| እቴጌ ጣይቱ በታሪክ መነጽር |
|
|
| Sunday, 18 May 2008 | |
![]() እቴጌ ጣይቱ ![]() ዶ/ር ኄራን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መጻሕፍት ማደራጃ ክፍል (ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ) እቴጌ ጣይቱ ታሪካዊ ተውኔትን በመጽሐፍ መልክ አሳትሞ በድል በዓል ዕለት ባስመረቀበት ጊዜ በእቴጌ ጣይቱ ሕይወት የፖለቲካ ጉዞና ተውኔት ዙሪያ ልዩ ልዩ ጥናቶች ቀርበው ነበር፡፡ ጥናት ካቀረቡት መካከል የታሪክ መምህርት ዶክተር ኄራን ሠረቀ ብርሃን ጣይቱ ብጡል በ1832 ዓ.ም አካባቢ መወለዳቸው፣ የትውልድ አካባቢያቸው በአባታቸው በብጡል ኃይለ ማርያም በኩል ሲቆጠር እስከ ስሜን አገረ ገዢ ሔሎስ እና ባለቤታቸው የአፄ ሱስንዮስ ሴት ልጅ እንደሚደርስ፣ በጣይቱ ሴት አያት በወ/ሮ ሒሩት ጉግሳ በኩልም የትውልድ ሐረጋቸው እስከ የጁው ኦማር ሼህ እንደሚቆጠር ያብራራሉ፡፡ በ40 ዓመት ዕድሜያቸው ምኒልክን ያገቡት ጣይቱ ለንጉሡ ሦስተኛ ሚስታቸው ነበሩ፡፡ በሁለቱ ጋብቻ ወቅት ምኒልክ የሸዋ ንጉሥ እንደነበሩና የጣይቱ የትውልድ ዘርና ማንነት ወደፊት አፄ ለመሆን ለሚያቅዱት ምኒልክ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደነበረው የገለፁት ዶ/ር ኄራን ስለ እቴጌ ጣይቱ ታሪክ ሲወሳ "ምኒልክ ይረሳሉ ወይም ያንሱብናል" የሚል አስተሳሰብ መኖሩን ጠቁመው ነገሩ በሌላ በኩል ያለውን አንድምታ እንደሚከተለው ይገልጹታል፡፡ የምኒልክ ጣይቱን ማግባት የሳቸውን ተራማጅ አስተሳሰብና የሴቶችም አስተዋጽኦ ተቀባይነት እንደነበረው ያመለክታል፡፡ ምኒልክ ከጣይቱ በፊት ያገቧቸው ወ/ሮ ባፈናም እንዲሁ ተሰሚነት የነበራቸው፣ በወቅቱ ከምኒልክ ዘመድ ከመሸሻ ሰይፉ ጋር በመሆን በ1870 ዓ.ም አካባቢ ሸዋ ውስጥ የመንግሥት ግልበጣ ሙከራ ያደረጉ ሴት ነበሩ፡፡ ልጆቻቸውንና ዘመዶቻቸውን እየሾሙ፣ በጋብቻ እያስተሳሰሩ ቆይተው በመጨረሻ የግልበጣው ሙከራ ስላልተሳካ ግዞት እንዲላኩ ተፈርዶባቸው ነው ከምኒልክ ጋር የተለያዩት፡፡ የወ/ሮ ባፈና እና የእቴጌ ጣይቱ ፀባይ መመሳሰል ምኒልክም ምን አይነት ሴቶችን እንደሚመርጡ በዚህ ማስተዋል ይቻላል፡፡ በእቴጌ ጣይቱ ዘመን ከዚያም ቀደም ብሎ በነበረው ሁኔታ አንዱ ትልቁ የፖለቲካ ማራመጃ ጋብቻ ነበር፡፡ ወሎ፣ ዋግ፣ ወረሼህ፣ የጁ፣ ጎንደር፣ ጎጃም፣ ትግራይ፣ ሸዋ፣ ስሜን፣ በስተኋላም ወለጋንና ከፋን ጨምሮ፣ የንጉሣዊ ቤተሰቦች ጋብቻ አገሪቷን ለማስተሳሰር እና የአንድነት ስሜት ለመፍጠር ዋና አስተዋጽኦ ነበረው፡፡ ጣይቱ በዕለቱ በቀረበው ፊልም እንደ ተጠቀሰው እቴጌ ሆነው ከነገሡ በኋላ፣ "የሸዋ መርፌ" የሚል ስያሜ ሊሰጣቸው የቻለበትን ምክንያት አጥኚዎች ሲቃኙ ዘመዶቻቸውን በመሾምና በመዳር የፖለቲካ መሠረታቸውን ማስፋት መያያዛቸውን በምሳሌ እንደሚከተለው አስረድተዋል፡፡ የወንድሞቻቸውን ልጆች ወ/ሮ ከፋይ ወሌን ለትግራዩ ራስ መንገሻ ዮሐንስ፣ ወ/ሮ ምንትዋብ ወሌን ለሸዋው ራስ መኰንን (በኋላም ለጎጃሙ ራስ ከበደ መንገሻ አቲከም)፣ ወ/ሮ የተመኙ አሉላን ለሹም ተምቤን ገብረ መድኅን ከዚያም ለነጋድራስ ኃይለ ጊዮርጊስ፣ የእህታቸውን ልጅ ወ/ሮ አሰለፈች ወልደ ሃናን (በ4 ልዩ ልዩ አጋጣሚ) ለራስ ልዑል ሰገድ፣ ለራስ ደምሰው ነሲቡ፣ ለደጃዝማች ይልማ መኮንን እና ደጃዝማች ሥዩም ተክለ ሐይማኖት (በኋላ ራስ ኃይሉ ለተባሉት) ድረዋቸዋል፡፡ የእቴጌ ጣይቱን ዘመዶች ሥልጣንና የጋብቻ ትስስር በማድነቅም በመደንገጥም የታዘቡት ጣሊያናዊው አስተዳዳሪ ፈርዲናንድ ማርቲን በ1892 - 93 አካባቢ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፡ "ግማሽ አገሪቷ በዘመዶቻቸው እጅ ናት፡፡ ራስ ወሌ (ወንድማቸው) የትግራይና የየጁ ገዢ ናቸው፣ ራስ ጉግሣ ወሌ (የወንድማቸው ልጅ) በጌምድርን፣ ደጃዝማች ገሠሠ (የአክስታቸው ልጅ) ስሜንና ወልቃይትን ይዘዋል፡፡ ራስ መኮንንም ለምንትዋብ ወሌ ድረው በቁጥጥራቸው ሊያውሏቸው ያስባሉ፡፡" ጋብቻ በጊዜው ለነበረው ፖለቲካ ዋና መሣሪያ እንደነበር ያሰረዱት ዶ/ር ኄራን ምናልባትም እንደ እቴጌ ጣይቱ ለሥልጣን የቀረቡ ሴቶች የፖለቲካ ሚዛኑን የሚቆጣጠሩበት፣ መረጃ የሚሰበስቡበት፣ ወዳጅን አቅርቦ ጠላትን የሚያርቁበት ጠቃሚ መሣሪያቸው ጋብቻ ነበር ማለት እንደሚቻል አስምረውበታል፡፡ እቴጌ ጣይቱ የእቴጌነት ማዕርግ ሲቀበሉ የመጀመሪያዋ አልነበሩም፡፡ ከሳቸው በፊት እቴጌ አድማስ ሞገሳ (የአፄ ሚናስ ሚስት (1559 - 63))፣ እቴጌ ማርያም ሥና (የአፄ በካፋ ሚስት (1721 - 30)፣ እቴጌ መነን (የራስ አሊ እናት)፣ እቴጌ ተዋበች (የአፄ ቴዎድሮስ ሚስት) እቴጌ ድንቅነሽ (የአፄ ዮሐንስ እህትና የአፄ ተክለ ጊዮርጊስ ሚስት) ነበሩ፡፡ የእቴጌነት ማዕርግ የአስተዳደር ኃላፊነት ነበረው፡፡ ምኒልክ በማይገኙባቸው አጋጣሚዎች በኋላም ታመው በተገኙበት ጊዜ እቴጌ ጣይቱ የመንግሥትን አስተዳደር ሥልጣንና ኃላፊነት ተረክበው የራሳቸውን ሹም ሽር እስከ ማድረግ ደርሰው ነበር፡፡ ጣይቱ በሳል ዲፕሎማት እንደነበሩ ያወሱት አጥኚዋ በአውሮፓውያን የአፍሪካ ሽሚያ ወቅት፣ ጣሊያን ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ለማዋል ባደረገችው ጥረት፣ እቴጌይቱ አርቀው በማሰብና የጣሊያን መንግሥት ወኪሎችን እንቅስቃሴ በቅርብ እና በጥርጣሬ በማጤን የግጭቱን አዝማሚያ አስቀድመው በመገመታቸውና አዝማሚያው ሲገባቸውም፣ ጦርነት እንደማይወገድ አውቀው ቁርጠኛ አቋም መያዛቸውንና ለቁስለኞች የሚያስፈልገውን ዝግጅት፣ ለስንቅ የሚያስፈልገውን ምግብ አሰናድተው ሲያበቁ፣ ከአፄ ምኒልክ ጦር ጋር የራሳቸውን ፈረሰኛ ጦርና እግረኛ ሠራዊት እየመሩ ወደ ትግራይ መዝመታቸውን ያስታውሳሉ፡፡ በቤተ መንግሥት ያካበቱት ዕውቀት በጦር ሜዳም አገልግሏቸው ኖሮ፣ እንዳ ኢየሱስ ላይ ጣሊያን የመሸገበትን ለማስለቀቅ በኃይል ሳይሆን በብልሃት ብለው በነደፉት እቅድ መሠረት የእቴጌ ጣይቱ ጦር ጠላትን ማርኳል፡፡ የአድዋ ድል ለሚቀጥሉት 40 ዓመታት የአገሪቷን ነፃነት አረጋግጧል፡፡ እቴጌ ጣይቱ ዘመናዊነትን በአገር ውስጥ ለማስፋፋት ጥረት ያደርጉ እንደነበር ያስታወሱት ዶ/ር ኄራን በጊዜው በነበሩ አንድ አንድ አውሮፓውያን በተፃፉ ሰነዶች ላይ አገር ወዳድ ብሎም በዚያው ልክ ለውጥ የማይፈልጉ፣ አዲስ የሆነውን ሁሉ በጥላቻና በፍርሃት የሚመለከቱ ተደርገው ቢጻፍም ጣይቱ የአውሮፓውያንን ዓላማ ይጠራጠሩ እንጂ ለውጥን የሚያናንቁ ሰው እንዳልነበሩ በማስረጃ ጠቅሰዋል፡፡ እንደ ዶ/ር ኄራን አገላለጽ ምኒልክ ወደ ሐረር ዘምተው ሳለ፣ መናገሻውን ከእንጦጦ ወደ አዲስ አበባ ያሸጋገሩት እቴጌ ዋና ከተማችንን ቆርቁረው ሰየሟት፡፡ ይህችን የቆረቆሯትን ከተማ የዘመናዊ ሥልጣኔ መንገድን እንድትከተል በአገሪቷ የመጀመሪያውን ሆቴል ከፍተው፣ ሰው ከቤቱ ወጥቶ መብላትን እንዲለምድ ለማድረግ ምግብ ዝግጅቱን መጀመሪያ ላይ ራሳቸው ይከታተሉ እንደነበር ይወሳል፡፡ በሌላ በኩል በጊዜው ልዩ የነበረ ታላላቅ (በአሁኑ ቋንቋ "ባለሃብቶችን") ያቀፈ የኢትዮጵያ ባንክ ለመመስረት ሞክረዋል፡፡ ለአጭር ጊዜ አቋቁመውት የነበረው እርሻና ንግድ ማስፋፊያ ማኅበር ገንዘብ በማበደር ይታወቅ ነበር፡፡ ታዲያ በነዚህ ሁሉ መንገዶች ስንመለከታቸው፣ እቴጌ ጣይቱ ለኢትዮጵያ ህልውና እና እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደነበራቸው እንረዳለን፡፡ እቴጌ ጣይቱ ከኢትዮጵያና ከአፍሪካዊ ሴት መሪዎች ንግሥታት አንፃርም አጥኚዋ እንደሚከተለው ተመልከተዋቸዋል፡፡ ቀደም ባለው የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ እንደ እቴጌ ጣይቱ ተሰሚነት የነበራቸው ብልህ ሴት መሪዎች ነበሩ፡፡ ከእነዚህም መሀል በ15ኛው ክፍለ ዘመን የሐድያ ተወላጅ የነበሩት ከአፄ ዘርዓ ያዕቆብ ቤተ መንግሥት ወደ ሥልጣን የቀረቡት ንግሥት እሌኒ፤ በ18ኛው ክፍለ ዘመን ደግሞ እንደ ሚስት፣ እንደ እናትና እንደ አያት የእቴጌነት ማዕርግ የነበራቸው የቋራዋ ኦሮሞ እቴጌ ምንትዋብ ይጠቀሳሉ፡፡ ጎንደርን ከወሎና ከትግራይ በጋብቻ በማስተሳሰር ይጥሩ የነበሩ እቴጌ እንደነበሩ ይታወቃል፡፡ ከአውሮፓ ቅኝ ግዛት አስቀድሞ በ1870ዎቹ ዓመታት የአፍሪካ ሴቶች የፖለቲካ ሥልጣንና የአስተዳደር ኃላፊነት የነበራቸው ሲሆን በዑጋንዳ፣ በዳሆሜ (ቤኒን)፣ በጋና አሳንቴ መንግሥታት፣ ሴቶች በአማካሪነት፣ በአገር ገዢነትና በሚኒስትርነት ያገለግሉ ነበር፡፡ "ንግሥት እናት" (Queen mother) ተብለው የሚታወቁት ከፍተኛ ሥልጣን የነበራቸው ሴቶች በ19ኛው ክፍለ ዘመን ምዕራብ አፍሪካ ውስጥ ነግሠው ነበር፡፡ ልጆቻቸው ለአመራር እስኪደርሱ አገር እያስተዳደሩ፣ በጋብቻ ነገዶቻቸውን በማስተሳሰር ሰላም እየፈጠሩ ኖረዋል፡፡ ቅኝ ግዛት ከሰፈረም በኋላ የበኩላቸውን ተጋድሎ አድርገዋል፡፡ በ16ኛው ክፍለ ዘመን በአንጎላ የፓርቱጋልን የቅኝ ግዛት ዓላማ በመታገል የሚታወቁት አርበኛና ዲፕሎማት ንግሥት ንዚንጋ ምባንዴን ስመጥር መሆናቸውን ያወሱት ዶ/ር ኄራን በዚህ መልኩ ሲታዩ እቴጌ ጣይቱም ከሌሎች አፍሪካውያን ንግሥታት አንዷ መሆናቸውን፣ ቅኝ ግዛትን በመታገል የበኩላቸውን ሥፍራ መያዛቸውን ገልጸውታል፡፡ ጸሐፌ ተውኔት ጌትነት እንየው በደረሰውና በመድረክ በቀረበው እቴጌ ጣይቱ ተውኔትን አጥኚዋ ዳሰውታል፡፡ እንዲህም ብለዋል፡፡ ቴአትሩ ከታሪከ ጋር ቅርብ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ የእቴጌ ጣይቱን ብዙ ገጽታዎች እንመለከታለን፣ ጠንካራ ተክለ ሰውነታቸውን፣ ብልህነታቸውን፣ ቁርጠኛነታቸውን፣ ልበ ጽኑነታቸውንም እናየዋለን፡፡ ቀልደኛና ሰው አክባሪም እንደ ነበሩ ከጣልያን መልዕክተኞቹ ጋር በነበራቸው ግንኙነት እንመለከታለን፡፡ ከቴአትሩ ገጸ ባሕሪያት ውስጥ በታሪክ የተመረጡም የቀሩም እንዳሉ (ለምሳሌ ራስ ተፈሪና ልጅ ኢያሱ) እናያለን፡፡ ምክንያቱም ምንድነው ብዬ ሳስብ አንደኛው ታሪክን በሙሉ መድረክ ላይ ማሳየት መክበዱ፣ ከዚያም በላይ ደግሞ ትኩረቱ እቴጌ ጣይቱ ላይ እንዲሆን መታሰቡ ይመስለኛል፡፡ በታሪክና በምናባዊ ፈጠራ መሃል ያለውን ሚዛን ጠብቆ መፃፍ ፈታኝ ነው፡፡ ጸሐፌ ተውኔቱም በሚደነቅ ሁኔታ ይህንን ሚዛን ጠብቋል፡፡ በቴአትሩ በስተመጨረሻ እቴጌ ጣይቱ ሥልጣን አስረክበው እንጦጦ ይመለሳሉ፡፡ ያሳለፉትን ሕይወት ወደ ኋላ እየቃኙ፤ "ተወዶ ከመኖር ተጠልቶ መውለድ፣ ማን ያይብኝ ነበር ይህን ሁሉ ጉድ" ብለው ራቁት ገበናቸውንና ብቸኝነታቸውን አንጀት በሚያላውስ አንደበት ይገልጹታል፡፡ ታላቅነታቸው እርቋቸው ማንም በሚለካበት ሚዛን - ልጅ ባለመውለዳቸው መገመታቸውን ያመላክቱናል፡፡ "ኢትዮጵያ" ብለው ላለሟት ሕልም ማሳረፊያ የሚፈልጉ፣ ሐረግ ጉንጉን ለመፍጠር የሚሹም ይመስላሉ፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |