Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version

Monday
Oct 13th
Home arrow Sections arrow 17 የጅማ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ
17 የጅማ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ E-mail
Sunday, 13 January 2008
በጅማ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እርስ በርስ ባደረጉት ግጭት አሥራ ሰባት ተማሪዎች መቁሰላቸውንና በግጭቱ ተሳትፈዋል የተባሉ አሥራ ሰባት ተማሪዎች በፖሊስ ቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የጅማ ዩኒቨርሲቲ ኘሬዚዳንት ዶ/ር ካባ ኡርጌሳ ለሪፖርተር አስታወቁ፡፡

ዶ/ር ካባ እንደገለፁት በተማሪዎቹ መካከል የተነሳው ግጭት ምክንያቱ ምን እንደሆነ ለጊዜው አልታወቀም፡፡ የግጭቱን መነሻ ፖሊስ እያጣራ ነው፡፡ ባለፈው አርብ በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ ውስጥ የተከሰተው የተማሪዎች ግጭት በቁጥጥር ሥር የዋለው በፌዴራል ፖሊስ ርዳታ ነው፡፡

ኘሬዚዳንቱ በግጭቱ ወቅት ተማሪዎቹ ድንጋይ፣ እንዲሁም በግቢው ውስጥ ያገኙትን ብረታ ብረት መጠቀማቸውን ገልፀዋል፡፡ በሰው ህይወትና በንብረት ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት እንዳልደረሰ ተናግረዋል፡፡

የተማሪዎቹ ግጭት ያለፈው ሳምንት በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በብሔር በመቧደን የተነሳውን ግጭት ተከትሎ የተቀሰቀሰ ነው ለሚለው ..በጅማ ዩኒቨርሲቲ የተቀሰቀሰው ግጭት ከአርባ ምንጩ ግጭት ጋር ተያያዥነት የለውም.. ሲሉ ፕሬዚዳንቱ አስተባብለዋል፡፡

..ምንም እንኳን የታሰሩት ተማሪዎች የአንድ ብሄር አባት ቢሆኑም የቆሰሉት ተማሪዎች የተለያዩ ብሄር አባላት ስለሆኑ ግጭቱ ብሄርን መሠረት ያደረገ ነው ለማለት ያስቸግራል.. በማለት ዶ/ር ካባ ገልፀዋል፡፡

ዶ/ር ካባ ግጭቱ መብረዱንና የተለመደው የመማር ማስተማር ሂደት እየተከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ግጭቱ እንዳያገረሽ የፌዴራል ፖሊስ አባላት በግቢው ውስጥ ተሰማርተው እንደሚገኙና የግጭቱን መንስዔ ፖሊስ እያጣራ መሆኑን የዩኒቨርሲው ኘሬዚዳንት ገልፀዋል፡፡ ዶ/ር ካባ በቁጥጥር ሥር በዋሉት ተማሪዎች ላይም የምርመራ ሥራ እየተካሄደ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በተሾመ ንቁ

 
< Prev   Next >