Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Thursday
Aug 28th
Home arrow Sections arrow በወሊድ ምክንያት የተጎዱ እናቶች
በወሊድ ምክንያት የተጎዱ እናቶች Print E-mail
Sunday, 01 June 2008
በታደሰ ገብረማርያም

ሥፍራው በአዲስ አበባ ፌስቱላ ሆስፒታል ሲሆን ጊዜያቱም ከጧቱ ሶስት ሠዓት ነው፡፡ በግቢው ውስጥ በወሊድ ምክንያት የተጎዱ እናቶች በቡድን በቡድን ተቀምጠው የጧት ፀሐይ ይሞቃሉ፡፡ ሁሉም አንድ አይነት ፒጃማ ለብሰዋል፡፡ ፎጣ ቢጤም ትከሻቸው ላይ ጣል አድርገዋል፡፡ ከመካከላቸውም የሰባትና የስምንት ዓመት ሕፃናት ይገኙባቸዋል፡፡
አንዳንዶቹ በተቀመጡበት ሥፍራ ሆነው ጥልፍና የሹራብ ሥራ ያከናውናሉ፡፡ ከፊሎቹ ፈንጠር ብለው በየተራ ፀጉራቸውን ሹሩባ ይሠራሉ፡፡ ሌሎቹ ደግሞ በዋናው ዋርድ በረንዳ ለይ ተቀምጠው በእርግዝናና በወሊድ ጊዜ ሊያደርጉ የሚገባቸውን ጥንቃቄ በተመለከተ የሚተላለፈውን የቴሌቪዥን ፕሮግራም ይከታተላሉ፡፡

ህፃናቱ ወላጅ እናቶቻቸውን ለማስታመም የመጡ እንጂ በሌላ የሚጠረጠሩ አይመስሉም፡፡ ወደ አንደኛዋ ህፃን ዘንድ ጠጋ አልኩና ማሚት ስምሽ ማን ነው? ከየት ነው የመጣሽው? ለምን መጣሽ? የሚሉ ጥያቄዎችን ደረደርኩላት፡፡ ከመሽኮርመም በስተቀር ምንም አልመለሰችልኝም፡፡ “እንደኛው ተጎድታ ሕክምና ለማግኘት ወረፋ በመጠባበቅ ላይ ነች” አለችኝ ሹሩባ  ከሚሰሩት ጉዳተኛ እናቶች መካከል አንደኛዋ፡፡

ሁሉም እንዳነጋግራቸው ፈቃደኛ ነበሩ፡፡ ነገር ግን ድርጅቱ ማወቅ አለበት የሚል እምነት ስላደረብኝ ወ/ት ቤቴል አማኑኤል የአዲስ አበባ ፌስቱላ ሆስፒታል የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊን ጠይኳት፡፡ “ይቻላል ነገር ግን ሆዳቸው ስለሚባባና ስለሚረበሹ ጥያቄዎች ላይ ጥንቃቀቄ አድርግ” አለችኝ፡፡

ያነጋገርኳቸው በሙሉ ከደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ሕዝቦች፣ ከአማራ፣ ከትግራይና ከኦሮሚያ ክልሎች የመጡ ናቸው ሁሉም ያለዕድሜ ጋብቻን አጥብቀው ይቃወማሉ፡፡ ሴት ልጅ ለአቅመ ሔዋን ብትደርስም ያለፍላጎቷ በቤተሰብ ተጽዕኖ ብቻ ለባል መሰጠት እንደሌለባት ነው የተናገሩት፡፡ ከእነዚህም መካከል አማረች አዱይማ በሰጠችው አስተያየት ..ዕድሜዬ 15 ዓመት ነው፡፡ ያለፍላጎቴ በቤተሰብ ተፅዕኖ ለባል ተሰጠሁ፡፡ ወዲያውኑ የዚህ አይነቱ (የፌስቱላ) ጉዳተኛ ለመሆን በቃሁ፡፡፡ እዚህ ሆስፒታል ከመጣሁ ሁለት ወር ሆኖኛል፡፡ የቀዶ ሕክምና ለመጀመር ወረፋ በመጠባበቅ ላይ ነኝ፡፡ የሕክምና ባለሙያዎችና የሌሎችም ጠቅላላ ሠራተኞች እንክብካቤ ተለይቶኝም አያውቅም፡፡ በንጽህና አጠባበቅ ላይ ትኩረት እንድናደርግ ይመክሩናል.. ብላለች፡፡

ፈለቀች ዳና የተባለችው ሌላዋ ጉዳተኛ የ25 ዓመት ወጣት፣ ባለትዳርና የሁለት ልጆች እናት መሆኗን፣ ለጉዳት የተዳረገችው ሁለተኛውን ልጇን በተገላገለችበት ወቅት እንደሆነ አስረድታለች፡፡ ሕክምናዋንም እንደጨረሰች ወደ ትውልድ ሥፍራዋ ተመልሳ በትዳሯ እንደምትቀጥል ገልጻለች፡፡

ለታይ ገብረ መድህን የተባለችው ሌላዋ አስተያየት ሰጪ ትዳር እንደነበራትና ልጅ ግን እንዳልወለደች ተናግራለች፡፡ ..ለጉዳት ከተዳረኩ በኋላ ከባለቤቴ ጋር ተፋታሁ፡፡ ወዲያውኑ ወደዚሁ የሕክምና ተቋም መጥቼ አስፈላጊው እርዳታ ከተደረገለኝ በኋላ ለከፍተኛ ሕክምና በቀጠሮ ወደ ትውልድ ሥፍራዬ ተመለስኩ፡፡ በቀጠሮዬ መሰረት መጥቼ ቀጣይ ሕክምና ለማግኘት ወረፋ በመጠባበቅ ላይ ነኝ፡፡ የሆስፒታሉ የፅዳት አጠባበቅ፣ የሕክምና አሰጣጥና የሐኪሞቹ አለመሰልቸት በራሱ ለኛ ፍቱን መድሃኒታችን ሆኖ አግኝተነዋል.. ብላለች፡፡

ተአቡ ብርሃኔ የ15 ዓመት ታዳጊ ወጣት መሆኗን ገልጻ ለሕክምና የመጣችውም በወላጅ አባቷ አማካይነት እንደሆነ አስረድታለች፡፡ “ይህ ሆስፒታል ባይደርስልን ኖሮ እንደ እኛ አይነቶቹ ፍጻሚያችን ወይም መጨረሻችን ምን ሊሆን እንደሚችል ሕብረተሰቡ ሊረዳው ይገባል” በማለት ተናግራለች፡፡

የአዲስ አበባ ፌስቱላ ሆስፒታል የሕዝብ ግንኙነት ቢሮ ባወጣው አጭር ማብራሪያ እንዳመለከተው እ.ኤ.ኤ በ2005 የተካሄደ ጥናት እንደሚያሳየው በገጠሪቱ ኢትዮጵያ 40ሺህ ሴቶች በወሊድ ሳቢያ ለጉዳት ተዳርገዋል፡፡ እ.ኤአ ከ1974 ጀምሮ ለ30ሺህ ሴቶች ሕክምና ተሠጥቷል፡፡ ከነዚህም መካከል 400 ያህሉ በሽታው ከፍተኛ ደረጃ ላይ በመድረሱ እስከ ሕይወታቸው ፍጻሜ ድረስ ሕክምናና ክትትል ያስፈልጋቸዋል፡፡

ቢሮው ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በ1997 ያወጣውን ጠቋሚ መረጃዎችን (ኢንዲኬተርስ) ጠቅሶ እንደዘገበው በሀገሪቱ 163 የጽንስና ማህጸን ሀኪሞችና 1509 አዋላጅ ነርሶች ይገኛሉ፡፡ ከሀኪሞቹም መካከል 44ቱ መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች፣ 17ቱ በሌሎች መንግሥታዊ በሆኑ ድርጅቶች 33ቱ በግል፣ 64ቱ በመንግሥት ተቋማት በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡ ከአጠቃላይ ሀኪሞች መካከልም 13ቱ ሴቶች ናቸው፡፡

በወሊድ ሳቢያ ለጉዳት ከሚዳረጉት በርካታ ክስተቶች መካከል ድህነት፣ የተመጣጠነ ምግብ እጦት፣ ከባድ ሥራ፣ በቂ ያልሆነ ወይም ምንም ትምህርት አለማግኘት፣ የሥርዓተ ፆታ ችግር፣ የወንድ ተሳትፎ አናሳነት ወዘተ ናቸው፡፡ እ.ኤ.አ በ1974 የተመሠረተው የአዲስ አበባ ፌስቱላ ሆስፒታል በአሁኑ ጊዜ ለ2ሺህ 200 ሕሙማን አስፈላጊውን የሕክምና አገልግሎት እየሰጠ ሲሆን በየዓመቱም እስከ 9ሺህ የሚጠጉ አዲስ ሕሙማንን ይቀበላል፡፡ በአፍሪካና ለሌሎችም ታዳጊ አገሮች ሐኪሞች ሥልጠና በመስጠት የጎላ ሚና ይጫወታል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ይኖራሉ ተብለው ከሚገመቱ 2.9 ሚሊዮን ነፍሰ ጡሮች ከየአንድ ሺህዎች መካከል ሦስቱ በወሊድ ሳቢያ እንደሚጎዱም አብራርቷል፡፡

የዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅት ዘገባን ዋቢ አድርጎ ቢሮው እንዳመለከተው በታዳጊ አገሮች ውስጥ ከሁለት ሚሊዮን በላይ የሚጠጉ ሴቶች ከፌስቱላ በሽታ ጋር አብረው ይኖራሉ፡፡ በዓመቱም 100ሺህ የፌስቱላ ሕሙማን ለሕክምና ይቀርባሉ፡፡

የተባበሩት መንግሥታት የስነ ሕዝብ ጉዳይ ድርጅት መረጃዎችን ዋቢ ያደረገው ይኸው ማብራሪያ በየደቂቃው አንድ ሴት፣ በየቀኑ ደግሞ 400 ሴቶች፣ በዓመቱ ደግሞ 529 ሺህ ሴቶች ከእርግዝናና ከወሊድ ጋር በተያያዙ ችግሮች ለሕልፈተ ሕይወት ይዳረጋሉ፡፡ በእናቶች ሞት ሳቢያ በየዓመቱ አንድ ሚሊዮን ሕፃናት ወላጅ አልባ ይሆናሉ፡፡ ከስምንት ሚሊዮን ሕፃናት መካከልም 3.4 ሚሊዮን ያህሉ በእናቲቱ የጤንነት ቀውስና በአግባቡና በትክክል ካለመወለድ የተነሳ በየዓመቱ ይሞታሉ፡፡

የአዲስ አበባ ፌስቱላ ሆስፒታል ግብ የፌስቱላ በሽታን በትምህርት፣ በመከላከልና በሕክምና መቀነስ ሲሆን ዓላማው ደግሞ በሽታው በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት ውስጥ ወደ 50 ከመቶ ዝቅ እንዲል ማድረግ፣ የትምህርቱን፣ የመከላከሉንና የሕክምናውን ፕሮግራም እንዲሁም የደጋፊዎችንና የአጋሮችን ቁጥር ማብዛት መሆኑን ከመግለጫው ለመረዳት ተችሏል፡፡

ሚስተር ብሩስ ዳቪስ የአውስትራሊያ ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት ዳይሬክተር ጄኔራል ድርጅቱ ለኢንቨስትመንት የሚውል 18 ሚሊዮን 500ሺህ ብር በሆስፒታሉ ስም ባንክ ለሁለት ዓመት ያህል እንደሚያስቀምጥ፣ ከተቀመጠው ከዚሁ ገንዘብ የሚገኘው ወለድ ለሆስፒታሉ ድጋፍ እንደሚወል ገልፀዋል፡፡ ይህም እ.ኤ.አ ከ1993 ጀምሮ ድርጅቱ የሰጠውን የእርዳታ መጠን ወደ 52 ሚሊዮን 720ሺ ብር ከፍ እንደሚያደርገው አስረድተዋል፡፡

ይህ አይነቱ እርዳታ የሆስፒታሉን የቀዶ ሕክምና ክፍሉን ጨምሮ አጠቃላይ ሥራውን ለማጎልበትና ለማሻሻል እንዲሁም ለሕንፃዎች ማስፋፊያ፣ ለቤተመፃህፍትና ለፓቶሎጂ ማጠናከሪያ መዋሉን ሚስተር ብሩስ ገልፀዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ለሆስፒታሉ ሁሉን አቀፍ ዕርዳታ ከመስጠት ወደ ኋላ እንደማይል፤ በየክልሎቹ ላሉት ቅርንጫፎችም ሆነ ወደፊትም ለሚቋቋሙት ተገቢውን እገዛ እንደሚያደርግ ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም የጤና ጥበቃ ሚኒስትር አስታውቀዋል፡፡

ሚኒስትሩና ጄኔራል ዳይሬክተሩ ይህንን የተናገሩት የሆስፒታሉን ልዩ ልዩ የመገልገያ ክፍሎች እየተዘዋወሩ ከጎበኙና በወሊድ ምክንያት ለተጎዱ እናቶች እያበረከተ ያለውን የሕክምና አገልግሎት በተመለከተ ማብራሪያና ገለፃ ከተደረገላቸው በኋላ ነው፡፡  
 
< Prev   Next >