|
Sunday, 11 May 2008 |
 በትዕግስት ዘሪሁን ተወልዳ ካደገችበት አሰላ ከተማ ውስጥ የምትኖረው ከአባቷ አክስቶች ጋር እንደነበር ትናገራለች፡፡ እናቷን ገና በልጅነቷ በሞት ስላጣች አታውቃትም፡፡ አባቷም ሌላ ትዳር መሥርቶ ሌላ አገር ይኖራል፡፡ የአባቷ አክስት እንደ ወላጅ እየተንከባከበች አሳድጋታለች፡፡
ገና የስድስተኛ ክፍል ተማሪ ሆና በት/ቤት ውስጥ በተለያዩ ክበባት በመሳተፍ ትታወቅ እንደነበር ታስታውሳለች፡፡ የፀረ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ክበብ አባል በመሆን የተለያዩ ድራማዎችን ትሰራ ነበር፡፡ የክበቡ አባል በመሆኗም በወቅቱ ስለ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ የተሻለ ግንዛቤ እንዳላት ታምናለች፡፡
ወደ ሰባተኛ ክፍል ከተዘዋወረች በኋላ የጓደኞቿ ባህሪ ከበፊቱ መቀየሩን አስተዋለች፡፡ ስለ አለባበሳቸውና ስለ ውበታቸው መጨነቅና ማውራታቸውን ለምዳዋለች፡፡ እሷ እንደምትለው ከጥቂት ጊዜ በኋላ እሷም የእነሱን መንገድ መከተል ጀመረች፡፡ የሚጋብዟቸው ወንዶች ከተገኙም ከወንዶች ጋር ካልሆነም እርስበርሳቸው የተለያዩ ኬክ ቤቶች እየገቡ መገባበዝ ልማዳቸው ሆነ፡፡ የሚገባበዙት ግን ቤተሰብ እንዳያያቸው በድብቅ መሆኑን ትናገራለች፡፡ ፀጉርን ማሰማመር መኳኳልና ስለአለባበስ መጨነቅ እሷም ሆነ ጓደኞቿ እንደ የዕለት ተዕለት ግዴታ ከማየታቸው በተጨማሪ ይሄንን ማድረጋቸውም በእድሜያቸው ውበታቸውን አይተው የሚመ"ቸውን ወንዶች ይበልጥ ይስብ እንደነበር አልሸሸገችም፡፡ ይህ ሁኔታ ግን በህይወቷ ትልቅ ስህተት ውስጥ አስገብቷት አልፏል፡፡
"ሰኔ 30 ነው፡፡ ጓደኛዬ ከቤት ጠራችኝና ካልሄድን አለችኝ፡፡ ልብሴን ቀይሬ አብሬያት ወጣሁ፡፡ የት እንደምንሄድ አላውቅም፡፡ እንደ በፊቱ ሳንቲም አግኝታ አንድ ኬክ ቤት ሄደን ቁጭ እንበል የምትለኝ መስሎኝ ተከተልኳት፡፡" ጓደኛዋ የወሰደቻት ኬክ ቤት ሳይሆን አንዲት ጠባብ መኖሪያ ክፍል ውስጥ ነበር፡፡ የወንድሜ ቤት ናት ብላ ዋሸቻት፡፡ ገብተው ጨዋታ ከጀመሩ በኋላ ከዚህ ቀደም ይጋብዟቸው ከነበሩ መካከል አንዱና አልፎ አልፎም ከረሜላና ማስቲካ እየያዘ ትምህርት ቤት ሲሄዱ መንገድ ላይ እየጠበቀ ይሰጣቸው የነበረ ሰው ብቅ አለ፡፡ ገብቶ ከእነሱ ጋር ጨዋታ እንደጀመረ ጓደኛዋ "መፀዳጃ ቤት ደርሼ መጣሁ" በሚል ሰበብ ጥላቸው ወጣች፡፡ ከዚያ በኋላ የሆነውን ወጣቷ ስትገልጽ "ሰውየው ጓደኛዬ ከወጣች በኋላ ተቁነጠነጠ፡፡ ቶሎ በሩን ከውስጥ ቀረቀረውና መጥቶ ያዘኝ፡፡ ወደዚህ ቤት መምጣቴ ትክክል እንዳልነበረ ገባኝ፡፡ እጮሃለሁ ስለው ፣ወዳኝ ነው የመጣችው እላለሁ፣ ብሎ አስፈራራኝ፡፡ ለነገሩ ብጮህ ሰው ይሰማኛል፣ ያየኛል፣ ቤተሰቦቼም መስማታቸው አይቀርም ብዬ ዝም አልኩ፡፡" ይህ የሆነው ከሁለት ዓመት በፊት ሲሆን ታሪኳን ያጫወተችን ልጅ በወቅቱ የ17 ዓመትና የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ነበረች፡፡
አጋጣሚውን ተጠቅሞ አስገድዶ ከደፈራት ሰው ጋር አልተለያዩም፡፡ ገንዘብ ይሰጣታል፣ ይንከባከባታል፡፡ ከቤተሰቦቿ እየተደበቀች ከእሱ ጋር መዝናናቷን ቀጥላለች፡፡ "ብር ይሰጠኛል ግን ብዙ አይደለም፡፡ እኔም ብዙ ብር አልፈልግም፡፡ በሚሰጠኝ ብር ጫማ ወይም ልብስ ብገዛ ቤት ውስጥ ከየት አመጣሽ ተብዬ እጠየቃለሁ፡፡ ስለዚህ የሚሰጠኝን ብር በሙሉ ጓደኞቼን ነው የምጋብዝበት፡፡ ወደ ትምህርት ቤት ስንሄድና ስንመለስ ሰው አየን አላየን እያልን ተደብቀን መናፈሻ ገብተን እንዝናናለን" ይህንን ስታደርግ ግን በግልፅ ብሩን ማን እንደሰጣት ለጓደኞቿ አትናገርም፡፡ ከሰውየው ጋር ግንኙነት የጀመረችውም በድብቅ እንደሆነ ትናገራለች፡፡
የወጣቷና የሰውየው ግንኙነት ዓመት ሳይደፍን ሰውየው አገር ለቆ ሄደ፡፡ ስሟን መግለፅ ያልፈለገችውና ታሪኳን ያወራችን ወጣት ስለ ሰውየው ትክክለኛ ማንነት ያወቀችውም ከዚሁ በኋላ ነበር፡፡ ሚስትና ልጆች እንዳሉት ጭምር ተነገራት፡፡ በዚህ ወቅት በጣም ለምትቀርባት አንድ ጓደኛዋ ሳትደብቅ የሆነውን ሁሉ ነገረቻት፡፡ ክብረንፅህናዋን ካጣች በኋላ ከሰውየው ጋር በድብቅ የፍቅር ግንኙነት እንደነበራት የምትጋብዛቸውም እሱ በሚሰጣት ብር እንደሆነ ገለፀችላቸው፡፡
ከሰውየው ጋር ግንኙነት እንድትፈጥር ያመቻቸችውና ጠባቧ ክፍል ውስጥ ጥላት የሄደችው ጓደኛዋ ከዚያ በኋላ እንደሸሸቻት ትናገራለች፡፡ በአፍላ የወጣትነት እድሜ እንደዚህች ወጣት አንዳንድ ሴቶች በጓደኞቻቸው ግፊት ሌሎች ደግሞ ጊዜያዊ ደስታና ብልጭልጭ ነገር እያታለላቸው ወደተሳሳተ አቅጣጫ ያመራሉ፡፡ የሚያደርጉትን በግልፅ ስለማይናገሩም መካሪ አጥተው ላልተፈለገ እርግዝናና ለተለያየ ችግር የሚጋለጡበት አጋጣሚ እንዳለ በየአካባቢያችን የምናስተውለው ነው፡፡
ታሪኳን ያጫወተችን ወጣት ስለ ኤች.አይ.ቪና የሥነ ተዋልዶ ጤና በትምህርት ቤት ውስጥ በክበብ ታቅፋ ሌሎች ተማሪዎችን በማስተማር፣ ድራማ በመሥራትና የተለያዩ ዝግጅቶችን በማቅረብ የታወቀች ቢሆንም ለራሷ ግን አልተጠቀመችበትም፡፡ ስለ ኤች.አይ.ቪ መተላለፊያ መንገዶችና መከላከያ ዘዴዎች ታውቃለች፡፡ ከሰውየው ጋር በነበራት የፍቅር ግንኙነት ወቅት ግን ሁሉንም ረስታዋለች፡፡ ኮንዶምም ተጠቅመው እንደማያውቁ ትናገራለች፡፡ የወር አበባ ማየት የጀመረችው በ15 ዓመቷ ቢሆንም የእርግዝና መከላከያ ተጠቅማ አታውቅም፡፡ "እግዚአብሔር ለዚያ አላጋለጠኝም እንጂ ስለ እርግዝናም አስቤ አላውቅም፡፡ ስንገናኝ ድንገት ክላስ ከያዝን ምንም ሳንጠቀም ወሲብ እንፈፅማለን፡፡ ግን በአጋጣሚ አላረገዝኩም"
እሷ እንደምትለው አንድ ቀን ታሪኳን እንደ ዋዛ ካጫወተቻት ጓደኛዋ ጋር የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ምርመራ ለማድረግ ጤና ጣቢያ ገብተው ደም ሰጡ፡፡ በማግስቱ የደም ውጤታቸውን ሲቀበሉ ውጤታቸው የእሷ ፖዘቲቭ የጓደኛዋ ደግሞ ኔጌቲቭ ነበር፡፡ "ሚስትና ልጆች እንዳሉት፣ ከሌላ ሴቶች ጋርም ግንኙነት እንዳለው ብሰማም ኤች.አይ.ቪ ይኖርበታል ብዬ ግን አስቤ አላውቅም ነበር፡፡ ውጤቴ ሲነገረኝ እውነትም አልመሰለኝም" ትላለች፡፡
ውጤቷን ይዛ እንደ እብድ እየሆነች ያመራችው በቅርቡ ትዳር የመሰረተች በዕድሜም ጓደኛዋ የሆነችው የአክስቷ ልጅ ጋር ነበር፡፡ "የአክስቴ ልጅ እንደ ጓደኛዬ ነበረች፡፡ ሄጄ አለቀስኩባት፡፡ እሷ ግን ማመን አቃታት፡፡ ምክንያቱም እኔን ከቤተሰብ እንዲህ ዓይነት ሕይወት ውስጥ ገብታለች ብሎ የሚጠረጥረኝ አልነበረም፡፡ በዕድሜ በጣም ልጅ ነኝ፡፡ በሰፈርም ከወንድ ጋር ታይቼ አላውቅም፡፡ አብረን ተላቅሰን ሲበቃን አብሬያት ለምኖረው ለአባቴ አክስት ነግሬያት ወደ ፀበል እንደምሄድ ተማምነን ተለያየን"
ትናንትና ድራማ ስትሰራበት የነበረው ኤች.አይ.ቪ እሷም ላይ በመድረሱ "እንዲህ ቅርብ ነው እንዴ?" ብላ እንድታስብ ቢያደርጋትም እውነት መሆኑን ውስጧ እያመነ ሲመጣ ግን ተስፋ ቆጠረች፡፡ ከዚያ በኋላ ወደ ትምህርት ቤት ፊቷን እንዳልመለሰችም ትናገራለች፡፡ ለመጀመሪያዎቹ ሁለትና ሦስት ቀናት ከትምህርት ቤት ስትቀር ያቀረበችው ምክንያት አሞኛል የሚል ነበር፡፡ በኋላ ግን በአክስቷ ልጅ ምክንያት ለቤተሰብ ጉዳዩ ይፋ ሆኖ ወደ ሸንኮራ ዮሐንስ ፀበል እንድትጠመቅ ተላከች፡፡
ገና በ17 ዓመቷ መጀመሪያ ጓደኛዋ በፈጠረችው መጥፎ አጋጣሚ በኋላም ራሷ ተገፋፍታ የገባችበት የፍቅር ግንኙነት የስምንተኛ ክፍል ትምህርቷን እንኳን ሳታጠናቅቅ በልጅነቷ ተስፋ እንድትቆርጥ ምክንያት ሆናት፡፡ ብቻዋን ጄሪካኗን አንጠልጥላ፣ የተሰጣትን ገንዘብ ቋጥራ ወደ ሸንኮራ ዮሐንስ ፀበል አመራች፡፡ ለሁለት ወር ፀበል በምትጠመቅበት ወቅት ብር ይዘውላት ከሚመጡ ሰዎች የምትሰማቸው ነገሮች ደግሞ የበለጠ ተስፋ እንድትቆርጥ አደረጓት፡፡ የአባቷ አክስት ለመጣው ሁሉ "የዘመኑ በሽታ ይዟት ፀበል ሄዳለች እያለች እንደምታወራና ልጆቼን ትበክላለች ተመልሳ እዚህ ቤት አትገባም" ማለቷን ሰማች፡፡ አባቷም ስለእሷ ሊጠይቁ ሲደውሉ ስለእሷ ሁኔታ እንደተነገረው አወቀች፡፡ ከዚያ በኋላ ወደ አሰላ ምድር አልተመለሰችም፡፡ ለሁለት ወር ፀበል ተጠምቃ እጇ ላይ ያለው ብር እያለቀ ሲሄድ አባቷ ወደሚኖርበት መተሃራ ተሳፍራ ሄደች፡፡ መተሃራ ደርሳ እንደገና ምርመራ ስታደርግ ቫይረሱ እንዳለባት በድጋሚ አረጋገጠች፡፡ |