| የዘውዲቱ ሆስፒታል በአሳዛኝ ሁኔታ ይገኛል |
|
|
| Sunday, 13 January 2008 | |
|
የአዲስ አበባ ጊዜያዊ ባላደራ አስተዳደር ከንቲባ ብርሃነ ደሬሳ የዘውዲቱ ሆስፒታል በየጊዜው ጥገና አለማግኘቱና ተገልጋዩ ሕብረተሰብ የሚያሰማው እሮሮ እንዳሳዘናቸው ከትናንት በስቲያ በተለይ ለሪፖርተር ጋዜጣ ተናገሩ፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ ሥር የሚገኘው የዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል ሥራውን ሊያቋርጥ እንደሚችል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የማህበራዊ ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ስጋታቸውን መግለፃቸውን አስመልክቶ ለጠየቅናቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ከንቲባ ብርሃነ ደሬሳ፣ ሆስፒታሉ በአሳዛኝ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ጠቁመው የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢውን ስጋት እንደሚጋሩት ተናግረዋል፡፡ የጊዜያዊ ባላደራ አስተደደሩ ካቢኔ በሆስፒታሉ ላይ ችግር መኖሩ ሪፖርት እንደደረሰው ልዩ ትኩረት በመስጠት ከካቢኔው የተወከሉ አባላት ሆስፒታሉን ጎብኝተው ሪፖርት እንዲያቀርቡ በመደረጉ፣ በሆስፒታሉ ተፈጥሮ የነበረውን የውሃና ፍሳሽ መስመር ችግር ለአጭር ጊዜ ጥገና 60ሺ ብር መድቦ ለቀጣይ ያለውን ችግር ለመፍታት፣ የመሰረተ ልማትና ግንባታ ሥራዎች ባለሥልጣን የሕንፃውን ጥገና ዝርዝር የዲዛይን ጥናት እንዲያሰራና ጉዳዩን ለፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ተከታትሎ እንዲያስፈጽም ውሳኔ ማስተላለፉን ከንቲባ ብርሃነ አብራርተዋል፡፡ የሆስፒታሉን ችግር ለዘለቄታው ለመፍታት በ2000 በጀት ዓመት ለመነሻ አራት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ለዕድሳት በጀት መመደቡን፣ የአገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል፣ በለተይ ለፕላንት፣ ማሽነሪና ለሌሎች መሳሪያዎች ግዥ ሁለት ሚሊዮን 170ሺ 360 በጀት መፈቀዱን ከንቲባው ተናግረዋል፡፡ ዘውዲቱ ሆስፒታል ለረጀም ጊዜ ጥገና ያልተደረገለት መሆኑን፣ የሚሰጣቸው አገልግሎቶች እንዲሻሻሉና መሰረታዊ ጥገና እንዲደረግ የከተማ አስተዳደሩ በተለየ መልኩ በጀት ከተመደበላቸወ ተቋማት አንዱ መሆኑን የገለፁት ከንቲባ ብርሃነ፣ ..እንደ ዘውዲቱ ሆስፒታል የመሳሰሉ ትላልቅ ለሕዝብ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትን በመንግሥት ብቻ መልሶ ለማቋቋም ከመጣር ይልቅ፣ እንደኔ አስተያየት ሌሎች አማራጮችን ማየት ያስፈልጋል.. ብለዋል፡፡ ለዜጎቻቸውና ለአገራቸው ወሳኝ አገልግሎት ለሚሰጡ (ዶክተሮች) ባለሙያዎች ልዩ ትኩረት መስጠትና ክፍያቸውን ተመጣኝ ማድረግ፣ (ሁሉም አገሮች የሚጠቀሙበት ዘዴ ነው) ቤት ሰርቶ ካልተሰጣቸው (ሆስፒታ ቅጥር ገቢ ውስጥ..፣ በነፃነትና በነፃ የሚኖሩበረት ነገር ካልተመቻቸላቸው፣ በቀላሉ የማይተኩ ሙያተኞችን ማጣት እንደሚያስከትልና ሆስፒታሎችም ሙያተኛ አልባ እንደሚሆኑ ያላቸውን ስጋት ተናግረዋል፡፡ ከንቲባ ብርሃነ እንደገለፁት ከተማ አስተዳደሩ የጤና ትምህርት ሴክተሮችን ግቦች ለማሳካት በቅርቡ አንድ ቢሊዮን ብር በእቅድ መያዙን፣ በበጀት ዓመቱ በጤና ዘርፍ የታቀዱትን ሥራዎች ለማስፈፀም በ1999 በጀት ዓመት ከነበረው ጠቅላላ የከተማው በጀት ሁለት በመቶ ወደ አምስት በመቶ እንዲያድግ ተደርጓል፡፡ በ2000 በጀት ዓመት ለዘርፉ የተመደበው ጠቅላላ በጀት ብር 159 ሚሊዮን 822 ሺ 806 ብር መድረሱን አቶ ብርሃነ ተናግረዋል፡፡ ኤች.አይ.ቪን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በ2000 በጀት ዓመት 53 ሚሊዮን 497ሺ 976 ብር መመደቡን፣ በአጠቃላይ በጤናቸው ዘርፍ 213 ሚሊዮን 320 ሺ 782 ብር መመደቡን ከንቲባ ብርሃነ ገልፀዋል፡፡ አስተዳደሩ በየወቅቱ ለሚከሰቱ የጤና ችግሮች ልዩ ትኩረት እንዲሚሰጥ የተናገሩት ከንቲባ ብርሃነ፣ በ1999 በጀት ዓመት ተከስቶ ለነበረው የአተት (አጣዳፊ ተቀማጥና ትውከት) መከላከያ 7 ሚሊዮን 730 ሺ 574 ብር በመመደቡ በሽታው ሳይስፋፋና ጉዳት ሳይደርስ መቆጣጠር መቻሉን፣ በአጎራባች ኦሮሚያ ክልል ተከስቶ የነበረውን ወረርሽኝ ለመከላከል 85ሺ 382 ብር የሚገመት ሙያዊ እገዛ ማድረጉንና በድሬዳዋ ተከስቶ ለነበረው ድንገተኛ የጎርፍ አደጋ ጋር ተከትሎ የሚመጣውን የጤና ጠንቅ ለመከላከልና ተጎጂዎችን ለማቋቋም አንድ ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰዋል፡፡ በታምሩ ጽጌ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |