| በደራሼ ልዩ ወረዳ በተነሳ ግጭት... |
|
|
| Sunday, 13 January 2008 | |
|
በደራሼ ልዩ ወረዳ በተነሳ ግጭት የፖሊስ አባላትና ሰላማዊ ሰዎች ተገደሉ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በደራሼ ልዩ ወረዳ ውስጥ በተነሳ ግጭት ሁለት የፖሊስ አባላትና ከአምስት በላይ ሰላማዊ ሰዎች መሞታቸውን የደራሼ ልዩ ወረዳ ፖሊስ ጽህፈት ቤት የአስተዳደርና ፋይናንስ ሀላፊ ዋና ሳጅን ገረሱ ገሪቴ ለሪፖርተር ገለፁ፡፡ ዋና ሳጅን ገሪቴ በልዩ ወረዳው ስር የሚገኙ የአዲስ ኦፕቲማ ቀበሌ ነዋሪዎች በዙሪያቸው የሚገኙ ቀበሌዎችን በማስተባበር በ25/04/2000 ዓ.ም ጀምሮ በወረዳው አምስት ቀበሌዎች ላይ ጥቃት መክፈታቸውን ገልፀዋል፡፡ እንደ ኃላፊው ገለፃ ግጭቱን ያስነሱት አካላት የልዩ ወረዳ ምስረታ ጥያቄ ማንሳታቸው ታውቋል፡፡ ግጭቱን ለማረጋጋት የወረዳው ፖሊስ ሀይል አባላት እንዲሁም ከክልልና ከፌዴራል ፖሊስ የተላኩ የፖሊስ አባላት ጥረት ቢያደርጉም ከአቅማቸው በላይ እንደነበር ተገል..ል፡፡ በዚህም ምክንያት የመከላከያ ሰራዊት አባላት በአካባቢው ተሰማርተው የማረጋጋት ስራ መጀመራቸው ታውቋል፡፡ በግጭቱ አንድ የአድማ በታኝ ፖሊስ፣ አንድ የፌዴራል ፖሊስ አባል ሲገደሉ አንድ የአድማ በታኝ ፖሊስ አባል በፅኑ መቁሰሉን ዋና ሳጅን ገረሱ ገልፀዋል፡፡ በአመፁ የተሳተፉ አባላት ከቀላል መሣሪያ እስከ ቢኬኤም መትረየስና ኤም 14 ከባድ መሳሪያ መታጠቃቸውን ዋና ሳጅን ገረሱ ተናግረዋል፡፡ በግጭቱ የአንድ ቀበሌ ቤቶች በአብዛኛው ሲቃጠሉ ሌሎች አራት ቀበሌዎች መጠነኛ ቃጠሎ ደርሶባቸዋል፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች በግጭቱ ተፈናቅለው መጠለያ አልባ መሆናቸውን ዋና ሳጅን ገረሱ አስረድተዋል፡፡ ስማቸውን ያልገለፁ ሌላ የፖሊስ አባል ከአምስት በላይ ሰለማዊ ሰዎች ህይወታቸው እንዳለፈ ገልፀዋል፡፡ ከወረዳው የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲን በመወከል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ሀይለየሱስ ከቲሞ በበኩላቸው፣ አንዳንድ ጥቅም ፈላጊ የወረዳው መስተዳድር አባላት ..የወረዳ ይገባኛል ጥያቄ በሀይልና በአመፅ ይመለሳል በማለት አመፅ አነሳስተዋል.. ሲሉ የወረዳውን አስተዳደር ወንጅለዋል፡፡ በማያያዝም ..የወረዳው መስተዳድር ለደረሰው ጥፋት ሀላፊነቱን መውሰድ አለበት.. ሲሉ አሳውቀዋል፡፡ አቶ ሀይለየሱስ ግጭቱ ከተነሳ በኋላ የወረዳው መስተዳድር የወሰደው የማረጋጋት እርምጃ አነስተኛ ነበር በማለት መስተዳደሩን ወቅሰዋል፡፡ በአካባቢው እንዲህ አይነት ግጭት ሲከሰት የአሁኑ ለአምስተኛ ጊዜ እንደሆነ አቶ ሀይለየሱስ በመጥቀስ መንግሥት ዘላቂ መፍትሄ እንዲፈልግ አሳስበዋል፡፡ በተሾመ ንቁ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |