Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Friday
Aug 29th
Home arrow Sections arrow በላ ልበልሃ!
በላ ልበልሃ! Print E-mail
Sunday, 08 June 2008
በጋዜጣው ሪፖርተር

ጥሩ ጥሩ ባሕሎቻችንና ልማዶቻችን ከኑግ የተገኘ ሰሊጥ እንዲሉ እየጠፉ፣ እየተደመሰሱ ነው፡፡ አሉ የሚባሉትም እየተበረዙና እየተከለሱ ነው፡፡ ብዙዎቹ ከውጭ አገር በመጡ ባሕሎች ጫና ተደርጎባቸው ቦታቸውን ለቅቀዋል፡፡
ከብዙዎቹ መካከል አንዱን አንስተን እንነጋገርበት ዘንድ ወደድኩ፡፡ "እሰጥ አገባ" ወይም "በላ ልበልሃ" የሚባለውን፡፡ በእሰጥ አገባ ሁለት ተሟጋቾች በቃላት ይጎሻሸማሉ፡፡ እኔ አሸንፍ እኔ አሸንፍ የፈጠራ ችሎታቸውንም ይጠቀማሉ፡፡

ሺበሺ ለማ "ተጠየቅ" በሚል ርዕስ በ1985 ለንባብ ባበቃው መጽሐፍ እሰጥ አገባን ለማስታወስ ሞክሯል፡፡ ደራሲው እንዳለውም ይህ የአደባባይ ስርዓት የአገራችን ብቻ ሳይሆን ብዙዎች የውጭ አገር ሰዎችን ትኩረት ጭምር የሚስብና የሚማርክ እንደነበር ጠቁመዋል፡፡

ባንድ ወቅት ከሳሽና ተከሳሽ እዳኛ ፊት ግራና ቀኝ ተቋቁመው ሲሟገቱ፤ አንደኛው የሌላውን ደካማ ጐን (እንከን) አውቆ ኖሯል፡፡ እንከኑም አደባባይን አለማዘውተሩና ከድህነቱም የተነሳ ሚስቱን ነጠላ እንጂ ኩታ አልብሷት የማያውቅ መሆኑ ነበር፡፡ ይህንን የተረዳው ጮሌ ተሟጋችም በዘመኑ የነበረውን የችሎት ላይ ያነጋገር ነፃነትና የአሞጋገት ስልትን በመጠቀም እንዲህ ብሎ ይሰድበዋል፡፡

በላ ልበልሃ"
ያጤ ስርአቱን የመሰረቱን
አልናገርም ሀሰቱን
ሁሌ እውነት እውነቱን"
ላምህ ብትወልድ ዛጐላ
ሚስትህ ብትለብስ ነጠላ
አንተ ብትውል እጥላ

ተሰዳቢው ተሟጋችም ምንም እንኳን አደባባይን የማያዘወትርና የኑሮ ደረጃውም ዝቅ ያለ ቢሆንም ቅሉ ነገር አዋቂና አራቃቂ ነበርና፤ እሱም በበኩሉ በ፣በላ ልበልሃ፣ የአሞጋገት ስልት እንዲህ ብሎ መለሰለት ይባላል፡፡

በላ ልበልሃ
ላሜ ብትወልድ ዛጐላ
አውራውን አስመስል ብላ፡፡
ሚስቴ ብትለብስ ነጠላ
ቀን እስቲያልፍ ብላ፡፡
እኔ ብውል እጥላ
ያንተን ብጤ ነገረኛ ብጠላ"

በተለይ ከመጀመሪያው ስድብ ሰንዛሪ ግጥም ለመረዳት እንደሚቻለው ህብረተሰቡ ለአደባባይ ሰው ይሰጠው የነበረው ግምት ለየት ያለ መሆኑን ነው፡፡ ይህ ለምን ሊሆን ቻለ? ብለን ስንጠይቅና ነገሩን ጠለቅ ብለን ማጤን ስንጀምር ደግሞ አንዳንድ ራሳቸውን የቻሉ ምክንያቶችን ልናገኝ እንችላለን፡፡

መሬት የአብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ መተዳደሪያና የህልውናው መሰረት እንደሆነ የሚታወቅ ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር በተለይ በአንዳንድ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ለሚገኝ ዜጋ፣ ርስት ኢኮኖሚያዊ ብቻ ሳይሆን ስነ ልቦናዊ ጠቀሜታንም ጭምር የሚያስገኝለት በመሆኑ በሱና ባፈርዋ መካከል ያለው ግንኙነት የጠነከረ ሆኖ ኖሯል፡፡ ይህንን ግንኙነት የሚያዛቡ ሁኔታዎች ሲከሰቱ ደግሞ ቢቻል በህግና በደህንነት አለበለዚያም ወደ ተባባሰ ቅራኔ በሚያመሩ የትግል ዘዴዎች መቋቋሙ የግድ ይሆናል፡፡

በለው በዲሞፍተር ድገመው በዋንዛ
ባባት ርስትና በሚስት የለም ዋዛ፡፡
የተሰኘው ህዝባዊ ግጥምም ይህንኑ የህብረተሰብ እውነታ የሚያንፀባርቅ ነው፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ህብረተሰቡ ስለ ህግና ፍትህ የነበረው ጥልቅ ስሜትም እንዲሁ የመሟገቻውን መድረክም ሆነ የባለጉዳዩን ብዛት ጐላ አድርጐ ማሳየቱ አልቀረም፡፡ በተለያዩ መፃህፍት መልክ ተጠቃለው ከሚገኙት ልማዳዊ ህጐች ሌላ በህብረተሰቡ የስነ ቃል ቅርሶች ውስጥ የሚታቀፉት ህግ ነክ ምሳሌያዊና ዘይቤያዊ አነጋገሮችም ይህንኑ የህዝቡን ከህግና ፍትህ ጋር የተጣመረ ስሜት የሚያንፀባርቁ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡
 
< Prev   Next >