| አፍሪካን አንድ ማድረግ... |
|
|
| Thursday, 12 June 2008 | |
|
አፍሪካን አንድ ማድረግ በ7 ዓመት ውስጥ ይጠናቀቃል?
በሰለሞን ጐሹ የአፍሪካ አህጉር ማህበራዊ፣ ፖለቲካና ኢኮኖሚ ጥያቄዎች ከቅኝ ግዛት በኋላ እየተንከባለሉ አሁንም መልስ እየጠበቁ ነው፡፡ መፍትሔ በማፈላለጉ ረገድ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ተተኪ የአፍሪካ ሕብረት ባለሥልጣናት፣ የአባል ሀገራቱ ተወካዮች፣ ፖሊሲ አውጭዎች፣ ተመራማሪዎች፣ ምሁራን እና የሲቪል ማህበረሰቡ ተወካዮች በተለያየ ጊዜ የተለያየ አማራጭ እይታቸውን አካፍለዋል፡፡ ሕብረቱ ተቋማዊ አደረጃጀቱ እንዲጠናከር ለማድረግ በርካታ ስምምነቶችን አባል ሀገራት እንዲፈርሙ አድርጓል፤ እያደረገም ነው፡፡ ነገር ግን ስምምነቶቹን ተፈፃሚ በማድረጉ ረገድ የተፈለገውን ያህል እርምጃ መራመድ ባለመቻሉ አሁንም አፍሪካ ከሰሜን ጫፍ እስከ ደቡብ ጫፍ ድረስ በደቀቀ ኢኮኖሚ፣ ባልተረጋጋ የፖለቲካ ከባቢ አየርና በግጭት ታጥራለች፡፡ የዓለም አቀፉ ህብረተሰብ ምላሽ በብዛት አወዛጋቢ ነው፡፡ ባለፈው ሚያዚያ ወር አጋማሽ ላይ በአዲስ አበባ የተገናኙት የአፍሪካ ሕብረት የፍትህ ሚኒስትሮች የአፍሪካ ሕብረት ዓለም አቀፍ ህግ ኮሚሽን ረቂቅ መተዳደሪያ ደንብን አርቅቀዋል፡፡ የአፍሪካ ሕብረት ዓለም አቀፍ ሕግ ኮሚሽን በረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 3 ላይ ከተዘረዘሩት አላማዎቹ መካከል ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን መከለስና አዳዲስ ስምምነቶች የሚያስፈልገውን አካባቢ መለየት፣ ሕብረቱን የሚመለከቱ የህግ ጉዳዮችን ማጥናትና ማማከር፣ የአፍሪካ አህጉርን ድንበር በካርታና በመሬት ማካለልን ጨምሮ ሰላምና ደህንነት የሚስፋፋበትን ልዩ የሕግ መፍትሔ ማፈላለግ፣ አባል ሀገራት በሚጋጩበትና በማይስማሙበት ጊዜ ህጋዊ የማማከር ሥራ መሥራት፣ የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራትን ልማድና አሠራር የያዙ ዓለም አቀፍ ህጎችን ማውጣት፣ የአፍሪካ ሕብረትን የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ውሕደትን የሚያቀላጥፉ ሕጋዊ ጉዳዮችን ማጥናት፣ አባል ሀገራት ለዓለም አቀፍ ህግ ለህብረቱና አካላቱ አክብሮት በማሳየት ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ማድረግን ያካትታል፡፡ የአፍሪካ ሕብረት ዓለም አቀፍ ሕግ ኮሚሽን በአፍሪካ አንድነት ድርጅትና በአፍሪካ ሕብረት የተፈረሙ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን የመከለስ ሥልጣን በረቂቁ አንቀጽ 14 ላይ ተሰጥቶታል፡፡ ይህን የሚያደርገውም በአሁኑ የሕግ እድገትና በስምምነቶቹ መካከል መስማማትን ለመፍጠር፣ ለአባል ሃገራት የረጅም ጊዜ ልምድና አሠራር ትኩረት ለመስጠት፣ ለሕብረቱ ደረጃውን የጠበቀ አሠራር መፍጠር አስፈላጊ እና ተገቢ በመሆኑና ዓለም አቀፍ ግዴታዎችን ከሀገራት ተግባር ጋር ማዛመዱ ተፈላጊ በመሆኑ ነው፡፡ የአፍሪካ ሕብረት ዓለም አቀፍ ሕግ ኮሚሽን በረቂቁ አንቀጽ 16 ላይ የአፍሪካ ሕብረት ሥራ አስፈፃሚን በአህጉሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በሚረዳ መልኩ የጋራ መከላከያን ለማዳበርና ለማርቀቅ የሚያስችሉ ተገቢ እርምጃዎችን በተመለተ የውሳኔ ሃሳቦችን ሊያካፍለው እንደሚችል፣ በአህጉሪቱ የሃይል እርምጃ የሚገደብበትንና አንፃራዊ የግጭት ማስወገጃ መንገዶች ላይ ጥናት ሊያካሂድ እንደሚችል እንዲሁም የአፍሪካ ሕብረት የሰላምና ደህንነት ካውንስል ባልዳሰሳቸውና በህብረቱ ፖሊሲዎች ላይ ተፅእኖ ማምጣት በሚችሉ ሰላምና ደህንነት ነክ ጉዳዮች ላይ ጥናት እንደሚያካሂድ ተገልጿል፡፡ ኮሚሽኑ በአፍሪካ አህጉርና አባል ሃገራት የካርታና የመሬት ድንበር ማካለል ዙሪያ ጥናት ማድረግና ለህብረቱ አስፈፃሚ አካል ሪፖርት እንደሚያደርግ በረቂቁ አንቀጽ 17 ላይ ተገልጿል፡፡ ረቂቁ ሕግ በጠቅላላ ጉባኤው ተቀባይነት ካገኘ ይፀድቃል፡፡ ረቂቁ ዓለም አቀፍ ህግን ተግባራዊ ለማድረግ በአህጉሪቱ ያሉ ሀገራት ያላቸውን ባህል፣ ልምድና የቆየ አሰራር ግምት ውስጥ ማስገባት ተገቢ መሆኑን በተደጋጋሚና በአጽንኦት ገልጿል፡፡ የአፍሪካ ህብረት ባለፈው ጥር ወር ይፋ ያደረገው የስምምነቶች ወቅታዊ ሁኔታ እንደሚያሳየው እ.ኤ.አ ከ1963 ጀምሮ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትና የአፍሪካ ህብረት አባል ሃገራት የ33 ስምምነቶች አባል መሆን ይችላሉ፡፡ ለአብዛኞቹ ስምምነቶች አባል ሃገራቱ በብዛት ያልፈረሙና በሂደት ያሉበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ የመጨረሻውንና የቅርቡን የአፍሪካ የዲሞክራሲ የምርጫና የአስተዳደር ስምምነት ለምሳሌ ሀገራችን ኢትዮጵያን ጨምሮ 17 ሀገራት ብቻ እስካሁን ፈርመዋል፡፡ እ.ኤ.አ በ2001 የተቋቋመው ኔፓድ በኢኮኖሚ፣ አ.ኤ.አ በ2ዐዐ2 የተቋቋመው አፍሪካ ሕብረት በፖለቲካው ውህደት ረገድ የሚጫወቱት ሚና የአፍሪካ አህጉር እ.ኤ.አ በ2015 የተባበረች አንድ አፍሪካን መፍጠር እንደሚያስችል የአባል ሃገራቱ መሪዎችና መንግሥታት ከተስማሙ ዓመታት ተቆጠሩ፡፡ እያንዳንዷ ጉዞ በውጣ ውረድና በአስቸጋሪ ፈተናዎች የተሞላ ነው፡፡ መሪዎቹ የአህጉሪቱን አንድነት እውን ለማድረግ ጊዜ የሚያጡት የራሳቸው የውስጥ ጉዳይ ትንፋሽ የሚያሳጥር በመሆኑ ነው፡፡ በተጨማሪም አፍሪካ አህጉራዊ አንድነትን ለማምጣት የምትጣጣርበት ጊዜ በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ከመንግሥት ባለሥልጣናት ይልቅ ግዙፍ ኩባንያዎች መሪነቱን የተረከቡበት ወቅት ነው፡፡ የዓለም ንግድ መፋጠን፣ የገንዘብ ተቋማት ነፃ መሆንና በመንግሥት ቁጥጥር ሥር የነበሩ ተቋማት ዛሬ በግለሰቦች እጅ መግባቱ ለአፍሪካ ከጥቅሙ ጉዳቱ አመዝኗል፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የውጭ እርዳታመጠን ቀንሷል፡፡ እዳዋ ግን ተቆልሏል፡፡ ምዕራባዊያን በአፍሪካ ሃገራት የውስጥ ጉዳይ ላይ ፈላጭ ቆራጭ ሆነዋል፡፡ በእነዚህ አስቸጋሪ ሁኔታዎችና እውነታዎችም ውስጥ አፍሪካን በኢኮኖሚና በፖለቲካው ረገድ አንድ ለማድረግ ሙከራዎቹ ቀጥለዋል፡፡ ከላይ ያነሳነውን ረቂቅ መተዳደሪያ ደንብ ጨምሮ በርካታ ሰነዶች የተዘጋጁ ሲሆን “አፍሪካዊ መንፈስ ለአፍሪካዊያን” በታላቁ ጋናዊ መሪ ክዋሜ ንኩሩማህ ተወልዶ እንደ ቅዥት ተረስቶ የነበረ መርህ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተፅእኖ መፍጠር የሚችሉ ግለሰቦችና ተቋማት እንዲሁም ተቀማጭ ሰነዶች ይህንኑ ሀሳብ እያቀነቀኑ ነው፡፡ በተለይም ክልላዊ የኢኮኖሚ ህብረት ድርጅቶች መጠናከር ሳይረጋገጥ የአፍሪካ ፖለቲካዊ ውህደት አይታሰብም የሚሉት አካላት አህጉራዊ አንድነትን ለማረጋገጥ ብሔራዊ ሉአላዊነት ቅድሚያ ሊሰጠው አይገባም ይላሉ፡፡ የውጭ ሃይሎች በአፍሪካ ማዕድን፣ ሃይልና የተፈጥሮ ሀብቶችን ለማግኘት የጥቅም ግጭት እስካላቸው ድረስ እነሱን በማሳተፍ አንድነትን መገደብ እንጂ ተግባራዊ ማድረግ አይቻልም፡፡ በአባል ሀገራቱ ያሉ ሲቪል ማህበረሰቦችና የግሉ ሴክተር አፍሪካን በራሷ ተጨባጭ እውነታ ተመርኩዞ እንዲያለማና ሌላ ዓላማ ያለውን ሃይል ሰላምና ደህንነቱን እንዳይባከል ለማድረግ በነፃነት እንዲሰራ ማድረግም ተፈላጊ ነው፡፡ መሪዎቻችንና መንግሥታቶቻችን ከ7 ዓመት በኋላ “አንድ እንሆናለን!” ብለው ቢስማሙም ጐዳናውን ወደ አንድነት በሚያመራው አቅጣጫ እየተራመድንበት አይደለም፡፡ ጉዳዩ የእያንዳንዱ የአፍሪካ ዜጋ መወያያ አጀንዳ እንዲሆንም ሥራ እየተሰራ ነው ለማለት ያስቸግራል፡፡ በልሂቃን ደረጃ በቅርቡ የተጀመረው ተከታታይ የውይይትና የምክክር መድረክ ግን ሊበረታታ ይገባል፡፡ የትምህርትና ጤና አገልግሎት፣ የመሠረተ ልማት ግንባታ፣ የመንገድ ግንባታ፣ የእርሻ ልማት፣ የምግብ ዋስትና እንዲሁም የኢንዱስትሪ ግንባታ ተቀላጥፎ ሰላምና ደህንነትን የሚያረጋግጡ ተቋሞችና ህጎች ተቋቁመውና ተደንግገው አፍሪካዊያን ልማት እንጂ ጦርነትና ግጭት የመጀመሪያ አጀንዳቸው እንዳይሆን እስካልተደረጉ ድረስ በመጪዎቹ 7 ዓመታት የአፍሪካ አንድ መሆን ከተራ የመሪዎቻችን ቅዥት የተለየ ትርጉም አይኖረውም፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |