| በ15 ሚሊዮን ብር የተገነባ... |
|
|
| Thursday, 15 May 2008 | |
በ15 ሚሊዮን ብር የተገነባ ፋብሪካ በግብረ ኃይል ፈረሰበአሰግድ ተፈራ በአንድ የቱርክ ዜግነት ባላቸው ባለሀብትና በሁለት ኢትዮጵያን በሽርክና የተቋቋመው የፒቪሲ ፋብሪካ የሚገኘው በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 02/03 በቤት ቁጥር 115 ተመዝግቦ ነው፡፡ “ከበላይ አካል ታዝዘን ነው” በማለት ቅጥር ግቢ ሰብረው በመግባት ፋብሪካውንና ቢሮዎቹን ሙሉ በሙሉ ያፈረሱት የቀበሌ አፍራሽ ግብረ ኃይል አባላት የፈፀሙት ተግባር ሊታመን የማይችል እንደሆነ የፋብሪካው ባለሀብቶች ይናገራሉ፡፡ ክፍለ ከተማው በበኩሉ በተሰጠው ስልጣን ፋብሪካው እንዲፈርስ ማድረጉ ትክክል መሆኑን ይገልፃል፡፡ ቱርካዊው ሸሪክ ሚ/ር ኤሮል ኩርት ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ለኢንቨስትመንት ምቹ መድረክ በመፈጠሩ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ መንግሥት ላደረገላቸው ቀልጣፋ ትብብርም ያመሰግናሉ፡፡ ፋብሪካው ሥራ በጀመረ በአስረኛ ወሩ “የማይታመን መአት ወረደ፤ ፋብሪካ አውድሙ ብሎ ትዕዛዝ የሰጠው ማን እንደሆነ መንግሥት ያጣራው” በማለት ይጠይቃሉ፡፡ የክፍለ ከተማው የደንብ ማስከበር ጊዜያዊ አስተባባሪ አቶ ካሳሁን ለማ ፋብሪካው ያረፉበት ቦታ የይዞታ ማስረጃ የለውም፡፡ የይዞታ ማስረጃ የሌለው ቦታ ላይ የግንባታ ፈቃድ አውጥቶ መገንባት ስለማይፈቀድ ፋብሪካው እንዲፈርስ መወሰኑን ያስረዳሉ፡፡ የፋብሪካው ከፍተኛ ባለድርሻ ያላቸው አቶ ሙዲን ፋሪስ እድሪስ የአቶ ካሳሁንን ምክንያት አይቀበሉትም፡፡ ይልቁኑም ክፍለ ከተማው በአንድ ኢትዮጵያዊ ላይ ሊፈፀም የማይገባ ርህራሄ የጐደለው ተግባር መፈፀሙን ነው የሚገልፁት፡፡ “ክፍለ ከተማው ከቶውን ሊተባበረን አልፈለገም፡፡ ጊዜ ጠብቆ በሽግግር ወቅት የለፋንበትን ንብረት አወደመብን፡፡ ለዚህም ተጠያቂው ዋና ሥራ አስፈፃሚው ናቸው” የሚሉት አቶ ሙዲን “አንድ ሕዝብን የሚመራ አስተዳደር ሦስት ዓመት ሙሉ ካርታና የይዞታ ማስረጃ ከልክሎ ሰያመላልሰን መቆየቱ ሊያሳዝነው ሲገባ ጊዜ ጠብቆ የለፋንበትን ንብረት ማውደሙ ያስጠይቃል” ባይ ናቸው፡፡ በክልል 14 መስተዳደር የዞን 5 የወረዳ 8 ፍርድ ቤት ሰኔ 15 ቀን 1987 ዓ.ም. የሟች አቶ ማህሙድ ባልድጋ ባለቤትና ወራሾች መሆናቸውን ማወቁን፣ የኘራይቬታይዜሽን ኤጀንሲም ከ10 ዓመት ክርክር በኋላ ታህሳስ 5 ቀን 1992 ዓ.ም. በቁጥር 20/ነ2/357/7471/92 ፋብሪካው ያረፈበት ቦታ ከአዋጅ ውጪ በቀላጤ የተወረሰ መሆኑን ጠቅሶ ለሟች ወራሾች እንዲመለስ ትዕዛዝ ማስተላለፉን መረጃ በማስደገፍ አቶ ሙዲን ያስረዳሉ፡፡ “ይህ ሁሉ ማስረጃ ክፍለ ከተማው እጅ መግባቱንና ካርታ እንዲሰጥ ከተጠየቀ ሦስት ዓመት ሞልቷል፡፡ ካርታ ከልክለው ካርታ አምጡ ይሉናል” በማለት ያማርራሉ፡፡ ቦታውን ሲረከቡ ቀደም ሲል የነበሩትን 23 አባወራዎች ከቀበሌ ጋር በመነጋገር በተሰጠ ቦታ ላይ ምትክ ቤት መስራቱን፣ ነዋሪዎቹ ሲነሱ የነበረው ቤት ሲፈርስ ለጊዜው የቆርቆሮ ጊዜያዊ መጋዘን እንዲሰሩ የቀድሞ አስተዳደር እንደወሰነላቸው የገለፁት አቶ ሙዲን “ጥፋት ቢኖርብን እንኳ ፋብሪካውን በማሸግ ወይም በማገድ ማስተካከያ ማድረግ ሲችል እንደ ጠላት ንብረት ፋብሪካውን በመውረር ማፈራረስ ንፁህ ህሊና ካለው ዜጋ የሚጠበቅ አይደለም፡፡ ይህ እንዲሆን ያዘዙት በሙሉ በፍርድ መጠየቅ አለባቸው” የክፍለ ከተማው ዋና ሥራ አስፈፃሚ ከማሟያ ምርጫው 1ዐ ቀን በፊት ጀምሮ ግንባታ የማፍረስ፣ ካርታ የመስጠትና ከመሬት ጋር ተያያዥነት ያላቸው ስራዎች እንዳይሰሩ ከጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ትዕዛዝ ተሰጥቶ እያለ ሚያዚያ 10 ቀን 2004 ዓ.ም. ፋብሪካው እንዲፈርስ ለምን ትዕዛዝ እንደሰጡ ተጠይቀው “ቦታው የይዞታ ማስረጃ ካርታ ካለው ብቻ እንነጋገራለን፡፡ ካርታ ስለሌለው ፈረሰ” የሚል መልስ ብቻ ሰጥተዋል፡፡ ከዚህ በላይ የተጠቀሱት ማስረጃዎችና ወራሾች ካርታ እንዲሰጣቸው የጠየቁበትና ጥያቄያቸው ላለፉት ሦስት ዓመታት መልስ ያላገኘበትን ምክንያት ለማብራራት ፈቃደኛ አይደሉም፡፡ የመሬት ልማት አስተዳደር ኃላፊ አቶ ዳንኤል ሊሬቦ የተለየ መልስ አላቸው፡፡ ላለፉት አምስት ወራት በኃላፊነት እንደቆዩ የገለፁት አቶ ዳንኤል ስለፋብሪካው መፍረስ፣ የይዞታ ማስረጃ ካርታ ስለመጠየቁ የሚያውቁት ነገር የለም፡፡ ጉዳዩም አልቀረበላቸውም፡፡ የደንብ ማስከበር ጊዜያዊ አስተባባሪው አቶ ካሳሁን ግን “ፋብሪካው እንዲፈርስ የተደረገው የመሬት ልማት አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈፃሚና ዋና ስራ አስኪያጁ በወሰኑት መሠረት ነው” በማለት የመሬት አስተዳደር ኃላፊው በውሳኔው ውስጥ አለበት ይላሉ፡፡ የመሬት አስተዳደር ኃላፊው “በጭራሽ ጉዳዩን አላውቀውም፡፡ የፈረሰ ፋብሪካ ስለመኖሩም አላውቅም፡፡ ከዛሬ ጀምሮ በእኔ በኩል መታየት ያለበት ጉዳይ ካለ አጣራዋለሁ” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ የፋብሪካው ሦስተኛ ሸሪክ አቶ ሰለሞን ኃይሉ 15 ዓመት ጀርመን ሲሰሩ ቆይተው የመጡ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ “በሰው አገር ለፍቼ ቀንና ሌሊት የሰራሁበትን አገሬ ይዤ መጥቼ ልማት ላይ አዋልኩ፡፡ በማይታመን ሁኔታ እንዲህ ተደረገ” በማለት የፋብሪካውን ፍርስራሽና በውሃ እየበሰበሰ ያለውን ማሽን እያሳየ ይናገራል፡፡ “በኢትዮጵያዊነቴ እንዴት ልኩራ?” ይላሉ አቶ ሰለሞን አንድ ኢትዮጵያዊ ሌላው ዜጋው ለፍቶ ያገኘውን ንብረት ያለርህራሄ ሲበታትነውና ከጥቅም ውጪ ሲያደርገው ያሳዝናል፡፡ “የጠላት ንብረት ይመስል ፋብሪካ ማውደም ምህረት የማያሰጥ በደል እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ ለማንኛውም መንግሥት ይፍረድ” “ወደ ውጪ አገር ስሄድ ተጠብቆ በማግስቱ ፋብሪካውን አፈራረሱት” የሚሉት አቶ ሙዲን ሁለቱ ሸሪኮቻቸው እሳቸውን አምነው ለአደጋ መጋለጣቸው አሳዝኗቸዋል፡፡ “ፋብሪካው ሙሉ በሙሉ ፈርሷል፡፡ የውጪ አጥር ተሰብሯል፡፡ ቢሮዎቹ ፈርሰዋል፡፡ ማሽኖቹ ዝናብ እየመታቸው ነው፡፡ ቢፈርስስ ብልሽት ሊፈጥር በማይችል መልኩ ሊከናወን አይችልም ነበር?” በሚል የተጠየቁት የደንብ ማስከበር ጊዜያዊ አስተባባሪው አቶ በለጠ “ግንባታው እንዲፈርስ ትዕዛዝ እስከተሰጠበት ጊዜ ድረስ ያለውን ጉዳይ አውቃለሁ፡፡ የማፍረስ ስራው ሲሰራ ግን ሌላ ሥራ ስለነበረኝ በአካል አልነበርኩም፡፡ ስለ አፈራረሱ ሁኔታ ማስረዳት አልችልም” የሚል መልስ ሰጥተዋል፡፡ ጊዜው የሽግግር በመሆኑ የአዲስ አበባ ከተማ ጊዜያዊ ባለአደራ አስተዳደርን ምላሽ ማግኘት አልቻልንም፡፡ አንድ ኃላፊ ግን “ቆርቆሮ ቤት ፈረሰባቸው፣ ቆርቆሮ ይስሩ” በማለት ባለጉዳዮች ፊት ተናግረዋል፡፡ የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም አቤቱታው እንደቀረበለት ሚያዚያ 9 ቀን 2ዐዐዐ ዓ.ም. ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማት አስተዳደር ዋና ሥራ አስኪያጅ ፅህፈት ቤት በፃፈው ደብዳቤ ጉዳዩን ዘርዝሮ ማብራሪያ ጠይቋል፡፡ “. . . ከቀረበው ጉዳይ አንፃር መርምረን የመፍትሄ ሃሳብ ለመስጠት እንችል ዘንድ ካርታና የግንባታ ፈቃድ የማይሰጥበት ምክንያት ምን እንደሆነ ይህ ደብዳቤ በደረሳችሁ በ1ዐ ቀናት ውስጥ እንድትልኩልን እናሳስባለን” ይላል የተቋሙ ደብዳቤ፡፡ ፋብሪካው ሲፈርስ በቪዲዮ ካሜራና በሞባይል ስልካቸው ሲቀርፁ የነበሩ የፋብሪካው ኃላፊዎች ፖሊስ አስሮ የቀረፁትን እንዳጠፋባቸው ስራ አስከያጁ ገልፀዋል፡፡ በጉዳዩ ላይ ፖሊስ መልስ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆነም፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |