Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Thursday
Aug 07th
Home arrow Sections arrow ቅንጅት ህጋዊ ባለቤት አገኘ
ቅንጅት ህጋዊ ባለቤት አገኘ Print E-mail
Sunday, 13 January 2008

ImageImageImage

"ኑ ወደ ቤታችሁ ተመለሱ" አቶ አየለ ጫሚሶ
"ከአሁን በኋላ በቅንጅት ስም ጫጫታው ቆሟል"
"መጀመሪያ አርማችን ከዚያ በኋላ ፓርቲያችን አንስተው ለሌላ ሰጡ"
አቶ ተመስገን ዘውዴ
"አቶ አየለ ወደ ቀድሞው መንፈስ ሊመለሱ ይገባል"

በቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ስም ከአሁን በኋላ መንጫጫቱ ቆሟል፡፡ "ኑ ወደቤታችሁ ተመለሱ" ሲሉ አቶ አየለ ጫሚሶ አስታወቁ፡ አቶ ተመስገን ህገወጥ ድርጊት እንደተፈተመባቸው ገለፁ፡፡ አቶ ሙሉነህ ኢዮኤል ያስተሳሰረን ዓላማችን እንጅ የፓርቲው ስም አይደለም ብለዋል፡፡

የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ህጋዊ ፈቃድ የተሰጣቸው አቶ አየለ ጫሚሶ ..ከአሁን በኋላ በቅንጅት ስም ጫጫታው ቆሟል፡፡ የቅንጅት ቤተሰቦች ኑ ወደ ቤታችሁ ተመለሱ በማለት ጥሪ አቀረቡ፡፡

አቶ አየለ ምርጫ ቦርድ የፓርቲው ህጋዊ ሰርተፊኬት እንደሰጣቸው በመግለፅ በቅንጅት ስም የሚደረጉ ማንኛቸውም መግለጫም ሆነ እንቅስቃሴዎች ህጋዊ እርምጃ ስለሚያስወስዱ እንዲቆሙ አስጠንቅቀዋል፡፡ በህጋዊ መንገድ የቅንጅት ቤተሰብ በሙሉ በጋራ ተሰብስበው ፓርቲውን በጋራ የሚመራበትን ሁኔታ መፈጠር አለበት ብለዋል፡፡ ለዚህም የቅንጅት ፓርቲ አባል እንዲሁም ደጋፊ ለፓርቲው መጠናከር በጋራ እንስራ ሲሉ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

አቶ አየለ በምርጫ ቦርድ ትዕዛዝ መሰረት ህጋዊ መሆናቸውን ሲገልፁ ለቅንጅት ቤተሰቦች ቀደም ሲል የተቀመጠው የሥራ አስፈፃሚነትና የላዕላይ ምክር ቤት አባላት መቀመጫ የተጠበቀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ቀደም ሲል በተደረገው ጠቅላላ ጉባኤ ከእስር የተፈቱትን የቅንጅት መሪዎች ጨምሮ ለመላው የቅንጅት ቤተሰብ መጠባበቂያ መቀመጫ እንዲኖር መወሰኑን የገለፁት አቶ አየለ "የአመራርነት ጥያቄ ፓርቲውን ከማዳንና ከመጠበቅ በኋላ የሚነሳ ጉዳይ በመሆኑ ፓርቲውን መቀስቀስ ለሚፈልጉ በሩ ክፍት ነው፡፡ እስከ አመራርነት ድረስ.." በማለት ተናግረዋል፡፡

ከኢንጂነር ኃይሉ ሻውል ቡድን ጋር ለመቀላቀል እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ተጠይቀው "ፈፅሞ አይደረግም" በማለት አቶ አየለ መልስ ሰጥተዋል፡፡ በወሬ ደረጃ እንደሚናፈስ የጠቆሙት አቶ አየለ ፖለቲካ መስመሩና አቅጣጨው ባይታወቅም በአሁኑ ወቅት በኢንጂነር ኃይሉ ሻውል ለሚመራው ቡድን ጭምር ጥሪ መተላለፉን እንጂ ሌላ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ገልፀዋል፡፡ በቀጣይስ ለተባሉት "በቀጣይ የሚሆነውን ዛሬ ላይ ሆኖ መናገር አይቻልም"

ሰዎች ፓርቲን ሲያቋቁሙ ተመሳሳይ ፍላጎት ያላቸው በአንድነት ፓርቲ ያቋቁማሉ በሚል በሕገመንግሥቱ የተሰጠ መብት እንዳለ ያስታወሱት አቶ ሙሉነህ ኢዮኤል ..ይህ በሕገመንግሥቱ የተቀመጠው መብት እያለ ፓርቲውን እገሌ ሲመራው ፈቃድ እሰጠዋለሁ፣ እገሌ ከመራው ደግሞ እከላክለዋለሁ የሚለው ዓይነት የቆየ ጨዋታ ነው፡፡ ይህ ተቀናቃኝ ፓርቲዎችን የማዳከም ባህሪ ኢሕአዴግ ይዞት የነበረና አሁንም እየቀጠለበት ያለ ጉዳይ መሆኑን አረጋግጠናል.. ብለዋል፡፡

የፖለቲካ ሂደቱን ግልፅ በማድረግ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚንቀሳቀሱበትን ሁኔታ የበለጠ ይከፍተዋል የሚል እምነትና ተስፋ እንደነበራቸው የገለፁት አቶ ሙሉነህ ..ቅንጅትን ቅንጅት ያደረገውና በሕዝብ እንዲደገፍ ያደረገው ስሙ ስለሚያምር ሳይሆን በአላማው ነው.. ሲሉ ቅንጅት የሚለው ስም ለሌላ አካል ቢሰጥም የቅንጅት ዓላማ ግን ከፓርቲው ደጋፊዎችና አመራሮች ጋር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በቅንጅት ዓላማ ውስጥ የገቡ ያንኑ የቀድሞውን ዓላማ እናራምዳለን የሚሉ ሰዎች በሌላም ሁኔታ ይዘው እንደሚነሱ የጠቆሙት አቶ ሙሉነህ፡፡ ያንንም አዲስ አካሄድ ሕዝቡ የሚደግፍበት ሁኔታ ሰፊ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

"ለዴሞክራሲ ግንባታ የሚደረገው ትግል ስም ተሰጠ፣ ስም ተከለከለ በሚል የሚቆም አይደለም" ያሉት አቶ ሙሉነህ ይህ የቆየ የኢሕአዴግ ድራማ ይበልጥ ለትግሉ ጥንካሬ ይፈጥራል እንጂ በፓርቲው አመራሮች ዘንድ የሚቀይረው ነገር እንደማይኖር አመልክተዋል፡፡

አቶ አየለ ጫሚሶ "ለስራ አስፈፃሚና ላዕላይ ምክር ቤት አባላት ቦታ አለ" በሚል ጥሪ አድርዋል ለሚለው ጥያቄ "የቅንጅት የምንለው ፓርቲና ዓላማው የሚመነጨው መስከረም 14 ቀን 1998 ዓ.ም ፓርቲዎች በፈቃደኛነት ከመሰረቱት ውህደት ነው" በማለት አቶ ሙሉነህ መልሰው "ከዚህ ዓላማና መንፈስ የወጣው አመራር ተቀባይነት አይኖረውም አቶ አየለም ሆኑ ሌሎች ተገንዝበው ወደ ቀድሞው መንፈስ ሊመለሱ ይገባል" ብለዋል፡፡

ከአቶ ተመስገን ዘውዴ ጋር ለመፍጠር የታሰበውን ውህደት የበለጠ እንደሚገፉበት የገለፁት አቶ ሙሉነህ "የምናራምደው ፖለቲካ ከፓርቲው ስም ጋር ሳይሆን ከዓላማው ጋር የተቆራኘ በመሆኑ ማንም ይህንን ተግባራዊ ከማድረግ አያግደንም" በማለት አስተያየታቸውን አጠቃለዋል፡፡

አቶ ተመስገን ዘውዴ በበኩላቸው አርማቸውና ፓርቲያቸው ያለአግባብ ለሌላ አካል መሰጠቱ ፍትሀዊ አለመሆኑን ገልፀዋል፡፡

አቶ ተመስገን ዘውዴ "መጀመሪያ አርማችን ከዚያም ፓርቲያችን ያለአግባብ ለሌላ አካል ተሰጠ" በማለት ምርጫ ቦርድን አማረሩ፡፡

"በመጀመሪያ አርማችን ከዚያ በኋላ ፓርቲያችን አንስተው ለሌላ ሰጡ" ያሉት አቶ ተመስገን የምርጫ ቦርድ ውሳኔ ፍትሀዊ ያልሆነ፣ ከአንድ ዴሞክራሲን ከሚገነባ ድርጅት የማይጠበቅ አድሎአዊ ውሳኔ ነው በማለት የምርጫ ቦርድን ውሳኔ ኮንነዋል፡፡

እርሳቸው የሚመሩት ቡድን ከአቶ አየለ ጫሚሶ ጋር በመሆን ጠቅላላ ጉባኤ እንዲጠራ ምርጫ ቦርድ ትዕዛዝ ሰጥቶ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ተመስገን "በትዕዛዙ መሰረት አቶ አየለ ጫሚሶ በጠቅላላ ጉባኤው ቢጋበዙም አለመገኘታቸውን ምርጫ ቦርድ ያውቃል ካሉ በኋላ በጉባኤው እንዲገኙ ጥሪው በምርጫ ቦርድ በኩል እንዲተላለፍ እንዲደረግ መጠየቁን ቦርዱ እያወቀ ሰርተፊኬቱ ለአቶ አየለ ተሰጥቷል ማለት ፍትሀዊነት የጎደለው መሆኑን አቶ ተመስገን ገልፀዋል፡፡

አቶ ተመስገን እንዳሉት እርሳቸው የሚመሩት ቡድን አባላትና የስራ ሃላፊዎች የሚቀጥለው ህጋዊ እርምጃ ምን መሆን እንዳለበት እየተመካከረ ነው፡፡ ውሳኔ ላይ ሲደረስ ይፋ እንደሚደረግም ገልፀዋል፡፡

እርሳቸው የሚመሩት ፓርቲ ፍትሀዊ ያልሆኑ ውሳኔዎች በተደጋጋሚ በሚወሰንበት ጊዜ ወደ ፍትህ አካላት እየሄደ ፍትሀዊ የሆኑ ውሳኔዎች ለማግኘት መሞከሩን የጠቆሙት አቶ ተመስገን አንዳንድ ጊዜ በጣም ቅር በሚያሰኝ ሁኔታና ውሳኔዎች እየተላለፉባቸው ቢሆንም በሕግ የበላይነት የሚያምን የፖለቲካ ፓርቲ በመሆኑ አሁንም ተስፋ ሳይቆርጥ በትግሉ እንደሚቀጥልበት ገልፀዋል፡፡

በጋዜጣው ሪፖርተሮች

 
< Prev   Next >