| የኤሌክትሪክ ሀይል ተፅዕኖ |
|
|
| Wednesday, 04 June 2008 | |
![]() ወጣት ተክሉ ደሳለኝን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተጀመረው የኤልክትሪክ ሀይል በፈረቃ መቋረጥ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች ተደራጅተው የሚንቀሳቀሱ ወጣቶች ላይ እያሳደረ ያለውን ተፅዕኖ ለመመልከት ወደ ልደታ ክፍለ ከተማ አመራን፡፡ በክፍለ ከተማው ውስጥ ፕሪካስትና ብሎኬት በማምረት ለቤቶች ልማት በማስረከብ የሚንቀሳቀሱ አምስት ወጣት ማህበራት አሉ፡፡ ከአምስቱ አንዱ የሆነውን የውበት ኮንስትራክሽን ወጣቶች ማህበር ወጣት ተክሉ ደሳለኝን አነጋግረነዋል፡፡ ማህበራቸው በቀበሌ ድጋፍ በ1997 መመሥረቱንና በማህበር ከመደራጀታቸው በፊትም እያንዳንዱ አባል በቀበሌ በኩል የተለያዩ የሙያ ሥልጠናዎችን ከዚያም በቤቶች ልማት በኩል የግንባታ ዘርፍ ሥልጠና ማግኘቱን ገልፆልናል፡፡ ወርክሾፓቸው የደረስነው ጠዋት ላይ ነበርና ሁሉም አባላት በጥድፊያ ከወዲያ ወዲህ እያሉ ሥራቸውን ሲያከናውኑ ተመለከትን፡፡ የኤሌክትሪክ ሀይል በማይኖርበት ቀን ያለምንም ሥራ ቁጭ ብለው ስለሚውሉ ተረኛ በማይሆኑበት ቀን የተፈጠረውን ክፍተት ለመሙላት የተቻላቸውን ጥረት እንደሚያደርጉም ገልፀውልናል፡፡ ነገር ግን የኤሌክትሪክ ሀይል በሚኖር እለት የቱን ያህልም በመንቀሳቀስ የሚያመርቱትን ፕሪካስት ቁጥር ለማሳደግ ቢሞክሩም የሚፈጠረውን ክፍተት መሙላት ቀላል እንዳልሆነ አመልክቷል፡፡ ውበት ኮንስትራክሽን አስራ ስምንት አባላት ያሉት ሲሆን አምስቱ ሴቶች ናቸው፡፡ ከብረትና ከኮንክሪት ፕሪካስቶችን በማምረት ለቤቶች ልማት ያስረክባሉ፡፡ አንድ ፕሪካስት ተሰርቶ ለቤቶች ልማት ከመረከቡ በፊት በደንብ እንዲደርቅ በወርክሾፑ ለሀያ አንድ ቀናት እንዲቆይ የሚደረግ ሲሆን የኤሌክትሪክ ሀይል በሳምንት ሦስትና ሁለት ቀናት መቋረጥ የምርት መጓተትን እንዳስከተለ አልደበቁም፡፡ “ብረቶች እየተበየዱ ቶሎ ቶሎ ኮንክሪት መሞላት ካልቻሉ እንከስራለን፡፡ ቤቶች ልማትም በተገቢው ጊዜ መረከብ የሚኖርበትን ፕሪካስት መረከብ አይችልም፡፡ ቤቶች ልማት የሚከፍለን ባመረትነው መጠን በመሆኑ የኤሌክትሪክ ሀይል መቋረጥ ለእኛ ከባድ ችግር ነው የሚፈጥርብን” ብሏል፡፡ ወጣት ተክሉ እንዳለው በኤሌክትሪክ ሀይል አለመኖር አባላት ሥራ ፈትተው እንዳይቀመጡና ጫና እንዳይፈጠር ያለኤሌክትሪክ ሀይል መከናወን የሚችሉ ሥራዎችን (ብረቶችን ለብየዳ ማመቻቸትና ማሠር) የመሳሰሉትን ሥራዎች ያከናውናሉ፡፡ ይህ ግን በወርክሾፑ አብዛኛውን ጊዜ የሚኖረው ብረታ ብረት መጠነኛ ስለሚሆን በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚጠናቀቅ ሥራ ነው፡፡ ስለዚህም የተለያዩ ጥረቶችን ማድረግ ቢቻልም ተፅዕኖውን ለመቋቋም የሚያስችል ዓይነተኛ አማራጭ የለም፡፡ የአባላት ወርሀዊ ክፍያ ምርትን መሠረት ያደገ በመሆኑ የምርት መስተጓጐል በወርሀዊ ደሞዛቸው ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አለው፡፡ የምርት መስተጓጐልን በተመለከተ ከቤቶች ልማት ጋር እስከ አሁን የተነጋገሩበት ሁኔታ አለመኖሩን የሚናገረው ወጣት ተክሉ የሀይል እጥረቱ በግለሰብም ሆነ በአገራዊ ደረጃ እያደረሰ ያለው ችግር ከሚገመተው በላይ ይሆናል የሚል እምነት አለው፡፡ አሥራ ስምንቱ ወጣቶች በአንድ ላይ ተሰባስበው ውበት ኮንስትራክሽንም ሆነ በክፍለ ከተማው (በልደታ) የሚንቀሳቀሱት ሌሎች ወጣት ማህበራት ሲመሠረቱ የማምረቻ ቦታን፣ ብድርና ሥልጠና በማግኘት በኩል ከሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት የተደረገላቸው ድጋፍ ጥሩ እንደነበር በመጠቆም ተደራጅተው በመንቀሳቀስ ላይ ያሉ አብዛኞቹ ወጣቶች የተሰማሩበት የምርት ዘርፍ ከኤሌክትሪክ ሀይል ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው በመሆኑ የሀይል እጥረቱ ከሞላ ጐደል ሁሉም ላይ አሉታዋ ተፅዕኖ እንደሚኖረው አመልክቷል፡፡ በልደታ ክፍለ ከተማ ከእነሱ ጋር ተመሳሳይ በሆነ የምርት ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ወጣቶች ያሉበትን ወቅታዊ የምርት እንቅስቃሴ በምሳሌነት መጥቀስ እንደሚቻልም ገል”ል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |