|
መከራን በጥበብ የተቋቋሙት ሠዓሊዋ ልዕልት |
|
|
|
Sunday, 01 June 2008 |
 ቅድስት ሥላሴ  አፄ ዮሐንስ  ደጃዝማች ዘውዴ በሔኖክ ያሬድ ከተርታው ኅብረተሰብ ባሻገር በዘውዳዊ ቤተሰብ (ሮያል ፋሚሊ) ውስጥ ያሉ እምብዛም በሥነጥበብ ሙያ ውስጥ ጐልተው አይታዩም፡፡ በተለይ ከእንስቶቹ መካከል ወደ ጥበብ የተጠጉ በቀደመው ጊዜ ብዙም አይደሉም፡፡
በቅኔ ጥበብ ከሚታወቁት የጎጃሟ እማሆይ ገላነሽ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በሰሜኑ የአገራችን ክፍልም (ትግራይ) በባህላዊው አሳሳል መንገድ የቤተክርስቲያን ሥዕል የሚስሉ ጠቢብ እናትም በቅርቡ አጋጥመውናል፡፡ ከዘውዳዊው ቤተሰብ ግን ብዙም አልተሰማም፡፡ በቅርቡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም የልዕልት ወለተ እሥራኤል ሥዩምን የሕይወት ዘመን ሥራዎችን በተቋሙ ዐውደ ሥነ ጥበባት (አርት ጋለሪ) ለሕዝብ እይታ አብቅቷቸዋል፡፡ በአሁን ጊዜ በመታየት ላይም ይገኛሉ፡፡
አፄ ዮሐንስ ቅድመ አያታቸው የሆኑት ልዕልት ወለተ እሥራኤል 25 ሥራዎቻቸው ናቸው ለእይታ የበቁት፡፡ ልዕልቲት የተወለዱት ጥር 14 ቀን 1906 ዓ.ም ሲሆን በ1917 ዓ.ም በ11 ዓመት ዕድሜያቸው ዘውዴ ገብረሥላሴን ይወልዳሉ፡፡ ባለቤታቸው ስላረፉ በ16 ዓመታቸው ፈት ቢሆኑም በ1926 ዓ.ም ሁለተኛ ባላቸውን ልዑል መርዕድ አዝማች አስፋ ወሰንን ያገባሉ፡፡ ጋብቻው በሁለቱ የፖለቲካ ተቀናቃኞች (በቀዳማዊ ኃይለሥላሴና በልዑል ራስ ሥዩም መንገሻ) መካከል ኅብረትን ይፈጥራል፡፡ ሁለተኛዋን ልጃቸው ልዕልት እጅጋየሁንም ይወልዳሉ፡፡ በፋሺስት ጣሊያን ወረራ (1928 - 1933) በኢየሩሳሌምና በእንግሊዝ ስደት የቆዩት ልዕልት ሁለተኛው ጋብቻቸውም ያበቃል፡፡ ቀሪ ሕይወታቸውን በብሕትውና በመወሰን መንፈሳዊ ጉዟቸውን ይቀጥላሉ፡፡
ከወጣትነታቸው ዘመን ጀምሮ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ትውፊት በመመሰጥ ሕይወታቸውን የመሩ ሲሆን ጥንታዊ ቅርሶችን ሃይማኖታዊ ሥዕሎችን በማየት በማደጋቸው ግእዝ፣ ዜማ፣ ቅኔ ማጥናታቸው ቅዱሳት መጻሕፍትን ገድለ ሰማዕታትን፣ መልክዐ መልክዕ፣ ስንክሳርን በወጉ በማንበባቸው ለሥዕል ሥራቸው እንደጠቀማቸው ይታወቃል፡፡
በሕይወታቸው ውስጥ አስከፊና ሰቆቃ የደረሰባቸው በ1969 .ም ተወዳጅ እናታቸው እማሆይ ደብሪቱ መኮንን ማረፋቸው ብቻ ሳይሆን ከሁለት ሳምንት ቆይታ በኋላ በደርግ እስር ቤት ውስጥ የታሰሩ ልጃቸው ልዕልት እጅጋየሁ አስፋወሰንም ያርፋሉ፡፡ የልጅ ልጆቻቸውም ከአገር ይወጣሉ፡፡ ልዕልቲቱ ለመከራ እጅ አልሰጡም፤ መንፈሳዊ መነቃቃትን አድሏቸው ወደ ሥነጥበቡ ማድላታቸው ይነገራል፡፡
በዐውደ ርእዩ የቀረቡት ሥራዎቻቸው ሁለት መልክ ሲኖራቸው አንደኛው በኦርዶቶዶክሳዊ ክርስትና ላይ የተመሰረቱና ሁለተኛው ደግሞ በታሪክ ውስጥ ዐቢይ ሥፍራ ያላቸው ንጉሥና መሳፍንት የሚያሳዩ ሥዕሎች ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም የልዕልቲቱን ሥራዎች ከቤተሰብና ከቀጨኔ መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን በማሰባሰብ "የእምነት እና ቅርስ ግላጼ" (Expressions of faith and heritage) በሚል ርእስ አቅርቦታል፡፡
ምንኩስናና ብሕትውናን ከሚያሳዩ ሥራዎቻቸው ከኢትዮጵያ አቡነ ተክለ ሃይማኖት፣ ከግብጽ አቡነ እንጦንስና ቅዱስ ሞክሲሞስን በትውፊታዊው አሣሣል ያቀረቡበት ነው፡፡
የአቡነ ተክለሃይማኖት ከተለመደው ስድስት ክንፎች በተለየ 12 ክንፎች አድርገውላቸው የሠሩት እጨጌ ተክለሃይማኖት በ13ኛው ክፍለ ዘመን በሥራቸው 12 ልዑካንን (ሐዋርያትን) በአገሪቱ ማሠራጨታቸውን ለማጠየቅ እንደሆነ ከታሪኩ መረዳት ይቻላል፡፡
ከመንፈሳዊ ሥዕሎች ጎን ለጎን ያቀረቧቸው የአፄ ዮሐንስና፣ የልዑል ራስ ሥዩም መንገሻ የባለቤታቸው የደጃዝማች ገብረሥላሴ፣ የልጃቸው የደጃዝማች ዘውዴ ገ/ሥላሴ ምስሎች ይገኙበታል፡፡
በኢትዮጵያ ነገሥታት አሳሳል ታሪክ ውስጥ አፄ ዮሐንስ ጐልተው የሚታወቁበት ሹሩባ ተሠርተው የተሣሉት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ልዕልቲቱ ግን በራሳቸው የፈጠራ መንገድ በዙፋን አስቀምጠው የሣሉት ለየት ይላል፡፡ እንደ ዶ/ር ደጃች ዘውዴ ማብራሪያ "ልብሰ መንግሥት፣ ልብሰ ክህነት አስለብሰው ዘውድና ሉልን በትረ መንግሥትም አስይዘው ያቀረቡበት ሥዕል ነው፡፡
ስለ አፄ ዮሐንስ ከውጭ አገር ያገኘሁት አለቃ ዘዮሐንስና አለቃ ለምለም የሚባሉ ሁለት ደብተሮች የጻፉት "ዜናሁ ለመዋዕለ ዮሐንስ" ልኬላት ስለነበር እርሱን መሠረት አድርጋ የንግሥ በዓላቸው ጊዜ እንዴት እንደነበረ ለማሳየት ሞክራለች፡፡
አፄ ዮሐንስ ክህነትም ስላላቸው ሲነግሡ መንኩሰዋል፡፡ ከልብሰ መንግሥታቸው በተደራቢ ልብሰ ተክህኖ በአረንጓዴ መልክ አልብሰዋል፡፡ በታሪኩ እንደተጻፈው ጳጳሱ ዘውዱን ይደፉላቸዋል፣ የአክሱም ንቡረ እድ ካባውን ያለብሳል የሚል ዝርዝር አለው፡፡
በፈረንሣይ ብሔራዊ ቤተ መጻሕፍት ከሚገኙ የአፄ ዮሐንስ ዜና መዋዕሎች አንደኛው እስከ ንግሥ በዓላቸው ድረስ ሲተርክ፣ ሌላኛው እስከግብጽ ጦርነት ድረስ ይገልፃል፡፡ መጻሕፍቱን ማሳተም እንደሚቻልና በተለይ ከ30 ዓመት በፊት ያሳተምሁት የንጉሠ ነገሥት ዮሐንስ ፖለቲካዊ ታሪክ ዳግም ተስፋፍቶ በአሜሪካ በመታተም ላይ ነው፡፡ በተያያዘም የአፄ ዮሐንስን ታሪክ ወደ አማርኛ በመተርጎም ለማሳተም ባስብበትም ከርሱ በፊት የኤርትራና ኢትዮጵያ ግጭት መንስዔና መፍትሄ የሚል በአማርኛ 500 ገጽ ጽፌአለሁ፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ይታተማል፡፡
እናቲቱ ልዕልት፣ የልጃቸውንም ምስል ከእውቀት ፍሬ ጋር አዛምደው ሰርተውታል፡፡ "ጊዜውን በትምህርት ላይ የሰዋ የረገጠው ሁሉ ፍሬ ነው" ይላል የሥዕሉ ዐቢይ ቃል፡፡ በ1939 ዓ.ም ከእንግሊዝ እንደተመለሱ የተነሱትን ፎቶግራፍ መሠረት አድርገው እስከ ዱክትርና የደረሱበት ዕውቀት ሠዓሊዋ ልዕልት ውድ በሆነ የፖም (አፕል) ፍሬ ትእምርትነት ከስተውታል፡፡
ሠዓሊዋ ልዕልት ከሠሯቸው ሃይማኖታዊ ሥዕሎች መካከል ከተለመደው ትውፊታዊ አሣሣል ወጣ ያለ፣ ካነበቧቸው መጻሕፍት በመነሳት ቅድስት ሥላሴን የገለጹበት መንገድ ልዩ ነው፡፡ የተለመደው በሰው አምሳል የተሣሉ፣ ሦስቱን የሚያሳይ ሲሆን በልዕልቷ ሥዕል ላይ ግን በእያንዳንዱ ምስል በወልድ ልብ ላይ በግ፣ በመንፈስ ቅዱስ ልብ ላይ ርግብ፣ በአብ ልብ ላይ ዓይን ተስሏል፡፡ በጉ የፋሲካ በግ መሆኑን፣ በርግብ አምሳል መንፈስ ቅዱስ መውረዱን ሲያሳይ፣ ዓይን ደግሞ በዋናነት ተሥሏል፡፡ አብን በዓይን መመሰላቸው የመልክዐ ሥላሴን ንባብ ያስታውሰናል፡፡
"ሰላም ለአዕይንቲክሙ እለተኬነዋ አዕይንተ" "ዓይኖችን ለፈጠሩት ዓይኖቻችሁ ሰላም እላለሁ፡፡"
ሥራዎቻቸውን ወደ ይደርሳሉ፡፡ ለትውልድ በሚተርፍ መልኩ በካታሎግ ለማዘጋጀት ሐሳቡ እንዳላቸውና በአሜሪካ በሠዓሊነት ሙያ የሚገኘው የልዕልት የልጅ ልጅ ይስሐቅ ፍቅረ ሥላሴ ሀብተ ማርያም እንደሚያዘጋጀው እምነታቸው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ስለ ልዕልት ጋብቻና የትዳር ሕይወት ደጃዝማች ዘውዴ ሲያነሱም፣ የመጀመሪያ ባላቸው በነበረው ሁኔታ አባቴን ስታገባ ከአባቷ ከራስ ሥዩም 18 ዓመት ይበልጣሉ፡፡ ጦርነት ሆኖ ብዙ ደም ተፋስሶ ስለነበር ደም ማድረቂያ ተብሎ ነው ጋብቻው የተመሰረተው፡፡ እናቴ 14 ዓመት ነው የምትበልጠኝ፡፡ አባቴ ሲሞቱ እናቴ እመንናለሁ ብላ ደብረ ሊባኖስ እሄዳለሁ ስትል ተያዘችና መጣች፡፡ ለአልጋ ወራሽ ተዳረች፡፡ አልጋወራሽን በዕድሜ ትበልጣለች፡፡ መንፈሣዊ በመሆኗ አንድም ጾም አይቀራትም፡፡ የዚህ ዓለም ክብር ክብር መስሎ አይታያትም ብለዋል፡፡
በማኅበራዊ ኑሯቸው 200 ሕፃናትንና አቅመ ደካማ አረጋውያንን ይቀልቡ የነበሩት ልዕልት፣ ደርግ ሥልጣን ላይ እንደወጣ ከልዑላኑ ጋር ሲያስራቸው የስም ልዕልት ናቸው እንጂ እንዴት ይታሠራሉ ብሎ ኅብረተሰቡ በመቃወሙ ማታውኑ መለቀቃቸውን ያስታውሳሉ፡፡
እቴጌ ጣይቱ፣ እቴጌ ምንትዋብ ሌሎች ትልልቅ ሴቶች ሥዕል ሳይ እየቀጠሩ በማሳል፣ በመርዳትና ጠባቂ (ፓትሮን) በመሆን ብዙ ተግባራት የፈጸሙ አሉ፡፡ የሴት ሠዓሊ ብዙም አላየን ያሉት ዶ/ር ዘውዴ፣ ሌላው ሙያቸው በገና የመደርደር እንደሆነ አውስተዋል፡፡
ልዕልት ወለተ እሥራኤል ልዑል አልጋወራሽን ካገቡ በኋላ ከመንበራቸው ደሴ ሄደው በተቀመጡ ጊዜ የጦሳን ተራራ ንድፍ ይሠሩ እንደነበረ የሚያስታውሱት ልጃቸው በተለያዩ ጊዜያት የሣሏቸውን 15 ሥዕሎች ለየአብያተ ክርስቲያናት መስጠታቸው፣ በአክሱም ጽዮን ማርያም ብቻ ይቀመጥ የነበረው "ድርሳነ ጽዮን" የተሰኘውን መጽሐፍ በብራና በማስገልበጥ ለእንጦጦ መንበረ ፀሐይ ቅድስት ማርያም፣ ለግሸን ማርያም ማበርከታቸውን ይጠቅሳሉ፡፡
በሥዕሎቻቸው ግርጌ የተጻፉት የዘመን መግለጫዎች ሥራዎቹ ከ1950ዎቹ ጀምሮ የተሣሉ መሆናቸው በተለይም በ1969 እናትና ልጃቸው ካረፉ በኋላ ሐዘናቸውን ለመወጣት ጊዜያቸውን ሙሉ ለሥዕል መስጠታቸው ይታወቃል፡፡
መፍቀሪተ ግእዝ (የግእዝ ወዳጅ) መሆናቸው ከሚያሳየው በሥዕሎቻቸው ራስጌ ከቅዱሳኑ ምስል ታሪክ ጋር የሚያያይዝ ኃይለ ቃል ማስቀመጣቸው ነው፡፡ ለምሳሌ የትንሣኤ ሥዕል ራስጌ በ6ኛው ምእት ዓመት ቅዱስ ያሬድ የደረሰውን "ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን" (ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ ተነሣ) የሚለውን ምልልስ በዕርገቱም ላይ እንዲሁ "ዐርገ በስብሐት ውስተ ሰማያት" ብለው ጽፈውታል፡፡
"ጸሎተ ኀሙስ" የተሰኘው ኢየሱስ ክርስቶስ በጌቴ ሰማኒ ያደረገውን ጸሎት፣ በቀራንዮ የሚያጋጥመውን ስቅለትና የሾሕ አክሊል (ኲርዓተ ርእሱ) በዳራነት ተሳስረው የተሣሉበት መንገድ የተመልካችን ቀልብ የሚስብ ነው፡፡
ሠዓሊዋ ልዕልት ሥራዎቻቸው በአክሱም፣ በሰሜን (ጎንደር) በአዲስ አበባ፣ ብሥራተ ገብርኤል፣ ቀጨኔ መድኃኔዓለም፣ አቦ ይገኛል፡፡
አባቴን በልጅነቴ ነው ያጣሁት፡፡ የአባቴ ገና በአራት ዓመቴ ካባ እያለበሱኝ ጌቶች እያሉ ተንከባክበውኛል፡፡ በስደት ወደ ግብፅ በሄድን ጊዜ ገዳመ አስቄጠስን ለማየት ሄድን ያረፍንበት ቤት ያስተናገደን ሰው ባለቤቱ እኔን ቤቱን እንድጠርግ ታዘኛለች፡፡ ተናደድሁና መኝታ ክፍል ገብቼ ተኛሁ፡፡ ሲመጡ እሰማለሁ የተኛሁ መስዬ አንኮራፋለሁ፤ እናቴ ከተኛሁበት ገልጣ ልቤ እስኪጠፋ በቀበቶ ገርፋኝ ማነህ ኧረ ለመሆኑ አንተ? ከአፈር የተፈጠርህ ኮርተህ ነው? ይህ ሰው በደግነቱ የትም ወድቀን እንዳንቀር ከቤቱ ያገባን፣ ቤት አልጠርግም የምትለው ጥጋብ ነው ብላ ወረደችብኝ፡፡ የዚያን ዕለት ዓይነ ጥላዬ ተገፈፈ፤ ከዚያ ወዲያ ሰው ሆንኩ፡፡ ማነኝ እኔ ለካስ በልጅነቴ ጌታዬ ጌታዬ እየተባልኩ ስታለል ኖሬአለሁ፡፡ ተራ ሰው ነኝ ብዬ ለማመን የበቃሁት በእናቴ ነው፡፡ ይህን እንደ ትልቅ ውለታ እቆጥረዋለሁ፡፡
መቀሌ አጼ ዮሐንስ ቤተመንግሥት በ1906 ዓ.ም የተወለዱት ልዕልት ወለተ እሥራኤል ያረፉት በ1980 ዓ.ም ነው፡፡
መንፈሣዊ መነቃቃታቸው፣ ሠዓሊነታቸው፣ የኅብረተሰቡ አርአያ የመሆናቸው ያህል ለወንዶች "ፓትርያርክ" እንደሚባለው ለሴቶችም "ማትርያርክ" የሚለው አጠራር የሚገባቸው መሆኑ አንድ ተመልካች አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡ |