|
"ኢንተርኔት የሚጠቀም፣ ስልክ የሚያነሳ . . . |
|
|
|
Wednesday, 28 May 2008 |
|
"ኢንተርኔት የሚጠቀም፣ ስልክ የሚያነሳ . . . ድንክ የሳሎን ውሻ . . ". በምሕረት አስቻለው
ቦሌ መድሀኒአለም ሸገር ሕንፃ ፊት ለፊት አስፋልት መሀል አንዲት ትንሽዬ ውሻ (ቡችላ) በእጁ ይዞ ከወዲያ ወዲህ እያለ ባጠገቡ ለሚያልፉ የመኪና አሽከርካሪዎች ያሳያል፡፡ ከወዲያ ወዲህ በማለት ቡችላዋን እየደባበሰ ለመኪና አሽከርካሪዎች ሲል ሰማነው "ኢንተርኔት የሚጠቀም፣ ስልክ የሚያነሳ ድንክዬ የሳሎን ውሻ፤ ይሻላል ከማይረባ ዘበኛ" ዳንኤል አሠፋ ተወልዶ ያደገው ጐንደር ሲሆን ወደ አዲስ አበባ ከመጣ ስምንት ዓመት እንደሆነው ይናገራል፡፡ ጐንደር ውስጥ በአነስተኛ ንግድ ይንቀሳቀስ የነበረ ሲሆን ከስምንት ዓመት በፊት ወደ አዲስ አበባ የመጣው በአዲስ አበባ በተሻለ መልኩ በንግድ እንቀሳቀሳለው ብሎ በማመን ነበር፡፡ "ንግድ፣ መሸጥ መለወጥ ይሆንልኛል፡፡ ሠዎችን በቀላሉ የመቅረብና የማግባባት ችሎታ አለኝ፡፡ ይህን በማሰብና የትም ይሁን የት ሰርቼ ማደር እንደምችል በመተማመን ወደ አዲስ አበባ መጣሁ" ብሏላ፡፡
አዲስ አበባ እንደመጣ ኘላስቲክ ኳሶችን፣ የፀሀይ መከላከያና የተለያዩ የሕፃናት መጫወቻዎችን፤ ጐተራ፣ ሣር ቤትና ቦሌ አካባቢ መሸጥ እንደጀመረ የሚናገረው ዳንኤል በዚህ ሁኔታ ለአጭር ጊዜ ከቆየ በኋላ ውሾችን መሸጥ እንደጀመረ ገልፆልናል፡፡ ዘወትርም ባይሆን ከውሾች በተጨማሪ ድመቶችንና ጥንቸሎችንም ይሸጣል፡፡ ሁሌም የተለያዩ ዝርያ ያላቸውን ውሾች ይዞ ሸገር ሕንፃ ፊት ለፊት ከሚገኘው አስፋልት ላይ ለመሸጥ ወዲያ ወዲህ ሲል ይታያል፡፡
ገዥዎችን ለመሳብና ለማግባባት የሚጠቀማቸው ቃላቶችና ተጫዋችነቱ ከሠዎች ጋር በቀላሉ መግባባት የሚችል ለመሆኑ ምስክሮች ናቸው፡፡
ሲ.ኤም.ሲ አካባቢ ለጉዳይ የሄደው ዳንኤል ውሻ ለመሸጥ ምክንያት የሆነው አጋጣሚ በዘያው እንደተፈጠረ "ሦስት ቡችሎች አንድ ላይ ተቀምጠው ነበር፡፡ አንድ የውጭ ዜጋ መኪናውን ቡችሎቹ ፊት ለፊት ሲያቆም ከእኔ ጋር ዓይን ለዓይን ተጋጨን፡፡ የውጭ ዜጋውም ቡችሎቹ ያንተ ናቸው ወይ በማለት በምልክት ጠየቀኝ፡፡ እኔም ራሴን በአዎንታ በመነቅነቅ የኔ መሆናቸውን ገለፅኩለት፡፡ የውጭ ዜጋውም ሀምሳ ብር ሠጥቶኝ አንዱን ቡችላ ወሰደ፡፡ በዚያ አጋጣሚ ውሾች መሸጥ ጀመርኩ" ብሎናል፡፡
ውሾችን፣ ድመቶችንም ሆነ ጥንቸሎችን የሚያመጡለት ሌሎች ሰዎች ናቸው፡፡ ካመጡለት ሠዎች ጋር በዋጋ ከተደራደረ በኋላ በእጥፍ ወይም ከዚያ በላይ በመሸጥ ላመጡለት ሠዎች የተስማማበትን ከፍሎ ቀሪውን ኪሱ ያደርጋል፡፡ በዚህም ከሠዎቹ (ከአምጪዎቹ) ይበልጥ እርሱ ተጠቃሚ እንደሚሆን ገልፆልናል፡፡ ውሾች ሲወለዱ ጠርተው የሚሸጡለት አንዳንዴም በነፃ የሚሰጡት ሰዎች መኖራቸውንም አልደበቀም፡፡ እርሱም በየአካባቢው መንደር ለመንደር በመዞር የሚፈልጋቸውን ዓይነት ውሾች ሲያገኝ አሳዳሪዎቻቸውን በማነጋገር የሚገዛበት ሁኔታ መኖሩን ነግሮናል፡፡
"ቀደም ሲል ውሾችን መሸጥ ስላልተለመደ ሽጣቸው ብሎ ውሾች የሚያመጣልኝ ሰው አልነበረም፡፡ ስለዚህ መንደር ለመንደር በመዘዋወር የምፈልጋቸውን ዓይነት ውሾች በመመልከት በአካባቢው የሚገኙ ሕፃናት የውሾቹን ባለቤቶች እንዲያሳዩኝ በማድረግ እገዛ ነበር" በማለት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በርካታ ሰዎች ውሾች እንደሚሸጡ በማወቃቸው እንደሚያመጡለት በመጠቆም በእጁ የያዘውን ቡችላ እኛን ከማግኘቱ የአንድ ሠዓት በፊት አንድ ሠው እንዳመጣለትና ለሠውዬውም አሥር ብር ሊሠጠው እንደተስማሙ ገልፆልናል፡፡
ዳንኤል እንዳለው ወሾችን ከሰዎች እንደተረከበ ለመሸጥ ወደ አስፋልት ይዞ ከመውጣቱ በፊት ያጥብና ያበጥራቸዋል፡፡ ለነሱ ባዘጋጀው ፎጣ አደራርቆ ለመሸጥ ያወጣቸዋል፡፡ ጐተራና ሣር ቤት አካባቢ ውሾችን ለረዥም ጊዜ ሸጧል፡፡ አሁን ደግሞ የዘወትር ቋሚ ቦታው ሸገር ህንፃ ፊት ለፊት ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ የሚሸጠው የተለያዩ የውጭ ዝርያ ያላቸውን ውሾች ነው፡፡ የውጭ ዝርያ ያላቸው ውሾች በሚሸጥበት ወቅት የውሾቹ ፆታ ብዙም ጥያቄ ውስጥ የማይገባ ሲሆን የሀበሻ ሴት ውሾች ግን ብዙም ተፈላጊ አይደሉም፡፡ የውሾቹ ዝርያ፣ ቀለማቸውና መጠናቸው በሚሸጡበት ዋጋ ላይ ተፅእኖ ያሳድራል፡፡ ቡል ዶግ፣ ዶቨር ማን፣ የአሜሪካና የጀርመን በማለት ይለያቸዋል፡፡ ፀጉራም ድንክ የሳሎን ውሻ እስከ አምስት መቶ ብር እንደሚሸጥና አንድ ውሻ በጣም በርካሽ ተሸጠ ከተባለ ከሀምሳ ብር በታች እንደማይሸጥ ይናገራል፡፡ "ጀርመን ሸፐርድ የሚባለው ቡናማ ውሻ በቀላሉ አይገኝም እንጂ እስከ አምስት መቶ ብር ይሸጣል" ብሏል፡፡
ሰዎች በገንዘብም ሆነ በነፃ ውሾች እንዲወስድ ሲጠይቁት የተለያዩ ባሕላዊ መንገዶችን (የምላሳቸውን ሁኔታ በመመልከት) በመጠቀም ጤንነታቸውን ለማረጋገጥ እንደሚሞክር ከንግግሩ ለመረዳት ችለናል፡፡ ቀደም ሲል ውሾችን በተደጋጋሚ ይገዙት የነበሩት የውጭ ዜጐች የነበሩ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በርካታ ኢትዮጵያውያን በይበልጥም ውጭ አገር ኖረው የመጡ እየተመላለሱ እንደሚገዙት አመልክቷል፡፡ ከዚህም ባሻገር ሥልክ ቁጥራቸውን በመተው የሚፈልጉትን ዓይነት ውሻ በመግለፅ የዚያ ዓይነት ውሻ ሲገኝ እንዲደውልላቸው የሚያደርጉ ደንበኞችም አሉት፡፡
ዳንአል እንደገለፀው እርሱ ውሾችን ከሰዎች ላይ ሲገዛ ከሰላሳ ብር ባላይ ከፍሎ አያውቅም፡፡ ውሾችም ሳይሸጡ እጁ ላይ አድረው አያውቁም፡፡ በቀን እስከ አሥር ውሻ የሚሸጥበት አጋጣሚም አለ፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ሥራ የሚጀምረው አረፋፍዶ ከጠዋቱ አራት ሠዓት ተኩል ገደማ ሲሆን ገበያ የሚኖረው ደግሞ ከአሥራ አንድ ሠዓት በኋላ ነው፡፡ ውሾቹን የሚሸጥበት አካባቢ ካሉ ካፍቴሪያዎችና ምግብ ቤት ሠራተኞች ጋር ያለው ግንኙነት መልካም በመሆኑ ከእነርሱ ትርፍራፊ ምግብ በመውሰድ ውሾቹን ይመግባቸዋል፡፡
እያነጋገርነው ሳለ በአካባቢው የነበሩ የፓርኪንግ ሠራተኞችና የካፍቴሪያ አስተናጋጆች ፣ፓፒ፣ እያሉ ሲጠሩት በመስማታችን ለምን እንደዚያ ብለው እንደሚጠሩት ጠየቅነው፡፡ "በተለያዩ ጊዜያት የምሸጣቸው ውሾች መጠንና ቀለም የሚለያይ ቢሆንም ሁሉንም ፓፒ በማለት ነው የምጠራቸው፡፡ የማግባቢያ ግጥሞችን የምጀምረውም ፣ፓፒ፣ ብዬ ነው" በማለት መልሶልናል፡፡
ውሻ ከገዙት ደንበኞች ጋር ጥብቅ ቅርበትን እንደሚመሰርት የሚናገረው ዳንኤል ውሾቹን በሚመለከት የተለያዩ መረጃዎችን ለምሳሌ ሲታመሙባቸው እርሱ ወደሚያውቃቸውና እዚያው በሚሸጥበት አካባቢ ወደሚገኙ የእንስሳት ሕክምና እንደሚመራቸው አስረድቷል፡፡ በግለሰብ ቤት ተከራይቶ ስለሚኖር እንጂ የተመቻቸና ሰፊ ቦታ ቢኖረው ውሾችን ከሌሎች ሰዎች ከመግዛት ይልቅ ራሱ ቢያረባ የተሻለ ሊሠራ እንደሚችል አመልክቷል፡፡ |