Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Friday
Aug 29th
Home arrow Sections arrow የእንግሊዝ ኩባንያ የነዳጅ ልማት...
የእንግሊዝ ኩባንያ የነዳጅ ልማት... Print E-mail
Sunday, 13 January 2008

የእንግሊዝ ኩባንያ የነዳጅ ልማት ስምምነት ሊፈራረም ነው

የማዕድን እና ኢነርጂ ሚኒስቴርና ዋይት ናይል የተባለ የእንግሊዝ ኩባንያ በኦሞ ሸለቆ የነዳጅ ፍለጋ ሥራ ለማካሄድ የሚያስችል ሥምምነት በመጪው ሳምንት እንደሚፈራረሙ ታወቀ፡፡

ዋይት ናይል በእንግሊዝ ስቶክ ኤክስቼንጅ ገበያ የተመዘገበ የነዳጅ ኩባንያ ሲሆን በደቡብ ሱዳን በነዳጅ ፍለጋ ሥራ ላይ የተሰማራ ነው፡፡ ኩባንያው ከመዐድን እና ኢነርጂ ሚኒስቴር የፔትሮሊየም ሥራዎች መምሪያ ጋር በመተባበር ላለፉት ሁለት ዓመታት በኦሞ ቤዚን 70..000 ስኩዌር ኪ.ሜ ስፋት ባለው ቦታ የተለያዩ የጂኦሎጂ ጥናቶችን አካሂዷል፡፡ የኦሞ ሸለቆ በኢትዮጵያ የተፈጥሮ ዘይት ክምችት ይገኝባቸዋል ተብሎ ከሚታመንባቸው አምስት ሴዲመንታሪ ቤዚኖች አንዱ ነው፡፡  በሱዳን በነዳጅ ምርት የሚታወቁት የሙግላድ እና ሜሉት ቤዚን ቅጥያ በጋምቤላ እና ኦሞ ሸለቆ እንደሚገኝ ከዋይት ናይል ድረ ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ዋይት ናይል በኦሞ ሸለቆ የነዳጅ ክምችት እንዳለ ለማወቅ የሚረዱ የጂኦፊዚካል እና ማግኔቲክ ግራቪቲ ሰርቬይ ካካሄደ በኋላ የሰበሰባቸው የጂኦሎጂካል መረጃዎች አበረታች በመሆናቸው በተጠቀሰው አካባቢ የነዳጅ ፍለጋ እና ልማት ሥራ ማካሄድ የሚያስችለው ፈቃድ እንዲሰጠው ለማዕድን እና ኢነርጂ ሚኒስቴር አመልክቷል፡፡ ኩባንያው ያቀረበውን እቅድ (ፕሮፖዛል) የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ኃላፊዎች እና ኤክስፐርቶች ከገመገሙ በኋላ በዕቅዱ ዙሪያ ከኩባንያው ተወካዮች ጋር ድርድር አካሂደዋል፡፡

የማዕድን እና ኢነርጂ ሚኒስትር አቶ ዓለማየሁ ተገኑ ለሪፖርተር ጋዜጣ እንደገለፁት፣ ዋይት ናይል ባቀረበው ዕቅድ ከሥምምነት ላይ በመደረሱ የነዳጅ ፍለጋ ፈቃድ ከሁለት ሳምንት በፊት ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ ፀድቋል፡፡ የዋይት ናይል እና የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የነዳጅ ልማት እና የምርት ክፍፍል ስምምነት (ፔትሮሊየም ዴቨሎፕመንት አግሪመንት ኤንድ ፕሮዳክሽን ሼሪንግ አግሪመንት) በመጪው ሳምንት እንደሚፈራረሙ ገልፀዋል፡፡

የኦሞ ሸለቆ ከሱዳን እና ኬንያ ድንበር የሚዋሰን ሲሆን የማሌዥያ ኩባንያ የሆነው ፔትሮናስ በጋምቤላ ክልል የነዳጅ ፍለጋ ሥራ የሚያካሂድበት የጋምቤላ ቤዚን አጠገብ ይገኛል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት በነዳጅ እና ማዕድን ፍለጋ እና ልማት ሥራ ላይ መሰማራት ለሚፈልጉ ኩባንያዎች አመቺ ሁኔታዎችን በመፍጠሩ በመስኩ የተሰማሩ ኩባንያዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እንደመጣ እንዲሁም የፔትሮሊየም እና የማዕድን ሕጎች እንዲሻሻሉ መደረጋቸውን በመስኩ ለሚሰማሩ የአገር ውስጥ እና የውጭ ባለሃብቶች አስፈላጊውን ትብብር እና ማበረታቻ በማድረግ ላይ እንደሆነ አቶ አለማየሁ አስረድተዋል፡፡

የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከ65 በላይ የማዕድን ልማት ፈቃድ ሰጥቷል፡፡ ፔትሮናስ (ማሌዥያ..፣ ፔክስኮ (ማሌዥያ..፣ ሳውዝዌስት ኢነርጂ (ሆንግኮንግ)፣ አፋር ኤክስፕሎሬሽንስ (አሜሪካ) እና ሉንዲን ፔትሮሊየም (ስዊድን) የተባሉ ኩባንያዎች በጋምቤላ፣ በኦጋዴን እና በአፋር ክልሎች የነዳጅ ፍለጋ ሥራ በማካሄድ ላይ ይገኛሉ፡፡ በተጨማሪም ኢንተርግሎባል የተባለ የአሜሪካ ኩባንያ በአፋር፣ በትግራይ እና በምሥራቅ አማራ ክልል የነዳጅ ፍለጋ ሥራ ለማካሄድ ጥያቄ አቅርቧል፡፡

በቃለየሱስ በቀለ

 
< Prev   Next >