|
Sunday, 11 May 2008 |
|
ዴሞክራሲ ጥሩ ነው ብሎ በሚቀበለው (ፕሬስን ጨምሮ) የማንፈታው መጥፎ ችግር የለም በአስፋው ነፃነት
ከ1995 ዓ.ም ጀምሮ ሲያሻውና ሲመቸው እያስገመገመ አለዚያም እያዘገመ፣ እያስፈራራ፣ እያስደነገጠ፣ አንዳንዴ እሳት ለብሶ እሳት ጐርሶ በግልጽና በአደባባይ እየመጣ፣ አለዚያም "ጨለማን ተገን" አድርጐ ተደብቆ፣ ተቀላቅሎ፣ ተመሳስሎና ሰርጐ እየገባ፣ ራሱን የሀሳብ ሸመታ ገበያ ውስጥ ውሱን በግልጽና በአደባባይ "መሸጥ" እና "መለወጥ" ሲያቅተው ቀስ እያለ እያደገ ከፊል አካሉን ዋና ዋና "ብልቶች"ን በ"ችርቻሮ" እና በጥቁር ገበያና በማጣሪያ ሽያጭ ይህነው የሚባል አቢይ ይዘቱን ሸጦ ለውጦ፣ እንደ ሕግም በየቦታው፣ በየአዋጁና በየደንቡ "ፀድቆ" ያለቀው የፕሬስ ሕግ ረቂቅ እነሆ በስድስት ዓመት ረዥም ጊዜ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያ መደበኛ የሕግ አወጣጥ ሥርዓት ውስጥ አጀንዳ ሆኖ ቀረበ፡፡
"የመገናኛ ብዙሃን እና የመረጃ ነጻነት በሚመለከት የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ መርምሮ" ለዝርዝር እይታ ለሚመለከተው ኮሚቴ መምራት የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚያዚያ 30 ቀን 2000 ዓ.ም በተራ ቁጥር አምስት ላይ የተመዘገበ የመጨረሻ "ከተራ እና ቅደም ተከተል አኳያ" አጀንዳ ነበር፡፡ ሦስተኛው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 28ኛ መደበኛ ስብሰባ አጀንዳው ያደረገው፣ ሚያዚያ 30 ቀን 2000 ዓ.ም ባደረገው 28ኛው መደበኛ ስብሰባው "መርምሮ ለዝርዝር እይታ" ለሕግ እና ለአስተዳደር፣ እንዲሁም ለማስታወቂያ እና ባህል ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች የመራው ይህ ረቂቅ ሕግ ለዚህ እስኪበቃ ድረስ በርካታ መስኮችንና፣ ውጣ ውረዶችን "ጽዱ" ያልሆኑ መድረኮችን አቋራጭና የቆረጣ መንገዶችና ዘዴዎችን አሳይቶናል፡፡
ከሁለተኛው የ1992 አገር አቀፍ ምርጫ በኋላ፣ ስለዚህም በ2ኛው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዘመን ከተለመደው፣ በወቅቱም ሆነ ከዚያ በፊት ከሚታወቀው አሰራር ውጭ በማስታወቂያ ሚኒስቴር አማካኝነት ድንገት ሳይጠበቅ በ1995 ዓ.ም ኅዳር/ታህሳስ ወር ብቅ ያለው የመጀመሪያው የአማርኛው ቅጽ ረቂቅ የፕሬስ አዋጅ እስከ 2000 ዓ.ም ሚያዚያ ወር ድረስ በርካታ የማሻሻያ ቅጽዎችን በየቋንቋው (አማርኛና እንግሊዝኛ) አይቷል፡፡ መጀመሪያ በ1995 የቀረበው በዚያው ዓመት በ"ግዮን ሆቴል" የመጀመሪያው ስብሰባ የተሻሻለው ለሐምሌ 96 የግዮን ሆቴል "ብሔራዊ ስብሰባ" የቀረበው፣ በዚህ መካከል በምርጫ 97 ሂደት ውስጥ ወዘተ ድምፁን አጥፍቶ ቆይቶ ኅዳር መጀመሪያ 1999 ዓ.ም ብዙ ዓይን ውስጥ ሳይገባ ብቅ ብሎ እንደገና ወዴት እንደገባ ድራሹ የጠፋው ቅጽ ይገኙበታል፡፡ ከዚያ በኋላ (አሁንም በአማርኛ ብቻ) ሦስት ሌላ የተሻሻሉ ቅጅዎች አይተናል፡፡
ኅዳር 2000 በፓርቲዎች ውስጥ የተሰራጨው፣ ከዚያም ፓክት በሚባል የአሜሪካ መንግሥተዊ ያልሆነ ድርጅት አማካኝነት ኅዳር መጨረሻ ላይ ለ"ውይይት" የቀረበው አሁን ደግሞ ለተወካዮች ምክር ቤት የሚያዚያ 30/2000 ስብሰባ ይፋ የተደረገው ይገኙበታል፡፡ እነዚህ ሦስት ከሞላ ጐደል አንድ ዓይነት ናቸው ሊባሉ ቢችሉም ሦስት የተለያዩ "አዲሽኖች" ስለመሆናቸው ግን እውነት ነው፡፡ በ2000 ዓ.ም የቀረቡትን ሁሉንም ከዚያ በፊት ከቀረቡት የ1995 የ1996 እና የ1999 ረቂቆች ጋር ልዩ ከሚያደርጓቸው መልክ /ገጽታዎች መካከል አንዱ ረቂቁ 2000 ሲጠባ፣ "ሚሌንየሙ"ን ተገን አድርጐ ያገኘው ስያሜ ነው፡፡ የፕሬስ ህግ ረቂቅ ሲባል የነበረው አሁን የመገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ነጻነት ህግ ረቂቅ ተብሏል፡፡
የመገናኛ ብዙሃን የሚለውን ስያሜ በተመለከተ እንዲያ ቢሆን ይሻላል/ይመረጣል የተባለው ስሙ እንደሚያመለክተው ፕሬስን ጨምሮ ሌሎችንም የመገናኛ ብዙሃን፣ ሁሉንም ሚዲያ የሚገዛ ነው ስለሚባል ነው፡፡ ውስጡ ሲገቡ የረቂቁን አዋጅ ሲከፍቱትና አገላብጠው ሲያዩት ይህ እውነት ስለመሆኑ ለመረዳት ብዙ ጥረትና እውቀት (ጊዜም ጉልበትም) የሚያስፈልግ አይደለም፡፡ የ"ጋዜጣ እና የመጽሔት" ሕግ ነው፡፡
ከ2000 በፊት የነበሩት የረቂቁ ሕጐች ቅጅዎች በሙሉ ክፍል ሦስታቸው (የእያንዳንዱን ረቂቅ ቅጅ ሰፋ እና ረዘም ያለ ድርሻ የያዘው ክፍል) መረጃ "የማግኘት መብት"ን የሚመለከት ነው፡፡ ነባር የረቂቅ አዋጁ ስም ያኔ የፕሬስ ሕግ ብቻ ነበር፡፡ አሁን ግን የፕሬስ ሕግ (በአዲሱ የመገናኛ ብዙሃን ሕግ"" መባሉ ሳይበቃ ቀርቶ "የመረጃ ነፃነት ሕግ" ጭምር የተባለው የ2000 ረቂቅ እንኳንስ በይዘት እና በሜሪት በመልክም በቅርጽም አዲስ ተጨማሪ ነገር ሳይዝና ሳይኖረው ነው፡፡
የማስታወቂያ ሚኒስቴር ስድስት ዓመት ያህል ከለፋበት፣ ልፋ ብሎት አለፋሁት ካለው የዚህን የፕሬስ ረቂቅ ሕግ በመረጃ ነጻነት ረቂቅ ድንጋጌዎች (ሦስተኛ ክፍል) ትርጉም የለሽ ወይም ዋጋ ቢስ ከሚያደርጉት ምክንያቶች አንዱ "የመረጃ ነጻነት"ን የሚመለከተው ነው፡፡ የተሰጠው ይህ የሕግ ማውጣት ርዕሰ ጉዳይ ራሱን የቻለ ለብቻው የሚታይ ለብቻው መውጣት ያለበት የየትኛውም አገር የፕሬስ ሕግ አካል አለመሆኑ (አንዱ) ነው፡፡ ይህም በመሆኑ ምክንያት ቅን ልቦና የሚመራው አካሄድና አሰራር ተከትሎ የአቅም ግንባታው ሚኒስትር ሀሳቡንና ጉዳዩን አነቃቅቶና አመንጭቶ ሪሶልቭ ግሩፕ የሚባል የአንድ የደቡብ አፍሪካ የባለሙያና የአዋቂ ቡድን ቋጥሮ ረዥም መንገድ ርቆ የሄደ፣ ከፍ ያለ እርምጃ ያስመዘገበ ሥራ ሰርቷል፡፡ በሪዞልቭ ግሩፕ አማካኝነት የአገሪቷን የኢንፎርሜሽን የነጻነት መብት ሕግ፤ አምጦ ለመገላገል (ጽንሰ ሀሳቡን ለማስተንተን የመሰረታዊ መርሆዎቹን ዳር ድንበር ለመወሰን ጭምር) የተደረገውና የማይነቃና ወደፊት የታሪክ የሰነድ ማስረጃ አስመዝግቦ ያለፈው፣ ነገር ግን የተጨናገፈው ጥረት ውድቅ የተደረገውና ከንቱ ሆኖ የቀረው የማስታወቂያ ሚኒስትር እና የ"ባለሙያዎቹ" ሥራ ይዘትና ሜሪት የተሻለ ሆኖ ብልጫ አግኝቶ ሚዛን ደፍቶ በጭራሽ አልነበረም፡፡
እንኳንስ ይዘትንና ፋይዳን በተመለከተ ቅርጽና መልክን በተመለከተ እንኳን ለፓርላማ የቀረበው "የመገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ነጻነት ሕግ" ገና ከስሙና ከጅምሩ ውድቅ መሆን አለበት የሚባለው የኢንፎርሜሽን ነጻነት ሕግ (አክሰስሎው) ከፕሬስ ሕግ ጋር የማይዳበል የማይደባለቅ በመሆኑ ነው፡፡ የአቅም ግንባታ ሚኒስቴር አማካሪው አድርጐ የቀጠረው የሪዞልቭ ግሩፕ ሥራውን ለብቻው የጀመረውና ይዞት የዘለቀው በዚህ ምክንያት ነው፡፡ የኢንፎርሜሽን ነጻነት ሕግ ራሱን የቻለ ሕግ ነው፤ ደባል ሕግ አይደለም የሚባለው ሪዞልቭ ግሩፕ የተከተለው አሰራር ይኸ በመሆኑ አይደለም፡፡ ወይም የኢንፎርሜሽን ነጻነት ሕግ ከፕሬስ ነጻነት ሕግ ጋር ግንኙነት የለውም ማለት አይደለም፡፡ ኢንፎርሜሽን የማግኘት የነጻነት መብት፣ እንዲሁም የመንግሥትም ሆነ የማንኛውም በሕጉ ውስጥ የሚካተት የግል ተቋም ኢንፎርሜሽን የመስጠት ግዴታ የሁሉም ሰዎች እንጂ የፕሬስ እና የጋዜጠኞች ብቻ አይደለም፡፡ ስለዚህም ራሱን የቻለ ሕግ ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የ1995 ዓ.ምን የፌዴራል መንግሥት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት በዘመኑ መጨረሻ ላይ ለፓርላማ ሲያቀርቡ ከጠቀሷቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ የፕሬስ ሕጉ ረቂቅ ጉዳይ ነበር፡፡ የ1995 ዓ.ም መጀመሪያ እቅድ፣ እንዲሁም ከ1994 ዓ.ም ጀምሮ እየተለመደ የመጣው የአገር የሌጂስሌቲቭ ፕሮግራም እንደ እቅድም በስምም ሳያነሳው የፕሬስ ሕጉ ረቂቅ ለመጀመሪያ ጊዜ በዚህ ደረጃ ስሙ የተነሳው የእቅድ አፈጻጸሙ ሪፓርት ሲቀርብ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፕሬስ ሕጉ ረቂቅ ወደተከታዩ የፓርላማ ዓመት መሸጋገሩን እና ምክንያቱን ሲገልጹ ያስረዱት ከፕሬስ ሕጉ ጋር የማስረጃ/ኢንፎርሜሽን ነጻነት ሕግ ጭምር ለብቻው ስለሚያስፈልግ ይህም እየተጠናና እየተዘጋጀ መሆኑን በማቅረብ ነበር፡፡
አገራችን ሀቀኛና ከፖሊሲ እና ከመርህ ቁርጠኝነት የመነጨ የኢንፎርሜሽን ነጻነት ሕግ እንደሚያስፈልጋት የማይካድ ከሆነ ይህ ሕግ ተወጥኖና ታቅዶ በአጭር እንዲቀር ሳይፈርድበት በፊት እንደተጀመረው ራሱን የቻለና ለብቻው መውጣት አለበት የሚል መከራከሪያ የማቀርበው ጉዳዩ ከዚህ በፊት በዚህ መልክ የተጀመረ ነው ሪሶልቭ ግሩፕ ያደረገውም ይህንኑ ነው፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የ1995 ሪፖርትም ይህንን ያረጋግጣል ከሚል መነሻ በመነሳት አይደለም፡፡ መንግሥት ከሌሎች መካከል የመረጃዎች አስቀማጭና ባለ አደራ የሚሆነው በሥራው አጋጣሚ ምክንያት በሕዝብ ስም ነው፡፡ ሕዝብም የራሱን መረጃ ኢንፎርሜሽን ማግኘትና ማወቅ አለበት፡፡ ማወቅና እውቀት ኃይል ነው፡፡ ድንቁርና ቀንበር ነው፡፡ የሕዝብ ሉዓላዊነት መገለጫው አንደኛው መንገድ በእውቀት ላይ የተመሰረተ ተሳትፎና ምርጫ እንዲሁም ተግባር ነው፡፡ የዚህም መረጃ ባለቤትነትና መብት ፕሬስና ጋዜጠኛ ብቻ ሳይሆን ማንም ሰው፣ የትኛውም የሰው ዘር በሙሉ ነው፡፡ ከዚህም የተነሳ የመረጃ/የኢንፎርሜሽን ነጻነት ሕግ የፕሬስ ሕግ አካል የመገናኛ ብዙሃን ሕግ ደባል አይደለም፡፡
የአገርን፣ የሕዝብን እና የፕሬስን ጭምር መሠረታዊ ሰብዓዊ መብቶችና ነጻነቶች እያመመ የእነሱም ሕመም እየሆነ እራሱም እየታመመ ስድስት ዓመት የዘለቀው የመገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ነጻነት ሕግ አርቃቂዎችና ሊቃውንት በዚህ ረገድ እና ባለፉት ስድስት ዓመታት የሚያቀርቧቸው መከራከሪያዎች ግን አለመታደል ሆኖ፣ በመርህ ወይም በፕሪንሲፕል ላይ የተመሰረቱ ሳይሆኑ "ከአገር ልስጥህ" ዓይነት የእንካ ስላንትያ ላይ የተንጠለጠሉ ናቸው፡፡ ስለዚህም የኢትዮጵያ የመረጃ ነጻነት ሕግ "እንደ ስዊድን የፕሬስ ሕግ የሚዲያና የመረጃ ነጻነት ድንጋጌዎችን በአንድ ላይ አካቶ የያዘ"". ነው፡፡ እውነት ነወይ?
እውነት ነወይ ስል መጀመሪያ ከተራ ቁም ነገር እና እውነት (ፋክት) አኳያ ነው፡፡ መጀመሪያ በ1766 የወጣው ከዚያም በኋላ በ1812 እንደገናም እንደ አዲስ በ1949 ዓ.ም ተሻሽሎ እስከ አሁን ድረስ በሥራ ላይ ያለው የስዊድን ዘፍሪደም ኦፍ ዘ ፕሬስ አክት ወይም የፕሬስ ነጻነት ሕግ አስራ አራት ምዕራፎች ያሉት ሲሆን ከእነዚህ መካከል አንዱ ማለትም ሁለተኛው ምዕራፍ On the public nature of official documents (የኦፊሴላዊ ሰነዶች ይፋነት) የሚል ስምና ርዕስ ያለው ነው፡፡ 16 አንቀጾች ያሉት "ፕሬስ ነጻነት ሕግ" ውስጥ የተካተተው የስዊዲን "የመረጃ ነጻነት" ሕግ ዓላማ የአገራችን የፕሬስ ሕግ አርቃቂዎች እንከተለዋለን እንደሚሉት የፎርምና የመልክ ሳይሆን ከዚያም በላይ የይዘትና የዓይነተኛነት (ሰብስታንስ) ፋይዳ ያለው ነው፡፡
ስዊድን የመረጃ ነጻነት ድንጋጌዎችን የያዘውን ምዕራፍ በአገሯ የፕሬስ ነጻነት ሕግ ውስጥ ያካተተችውና የሱም አካል ያደረገችው ራሱ የስዊድን የፕሬስ ነጻነት ሕግ የአገሪቷ ሕገ መንግሥት አካል በመሆኑ ነው፡፡ ስለዚህም የስዊድን ሕገ መንግሥት የሚባሉት ሰነዶች መካከል አንዱና ዋነኛው የፕሬስ ነጻነት ሕግ ነው፡፡ ሌሎቹና ዋነኞቹ ዘ ኢንስትሩመንት ኦፍ ገቨርንመንት የፓርላማ አሰራር ሕግ የዘውድ አወራረስና ተራ ሕግ ናቸው፡፡
የስዊድንን የፕሬስ ሕግ (የኦፊሴል ዶኪዩሜንቶችን ይፋና ግልጽነት ከሚደነግጉት አንቀጾች ጋር) የአገር መሠረታዊና የሁሉም የበላይ ሕግ የማድረግ አስፈላጊነት የመጣው የትኛውም የሕግ መንግሥቱ ክፍልና አካል (የፕሬስ ነጻነት ሕግ እያንዳንዱን ድንጋጌ ጨምሮ) ለማሻሻልና ለመለወጥ በመካከላቸው አጠቃላይ ወይም አገር አቀፋዊ ምርጫ የሚለያየው የሁለት ፓርላማዎች አንድ ዓይነትና ቁርጥ-አምሳያ የሆነ ውሳኔ ያስፈልጋል፡፡ ምን ማለት ነው? ስዊድን ውስጥ የፕሬስ ነጻነትን ሕግ በመላ ወይም አንዲት አንቀጽ ለመለወጥና ለማሻሻያ መጀመሪያ በአንድ የፓርላማ የሥራ ዘመን ውስጥ የፕሬስ ሕጉን የሚያሻሽለው የሚለውጠው ሕግ መጽደቅ አለበት፡፡ በዚህ ብቻ ግን አያበቃም፡፡ ይህ ፓርላማ የሥራ ዘመኑን ከፈፀመና ከተበተነ በኋላ ሌላ በምርጫ ሥልጣን የሚይዘው ፓርላማም ከእሱ በፊት የነበረው ፓርላማ በተናገረበት ቋንቋና ቃል የእነሱ ተመሳሳይ የማሻሻያ ሕግ፣ ማፅደቅ አለበት፡፡ በሁለቱ አምሳያ የሕግ ማሻሻያዎች መካከል ቢያንስ የአንድ ዓመት ልዩነት ሊኖር ይገባል፡፡
የኢትዮጵያ የፕሬስ ሕግ ረቂቅ ይህን ያህል ዘመን ፈጅቶ አሁን "በመጨረሻ" ፓርላማ ለመቅረብ የታደለው ይህን የመሰለ እልክ አስጨራሽና ጥብቅ የሕግ አወጣጥ ስነስርዓት የሚከተል ስለሆነ እሱንም ስለመከተሉ ሊያረጋግጥ አለመሆኑን አሁን ሁሉም እያወቀው መጥቷል፡፡ አሁን ለፓርላማ የቀረበው ሚያዚያ 30 የዋለው የ28ኛው (የ3ኛው ፓርላማ 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን) መደበኛ ስብሰባ አጀንዳ ለመሆን የበቃው የሕግ መሻሻያ ረቂቅ እዚህ ከመድረሱ በፊት በርካታ ዋነኛና አበይት አካሎቹንና ድንጋጌዎቹን በየቦታውና በየጊዜው እያራገፈ ሕግ ሆነው መዳኘታቸውን በጉልበቱ እያረጋገጠ አምሳያና ተወዳዳሪ የሌለው "ጀብድ" የሠራ የሕግ ረቂቅ ነው፡፡
ይህ አሁን በረቂቅነት የቀረው ረቂቅነቱ እንዲፀድቅለት የሚያደርገው ሕግ ካለውና ቀድሞን ካልፀደቀ በቀር ወደፊት በሕጉ የይዘት እና የሜሪት ዝርዝር ላይ በሰፊው እናወራለን እንነጋገራለን ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ከፀደቀም የሚመጣ ልዩነት ይኖራል ብዬ ስለማልገምት በተመሳሳይ ሁኔታና በዚያው ልክ የምናወራውና የምንነጋገርበት ነገር ያንኑ ያህል ብዙና ሰፊ ነው ብዬ እገምታለሁ፡፡ በሁለቱ ዓይነት ውይይቶችና ንግግሮች መካከል ሊኖር የሚችለው ልዩነት የኋለኛው ጨርሶና የለየለት የድህረ ምት (ፓስት ሞርተም ኤግዛሚኔሽን) ምርመራ ውጤት ስለሚሆን ብቻ ነው፡፡
እዚህ ላይ አንድ መሠረታዊ ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም፡፡ ይህን የፕሬስ ረቂቅ ህግ ሲጀመር አንስቶ የለየለት አፋኝና ጨቋኝ ነው፡፡ ድራኰንያን ነው፡፡ አልተባለም ወይ? ሕጉ ወጣም አልወጣም ነባሩ ሕግ ቀጠለ አልቀጠለም እስካሁን እንዳየነው በየትኛው ዘርፍ የአገር መተዳደሪያ ሕግ ሳይሆን የሆነ "በጐ ፈቃድ"ና መልካም ምኞት ነው፡፡ ይህ በተለዋወጠ ቁጥር ውሎውም አስተዳደሩም ይለያያል፡፡
ለፓርላማ የቀረበው የሕግ ረቂቅ አዲስ ነገር አለበት ወይ ብሎ መጠየቅም ተገቢ ነው፡፡ አዲሱ ነገር የይዘት ሳይሆን ሕጉን ለማውጣት መሠረትና መነሻ የተደረገው ምክንያት ነው፡፡ የረቂቁ ማብራሪያ ይህንን በሚከተለው መልክ ያቀርበዋል፡፡
ይህን ግብ ተግባራዊ ለማድረግም በግሉ የሚድያ ዘርፍ ውስጥ የሚታዩትን መሠረታዊ ችግሮች በመለየት ችግሮቹን ለመቅረፍ በመንግሥት መወሰድ የሚኖርባቸው እርምጃዎች በዝርዝር ተለይተዋል፡፡
በግሉ የመገናኛ ብዙሃን ዘርፍ ውስጥ ላሉ ችግሮች አስተዋፅኦ በማድረግ የጎላ ድርሻ ከነበራቸው መሠረታዊ ምክንያቶች መካከል፡-
በንግዱ ሕብረተሰብ ውስጥ ሰፍኖ የቆየው የኪራይ ሰብሳቢነትና ያየር ባየር አሰራር ከታዳጊው የንግድ ሚድያውም ውስጥ ሰፍኖ መቆየቱና ሚድያው እንደ አንድ የኢንዱስትሪ ዘርፍ ተዋቅሮ በኩባንያዎች ለመንቀሳቀስ አለመቻሉ የባለቤት የትርፍ ፍላጎቶች ከሙያ ግዴታዎች ጋር የጥቅም ግጭቶች የሚፈጥሩበትን ሁኔታ በመፍጠር የሙያ ነፃነትን የሚያስተጓጉል የባለንብረቶቹንና የሙያተኞቹን ግንኙነት ያዘባረቀ አሰራር መስፈኑን፣ የበርካታ ንግድ ሚድያዎች ኢኮኖሚያዊ ህልውና ከማስታወቂያ ገቢ ሳይሆን ከህግ ውጭ በቀጥታና በእጅ አዙር መንገድ በሚደጉሟቸው የውስጥና የውጭ ደጓሚዎች ላይ ተንጠልጥሎ መቆየቱ፡፡ ይህም በሚዲያው መሀል መኖር የሚገባውን ጤናማ ውድድር በመገደብ በኃላፊነት ስሜት የማይመራ ኢ ስነምግባራዊና ጋጠወጥ አሰራርን የመደበኛው ፕሬስ (main stream press) ይዘት አብይ መለዮ ሆኖ መቆየቱ፡፡ በነጻ ገበያ እና በህግ የበላይነት መርህ የሚንቀሳቀስ የሚዲያ ኢንዱስትሪ ለማጠናከር የሚያስችሉ ተቋማዊና መዋቅራዊ ችግሮች ለንግድ ውድድሩ ፍትሀዊነት ዋስትና የሚሰጥ የሕግ ማዕቀፍ አለመኖሩ (ለምሳሌም የመገናኛ ብዙሃኑ ዋነኛ የገቢ ምንጭ የሆነውን ማስታወቂያን የሚመለከት የህግ ድንጋጌ አለመኖሩ) ወዘተ ተጠቃሽ ሊሆኑ የሚችሉ ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው፡፡
ህልውናቸው ከማስታወቂያ በሚገኝ ገቢ ላይ ያልተመሰረተው በርካታዎቹ የግል ህትመት ሚድያ ተቋማት በስውር ወይም በተዘዋዋሪ መንገድ ለሚደጉሟቸው ሕገወጥ የሃገር ውስጥና የውጭ የፋይናንስ ምንጮች ህገወጥ ዓላማዎች ማስፈፀሚያ ሆነው ቆይተዋል፡፡ በህገ መንግሥታዊና በዴሞክራሲያዊ ተቋማትና አሰራሮች እንዲሁም በተቋማቱ መሪዎች፣ በተለያዩ የህብረተሰቡ የቋንቋ፣ የባህልና የእምነት ቡድኖች ላይ ተደጋጋሚ ስልታዊ የማጥላላትና የማነሳሳት ጥቃቶችን ሲፈፅሙ ቆይተዋል፡፡ የህዝቡን ዴሞክራሲያዊና ልማታዊ ተሳትፎና ተነሳሽነቶች ለማምከን የታሰቡ ስልታዊ ጥቃቶችን በይፋ አካሂደዋል፡፡ ከእነሱ የተለዩ ተወዳደሪ የሚድያ ውጤቶች ሕዝቡ እንዳያነባቸው ይፋዊ የማዕቀብ ጥሪዎችን በማድረግና የማከፋፈያ ኔትወርኮችን አገልግሎት በመንፈግ፣ በሀሰት በመወንጀልና በማጥላላትና በርካታ ህትመቶችን ለኪሳራ ዳርገዋል፡፡ ለፕሬስ ነጻነት ተፃራሪ የሆኑ በርካታ ህገወጥ ጫናዎችንም ፈጥረዋል፡፡ ለብሔራዊ ፀጥታና ደህንነት አስጊ በሆኑ ህገወጥ የጥፋት ተግባራት (ህገ መንግሥታዊ ስርዓቱን በሃይልና በአመፅ ለማፍረስ በማነሳሳት፣ ብሔራዊ ኢኮኖሚውን የሚያዳክሙ ህገወጥ አድማዎችንና ማእቀቦችን በማነሳሳት ህዝቡ ከዴሞክራሲያዊና ልማታዊ ተሳትፎዎች እንዲታቀብ በይፋ በመቀስቀስ ወዘተ ተግባራት) ላይ እስከመሰማራት የደረሱባቸው ሁኔታዎችም ጥቂት የሚባሉ አልነበሩም፡፡ ችግሩ የቱ ነው? ረቂቁ ሕግ፣ ከዚያም በፊት በ"ችርቻሮ" የፀደቁት የረቂቁ ሕግ አካል የነበሩ ክፍሎቹና ድንጋጌዎቹ ያቀረቡት "መፍትሄ"? ወይስ መፍትሄውን በውጤትነት አስከትሎ የተባሉት "ችግሮች" "መፍትሄ" የተባለውን ነገር ለመቅረፍ የቀረበውን ምክንያት ጨምሮ መፍትሄ የተባሉት ሁሉ ዴሞክራሲን መሠረት ያላደረጉ መሆናቸው ከዴሞክራሲ ማዕቀፍ የወጡ በመሆናቸው ራሱ አንድ ትልቅና አብይ ችግር ነው፡፡
ዴሞክራሲያ ውስጥ ከሚገኝ ከየትኛውም ጥሩ ነገር ወጥተን የምናስወግደው ምንም ዓይነት መጥፎ ነገርም ሆነ ችግር የለም ብሎ ማመን ራሱ የዴሞክራሲ መሠረተ ሀሳብ ሀሁ ነው፡፡ |