| መሬት ሰላምን ያስገኛል?... |
|
|
| Sunday, 25 May 2008 | |
![]() መሬት ሰላምን ያስገኛል? ወይስ ሰላም መሬትን ያስገኛል?በየማነ ናግሽ በቅርቡ በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል የ”ድንበር ይገባኛል” ጉዳይ አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ መካለሉ አለመጀመሩና አንድም የተፈናቀለ አርሶ አደር እንደሌለ ተናግረዋል፡፡ አንዳንድ የአካባቢው የፓርላማና የወረዳ ተወካዮች በበኩላቸው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ መሠረት እንደሌለውና በሪፖርቱ ማፈራቸውን ይናገራሉ፡፡ ከትላንትና በስቲያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት “ሶስተኛ የሥራ ዘመን ሁለተኛ ልዩ ስብሰባ” በሚያደርጉበት ወቅት በገዢው ፓርቲ አባል የፓርላማ ተወካይ የኢትዮ-ሱዳን የድንበር ጉዳይ አስመልክቶ በተወካዩ አባባል “ለተወራው አሉባልታ” ማብራሪያ እንዲሰጣቸው ጥያቄ ቀርቧል፡፡ ቀደም ሲል ጉዳዩ በአጀንዳነት የተያዘው በአቶ ተመስገን የፓርላማ ቡድን በመሆኑ የጥያቄው አቅራቢና አቀራረቡ በአቶ ተመስገን ተቃውሞ ቀርቦበታል፡፡ አቶ መለስ “ውዠምብር” እየፈጠረ ያለው በድንበሩ አካለል ታሪክ ላይ ግልፅ የሆነ መረጃ ከማጣት መሆኑን ገልፀው ከመጀመሪያው ለማስረዳት ሞክረዋል፡፡ እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ፣ እንደ ሌሎች ድንበሮች ሁሉ በአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት በ1907 ዓ.ም በወቅቱ ሱዳንን በቅኝ ገዢነት ሲያስተዳድር የነበረው እንግሊዛዊው ሻለቃ ጎይንና በኢትዮጵያ መንግሥት መካከል በተደረገው ስምምነት መሠረት በ1909 ዓ.ም ድንበሩን ተካሏል (ስቂሮቈሰሮ”ስሳ”፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አባባል ሌሎች የኢትዮጵያ ድንበሮች ያልተካለሉ በመሆናቸው አካባቢው ይህ ልዩ ያደርገዋል፡፡ ሱዳን ከቅኝ ገዢነት ነፃ ከወጣች በኋላ የማካለል አፈፃፀሙን ለማስተካከል በአፄ ኃ/ሥላሴና በሱዳን መንግሥት መካከል ተከታታይ ውይይቶች ተደርገዋል፡፡ በወቅቱ ጉዳዩ ሙያተኛ ተመድቦለት እንዲጠና ከተደረገ በኋላ ቡድኑ በደረሰው “የጎይን መስመር” በተሻለ ሁኔታ ኢትዮጵያን እንደሚጠቅም ድምዳሜ ላይ መድረሱን ተናግረዋል፡፡ እ.ኤ.አ በ1972 ዓ.ም በጉዳዩ ላይ በተደረሰው ስምምነት መሠረት የጉይን መስመርን መቀበልና (ከዳግላሽ ተራራ እስከ ተከዜ ባለው አካባቢ) ደግሞ እንዲካለል (to be redemarkated) መወሰኑን ነገር ግን ንጉሡ ይህንን ተፈፃሚ ከማድረጋቸው በፊት ከስልጣን በመውረዳቸው ሳይሳካ መቅረቱን አስረድተዋል፡፡ እስኪካለል ድረስም ባለበት ሁኔታ (Status quo) እንዲጠበቅ ተስማምተዋል፡፡ በመቀጠልም እ.ኤ.አ በ1980 ዓ.ም ስልጣን ላይ የነበረው የደርግ መንግሥትም በተመሳሳይ በጉዳዩ ላይ ዕውቀት ያላቸው ሙያተኞችና ፕሮፌሰሮች እንዲያጠኑት በማድረግ አሁንም የጎይን መስመር ከመቀበል አማራጭ እንደሌለና በአካባቢው ሕዝብ ላይ ችግር እንዳይፈጥር ሕብረተሰቡን ማማከርንና መወያየት እንደሚያስፈልግ ቡድኑ መጠቆሙን ተናግረዋል፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን በበኩላቸው አብረዋቸው ካጠኑት ፕሮፌሰር ታደሰ ታምራት፣ ፕሮፌሰር መርዕድ ወ/አረጋይ፣ ፕሮፌሰር ብርሃኑ አበበ እና ወርቁ ተፈራ (በህይወት የሌሉ) ጋር ያቀረቡት ጥናት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ እንደተናገሩት “ከጎይን መስመር ሌላ አማራጭ የለም” የሚል ድምዳሜ የሌለበት መሆኑን ለጀርመን ድምፅ ሬዲዮ በሰጡት ቃለ ምልልስ አስተባብለዋል፡፡ ጉዳዩን እልባት ሳያገኝ አሁንም ደርግ ከስልጣን በመውረዱ የኢህአዴግ መንግሥት ላለፉት 17 ዓመታት ከሱዳን መንግሥት ጋር ተከታታይ ውይይት ማድረጉን አቶ መለስ አስታውሰዋል፡፡ በመሐል በአዲስ አበባ ይካሄድ በነበረው የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ወቅት በግብፅ ፕሬዚዳንት የግድያ ሙከራ በመደረጉ በኢትዮጵያና በሱዳን መንግሥታት መካከል የነበረው ግንኙነት በመሻከሩ ምክንያት የተጀመረው ድርድር መቋረጡን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡ በዚህ ወቅት ከዳግላሽ እስከ ተከዜ ባለው አካባቢ በድንበር ዙሪያ በኢትዮጵያና በሱዳን መከላከያ ኃይሎች አንዳንድ ግጭቶች መከሰታቸውን አምነዋል፡፡ በተፈጠሩት ግጭቶች ምክንያት የሱዳን ወታደሮች ቦታውን ለቀው በመውጣታቸው በአካባቢው የነበሩት የሱዳን አርሶ አደሮችና ኢንቨስተሮች ስጋት አድሮባቸው መሬታቸውን ለቀው በመሄዳቸው መሬቱ በአንዳንድ ኢትዮጵያውያን ጥቅም ላይ ውለዋል፡፡ በሁለቱም አገሮች መካከል ውይይት ተጀምሮ “የጎይን መስመር የትም ይሁን የትም የማካለል ሥራ በሚሰራበት ወቅት አንድ ኢትዮጵያዊ ወይንም አንድ ሱዳናዊ አሁን እያረሰ ካለው መሬት መፈናቀል የለበትም” የሚል የኢትዮጵያ ጥያቄ በሱዳን መንግሥት ተቀባይነት ማግኘቱ “ከፍተኛ እምርታ” ብለውታል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚሉት “በንጉሡ ጊዜ ከተደረሱ ስምምነቶች መካከል ያለው ሁኔታ ባለበት እንዲቆይ” የሚል በኢትዮጵያውያን ተጥሰዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን የጎይን መስመር እያለፉ መሬት እያረሱ ነው የሚል የሱዳንያውያን ተከታታይ ስሞታ ነበር ብለዋል፡፡ ይህ ከ1995 ዓ.ም ጀምሮ በሁለቱም አገሮች መካከል የነበረው የመሻከር ግንኙነት ተከትሎ በተፈጠረው ግጭት የሱዳን ኢንቨስተሮችና አርሶ አደሮች ለቀውት የወጡት መሬት በኢትዮጵያውያን መያዙንም ይናገራሉ፡፡ እንደ እሳቸው አነጋገር ከሆነ በኢህአዴግ ዘመነ መንግሥት ኢትዮጵያውያን በተደጋጋሚ ወደ ሱዳን እየዘለቁ መሬት ይዘዋል፡፡ በድንበር ጉዳዩ ታሪኩ ላይ ጥናት አድርገዋል የተባሉትንና የታሪክ ምሁሩን አስተያየት እንዲሰጡን ጠይቀን ፈቃደኞች ሊሆኑ አልቻሉም፡፡ በሰሜን ጎንደር የመተማ ወረዳ ታችና ምዕራብ አርማጮሆ በቀድሞ ቅንጅት ስም ለፓርላማ የተመረጡ ተወካይ አቶ አግባው ሰጠኝ እንደ የአካባቢው ተወላጅነታቸውና የፓርላማ ተወካይነታቸው በጉዳዩ ላይ አስተያየት ሰጥተውናል፡፡ እሳቸው የሚሉት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር በተቃራኒ ነው፡፡ አሁን እያወዛገበ ያለው “የመሬት ይገባኛል” ግዛት በኢህአዴግ ዘመን በኢትዮጵያውያን የተያዘ ሳይሆን ቀድሞም የሱዳን ሆኖ የሚያውቅበት ዘመን የለም፡፡ “ከተወለድኩ ጀምሮ እንደማውቀው ቦታው መቼውም በእኛ እጅ የነበረ ነው” ብለዋል፡፡ አቶ አግባው እንዳሉት ጉዳዩ የተነሳው ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ መሆኑና በወቅቱ በኢትዮጵያ የመንግሥት ለውጥ በተደረገበት የሱዳን ወታደሮች የመተማን አካባቢ ተቆጣጥረዋል፡፡ ወታደሮቹ ከአንድ ዓመት በላይ ወረው ከቆዩ በኋላ ለቀው መውጣታቸውን ተናግረዋል፡፡ በ1998 ዓ.ም የሱዳን ወታደሮችና ፖሊሲዎች 17 ሰዎች ገድለውና በሌሎችም ጉዳት አድርሰው መሬቱን መልሰው እንደያዙት ይናገራል፡፡ የኢትዮጵያ ወታደሮች ገዳዮቹን በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን የሚናገሩት አቶ አግባው፣ በመንግሥት ትዕዛዝ እንዲለቀቁ መደረጋቸውን አስረድተዋል፡፡ የሱዳን ወታደሮቹ “ዘለቀ የእርሻ ልማት” የተባለው አካባቢ ተቆጣጥረው እዚያው ካምፕ ሰርተው መቀመጣቸውን አክለው ገልፀዋል፡፡ ይህ የአቶ መለስን ንግግር ይቃረናል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ እንዳሉት እ.ኤ.አ ከ1996 በፊትም በኋላም በኢትዮጵያ አርሶ አደሮች የተያዘ መሬት ከዚህ በፊት በተያዘ መልክ እንዲቆጠር፣ የኢንቨስተሮቹ ግን እንዲመለስላቸው የኢትዮጵያ መንግሥት ስምምነት ላይ ደርሷል፡፡ እንዲሁም ሱዳንያውያን ባልታረሰ መሬት ላይ ካልሆነ በስተቀር ኢትዮጵያውያን አፈናቅለው እንዳያርሱ መስማማታቸውን ገልፀዋል፡፡ አቶ አግባው በዚህ አይስማሙም፡፡ እሳቸው እንደሚሉት በ1984 ዓ.ም በኢትዮጵያ መልሶ የተያዘው መሬት በ1983 ዓ.ም ህወሐትና ብአዴን እዚያ አካባቢ በነበሩበት በሱዳናውያን ተወሮ የተያዘ እንጂ በፊትም የኢትዮጵያን የነበረው ነው፡፡ ይህ አንጎንግ በመባል የሚታወቀው ለም መሬት ከመተማ እስከ አርማጮው የሚዘረጋ አካባቢ ነው፡፡ ሱዳናውያን በ1998 መልሰው የያዙት ቦታ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር የእኛ ሰዎች ወደ ሱዳን ዘልቀው የያዙት የሚሉት መሬት ይሄው ነው፡፡ ተወካዩ እንደሚሉት ከሆነ በዚህ ደለሎ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ የሚገኘው ከቁጥር 1 እስከ ቁጥር 8 “ዘለቀ የእርሻ ልማት” ከቁጥር 1 በስተቀር በሱዳናውያን ተወስዷዋል፡፡ በዚህ ምክንያት በ1998 ዓ.ም ብቻ ከ474 አርሶ አደሮችና ኢንቨስተሮች በላይ መፈናቀላቸው ያስታወሱት አቶ አግባው፣ በእርሻ ይዞታው ላይ የነበረው ሰብል በሱዳን ወታደሮች መቃጠሉን አብራርተዋል፡፡ “የተፈናቀለው የለም” የሚለው የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ምላሽ የሚቃወሙ የፓርላማ አባሉ፣ አርሶ አደሮቹንና ባለሐብቶቹን በሌሎች አርሶ አደሮች ይዞታ ላይ በማሸጋሸግ ማስፈሩን አስታውሰዋል፡፡ በዚህ ምክንያት በተፈናቃዮቹና በባለ ይዞታ አርሶ አደሮች መካከል ግጭት ተፈጥሮ የፀጥታ ኃይል ደርሶ ጣልቃ መግባቱንም አስታውሰዋል፡፡ በዚህም በመተማ ብቻ ተወስኖ የነበረው የመሬት ወረራ ተስፋፍቶ በቅርቡ በአርማጮሆና በቋራ አካባቢ መቀጠሉን አባሉ ገልፀዋል፡፡ የደላሎ የእርሻ መሬትም ተመሳሳይ ችግር እንደገጠመው በምሳሌነት የሚጠቅሱ አቶ አግባው፣ በቋራ ነፍስ ገበያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በተደረገው ወረራ ከ28 ሰዎች በላይ ታፍሰው ወደ ሱዳን ከተወሰዱ በኋላ የት እንደገቡ እንደማይታወቅ ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ቀደም ሲል 17 ሰዎችን የገደሉና በአካባቢው ነዋሪ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሱ የሱዳን ወታደሮች በነፃ እንዲለቀቁ ከማድረጉ ባሻገር ለሟች ቤተሰቦች ወይም የሞራልና የካሳ ድጋፍ አለማድረጉ “ለዜጎቹ ያለው ክብር እስከዚያም ነው” ሲሉ ወቅሰዋል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር አሁንም ግልፅ አይደለም፡፡ በአንድ በኩል የጎይን መስመር አለመካለሉን እየተናገሩ በሌላ በኩል፣ “ኢትዮጵያን የማያርሱ መሬት ሱዳናውያን እንዲያርሱት ተስማምተናል”. ረይህምሪ የጎይንን መስመር የሱዳን ድንበር ነው ብሎ በግልፅ ባመላከተው ቦታ ላይ ብቻ ነው” በማለት በውል ባልተካለለ ቦታ ላይ የታረሰም ይሁን ያልታረሰ መሬት ለሱዳናውያን ባለቤትነት ማስረከቡ እርስ በርሱ የሚጣረስ ነው፡፡ “ኢትዮጵያውያን በፊት የገቡም ይሁኑ አካባቢውን መከላከያ ኃይላችን ሲቆጣጠረው የያዙት መሬት እንደያዙት ይቆጠራል “. ድንበሩ በሚከለልበት ወቅትም አይፈናቀሉም” የሚል ስምምነት መፈራረማቸው ተናግረዋል አቶ መለስ፡፡ ሲጀመር የአካባቢው ተወካይ የፓርላማ አባል እንዳሉት ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ በርካታ ሰዎች መፈናቀላቸውን ግልፅ ሆነዋል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ “ሲካለልም ጭምር የሚፈናቀል አይኖርም” የሚል መርህ ከምን የመነጨ እንደሆነ ግልፅ አይደለም፡፡ ይህንን አመለካከት ሁለት መሠረታዊ ጥያቄዎች ያሳንሳል፡፡ አንደኛ፣ መካለል ሲኖር “አንድም አይፈናቀልም” ሲባል በአንድ በኩል አሁን ካለው የድንበር ሁኔታ የሚደረግ ለውጥ አይኖርም ማለት ነው፡፡ በጎይን መስመር መሠረት ለውጥ ከተደረገም አንድ አትዮጵያዊ አርሶ አደር መሬቱ ወደ ሱዳን ከተካለለ ዜግነቱ ሱዳናዊ እንዲሆን ማስገደድ ነው፡፡ መፈናቀል አለመኖሩ ምናልባት ሊደርስ የሚችል ሰብዓዊ ቀውስ ሊያስቀር ይችላል እንጂ ሊያስከትለው የሚችል “ዜግነታዊ ቀውስ” ግን ልብ አልተባለም፡፡ ወይስ የግዴታ ዜግነት (forced citizenship) ተቀበል ሊባል ነው፡፡ ይህንን የተዳፈነ ንግግር ለሕዝብ ግልፅ ማድረግ የመንግሥት ግዴታ ይሆናል፡፡ ምንአልባትም አንድ ግለሰብ ኢትዮጵያዊ ዜግነት ይዞ በሱዳን መሬት የመኖር መብት የሚፈቅድ ዓለም አቀፍ ወይም አህጉራዊ ህግ ካለ ሊያጣቅሱልን ይገባል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡ የመፈናቀልና አለመፈናቀል ጉዳይ ሰብዓዊ ቀውስ የሚያስከትል በመሆኑ ትኩረት አያሻም ባይባልም ቀዳሚ ትኩረት የሚሻ ግን የይገባኛል ጥያቄውን ነው፡፡ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ምሁራን እንደሚሉት አፄ ምኒልክ ከእንግሊዝ ጋር ሲካለሉ በመጀመሪያ ቅር ተሰኝተው እንደነበርና በዚህም ደብዳቤ መፃፋቸው ይነገራል፡፡ የእንግሊዝ መንግሥትም ይቅርታ በመጠየቅ ካርታውን አሻሽሎ ልኮላቸዋል፡፡ “በአዲሱ ስምምነት መሠረት ከገላባት ጀምሮ እስከ አምሃጀር ያለውን መስመር ለውጦታል” ይላሉ ፕሮፌሰር መስፍን፡፡ ገላባት ተነስቶ ወደ አምሃጀር ከመግባት ይልቅ ወደ ሳቲት አካትቶ እንዲሄድ እንደሚያደርገው የተናገሩት ፕሮፌሰር መስፍን በማያወላውል የእኛ መሬት መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ምሁራን እንደሚሉት ያ መስመር መነሻው መተማ ሆኖ በገለባት በኩል ወደ የሱዳን ከተማ የሆነችው ኦማሃጀር ላይ ያልፋል፡፡ አቶ አግባው እንደሚሉት አሁን እየተሰራው ካለው ማካለል መሠረት አሞሃጅር አሁን ጭራሽ ርቃናለች፣ አናገኛትም፡፡ በሁለቱም ካርታዎች መሠረት ጉዋንግ የሚባለው ወንዝ ወደ ኢትዮጵያ ነው የሚሆነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት መካለል የሚባል አልተጀመረም፡፡ የአካባቢው ሰዎች ግን መካለሉንና በመተማ በኩል ብቻ ከ200 ሺ ሄክታር በላይ መሬት ለሱዳን መሰጠቱን ይናገራሉ፡፡ አንዳንድ የአካባቢው የፓርላማ አባላትና የወረዳ ተመራጮች ይህንኑ ያረጋግጣሉ፡፡ የአርማጮሆውም ተካልሎ ያለቀ ቢሆንም ሕዝቡ “ከአባቶቻችን መሬት አንለቅም” በማለቱ ተፈፃሚ አልሆነም፡፡ አቶ ልብሰወርቅ ጥሩነህ የመተማ የወረዳ ተመራጭ ሲሆኑ የሱዳን ወታደሮች ድንበር ጥሰው በመግባት በኢትዮጵያውያን ላይ ጉዳት ማድረሳቸውና መሬቱ ተካልሎ ለሱዳን መሰጠቱን በስልክ በሰጡን ቃለ ምልልስ አረጋግጠዋል፡፡ አቶ አግባው እንዳሉት “ሱዳን በታሪክዋ ከኢትዮጵያ ተራራ አገኘች” የሚባል ተረት ተጀምረዋል፡፡ አቶ አግባው ይህንን አስመልክተው (አፄ ምኒልክ ተዋዋሉት የተባለው ካርታ) “ይሄ መስመር ወደ ቋራ አይመልስም፣ አሁን ግን በቋራ አካባቢ ነብስ ገበያ በመባል የሚታወቀው ትልቅ የእርሻ ቦታ ለሱዳን ተሰጥቷል ሲባል ገርሞኛል” ብለዋል፡፡ በዚህ አካባቢ በመንግሥት የተመሩ ሰዎች በሱዳን ከተወሰዱ በኋላ በሰላማዊ መንገድም ቢሆን ለማስመለስ መንግሥት የወሰደው እርምጃ አለመኖሩ አሳዝኗቸዋል፡፡ እንደ እሳቸው አነጋገር የወረዳ አስተዳደሮች መሬቱን መካለሉ ለሕዝቡ የተናገሩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ “አልተካለለም” ሲሉ “የክልሉ መንግሥትና የፌዴራል መንግሥት አሰራር የተለያየ ነው እንዴ?” የሚል ጥያቄ አስነስቷል፡፡ ሕዝቡንም ወዥምብር ውስጥ መግባቱ አስታውሰዋል፡፡ “ሌላ በጣም እየቀፈፈኝ ያለው ለሱዳን የተሰጠው ቦታ አፄ ዮሐንስ የሞቱበት የኢትዮጵያ መሬት ነው” ብለዋል፡፡ አቶ አግባው እንደየአካባቢው ተወላጅ በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ንግግር ተበሳጭተዋል፡፡ በቅርቡ እዚያ መኖራቸው ገልፀው “አልተካለለም፣ የተፈናቀለ ሰው የለም ሲሉ አዘንኩኝ” ብለዋል፡፡ በአንድ በኩል ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር በኋላ ሕዝቡ መሬቱ የሚመለስለት መስሎት ተደስቷል፡፡ “የተካለለው መሬት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተሽሯል” የሚል ስሜት ፈጥሮበታል፡፡ “ይሄ አወዛጋቢ ጉዳይ አፄ ምኒልክ፣ አፄ ኃይለሥላሴ ሆኑ ደርግም አልተቀበሉትም” የሚሉት አቶ አግባው፣ አሁን የኢህአዴግ መንግሥት ታሪካዊ የሆነ ስህተት እየፈጠረ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ለወደፊቱ መንግሥት ጉዳዩን ለመፍታት በደንብ ሊያየው እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |