| ፀረ ሙስና በተጭበረበረ ወርቅ... |
|
|
| Sunday, 13 January 2008 | |
|
ፀረ ሙስና በተጭበረበረ ወርቅ በተፈፀመው ዝርፊያ ክስ አልመሰረተም "በአገር ላይ የተፈፀመ ውስብስብ ወንጀል" ከብሄራዊ ባንክ በተጭበረበረ ወርቅ የተፈፀመውን ወንጀል ተከትሎ የፌዴራል ስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ክስ አልመሰረተም፡፡ ኮሚሽነር አሊ ሱሌማን የምርመራ ስራው መጠናቀቅ እንዳለበት ገልፀዋል፡፡ የፌዴራል ፖሊስ ድርጊቱን "አገር ላይ የተፈፀመ ውስብስብ ወንጀል" ብሎታል፡፡ ከወርቅ ግዢ ጋር በተያያዘ ብሄራዊ ባንክን አዘርፈዋል፣ ዘርፈዋል የተባሉና የተጭበረበረ ሙያዊ አስተያየት ሰጥተዋል በሚል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር በዋሉት ላይ የሚደረገው ምርመራ በርካቶችን እያነካካ ነው፡፡ ታዋቂ ሰዎችና ነጋዴዎች እየታሰሩ ነው፡፡ ባሌስትራውን ወርቅ ነው በማለት ብሄራዊ ባንክ ከሁለት መቶ ሚሊዮን ብር በላይ እንደተዘረፈ ሲታወቅ ከወርቅ ግዢ ጋር ግንኙነት ያላቸው የባንኩ ሰራተኞች፣ የደህንነት ሰራተኞችና የማዕከላዊ ጂኦሎጂካል ላቦራቶሪ ሰራተኞች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ መደረጉ አይዘነጋም፡፡ ፖሊስ በተጠርጣሪዎቹ ላይ ክስ ከመሰረተ በኋላ ፍርድ ቤት ወንጀሉ ከሙስና ጋር የተያያዘ በመሆኑ ጉዳዩን የፌዴራል ፀረ ስነምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን እንዲይዘው አስተላልፎለታል፡፡ ኮሚሽኑ ግን ክስ አለመመስረቱ ታውቋል፡፡ ኮሚሽኑ ጉዳዩን በባለቤትነት ከያዘ በኋላ ክስ ሳይመሰርት የቆየበትን ምክንያት እንዲያስረዱ የተጠየቁት ኮሚሽነር አሊ ሱሌማን "በቅድሚያ የኦዲት ስራ እንዲሰራ ለፌዴራል ዋና ኦዲተር ትዕዛዝ አስተላልፈናል" በማለት መልስ ሰጥተዋል፡፡ በአብዛኛው የህብረተሰብ ክፍልና ብሄራዊ ባንክን ጨምሮ በተለያዩ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች በስፋት እያወያየ ባለው የማጭበርበር ተግባር ላይ እየተደረገ ያለው ምርመራ ውስብስብና በርካታ ሰዎችን እያነካካ በመሆኑ ምርመራውን የያዙት ክፍሎች መረጃ ለመስጠት እንደሚቸገሩ ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ታዋቂ ሰዎችን ጨምሮ በቁጥጥር ስር እየዋሉ እንደሆነ ታውቋል፡፡ ፀረ ሙስና ኮሚሽን፣ የፌዴራል ዋና ኦዲተር፣ የፌዴራል ፖሊስና የሚመለከታቸው አካላት በአንድነት "ልዩ" ምርመራ እያደረጉበት ስላለው የተጭበረበረ ወርቅ ሽያጭ ኃላፊዎች የተለያየ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ የፌዴራል ፖሊስ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር ደምላሽ ኃይሉ "ጉዳዩ በአገር ላይ የተፈፀመ ውስብስብና ብዙ ሰዎችን የሚያነካካ ወንጀል" ነው ያሉት የብሄራዊ ባንክ ወርቅ መጭበርበር ጉዳይ ምርመራው ጥንቃቄ ያሻዋል፡፡ ከሁለት መቶ ሚሊዮን ብር በላይ ባሌስትራ ወርቅ እየተባለ ሲመዘበር የቆየው ብሄራዊ ባንክ ይህንን ያህል ገንዘብ እስኪጭበረበር ድረስ እንዴት ሳያውቅ ቀረ? የሚለው የህዝብና የሰራተኞች ጥያቄ ነው፡፡ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው የማጣራት ስራ እየተሰራ መሆኑን የጠቆሙት ኮማንደር ደምላሽ "ወንጀሉ ከባድ በመሆኑ ጥንቃቄ የተመረጠው የተፈላጊዎች ዱካ እንዳይጠፋ ነው" "እነማን፣ እንዴት፣ ከማን ጋር ይህንን ወንጀል ሲፈፅሙ ነበሩ" የሚለው የህዝብ ጥያቄ ምርመራው ሲጠናቀቅ በግልፅ ለህዝብ ይፋ እንደሚሆን ኮማንደር ደምላሽ ተናግረዋል፡ ህዝቡም የማወቅ መብት አለው ግን ምርመራው እስኪያልቅ ትዕግስት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ የፌዴራል ስነምግባር ፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አሊ ሱሌማን ለሪፖርተር እንደገለፁት የፌዴራል ዋናው ኦዲተር ምርመራ እንዲያካሂድ ማዘዛቸውን ገልፀዋል፡፡ የምርመራው ውጤትም እየተጠበቀ ነው፡፡ የዋናው ኦዲተር ጉዳዩን እንዲመረምር ልዩ ትዕዛዝ የተሰጠው ኮሚሽኑ ከሳሽ በመሆኑ ምርመራው በገለልተኛ ወገን መጣራት ስላለበት እንደሆነ ኮሚሽነር አሊ አስታውቀዋል፡፡ "ምርመራው ሳይጠናቀቅ ክስ መመስረት አንችልም" ያሉት ኮሚሽነሩ ኮሚሽኑ ክስ የሚመሰረተው ምርመራው ከተጠናቀቀ በኋላ አቃቤ ሕግ ሲወስን ነው፡፡ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ የታሰሩትን አስመልክቶ "ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል የታሰሩት ለምርመራ ነው" በማለት አቶ አሊ ተናግረዋል፡፡ የባንኩ ባለሙያዎችና የጂኦሎጂካል ሰርቬይ ባለሙያዎች እጃቸው ሳይኖርበት ወንጀሉ ይፈፀማል የሚል እምነት እንደሌላቸው ግን ኮሚሽነሩ አልሸሸጉም፡፡ በሌላ በኩል የፌዴራል ስነምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በብሄራዊ ባንክ አሰራር ላይ ትኩረት ሰጥቶ ጥናት ማካሄድ እንደሚጀምር ታውቋል፡፡ ይህ የሚደረገው ለወደፊት ዝርፊያንና መጭበርበርን ለመከላከል እንደሆነም ተመልክቷል፡፡ የፌዴራል ዋናው ኦዲተር የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው "በብሄራዊ ባንክ ተጭበረበረ በተባለው ወርቅ ጉዳይ በልዩ ትዕዛዝ ምርመራ እየተደረገ ነው" ብለዋል፡፡ በምርመራው ወርቅ እንዴት ይገባል፣ የወርቅ ማስቀመጫ ሕጉ፣ ደንብና መመሪያው ይመረመራል፡፡ ልዩና ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ሲፈጠር በሚመለከተው በየትኛውም መንግሥታዊ አካል ልዩ ትዕዛዝ እንደሚሰጥ ያስታወሱት ሃላፊው በብሄራዊ ባንክ ላይ ምርመራ እንዲካሄድ የፌዴራል ዋና ኦዲተር በተመሳሳይ መልኩ ልዩ ትዕዛዝ ተሰጥቶታል፡፡ ትዕዛዙ በመንግሥት በኩል ልዩ ትኩረት ለጉዳዩ መሰጠቱን ያሳያል ብለዋል፡፡ የሱፐርቪዥን፣ የቡድን መሪ፣ ኦዲተርና ረዳት ኦዲተር ያካተተ የባለሙያዎች ቡድን በብሄራዊ ባንክ ተመድቦ የኦዲት ስራ በመስራት ላይ መሆኑን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው አመልክተዋል፡፡ በኦዲት ስለተገኘው ውጤት ተጠይቀው "ከወርቁ ጋር በተያያዘ የሚሰራው ምርመራ ጥልቀት ያለው የምርመራ (ኢንስሲቲጌሽን) ሥራ ይጠይቃል፡፡ ስራው በዚሁ መልክ ተጀምሯል፡፡ ሳይጠናቀቅና ለጠየቀው ክፍል ሪፖርት ሳይቀርብ ስለውጤቱ ምንም መናገር አይቻልም" የሚል መልስ ሰጥተዋል፡፡ የብሄራዊ ባንክ የባንኪንግ የውጭ ምንዛሪ ዳይሬክተሮች ዳይሬክተር አቶ ሰይፈ ደስታ ባንኩ ተጭበረበረ ስለተባለውና ሕዝብ በስፋት እየተነጋገረበት ስላለው ጉዳይ ማብራሪያ እንዲሰጡ ተጠይቀው "እስካሁን መረጃ እንድሰጥ ትዕዛዝ አልተሰጠኝም፡፡ ስለዚህ መረጃ አልሰጥም" ካሉ በኋላ "በርግጥ ዳይሬክተር ነኝ፡፡ ጉዳዩ በፖሊስ እጅ ተይዟል፡፡ ወደፊት ባንኩ የራሱን መግለጫ ይሰጣል፡፡ ከዚህ ውጪ የምሰጠው አጭርም ሆነ ረዘም ያለ መግለጫ የለም" የሚል መልስ ሰጥተዋል፡፡ ባሌስትራ ወርቅ ነው በማለት ዝርፊያ የሚያካሂዱት ንግድ ፈቃድ የሌላቸውን ወጣቶች ከበስተጀርባ በመሆን መጠቀሚያ በማድረግ እንደሆነ፣ ይህንን ያህል የከፋ የአገር ሀብት ሲዘርፉ ዝም ያሉ፣ እንዲዘረፍ ያመቻቹና ተባባሪ የሆኑ ተመጣጣኝ ቅጣት ሊሰጣቸው እንደሚገባ ተቆርቋሪ ዜጎችን ጠቅሰን መዘገባችን አይዘነጋም፡፡ የተጭበረበረው ወርቅ ለኤክስፖርት ተልኮ ደቡብ አፍሪካ ከደረሰ በኋላ እሽጉ ሲከፈት ባሌስትራ መሆኑ ታውቆ እንዲመለስ መደረጉም የሚታወስ ነው፡፡ በአሰግድ ተፈራ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |