| ኮሎኔል አለምሰገድ አባይ... |
|
|
| Sunday, 08 June 2008 | |
ኮሎኔል አለምሰገድ አባይ የመከላከያ ኢንዱስትሪ ዘርፍ የሚሌኒየም ኤግዚቢሽን ዝግጅት ኮሚቴ ሰብሳቢ አነጋግረናቸዋል፡፡ሪፖርተር፡- የኤግዚቢሽኑ ዋና ዓላማ ምንድን ነው? ኮሎኔል አለምሰገድ፡- የኤግዚቢሽኑ ዋና ዓላማ የኢንዱስትሪ ተቋማቱን ደረጃ ለሕዝቡና ለሠራዊቱ ለማሳወቅ ነው፡፡ በራስ አቅም ራስን መገንባት እንደሚቻልም ለሕዝቡ ለማሳየት ነው፡፡ ሪፖርተር፡- የመከላከያ ኢንዱስትሪ ዘርፍ በምን ደረጃ ላይ ይገኛል? ኮሎኔል አለምሰገድ፡- ዘርፎቹ በንጉሱም በደርግም የጀመሩ ነበሩ፡፡ አብዛኞቹ በደርግ ጊዜ የተጀመሩ ነገር ግን ወደስራም ያልገቡና ውጤት ያለው ሥራ ለሠራዊታችን የሚሠሩ አልነበሩም በአሁኑ ሰዓት ዘርፉ ደረጃ በደረጃ እየተሻሻለ እያንዳንዱ ተቋም ሥራውን በአግባቡ ሊያካሂድ የሚችልበት ዓላማና ተልዕኮ በሚገባ ተቀምጦለት ተልዕኮውን መሠረት አድርጐ ለመንቀሳቀስ እየጀመረ ነው፡፡ ተጨባጭ የሆነ አቅጣጫ ማስቀመጥም አለብን፡፡ ሪፖርተር፡- ተጨባጭ አቅጣጫ ማስቀመጥ አለብን ሲሉ? ኮሎኔል አለምሰገድ፡- ለመሥራት ተጨባጭ የሆነ አቅጣጫ ማስቀመጥ አለብን፡፡ ከዚህ አንፃር አቅጣጫቸው ብዙ ግልፅ ያልነበሩ ተቋማት በአሁኑ ጊዜ ትክክለኛ የሆነ አቅጣጫ፣ የሥራ መደብና ተልኮአቸው ተቀምጦላቸው ይህንን ለማሟላት የሚያስፈልጋቸው አደረጃጀትና የሰው ኃይል ደረጃ በደረጃ አገሪቱ ካላት የሰው ኃይል አንፃር እየተሟላላቸው ተስፋ ሰጭ በሆነ መንገድ ተደራጅተው ሥራቸውን የጀመሩበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ እንደዚህ ከወደቀው ስርዓት በተጠናከረ ሁኔታ ተረክበን ወደ አሁኑ ሁኔታ የገባንበት ሁኔታ አልነበረም፡፡ አንዳንዶቹ ተቋማት ቢኖርም ከሥራ ውጭ ሆነው ነው የቆዩት፡፡ ለእነሱ የሚሟላ አሟልተን፣ መሣሪያዎችን አስገብተን፣ የሰው ኃይል አጠናክረን ሥራ የመጀመሩ ሁኔታ በጣም ከባድ ቢሆንም መንግሥትም ትልቅ ትኩረት ሰጥቶት አሁን ከሚገኙበት ደረጃ ለማድረስ ከባድ ጥረት ተደርጓል፡፡ ሪፖርተር፡- የሚያመርቱት ለሃገር ውስጥ ፍጆታ ብቻ ነው፡- ኮሎኔል አለምሰገድ፡- አሁን ካለው ስርዓት አንፃር በዋናነት እነዚህ ተቋማት የሠራዊቱን የትጥቅ ፍላጐት የሚያሟሉ ናቸው፡፡ ትልቁ ግዳጃቸውን ይኸው ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር የሚያመርቱት ምርትና የሚሰሩዋቸው ሥራዎች በሙሉ በጥራትና በዋጋ ተወዳዳሪ ሆነው ትርፋማ ሆነው የራሳቸውን ወጪ ራሳቸው እየደፈኑ አስፈላጊም ሲሆን የመከላከያን ወጪ የሚጋሩበት አቅጣጫ በግልፅ ተቀምጧል፡፡ እያንዳንዱ ተቋም ከአሁን በኋላ ተወዳዳሪ በሆነ መንገድ እንዲያመርትና በጥራት እንዲሆን በአቅጣጫ ተቀምጧል፡፡ ወደ ሥራ እየተገባበት ያለም ነው፡፡ ወደ ሥራ በምንገባበትም ጊዜ ለሠራዊታችን የምናስታጥቃቸው የተለያዩ የጦር መሣሪያዎች ጥራታቸውን የጠበቁና በዋጋም ተወዳዳሪ መሆን አለባቸው፡፡ ሪፖርተር፡- በዋጋ ተወዳዳሪ ሲባል፡- ኮሎኔል አለምሰገድ፡- ከውጭ የምናመጣውን መቀነስ አለብን፡፡ የውጭ ምንዛሪም ማዳን አለብን፡፡ ይህንን ለማድረግ ጥራት ያለው ተወዳዳሪ ምርት ሊኖረን ይገባል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ሁሉን አሟልተናል ባንልም አቅጣጫው ተቀምጦላቸው በደረጃ ለመሥራት እየንቀሳቀስን ነው፡፡ ሕዝባችንን በኤግዚቢሽን የተደረሰበትን ደረጃ የማሳየቱ ሥራ የተከናወነው አሁን ያለንበትን ደረጃችንንና የወደፊት አቅጣጫን ለማሳወቅ እንዲሁም ዋና ስራችን ሰላምን ለማስጠበቅ መሆኑን ለማሳየት ነው፡፡ የሠራዊቱ ትልቁና ዋናው ሥራ ሰላም መጠበቅ ነው፡፡ ሰላም መጠበቅ በአንድ በኩል ሊመጣ ስለማይችል የግድ ወሰን ማዘጋጀት ይገባል፡፡ ጦርነትን ከሩቅ ለማስቀረት ቁጭ ተብሎ ሳይሆን ራስንም በማዘጋጀት ነው፡፡ ስንዘጋጅ ደግሞ ወጪን እየቀነስን መሆን አለበት፡፡ ሪፖርተር፡- በደርግ ጊዜ የነበሩ ተቋማት ስትረከቡዋቸው እንዴት ነበሩ? ኮሎኔል አለምሰገድ፡- አንዳንዶቹ የግንባታ ሥራቸውን ያላጠናቀቁ ነበሩ፡፡ ግንባታውን አጠናቆ ወደ ሥራ የማስገባቱ ሥራ ባለንበት ስርዓት ነው የተፈፀመው፡፡ አንዳንዶቹም ጅማሮ የነበራቸው ቢሆንም በተሟላ ሁኔታ አይሰሩም ነበር፡፡ አሁን የነበሩትን የመከላከያ የኢንዱስትሪ ዘርፍ ተቋማት በሰው ኃይልና በማሽነሪዎች አደራጅቶ የመሄዱ ጉዳይ በተሟላ መልኩ ተፈፅሞ ወደ ሥራ እየተገባ ነው፡፡ በኤግዚቢሽኑ የቀረቡትም የተለያዩ ምርቶች የኢንዱስትሪዎቹ ውጤቶች ናቸው፡፡ ከመጠቁት አገሮች ጋር ማወዳደር ባይቻልም፡፡ ራስን በመቻልና የሚያስፈልጉ ነገሮችን በማምረት ወደፊት የውጭ ምንዛሪን ማዳን የሚቻልበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ ድህነትን ለማጥፋት በሚደረገው ርብርብም የራሱ አስተዋፅኦ ይኖረዋል፡፡ ሪፖርተር፡- የኢንዱስትሪ ዘርፎቹ ራዕይ ምንድን ነው? ኮሎኔል አለምሰገድ፡- በመከላከያ ስር ያሉ የኢንዱስትሪ ዘርፎች ወደ ፊት ራዕያቸው ኢትየጵያን በጦር መሣሪያ አልቆ ለማሳየት ሳይሆን ሰላምንና ኢኮኖሚዋን ለመጠበቅ ነው፡፡ ሪፖርተር፡- በኤግዚቢሽኑ ላይ በኢንዱስትሪ ተቋማቱ የተመረቱ፣ የተሻሻሉ ምርቶችን ግልፅ ስታደርጉ ከፀጥታና ከምስጢራዊነት አኳያ እንዴት ያዩታል? ያለውን የመሣሪያ አቅም ለሌላው ማሳየቱ ችግር የለውም? ኮሎኔል አለምሰገድ፡- በተለያዩ መንገዶች መረጃ ሊያገኙ የሚችሉበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ ዋናው የእኛ ዓላማ ሰላማችንን ማስጠበቅ ነው፡፡ ሰላማችንን ለማስጠበቅ ራሳችንን መዘጋጀት ይገባናል፡፡ ሰላም ለማስጠበቅ ደግሞ የውጭ ምንዛሬ መጠየቁ አይቀርም፡፡ የውጭ ምንዛሪውን እዚሁ ለማስቀረትና እየተደረገ ላለው ድህነትን የመቅረፍ እንቅስቃሴ የራሱ አስተዋፅኦ እንዲኖረው ለማድረግ ነው፡፡ በራሳችን አቅም እየሰራን ነው፡፡ የተሸሸገና የማይታወቅ አይደለም፡፡ ሌሎች በተለያየ መንገድ ሊያውቁት ይችላሉ፡፡ ሌሎቹ የሚያውቁትን ከሕዝባችን መደበቅ አያስፈልግም፡፡ እኛ የምናዘጋጃቸው ለሰላም ጥበቃ ነው፡፡ ግን ሰላም በአንድ ወገን ብቻ ስለማይመጣ ተጠንቅቆ ለመጠበቅ ነው፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |