| ዲሽ የሌላችሁ ... እንደምን አመሻችሁ |
|
|
| Sunday, 13 January 2008 | |
|
የሳተላይት ዲሽ የሌላችሁ እንደምን አመሻችሁ፡፡ ከዚህ ቀጥለን ዜና እናሰማለን..... እያለ ሰላምታ እንደሚያቀርብ፣ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ዝግጅት ይዘትና አቀራረብ ቅሬታ ያላቸው ሰዎች ያወራሉ፣ ይቀልዳሉ፡፡ አባባሉ ዲሽ ያለው ቤተሰብ በአሁኑ ጊዜ ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እየራቀ የውጭ ፕሮግራሞችን በሳተላይት ዲሽ ማየቱን እየመረጠ ነው ለማለት ነው፡፡
በደስታ የሚነገር ቀልድና ስላቅ ሳይሆን ቴሌቪዥናችን ከዚህ የተሻለ አቀራረብ ለምን የለውም? ከሚል ቅሬታና ንዴት የመነጨ በመሆኑ ቀልዱ መራር ይሆናል፡፡ የሚሳለቅ ባይጠፋም አብዛኛው ግን ከተቆርቋሪነትና የተሻለ ሊሰራ ይገባል ከሚል አዎንታዊ መንፈስ ነው፡፡ በርግጥም የተሻለ አቀራረብና ይዘት ሊኖረው ይገባል፡፡ በተለይ በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ከኢትዮጵያ ድንበር ወጥቶ በአሜሪካ፣ በአውሮፓ፣ በአፍሪካ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ እየተሰራጨ በመሆኑ በርካታ ኢትዮጵያውያን ሊከታተሉት እድል ያገኘ ስለሆነ ራሱን አሻሽሎ መቅረብ ይገባዋል፡፡ ይህን ለመፃፍ የተነሳሳነው ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጥሩ ገፅታ አዝነንና አስበን አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በሕዝብ ገንዘብ የሚንቀሳቀስ ድርጅት ነው፡፡ ስለዚህም የሕዝብ ገንዘብ በአግባቡ ሥራ ላይ መዋል አለበት፡፡ በጀት ሥራ ለማከናወን ተብሎ የሚመደብ ስለሆነ የተመደበው በጀት በተፈለገው ሥራ መገለጡንና አለመገለጡን ማንሳት የህዝብ አጀንዳን ማንሳት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የሕዝብ ገንዘብና በጀት በአግባቡ ሥራ ላይ እየዋለ ነው ለማለት አይቻልም፡፡ በሕዝብ በጀት እየተሰሩ ያሉት ዝግጅቶች ሕዝብ ራሱ ካልተከታተላቸውና ቴሌቪዥን የማይመለከት ከሆነ ገንዘቡ ለሕዝቡ ጥቅም ውሏል ለማለት አይቻልም፡፡ የተወሰነው ጥሩ ጥሩ ፕሮግራሞች ይከታተላል፡፡ ሌላው አይከታተልም፡፡ ለማይታየው የወጣው ገንዘብ እየባከነ ነው ማለት ነው፡፡ እኛ ካቀረብን ባይከታተል ..የራሱ ጉዳይ ነው.. ተብሎ ሃላፊነት ማውረድም አይቻልም፡፡ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ችግር የበጀትና ገንዘብ የማባከን ችግር ብቻ አይደለም፡፡ ሕብረተሰቡ ተገቢውን መረጃ እንዲያገኝ ያለማድረግ ችግርም ነው፡፡ እንኳን መንግሥትን የማይደግፍ እንቅስቃሴ ሊያሳውቅ ይቅርና የመንግሥትን አኩሪ ስራዎችና እንቅስቃሴዎችንም በአግባቡ ለሕዝብ ማድረስ አቅቶታል፡፡ መንግሥት ስለሰራቸው መገናኛዎች፣ መንገዶች፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የሃይል ማመንጫዎች፣ ሕንፃዎች እና ከተሞች እንዲሁም የኤሌክትሪክና የእርሻ ኢንቨስትመንቶች በአግባቡ ለሕዝብ መቅረብ አልቻሉም፡፡ ችግሩ የይዘት ብቻ አይደለም፡፡ የአቀራረብ ጭምር ነው፡፡ እጅግ አሰልቺ የሆነ አቀራረብ አለ፡፡ ይዘቱ ጥሩ ባይሆንም አጥሮና ሳቢ አድርጎ ከማቅረብ ይልቅ የተንዛዛና አሰልቺ የሆነ አቀራረብ ዋነኛው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ስልት ስለሆነ ሕዝብ ሰልችቶት እስከ መጨረሻው ለማየት አይቃጣም፡፡ በተለይም ዲያስፖራው የተለያየ የቴሌቪዥን አቀራረብ የማየት ዕድል ስላለው የእኛውን አሰልቺና የተንዛዛ አቀራረብ አይወደውም፡፡ ስለዚህ ሳይወድ ይርቃል፡፡ የሚርቀው እየተናደደ ነው፡፡ እንደዚህ ያለ ቴሌቪዥን መንግሥትን እንዴት ሊጠቅም ይችላል? አንዱ በቴሌቪዥን አቀራረብ የሰለቸ ተመልካች ..ልጆቼ ተኙ ብያቸው እምቢ ካሉኝ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ፊት አስቀምጣቸውና ፍንግል፣ ፍንግል ብለው ይተኙልኛል.. እያለ የሚቀልደው ብዙ ሊገልፅ ይችላል፡፡ ምናልባት ይህ አላስፈላጊ ፅንፈኛ አገላለጥ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ቅሬታ ያለው ግብር ከፋይ የሚጠቀምበት አገላለፅ ስለሆነ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ ምናልባት የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን ለማየት የማይወዱ ሰዎች መንግሥትን የማይወዱና ተቃዋሚዎች ናቸው፤ የሚል ጊዜው ያለፈበትና የተለመደ መልስ ሊሰጥ ይችል ይሆናል፡፡ ነገር ግን ይህ አባባል በእጅጉ የተሳሳተ ነው፡፡ ተቃዋሚ የመሆንና አለመሆን አይደለም፡፡ የመንግሥትን እንቅስቃሴ ማወቅ የሚፈልጉ፣ ስለአገራቸው በጎ ነገር የናፈቁ ሰዎች በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ላይ ያላቸውን ቅሬታ እንደሚገልጡ መጠራጠር ጥቅም የለውም፡፡ ስለዚህ ምን ይደረግ? ችግሩ ከታወቀ የባለሙያ እጥረት ነው? የአመራር ችግር ነው ወይስ ሌላ? ተብሎ ተጠንቶ አስፈላጊ አወቃቀርና ፖሊሲ ሊቀረፅለት በስልጠናም ሊታገዝ ይገባል፡፡ አንዱ የሚታየው ችግር የአሰሪ ብቃትና የፈጠራ ነፃነት አለመኖር ስለሆነ ዴሞክራሲያዊና ሙያዊ ሁኔታ ሊፈጠር ይገባል፡፡ ዴሞክራሲያዊ ሂደት እንዳይኖር ያደረጉ ሰዎች፣ ራሳቸውም ተመልሰው የማያሰራ ኢዴሞክራሲያዊ ሁኔታ አለ ማለት የሚጀምሩት ብዙ ጥፋት ከፈፀሙ በኋላ መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ በነገራችን ላይ አንድ መነሳት ያለበት ነጥብ አለ፡፡ ቴሌቪዥን ከመንግሥት ወጥቶ በግል መያዝ የሚለው ሃሳብ በየትኛውም አለም ያለ አስተያየት ነው፡፡ እኛ ግን ይኸ ሁሉ ቀርቶብን እስቲ የመንግሥት ቴሌቪዥን ይኑርና ይዘቱ ግን የሕዝብ አገልጋይ እናድርገው እያልን ነው፡፡ ይህን አንገብጋቢ ጥያቄ አድርገን ከመውሰድ ይልቅ መንግሥት ቴሌቪዥን የሚያሻሽል አዋጅ ያውጣ እንላለን፡፡ ጎን ለጎን ግን የግል ቴሌቪዥንም መፈቀድ እንደሚገባ መርሳትም ስህተት መሆኑን እናስታውሳለን፡፡ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የማስተካከያ ርምጃ ጊዜ የሚሰጥ አይደለም፡፡ አስቸኳይ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ከማንም የተሻለና የተጠናከረ ውጭ አገርም የሚሰራም መገናኛ ብዙሃን ነውና፡፡ በአሁኑ ጊዜ መንግሥት ጭምር ተጠቃሚ አይደለም፡፡ ሁሉም ተጠቃሚ እንዲሆን በአስቸኳይ ይለወጥ.. ይዋቀር.. ፖሊሲ ይውጣለት.. ባለሙያ ይኑረው.. ..ዲሽ የሌላችሁ.. የሚለውን ትቶ በቀጥታ ..እንደምን አመሻችሁ.. ብሎ የሚጀምር ቴሌቪዥን እንዲሆን ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |