|
Sunday, 25 May 2008 |
|
በታደሰ ገብረማርያም
በዘንድሮ የትምህርት ዘመን በሚሰጡ ሀገር አቀፍ ፈተናዎች ላይ የፈተና ደንብና መመሪያ እንዳይጣስ ለማድረግ የሚያስችል ጥንቃቄ ተደርጓል፡፡ በዚህም መሠረት ፈታኞችና ሱፐርቫይዘሮች በሚሠሩባቸው ትምህርት ቤቶች እንደማይፈትኑና በልዩ ሁኔታ ከሚፈቀድላቸው በስተቀር ማንኛውም ሰው ወደ ፈተና ጣቢያው መግባት እንደማይፈቀድለት የአጠቃላይ ትምህርት ጥራት ማረጋገጫና የፈተናዎች ኤጀንሲ ተጠባባቂ ሥራ አስኪያጅ አስታውቀዋል፡፡
ተጠባባቂው ሥራ አስኪያጅ አቶ ታከለ ገብረ ኪዳን እንደገለፁት የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህርም ቢሆን ለሥራው አስፈላጊ ሆኖ የጣቢያ ኃላፊው እንዲገባ ካልፈቀደና በጥበቃ ላይ ያሉ ፖሊሶችም ለልዩ ዕርዳታ ካልሆነ በስተቀር ወደ ፈተና አዳራሽ እንዲገቡ አይፈቀድም፡፡
ሞባይልና ካልኩሌተር ይዞ ወደ ፈተና አዳራሽ መግባት የተከለከለ ነው፡፡ እነዚህን መገልገያዎች ይዘው በሚመጡ ተፈታኞች ላይ ከፍተኛ ቁጥጥር እንደሚደረግ፣ ሞባይልን ይዞ ዘግቸዋለሁ፣ ሳይለንት አድርጌዋለሁ የሚለው አባባል ተቀባይነት እንደሌለውና እበር ላይ አስቀምጦ መግባትም አስቸጋሪ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
በትልልቅና ከአንድ በላይ አስፈታኝ ትምህርት ቤት ባሉባቸው ከተሞች በዚያው ከተማ ውስጥ ባለ በሌላ ትምህርት ቤት ወይም ለከተማው ቅርብ በሆነ ጐረቤት ወረዳ ሄደው እንዲፈተኑ ይደረጋል፡፡ የገጠር ወረዳዎችና አንድ አስፈታኝ ትምህርት ቤት ብቻ ያለበት ወረዳ ወደ አጎራባች ወረዳ በመሄድ ይፈተናሉ፡፡ ለዚህም የውሎ አበልና የትራንስፖርት ክፍያ ተመቻችቷል፡፡
ተጠባባቂው ሥራ አስኪያጅ እንዳብራሩት ተፈታኞች ለገለፃ በሚጠሩበት ቀንና በፈተናው ዕለት መታወቂያቸውና የፈተና አዳራሽ መግቢያ ካርድ በመያዝ ሰዓት አክብረው በፈተና ጣቢያ መገኘት ይኖርባቸዋል፡፡ በመግቢያ በር ላይ ተሸፋፍኖ ለመግባት መሞከርና ማንነትን አለማሳየት ትክክል አይደለም፡፡ ማንነቱ ያልታወቀ ተፈታኝ ወደ አዳራሽ እንዲገባ አይፈቀድም፡፡ ቢፈተን እንኳን ውጤቱ አይያዝለትም፡፡
"ለአሥረኛና ለ12ኛ ክፍል ተፈታኞች በጠቅላላው በ768 ጣቢያዎችና በ1236 አስፈታኝ ትምህርት ቤቶች የሀገር አቀፍ ፈተና ለመስጠት ዝግጅት ተደርጓል" ያሉት አቶ ታከለ የአሥረኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና ከግንቦት 26 እስከ ግንቦት 29 ቀን 2ዐዐዐ እንዲሁም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከሰኔ 2 እስከ ሰኔ 4 ቀን 2ዐዐዐ ድረስ እንደሚሰጥ አስረድተዋል፡፡
ለአሥረኛና ለ12ኛ ክፍል ፈተና በድምሩ ከአንድ ሚሊዮን 5ዐ ሺህ በላይ ተፈታኞች መመዝገባቸውን፣ ከእነዚህም ውስጥ ለ1ዐኛ ክፍል ፈተና የተመዘገቡት 961 ሺህ 641 ተፈታኞች ሲሆኑ ለ12ኛ ክፍል ፈተና የተመዘገቡት ደግሞ 91 ሺህ 660 ተፈታኞች መሆናቸውንና ከአጠቃላዩ ተፈታኞች መካከልም 391 ሺህ 357 ሴት ተፈታኞች መሆናቸውን ከአቶ ታከለ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡
ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ1ዐኛ ክፍል በ206 ሺህ 777 የጨመረ ሲሆን በመቶኛ ሲሰላ በ27.4 በመቶ ከፍ ብሏል፡፡ የ12ኛ ክፍል ደግሞ በ2ዐ ሺህ 462 የጨመረ ሲሆን ይህም በመቶኛ ሲሰላ በ28.74 አድጓል፡፡ ከአዲስ አበባ ብቻ ከ900 በላይ የጣቢያ ኃላፊዎች ተመልምለው አስፈላጊው ኦሬንቴንሽን ተሰጥቷቸዋል፡፡ ፈተናው ታትሞና ተቆጥሮ በሸራ ታሽጐ ነው የሚገኘው፡፡ ፈተናው በጨረታ በተገኙ የጭነት ተሽከርካሪዎችና የጣቢያ ኃላፊዎች ደግሞ በሕዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት ይጓጓዛሉ፡፡
ለፈተናው ዝግጅት 36 ሚሊዮን ብር ተመድቧል፡፡ የፈተና አዳራሽ መግቢያ ካርድ ተዘጋጅቶ ተሰራጭቷል፡፡ በፈተና አዳራሽ መግቢያ ካርድ ላይ የስም፣ የምዝገባ ቁጥር የጣቢያ ኮድ ወዘተ. ስህተቶች ያሉባቸው ካርዶች ተሰብስበው በመስተካከል ላይ ናቸው፡፡ እንዳለቁም ይላካሉ፡፡ የጣቢያ ኃላፊዎችም ይዘዋቸው ይሄዳሉ፡፡
ቀደም ባሉት ዓመታት ካጋጠሙት ችግሮች መካከል አንዱና ዋነኛው ችግር የፈተና ደንብና መመሪያ መጣስ ነበር፡፡ ይኸውም መቀዳዳት ወይም መኰራረጅ፣ በቡድን ፈተናውን መሥራት፣ አስገድዶ የፈተና መልስ መንጠቅ፣ በሕገ-ወጦች አማካይነት ፈተና ከውጪ አሠርቶ ማስገባት ወዘተ. ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ በራስ ሠርቶ ከመጠቀም ይልቅ በሌላ ሰው ትከሻ ተንጠልጥሎ አለአግባብ ለማትረፍ መሞከር ስለሆነ በከፍተኛ ደረጃ ሙስና ነው፡፡ ዘንድሮ ይህንን በሚፈጽሙ ላይ ከፍተኛ እርምጃ ይወስዳል፡፡ ስለዚህ ተፈታኞችና ሌሎች የሚመለከታቸው ከዚህ ሕገ-ወጥ ድርጊት ከመሳተፍ መቆጠብ ይኖርባቸዋል፡፡
"በሂደት ካጋጠሙን በርካታ ችግሮች መካከል ቁልፍ ችግር ሕገ-ወጦች ፎርጅድ ሰርተፊኬት እያዘጋጁ ማቅረባቸው ነው" ያሉት አቶ ታከለ ይህንን ሕገ ወጥ ሥራ የሚያከናውኑትም በሁለት መንገድ መሆኑን፣ አንደኛው ኤጀንሲው ከእንግሊዝ እያስመጣ የሚጠቀምበት ዓይነት ተመሳሳይ ወረቀት በማስመጣትና ማህተም በማስቀረጽ ሰርተፊኬት ማሳተም፣ እንዲሁም ከኦሪጅናል ሰርተፊኬቱ ላይ በልዩ ኬሚካል ሰምንና ውጤትን በመፋቅ እንደገና እዛ ላይ የሚፈልጉትን ስምና ውጤት በመፃፍ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ለዚህም ዓይነቱ ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴያቸው የሚረዳ የሕትመት ማሽን ከውጭ አገር ማስገባታቸውንና በዚህም የሀሰት ሰርተፊኬት እያተሙ ወይም እያዘጋጁ መንግሥትንና ሕብረተሰቡን በማጭበርበር ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
አሁን ግን ኤጀንሲው ከብርሃንና ሠላም ማተሚያ ቤት ጋር በመነጋገር ልዩ ወረቀት ከፈረንሳይ ገዝቶ አስገብቷል፡፡ በዚህ ዓይነቱ ወረቀት ላይ የተፃፈ ጽሁፍ በኬሚካል በምንም ዓይነት አይጠፋም፡፡ የሚጠፋ ከሆነ ደግሞ ወረቀቱ ይቀደዳል፡፡ የመገልገያውን ዘዴ በየዓመቱ በመለዋወጥ ወይም በመቀያየር ፎርጅድ እንዳይሠራ ለማድረግ ሙከራ ይደረጋል፡፡
ከዚህም ሌላ በቀላሉ ፎቶ ኮፒ የማይሆንና ላሜትድ (በኘላስቲክ የተለበደ) የሆነ ሰርተፊኬት ለማዘጋጀት እየታሰበ ነው፡፡ አዲሱ ዓይነት ሰርተፊኬት ለማሳተም ከብርሃንና ሠላም ማተሚያ ቤት ጋር ስምምት ተደርጓል፡፡ ህትመቱም በቅርቡ ይጀመራል፡፡ የወደፊት ሀሳብ ደግሞ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተማሪዎችን ውጤት በኢንተርኔት እንዲያገኙት በማድረግ ላይ ያተኮረ ይሆናል፡፡ ለዚህም እውን መሆኑ ከተወሰኑ የቻይና ኩባንያዎችና ከአንድ የጀርመን ኩባንያ ጋር የሀሳብ መለዋወጥ ተደርጓል፡፡ |