| የኤሌክትሪክ ፈረቃና የትምህርቱ ሂደት |
|
|
| Sunday, 18 May 2008 | |
![]() አቶ ጋይም ተሻለ ![]() አቶ ከበደ ገብረመድህን ኤሌክትሪክ በፈረቃ መሰጠት ከተጀመረ ወዲህ በመደበኛው የመማር ማስተማር፣ በማታው የትምህርት መርሃ ግብርና በአጠቃላይም በትምህርት ጥራት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እያሳደረ መምጣቱን በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ አንዳንድ የመንግሥትና የሕዝብ ትምህርት ቤቶች ርዕሰ መምህራን አስታወቁ፡፡ ርዕሰ መምህራኑ እንዳመለከቱት በመማር ማስተማሩ እንቅስቃሴ ላይ እየተጋረጡ ከመጡት እንቅፋቶች መካከል ለማስተማሪያና ለሌላም አገልግሎት የሚውሉ ጽሁፎችን፣ መማሪያዎችንና ወርክ ሽቶችን አዘጋጅቶ ለመምህሩና ሌላም የሚመለከተው አካል እንዲጠቀምበት ለማድረግ ያልተቻለበት ሁኔታ መከሰት ይገኝበታል፡፡ በዚህም የተነሳ ሥራው በአግባቡና በተፈለገው መልኩ እየተካሄደ አይደለም፡፡ በላቦራቶር (ቤተሙከራ) የተደገፈ ትምህርት መስጠት ትምህርቱን ተጨባጭ ከማድረግ አንፃር ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ቢታወቅም በፈረቃው ሳቢያ ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ አልተቻለም፡፡ ሁለተኛው ሴሚስተር አብዛኛው አመታዊ የትምህርቱ ክፍል የሚጠቃለልበት፣ ተማሪው የተሰጡትን ትምህርቶች በአግባቡ ተገንዝቦ ጠቃሚ እውቀት መያዝ አለመያዙ የሚፈተሽበት ወቅት መሆኑን ርዕሰ መምህራኑ አመልክተው በዚህ አይነቱ ወቅት ኤሌክትሪክ በፈረቃ ማግኘት ወይም መቋረጥ ማለት በተማሪው ውጤት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያስከትል አስረድተዋል፡፡ የማታ ተማሪዎች ከአምስት ቀናት ውስጥ ሁለቱን ቀናት እንደማይማሩ፣ ይህን ያህል ቀን አለመማር ማለት ደግሞ የትምህርቱን ክፍል ከማጠናቀቁና የትምህርቱን ጥራት ከመጠበቅ አንጻር ከፍተኛ ጉዳት እንዳለው ከርዕሳነ መምህራኑ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡ የማታ ተማሪዎች ኤሌክትሪክ ጠፍቶ ብቻ ሳይሆን ኤሌክትሪክ እያለም የትምህርት ክፍል ከመጨረስ አኳያ ወደኋላ የመጓተት እንቅስቃሴ ይታይባቸዋል፡፡ ይህም የሚሆንበት ምክንያት ከቀን ተማሪዎች ጋር እኩል መራመድ ስለማይችሉ፣ የዕድሜና የሥራም ችግር ስላለባቸው ነው፡፡ ችግሩን ለማቃለል ሲባልም እስከ ሁለተኛው ፔሬድ ድረስ በብርሃን ማስተማር፣ የቀሪውን የትምህርት ክፍለ ጊዜያት ደግሞ በትርፍ ሰዓት (ቅዳሜና እሁድ) ማስተማር እንደ አማራጭ ተደርጎ ተወስዷል፡፡ ይህ አማራጭ ደግሞ የሁሉም መምህር ሀሳብና ፍላጎት ባለመሆኑ ብዙ ለውጥ አላመጣም፡፡ አቶ ጋይም ተሻለ የአፍሪካ አንድነት የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ የሕዝብ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር በበኩላቸው እንዳመለከተቱ "ኤሌክትሪክ በፈረቃ የማግኘቱ አካሄድ ፈተናዎችን በአግባቡ አዘጋጅቶ ለመስጠት ጊዜ ፈጅቶብናል፡፡ በዚህ የተነሳ ውዝፍ ሥራ በትርፍ ሰዓት ክፍያ (ኦቨር ታይም) እንዲሠራ ለማድረግ ተገደናል፡፡ ይህም ለከፍተኛ ወጪ ዳርጎናል" ብለዋል፡፡ በማታው የትምህርት መርሃ ግብር መሰረት ከአንደኛ እስከ አሥረኛ ክፍል የሚማሩ ከ700 ያላነሱ ተማሪዎች እንዳሉና ዩኒቲ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅም በዚሁ ትምህርት ቤት የከፈተውን የማታ ትምህርት የሚከታተሉ ተማሪዎች ቁጥር ከፍተኛ እንደሆነ አቶ ጋይም ጠቁመው መብራት በፈረቃ የማግኘቱ ጉዳይ የመማር ማስተማርን ሰዓት ከ30 በመቶ በላይ እንዲስተጓጎል እንዳደረገው አስረድተዋል፡፡ "ከዚህ ችግር ለመላቀቅ ሲባል ትምህርት ቤቱ ከመንግሥትና ከሕብረተሰቡ ጋር በመተባበር ጄኔሬተር ገዝቶ የማስተከል ሃሳብ አለው" ያሉት አቶ ጋይም ወደ ተግባር ሲገባ ግን ጉዳዩ ከሕብረተሰቡ አቅም ውስንነት፣ ከመንግሥት ዝግጁነት ማነስና ከትምህርት ቤቱ በጀት እጥረት አኳያ ችግር ሊያጋጥም ይችላል የሚል እምነት እንዳላቸው አስረድተዋል፡፡ አቶ ከበደ ገብረመድህን የዳግማዊ ምኒሊክ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር "ትምህርቱ በአብዛኛው የሚሰጠው በፕላዝማ አማካይነት ነው፡፡ በፈረቃው ሳቢያ ሥርጭት ከጣቢያው ሲቋረጥ የክፍሉ መምህር ወዲያውኑ በራሱ የትምህርት መረጃ መሳሪያ በመጠቀም የፕላዝማውን አይነት ትምህርት ይሰጣል፡፡ ይህም የሚያሳየው በፈረቃው ሳቢያ የፕላዝማው አገልግሎት መቆም የሚያስከትለው ችግር የሌለ መሆኑን ነው" ብለዋል፡፡ በኤሌክትሪክ እጦት ፕላዝማው በተቋረጠ ቁጥር የክፍሉ መምህር ጣልቃ ገብቶ ትምህርቱን በሚቀጥልበት ጊዜ በተማሪዎች ላይ አልፎ አልፎ ብዥታ ይፈጥራል የሚሉ ወገኖች መኖራቸውን ርዕሰ መምህሩ ጠቁመው ይህ ግን ትክክል እንዳልሆነ፣ ምክንያቱም ኤሌክትሪክ ባይቋረጥም ትምህርቱ አርባ አምስቱን ደቂቃ በሙሉ በፕላዝማ ብቻ ይተላለፋል ማለት እንዳልሆነና የክፍሉ መምህር በመካከል ጣልቃ እየገባ የሚያብራራበት የአሥር ደቂቃ ጊዜ እንደሚኖረው አስረድተዋል፡፡ ይህ ሲባል የኤሌክትሪክ መቋረጥ በተማሪዎች ላይ ምንም አይነት ችግር አያስከትልም ማለት አይደለም፡፡ ምክንያቱም የክፍሉ መምህር ሳያብራራው ያለፈውን የትምህርት ክፍል ከፕላዝማው ሊያገኙ ይችሉ እንደነበር ነው ርዕሰ መምህሩ የተናገሩት፡፡ ትምህርት ቤቱ በዚህ ዓመት ሙሉ ለሙሉ ወደ ፕሪፖራቶሪ (መሰናዶ) እየተለወጠ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ በ57 የመማሪያ ክፍሎች በፕላዝማ የሚገለገሉ 2ሺህ 700 የቀን ተማሪዎች ይገኛሉ፡፡ ከዚህም ሌላ በ15 የትምህርት መስጫ ክፍሎች ውስጥ የሚሰጠውን የማታ ትምህርት የሚከታተሉ ተማሪዎች እንዳሉም ለማወቅ ተችሏል፡፡ በማታው ትምህርት መርሃ ግብር አራት ፔሬዶች አሉ፡፡ ተማሪዎቹ አንደኛና ሁለተኛውን ፔሬዶች ከተማሩ በኋላ ስለሚጨልም ተከታዮቹን ፔሬዶች ሳይማሩ ወደየቤታቸው ይመለሳሉ፡፡ በዚህም ምክንያት መስጠት ያለበት የትምህርት ክፍል ሳይሸፈን ይቀራል፡፡ ክፍተቱን ለመሙላት ምን መደረግ አለበት በሚለው ዙሪያ መምህራኑና አስተዳደሩ እየተነጋገሩበት ነው፡፡ አቶ ተፈሪ በለው የቦሌ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር መብራት በፈረቃ የማግኘቱ ጉዳይ በማታው የትምህርት መርሃ ግብር ላይ ካልሆነ በስተቀር በመደበኛው ትምህርት ላይ የጎላ ችግር አላስከተለም፡፡ በማታው ትምህርት ላይ ያስከተለውን ተጽዕኖ ለማቃለልም ቅዳሜና እሁድን ጭምር በማስተማር ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ርዕሰ መምህሩ አስረድተዋል፡፡ አቶ ሀጎስ ኃይሌ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ስለዚሁ ጉዳይ በስልክ ተጠይቀው በሰጡት መልስ "ኤሌክትሪክ በፈረቃ በመቅረቡ ሳቢያ የመማር ማስተማሩ ሂደት ላይ ያጋጠመውን ችግር በተመለከተ ተወያይተውበታል፡፡ ለዚህም እንደ አማራጭ መፍትሄ ተደርጎ የተወሰደው የየት/ቤቶቹ ርዕሰ መምህራን፣ መምህራንና ሌሎችም አካላት ተግባብተውና ተረዳድተው በመሥራት ችግሩን በጋራ እንዲወጡ ማድረግ ብቻ ነው" ብለዋል፡፡ ይህም የሚሆነው የእረፍት ጊዜያትን ጭምር በሥራ ላይ በማዋል መሆኑን ኃላፊው አመልክተው በተለይ መምህሩ የፕላዝማ ስክሪንን ብቻ ተማምኖ መንቀሳቀስ እንደማይገባው፣ ፕላዝማ ኖረም አልኖረም የራሱን ሌሰን ፕላን አዘጋጅቶ መግባት እንደሚኖርበት አስረድተዋል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |