| ፀረ ሙስና በስድስት የጉምሩክ ሰራተኞችና... |
|
|
| Sunday, 13 January 2008 | |
|
ፀረ ሙስና በስድስት የጉምሩክ ሰራተኞችና በአንድ ነጋዴ ላይ ክስ መሰረተ የፌዴራል ሥነ - ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ዐቃቤ ሕግ ስልጣን አላግባብ በመጠቀም በሕዝብና በመንግሥት ጥቅም ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል በሚል በጠረጠራቸው ስድስት የኢትዮጵያ ጉምሩክ ሰራተኞችና በአንድ ግለሰብ ነጋዴ ላይ ታህሳስ 16 ቀን 2000 ዓ.ም ክስ መሰረተ፡፡ የኮሚሽኑ ዐቃቤ ሕግ ክስ የመሰረተባቸው ተጠርጣሪዎች፣ በአዲስ አበባ ላገር ጉምሩክ ሁለት የጨረታ ኮሚቴ አባሎች፣ አንድ የጨረታ ኮሚቴ አባልና ፀሐፊ፣ አንድ ተጠባባቂ የመጋዘን ሀላፊና ለጨረታ ሽያጭ የሚቀርቡ ዕቃዎች ዝርዝር መዝግቦ አቅራቢ፣ አንድ የውርስ መጋዘኖችና የሃራጅ ሽያጭ ዋና ክፍል ሃላፊና አንድ ግለሰብ ነጋዴ ናቸው፡፡ ተጠርጣሪዎቹ በ1949 የወጣውን የኢትዮጵያ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ አንቀፅ ቁጥር 32(1) (ሀ)፣ 33 እና የተሻሻለውን ልዩ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ አዋጅ ቁጥር 214/74 አንቀጽ 23/1/ሀ/ለ/እና /2/ ላይ የተመለከተውን በመተላለፍ ወንጀል ፈፅመዋል በሚል ነው፡፡ ተጠርጣሪዎቹ የተሰጣቸውን ሀላፊነት ወደ ጎን በመተው በአዲስ አበባ ላጋር ጉምሩክ ጣቢያ በ16/3/91 ዓ.ም በኮንትሮባንድ ተይዘው በሞዴል 265 የደረሰኝ ቁጥር 195910 ገቢ ከተደረጉት ለግድግዳና ለጠረጴዛ አገልግሎት የሚውሉ ፕላስቲኮች (ፒ.ቪ.ሲ ሺትስ) ብዛት 877፣በ27/07/96 በጨረታ ቁጥር 034/96 ዕቃው ተይዞ ገቢ የተደረገበትን ለጠረጴዛና ለግድግዳ አገልግሎት የሚውሉ የሚለውን ስም በመቀየር የግድግዳ ወረቀት በማለት፣ እንዲሁም በገቢዎች ሚኒስቴር ሕዳር 9 ቀን 1996 በቁጥር መተ4አ/65/5 የተሰጠውን መመሪያ ወደ ጎን በመተው ከላይ የተጠቀሱትን ዕቃዎች ለሀራጅ በማቅረብ በዝቅተኛ ዋጋ እንዲሸጡ አድርገዋል በሚል ክስ መመስረቱን የኮሚሽኑ ዐቃቤ ሕግ ያቀረበው የክስ ቻርጅ ያመለክታል፡፡ በአጠቃላይ ተከሳሾቹ የአዲስ አበባ ላጋር ጉምሩክ ጣቢያ በ16/03/91 ዓ.ም በኮንትሮባንድ ተይዘው በሞዴል 265 የደረሰኝ ቁጥር 195910 ገቢ ከተደረጉት ለግድግዳና ጠረጴዛ አገልግሎት ሊውሉ ከሚችሉት ፕላስቲኮች (ፒ.ቪ.ሲ ሺት .. ብዛቱ 877 ሮል /ጥቅል መካከል በ27/7/96 ዓ.ም በጨረታ ቁጥር 034/96 የዕቃውን ስም በመቀየር የግድግዳ ወረቀት በማለት 762 የሆነውን ሮል/ጥቅል በትክክለኛ የጨረታ ሥነ ስርዓት ዋጋ ቢሸጥ ከ1 ሚሊዮን 900 ሺ ብር በላይ ሊያወጣ የሚችለውን በዝቀተኛ ዋጋ በሀራጅ ሽያጭ አንዱን ሮል/ ጥቅል በብር 50.00 ሂሳብ 762ቦ50 ብር 38ሺ 100 ሸጠው በመንግሥት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዲደርስበት በማድረጋቸው፣ ወንጀሉንም በሙሉ ፈቃዳቸው ለድርጊቱ ሙሉ ተካፋዮች በመሆን በፈፀሙት ስልጣንን ያለአግባብ መገልገል የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ተከሰዋል፡፡ የኮሚሽኑ ዐቃቤ ሕግ ባቀረበው የክስ ቻርጅ ላይ 11 የሰው፣ የኤግዚቢትና ሰባት የሰነድ ማስረጃዎችን አያይዞ ያቀረበ ሲሆን ዐቃቤ ሕግ ስለዋስትና አስተያየቱን እንዲያቀርብ ለጥር 23 ቀን 2000 ዓ.ም ፍርድ ቤቱ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ በታምሩ ጽጌ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |