Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Saturday
Jul 05th
Home arrow Sections arrow "ህወሓት በዓረና ላይ የማጥላላት...
"ህወሓት በዓረና ላይ የማጥላላት... Print E-mail
Sunday, 13 January 2008

Image"ህወሓት በዓረና ላይ የማጥላላት ዘመቻ እያካሄደ ነው"
ወ/ሮ አረጋሽ አዳነ

በቅርቡ የተመሰረተው የዓረና ትግራይ ለዴሞክራሲና ለሉዓላዊነት ፓርቲ መስራችና ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ወ/ሮ አረጋሽ አዳነ፣ ህወሐት በአዲሱ ፓርቲያቸው ላይ የማጥላላት ዘመቻ እያካሄደባቸው መሆኑን ገለፁ፡፡

ወ/ሮ አረጋሽ ይህንን ያሉት ከሪፖርተር ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ነው፡፡ እንደ እሳቸው አባባል አዲሱ "ዓረና" ፓርቲ በሕዝብ እንዲጠላና ፕሮግራሙን እንዳያስተዋውቅ ለማድረግ ህወሐት የማጥላላት ዘመቻ እያካሄደባቸው ነው፡፡ በትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ፀጋይ በርሀ የተሰጠው መግለጫ በክልሉ አንድ ተቃዋሚ ሀይል ፕሮግራሙን ሕዝቡ ድረስ ወርዶ ለማስረፅ አያስችልም፡፡

ወ/ሮ አረጋሽ ይህንን ሲያብራሩ በመግለጫው የተሰጠው ትችት በያዙት ፕሮግራምና አመለካከት ላይ የተመሰረተ ሳይሆን፣ ድርጅቱ ወደ ሕዝብ እንዳይቃረብና ሕዝብ የተለየ ሀሳብ እንዳይሰማ በሩን የመዝጋት አጠቃላይ የማጥላላት ዘመቻ መሆኑን ነው፡፡

"ረዓረናሪ ተጨባጭ አላማ የሌለው፣ የትግራይን ሕዝብ ለመከፋፈል የመጣ፣ እንዲሁም የተጀመረውን የዲሞክራሲና የልማት ሂደት ለማደናቀፍ የተደራጀ ፓርቲ ነው ወዘተ." በሚል የማጥላላት ዘመቻ ተከፍቶበታል ያሉት ወ/ሮ አረጋሽ፣ "ህወሐት የተለየ ፕሮግራም ይዞ የሚመጣና የፖለቲካ ድርጅት ለማስተናገድ ምንም አይነት ዝግጅት እንደሌለውና የዴሞክራሲ ሂደቱ ልዩነቱን የሚያቻችል ሳይሆን ወደ ግጭት የሚያመራ አቅጣጫ ያዘለ መልክት ነው" ብለዋል፡፡

"በትግራይ ውስጥ ከሕወሐት ውጭ ምንም አይነት ፓርቲ እንደማያስፈልግና ክልሉ ከአንድ ፓርቲ በላይ የመሸከም አቅም የለውም የሚል አስተሳሰብ በህወሐት እየተሰራጨ መሆኑን ወ/ሮ አረጋሽ አረጋግጠዋል፡፡ የሕዝቡን አንድነት አስመልክተው "የትግራይ ሕዝብ በምክንያት እንዲሰባሰብ እንጂ በስሜት እንዲከፋፈል የኛ አቋም አይደለም" ብለዋል፡፡

ወ/ሮ አረጋሽ የትግራይ ሕዝብ እንደማንኛውም የኢትዮጵያ ሕዝብ አማራጭ እንዲያገኝና የፖለቲካና የመደራጀት ነፃነቱ እንዲጠበቅለት በማሳሰብ፣ "ፓርቲያችን ፕሮግራም ለሕዝብ የሚጠቅም አማራጭ አስቀምጧል ወይስ አላስቀመጠም በሚል ብቻ መፈተሽና መመርመር አለበት" ብለዋል፡፡

"ሌሎች ሕዝቦች ለምን አይከፋፈሉም?" በማለት የጠየቁት ወ/ሮ አረጋሽ፣ "የትግራይ ሕዝብ ሊከፋፈል የሚችል አማራጭ ሳያገኝ ሲቀር እና ነፃነቱ ሲታፈን ብቻ ነው" በማለት የህዝቦች አማራጭ የማግኘት መብታቸው ሊከበር እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

"የሕወሐት አላማ" አሉ ወ/ሮ አረጋሽ፣ "የህወሐት አላማ በጣም ግልፅ ነው፡፡ ድርጅቱ ትግራይ ውስጥ ያመጣው ለውጥ የለም፣ ሕዝቡ መሮታል፡፡ ስለሆነም አማራጭ የፖለቲካ ድርጅት ከመጣ ሕዝቡ ህወሐትን እንደማይመርጥ ጠንቅቆ ያውቃል፡፡" በማለት እንቅስቃሴው የፖለቲካውን የመወዳደር መድረክ በመዝጋትና የሰውን አዕምሮ ስሜት ውስጥ አስገብቶ ለመቆጣጠር መሆኑን ግልፅ አድርገዋል፡፡ ወ/ሮ አረጋሽ አዳነ በቆይታ አምድ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በየማነ ናግሽ

 
< Prev   Next >