Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Wednesday
Aug 20th
Home arrow Sections arrow የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት...
የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት... Print E-mail
Thursday, 15 May 2008
የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ም/ቤት ሕንፃ ተመለሰ

በዳዊት ታዬ

የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት በአዋጅ ተወርሶበት የነበረውን ባለ ሠባት ፎቅ ሕንፃ መልሶ እንዲመለስለት በቀድሞ መንግሥት ውሣኔ ላይ መደረሱን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ መግለፃቸውን ተከትሎ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ ግርማ ብሩ በትላንትናው ዕለት ሕንፃው መመለሱን ለምክር ቤቱ በደብዳቤ አረጋገጡ፡፡ ሕንፃው ለተገነባበት ዓላማ እንደሚውልም የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት አስታወቁ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከትናንት በስቲያ ከንግዱ ሕብረተሰብ ጋር በጽ/ቤታቸው አዳራሽ ባደረጉት ውይይት ላይ እንደገለፁት የንግድ ምክር ቤቱ ሕንፃ እንዲመለስ ተደጋጋሚ ጥያቄ ቀርቦ እንደነበር አስታውሰው በቅርቡም ጥያቄው በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በኩል ቀርቦ በጥያቄው ዙሪያ ጥናት ሲደረግ መቆየቱንና የሕንፃው መመለስ ተገቢ መሆኑ እንደታመነበት አመልክተዋል፡፡

ይህንን ሕንፃ ለመመለስ እንደ ችግር ይታዩ ከነበሩት ምክንያቶች ውስጥ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ሊዛወሩት የሚችሉበት ቦታ የሌላቸው መሆኑና የእነርሱን የሥራ ቦታ ለመሸፈን የሚጠይቀው ወጪ ቀላል ባለመሆኑ እንደነበርም አስረድተዋል፡፡

“በሌላ በኩል ግን ከምክር ቤቱ እንደተጠቀሰው ምክር ቤቱ ራሱን ችሎ እንዲንቀሳቀስ ለመደገፍና ቢያንስ መነሻ እንዲሆንና ገቢ እንዲያገኝ ሕንፃው መመለሱ ሊደግፈው እንደሚችል በተደረገው ጥናትና በተደረገው ምክክር መሠረት መንግሥት ላይ የሚፈጥረው ጫና ቀላል ባይሆንም ሁሉንም አማራጮች በማየት ሕንፃው ለምክር ቤቱ ቢመለስ ይሻላል የሚል አቋም ተይዟል” በማለት ህንፃው እንዲመለስ መወሰኑን ለንግዱ ሕብረተሰብ አብስረዋል፡፡

በዚሁ ሕንፃ መመለስ ዙሪያ በሰጡት የማጠቃለያ መልስ ላይ “በዚሁ መሠረት ሕንፃው ይመለስላችኋል” ብለው “በሕንፃው ላይ ያሉ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች አማራጭ እስኪገኝላቸው ድረስ በተመጣጣኝ ዋጋ እንደምትከራዩን ተስፋ አደርጋለሁ” ብለዋል፡፡

ይህ የምክር ቤቱ ህንፃ ሊገነባ የቻለው በ1951 ዓ.ም የንግድ ምክር ቤት ሕንፃ እንዲገነባበት አፄ ኃይለሥላሴ 3 ሺህ 994 ካሬ ሜትር ቦታ ከሰጡ በኋላ ሲሆን የሕንፃው የመሠረት ድንጋይም በ1954 ዓ.ም አኑረዋል፡፡

ይህ በሜክሲኮ አደባባይ አካባቢ የሚገኘው ሕንፃ 152 ክፍሎች፣ ሁለት የኮንፈረንስ አዳራሾች፣ አንድ ኮሚቴ መሰብሰቢያ ክፍል፣ አንድ የኤግዚቢሽን አዳራሽና የተሟላ ባርና ሬስቶራንት ኖሮት ባለሰባት ፎቅ ሆኖ የተሠራ ሲሆን ግንባታው ተጠናቅቆ ሥራ የጀመረው በ1957 ዓ.ም መሆኑንም ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡

ይህ ሕንፃ በወቅቱ የተገነባው ከንግዱ ሕብረተሰብ በተዋጣ ገንዘብና መንግሥት በቦታ መልክ ለሰበሰበው ቀረጥ ለህንፃው ማሰሪያ በማዋለ ነው፡፡ በዚህ መንገድ የተገነባው ይህ ሕንፃ በወቅቱ የፈጀው ሙሉ ወጪ 1 ሚሊዮን 806 ሺህ ከ63 ሣንቲም ብቻ ነበር፡፡

በአሁኑ ወቅት የዚህ ሕንፃ ግምት ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ሊኖረው እንደሚችል አንድ ያነጋገርናቸው አርክቴክት ገልፀው ሕንፃው የተገነባበት ዋጋ በሜክሲኮ አደባባይ አካባቢ በአሁኑ ወቅት ለ4000 ካሬ ሜትር ቦታ ከሚከፈል የሊዝ ዋጋ ከእጥፍ በላይ የሚያንስ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው አየነው እንደገለፁት የሕንፃው መመለስ ትልቅ ድል ነው፡፡ ከዚህ በኋላም ሲገነባ ለተቋቋመለት ዓላማ ይውላል፡፡

በአሁኑ ጊዜ በአዲስ አበባ ውስጥ ያሉ የምክር ቤቱ አባላት የሆኑ የዘርፍ ምክር ቤቶች በተበታተነ ቦታ የሚኖሩ በመሆኑ ሁሉም ወደዚህ ሕንፃ እንዲገቡ ይደረጋል ብለው በሕንፃው ላይ ከ3 - 7ኛ ፎቅ ላይ የሚገኘው የአገር ውስጥ ገቢ ባለስልጣን መሥሪያ ቤትም አማራጭ ቦታ እስኪያገኝ በተመጣጠነ ዋጋ እንዲገለገልበት ይደረጋልም ብለዋል፡፡ ቀሪ ክፍሎችን ደግሞ በማከራየት ለምክር ቤቱ ማጠናከሪያ እንደሚውልም አመልክተዋል፡፡
 
< Prev   Next >