Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Friday
Aug 29th
Home arrow Sections arrow "አልሸባብ ጉሪን አልተቆጣጠረም"
"አልሸባብ ጉሪን አልተቆጣጠረም" Print E-mail
Sunday, 13 January 2008

አቶ ዋህድ በላይ የውጭ ጉዳይ ሚ/ር ቃል አቀባይ

ጉሪ የተባለችው የሶማሊያ ከተማ በአልሸባብ ቁጥጥር ስር እንደወደቀች ተደርጎ በተለያዩ ሚዲያዎች የተዘገበው ሀሰት መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አቶ ዋህድ በላይ ለሪፖርተር ጋዜጣ ገለጹ፡፡

ጉሪ ከተማ በሽግግር መንግሥቱ ቁጥጥር ሥራ የነበረችና አልሸባቦች እንደመተላለፊያ ይጠቀሙባት እንደነበር የጠቆሙት ቃል አቀባዩ የኢትዮጵያ ሰራዊት ይህንን የአልሽባቦች እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር ሲል ከነበረበት የጦር ሰፈር ተነስቶ ወደ ጉሬ ከተማ መሄዱንና ምንም ችግር ስላልተከሰተ ከከተማዋ ተመልሶ እንደወጣ አብራርተዋል፡፡

በአሁኑ ሰዓት ከተማዋን የሚቆጣጠራት የሽግግር መንግሥቱ እንጅ አልሻባብ አለመሆኑንም አቶ ዋህድ ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል የቀድሞው የሶማሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር መሀመድ ጌዲ ከሀላፊነታቸው ከተነሱ በኋላ በአዲስ መልክ የተቋቋመው የሶማሊያ ካቢኔ ተስፋ የተጣለበት መሆኑን  ቃል አቀባዩ አስታውቀዋል፡፡

የቀድሞው የሶማሊያ የሽግግር መንግሥት ካቢኔ ሁሉንም ጎሳዎች አላካተተም በሚል በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ላይ ትችት ይሰነዘር እንደነበር ያስታወሱት አቶ ዋህድ አሁን የተቋቋመው ካቢኔ ግን "ያገባናል" የሚሉትን አካላት ያካተተና ሰፊ በመሆኑ ትልቅ እምነት እንደተጣለበት ተናግረዋል፡፡ እንደ ቃል አቀባዩ ገለፃ አዲሱ ካቢኔ የተዋቀረው ከተለያዩ የጎሳ መሪዎችና ባለሙያዎች ጋር ውይይት ከተደረገ በኋላ በመሆኑ እስካሁን ድረስ ምንም አይነት ትችት አልደረሰበትም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ተቀባይነት እያገኙ መጥተዋል፡፡

ቀደም ባሉት ጊዚያት በሶማሊያ ሰላም ለማስፈን ወሳኙ ነገር ፖለቲካዊ መፍትሄ መሆኑን ኢትዮጵያ ስታሳስብ መቆየቷን የገለጹት አቶ ዋህድ ፖለቲካዊ መፍትሄ በሚፈለግበት ጊዜም ሁሉንም ህብረተሰብ የሚወክል የፖለቲካ ቅርርብ ማድረግ፣ በግጭት ብቻ የሚያምኑ አሸባሪዎች ካልሆኑ በስተቀር ለዘብተኛ አቋም ያላቸው የእስላማዊ ፍርድ ቤት ሀይሎች ጭምር በሰላማዊ ሂደት ላይ መሳተፍ እንዳለባቸው የኢትዮጵያ መንግሥት እምነት እንደነበር አመልክተዋል፡፡

በቅርቡ ወደኢትዮጵያ እየገቡ ስላሉት ኤርትራውያን ስደተኞች ቁጥር መጨመር እና ኢትዮጵያ እያደረገች ስላለው ጥንቃቄ ከሪፖርተር ጋዜጣ ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ዋህድ "የኤርትራውያን ስደተኞቹ ቁጥር እየጨመረ የመጣ ቢሆንም ስደተኞቹ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ተማረውና ተገፍተው በመሆኑ ወደ መጠራጠር መሄድ ተገቢ አይደለም፡፡ ስደተኞቹ ላይ ጣታችን የምንጠቁምበት ጉዳይ የለም" ብለዋል፡፡

ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡት ስደተኞች ቁጥር በወር እስከ ስድስት መቶ እንደደረሰ የጠቆሙት ቃል አቀባዩ በተለይ በቅርቡ የኤርትራ መንግስት "ኢትዮጵያ ልትወረኝ ነው" ብሎ ሕዝቡንና ጦሩን ውጥረት ላይ ከከተተው በኋላ የስደተኞች ቁጥር እየጨመረ መሄዱን አስረድተዋል፡፡

በአሁኑ ሰዓት ወደ ኢትዮጵያ የገቡት ኤርትራውያን ስደተኞች ቁጥር ከ23 እስከ 24ሺ እንደሚገመት የገለጹት አቶ ዋህድ አብዛኛዎቹ ስደተኞች ሺመልባ በተባለው ካምፕ እንደሰፈሩ ተናግረዋል፡፡

በተያያዘ ዜና የኤች አር 2003 አርቃቂ ዶናልድ ፔይን በቅርቡ በኤርትራ ያደረጉት ጉብኝት የኢትዮጵያ መንግሥት ይዞት የነበረው አቋም ትክክለኛ መሆኑን እንደሚያረጋግጥ አቶ ዋህድ ገልፀዋል፡፡

ኤች አር 2003 ኢትዮጵያ ላይ ያንዣበበ የጠላት ረቂቅ ሕግ እንደሆነ ኢትዮጵያ ስትገልጽ እንደነበር የጠቆሙት አቶ ዋህደ የረቂቅ ሕጉ አርቃቂ ዶናልድ ፔይን ሞቅ ያለ አቀባበል ወደ ተደረገላቸው ኤርትራ ሄደው ስለኢትዮጵያ መጥፎ ነገር መናገራቸው "ኤች አር 2003 የዶናልድ ፔይን፣ የሻዕቢያና በጣም አክራሪ የሆኑ ተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ሴራ መሆኑን የሚያመላክት ነው" ብለዋል፡፡

የኤች አር 2003 አርቃቂው ዶናልድ ፔይን በኤርትራ ጉብኝታቸው ወቅት ኢትዮጵያ አካባቢውን እያመሰች መሆኗንና የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔም እንድትቀበል ጫና እንደሚያደርጉ መናገራቸው ተሰምቷል፡፡ 

በኃይሌ ሙሉ

 
< Prev   Next >