጉራጌ አባወራ አቅም ካለው በህይወት ዘመኑ አራት ቤት መገንባት ይጠበቅበታል፡፡ የመጀመሪያው አዲስ መኖሪያ ቤት መገንባት ሲሆን አባወራው ይህንን የሚሰራው ከጋብቻው በመጀመሪያዎቹ ሁለት ዓመታት ውስጥ ነው፡፡ በዚህ ወቅት የሚሰራው ቤት በጣም ትልቅ እንዲሆን አይጠበቅም፡፡ ሆኖም አዲሷን ሙሽራ፣ ሁለት ልጆች እንዲሁም ጥቂት ከብቶችን መያዝ የሚችል መሆን ይኖርበታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አባወራው በሰላሳዎቹ የእድሜ መጨረሻው አካባቢ የሚገነባው ቀጣይ ቤት እስከሚተካው የሚደርስ እድሜ ሊኖረው ይገባል፡፡ አባወራው 4ዐ ዓመት አካባቢ ሲደርስ በቂ ዝግጅቶችን አድርጐ ቀጣዮቹን ሦስት ቤቶች መሥራት ይኖርበታል፡፡ የእነዚህ ቤቶች ግንባታ የሚያስፈልገው ለጋብቻ ለደረሱ ለሴትም ሆነ ለወንድ ልጆች ለጋብቻ ስጦታ ለማበርከት ለድግስና ለተለያዩ በዓላት ማክበሪያነት ስለሚያገለግሉ ነው፡፡ በሌላም በኩል ለዚህ እድሜ የደረሰ አባወራ ቤቶቹን ሰርቶ ማሳየቱ እንደ አንድ የህይወት ግብ ወይም ስኬት ተደርጐ ስለሚወሰድለት ነው፡፡ ሦስቱ ቤቶች የሚገነቡት የእንሰት ተክልን ከግርጌ አድርጎ ነው፡፡ ቤቶቹን ለመስራት ከፍተኛ ሥፍራዎች የሚመረጡትም በእንሰት ተክሎች ላይ የሚደርስ ማኝኛውንም ጥፋት ለመቆጣጠርና ለመቃኘት እንዲያመች ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ጉብታው ላይ ካሉት ቤቶች ሆኖ የእንሰቱን ተክል ልምላሜና መስህብ እያዩ የልምላሜውን ማራኪነት ለማጣጣም ነው፡፡ በአርባዎቹ እድሜና ከዛም በላይ ባለው የዕድሜ ዘመን አባወራው የሚገነባቸው ሦስት ቤቶች በተለያዩ ጊዜያት ሲሆን መጠናቸውም የተለያየ ነው፡፡ የመጀመሪያው ቤት ትልቅ፣ ሁለተኛው መካከለኛ ሦስተኛው አነስ ያለ ነው፡፡ በመሃከላቸው ያለው ርቀትም ከሰላሳ እስከ ሃምሳ ፊት ይሆናል፡፡ ቤቱ የሚገነባው በአካባቢው ለሚኖሩ ማኅበራዊ ክንውኖች አመቺ በሆነ ሥፍራ ነው፡፡ ቤቱ ሲሰራ ከፍ ካለ ሥፍራ ላይ እንዲሆን የሚመረጥበት ሌላው ምክንያት ቁልቁል የሚታየውን ለምለምነት ለማጣጣም ብቻ ሳይሆን አዛውንቶች ተሰባስበው የአካባቢውን ባህላዊና ተፈጥሯዊ ሁኔታ መቆጣጠር ስላለባቸወም ነው፡፡ አካባቢውም የአካባቢውን ማኅበረሰብ ልማዶች ሊያስተናግድ የሚችል መሆን አለበት፡፡ ቤቱ የሚሰራበት አካባቢ ማኅበረሰቡ ለሚያደርገው የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ በቀን ሦስት ጊዜ ቡና አፍልቶ ለመጠጣት፣ መረጃ ለመለዋወጥና የሥራ እቅድ ለማውጣት አመቺ መሆን ይኖርበታል፡፡ እንሰትን ማብቀል ባህላቸው ባደረጉ የጉራጌ አካባቢዎች ተክሎቹ ባሉበት ዙሪያ የሕዝቡን ባህልና አኗኗር መሠረት ያደረገ ቤት የግድ ይኖራል፡፡ ይህ ደግሞ ከጥንት ጀምሮ እያደገ የመጣ መሠረት ያለው ሲሆን የቤቱ አሰራርም የአካባቢውን ሥነ ምህዳራዊ፣ የሃብት ምንጭና ማኅበራዊ ደንቦችን አሟልቶ ነው፡፡ በጉራጌ ቤት እንደሚሰራው የቤት ዓይነት የተለያዩ ዓይነቶች ሙያ ያላቸው ሰዎች ተሳታፊ ይሆናሉ፡፡ ብዙ ወንዶችን የሚያሳትፈው የቤት ግንባታ ወራትን ሊፈጅ ይችላል፡፡ በግንባታው አብዛኛውን ቁጥር ወንዶች ይያዙ እንጂ ለግንባታው አስተዋፅኦ ያደርጋሉ ከሚባሉ የአካባቢው ሰዎች ሴቶች ተሳታፊ እንዲሆኑ ይደረጋል፡፡ የቤቱ አባወራ (የጊ አቢ ወይም አበቃጥ) ለቤቱ ግንባታ ከፍተኛ የጉልበት አስተዋፅኦ የሚያደርጉትን ወንዶች የሚያሰባስብ ሲሆን ሚስቲቱ (የጊ ኢሚት ወይም የቤት እም) ደግሞ ቤቱን ለሚገነቡት ምግብ ለማዘጋጀት ብቻ ሳይሆን ቤቱን ለማስዋብ፣ ለማስጌጥና የግንባታውን የመጨረሻ ሥራ ለማከናወን ሴቶችን ታሰባስባለች፡፡ በሁለቱም ፆታ በኩል የሚሰባሰቡት ለቤት አሰራር ሙያዊ ክህሉት ያላቸው ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ያልሆኑት ደግሞ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ለማድረግ ይመጣሉ፡፡ በጉራጌ የቤት ሥራ የመጀመሪያው የጥድ ግንድ መሰብሰብ ነው፡፡ ለቤቱ ግንባታ የሚከማቸው ግንድ የደረቀውና ቀለሙ ወደ ቀይነት የተቀየረው ነው፡፡ በባህሉ መሠረት ትልቁን ቤት (ማልቅ ጌ ወይም ጐየ) ለመገንባት የጥድ ግንድ ማሰባሰቡ ሥራ ዓመታትን ይወስዳል፡፡ በቤቱ መሃል ለመሃል የሚቆመው ጥድ (ቺባን ወይም ኸችባ) ቀጥ ካለ የጥድ ዛፍ የተቆረጠ መሆን ይኖርበታል፡፡ ለቤቱ ግንባታ የሚያስፈልጉት ቀርክሃ፣ አጠና፣ የዘንባባ ቅጠል ወይም ስንደዶ የመሳሰሉትም በዚሁ ጊዜ አብረው የሚሰበሰቡ ናቸው፡፡ ለግንባታ የሚውሉ ቁሳቁሶች ከተሰበሰቡ በኋላ ቀጣዩ ለግንባታው የሚያስፈልግ መሬት (ከቢት ወይም ሸመነ"ን ማማረጥ ነው፡፡ ቦታው ከተመረጠ በኋላ ከቦታው መሃል ለመሃል ለሚተከለው ቋሚ እንጨት ትክክለኛ ስፍራ ተይዞ በእርምጃ እየተለካ በክብ ይሰመራል፡፡ የመሃል ቋሚው ከተተከለበት በሁሉም አቅጣጫ በእኩል እርቀት ተለክቶ በተሠመረው ክብ መስመር የግድግዳው ቋሚዎች ይተከላሉ፡፡ ጣራውን ለመገንባት ሁለት ዓይነት መንገዶች አሉ፡፡ የመጀመሪያው ዓይነትና ለትልቅ ቤት ግንባታ የሚጠቀሙት ጣሪያ የመሃል ለመሃል ቋሚው አናት ካለበት ተነስቶ ወደ ታች የሚወርድ ነው፡፡ ይህ የሚሆነው ቋሚው በቅጡ ከተተከለና የግድግዳው እንጨቶች ከተማገሩ በኋላ ነው፡፡ ሁለተኛው ዓይነት የጣሪያ ግንባታ አባወራው ከ4ዐዎቹ እድሜው ጀምሮ ለሚገነባቸው ለቀሪዎቹ ለሦስቱ ዓይነት ቤቶች የሚውል ሲሆን አሰራሩም ለብቻው ተነጥሎ መሬት ላይ ነው፡፡ ግድግዳውም ሆነ ጣሪያው ለየብቻቸው ሥራቸው ከተገባደደ በኋላ የመሃል ለመሃል ቋሚውን በመጠቀም መሬት ላይ የተሠራውን ጣሪያ በመግፋት የመሃል ለመሃል ቋሚውን በመወጠር፣ ቤቱ ቅርፁን ይዞ እንዲቆም ይደረጋል፡፡ የጣሪያው የግንባታ መዋቅር ከተዋቀረ በኋላ ከታች ጀምሮ እስከ ላይ ድረስ የማልበስ ሥራው ውበት ባለው መልኩ ይከናወናል፡፡ ጣሪያውን ከስር የማልበስ ሥራው ሲከናወን በቅጡ ለማሠር እንዲመች የቀርክሃ ወይም የባህር ዛፍ እንጨቶች ከስሩ ይደረጋሉ፡፡ ከሸክላ የተሠራ ገንቦም ከውጪ ወጥቶ በሚታየው በቤቱ ቋሚ አናት ላይ ይደረጋል፡፡ ይህ የሚሆነው የቤቱ አናት ውሃ አስርጐ እንዳያሳልፍ ነው፡፡ ግድግዳው በቅጡ በተቦካ ጭቃ ይለሰናል፡፡ በቀይና በነጭ አፈርም ይዋባል፡፡ በሩ የሚሠራው በባህላዊ መልኩ በተዋበና በተለሰለሰ የቀርክሃ እንጨት ነው፡፡ የቤቱ የውስጥ ክፍልም እንደአስፈላጊነቱ እየተለካና ቅርፅ እየተበጀለት ይከፋፈላል፡፡ ቆጥ (ኮቶ) በጉራጌ ባህል የቤት አሰራር መዋቅር ትልቅ ስፍራ የሚሠጠው ሲሆን የሚሰራውም የከብቶች ክፍል ከሆነው አናት ላይ ነው፡፡ በቆጡ ላይም እርጥብ እንጨትን (እንዲደርቅ) ጨምሮ ሌሎች እቃዎችም ይቀመጡበታል፡፡ በቤቱ ውስጥ ለእሳት ማንደጃ የሚሆን መደብ (ጐድረት) የሚሠራ ሲሆን ይህን የምትሰራውም ሴቲቷ የጐረቤቶቿን ጉልበት በማስተባበር ነው፡፡ ቤትን የማስዋብና የማስጌጥ ሥራ ለሴቷ የተተወ ነው፡፡ ግድግዳውን በቀለም ታስጌጣለች፡፡ መሬቱን በአዛባ ታለሰልሳለች፡፡ በሌላም በኩል ለቤቱ ማስጌጫና ለእለት ተእለት መገልገያ ቁሳቁሶች የሆኑትን ማሰሮ፣ የምግብ ሣጠራ፣ መጠጫ፣ ሳህን፣ ማብሰያና የመሳሰሉትን ትገዛለች፡፡ የሚያስፈልጉ እቃዎችን ለሟሟላት ለሚስቲቱ የዓመታት ጊዜን የሚወስድ ሲሆን ጠቀም ያለ ገንዘብ ማጠራቀምም ይኖርባታል፡፡ ከእንሰት ተክል የሚገኘውን ክር ከሳር (አንቾች) ጋር በመግመድ የተለያየ ዲዛይን ያላቸው የወለል ምንጣፎችንም ታዘጋጃለች፡፡ ቤቱን ከመገንባቱም በበለጠ ትልቅ ስፍራና ትኩረት የሚሰጠው በቤቱ ውስጥ መሟላት ያለበት እቃ፣ የቤቱ አጋጌጥና ውበት ነው፡፡ የጉራጌ ባህላዊ ቤት በሚገነባበት ጊዜ ስለግንባታው ከባለሙያው በተጨማሪ የአካባቢው ማኅበረሰብ አስተያየት ይሰጣል፡፡ ይተቻል፡፡ ያየውን ጉድለት ይናገራል፡፡ መስተካከል ያለበትን ይጠቁማል፡፡ የቤቱ ባለቤትም በተሰጠው አስተያየት መሠረት ማስተካከያዎችን ያደርጋል፡፡ በጥንቱ ጊዜ ይሠሩ የነበሩ ባህላዊና ውበት የተላበሱ የጉራጌ ባህላዊ ቤቶች በተለይ ክዳናቸው በቆርቆሮ እየተለወጠ፣ መስኮትና በራቸውም በብረት እየሆነ ነው፡፡ ለቤት ውስጥ ማጋጌጭያ የሚውሉ ቁሶችም በዘመናዊው መንገድ በመተካት ላይ ናቸው፡፡ ነገር ግን አሁንም የጥንቱን ባህላዊ ይዘት አልለቀቁም፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |