Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Thursday
Aug 07th
Home arrow Sections arrow "የራሱን ትርፍ ከማሳደግ ውጪ አገርን...
"የራሱን ትርፍ ከማሳደግ ውጪ አገርን... Print E-mail
Sunday, 13 January 2008

"የራሱን ትርፍ ከማሳደግ ውጪ አገርን ለመገንባት የሚጥር ባንክ የለም"
አቶ ክቡር ገና

አቶ ክቡር ገና የኢኒሼየቲቭ አፍሪካ የሚባል የአገር ውስጥ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡ በአገራችን ኢንዱስትሪዎችና የገንዘብ ተቋማት በዘርፉ እያደረጉ ስላለው እንቅስቃሴ አነጋግረናቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ኢንዱስትሪዎቻችን አደጉ ወይስ ወደቁ?

አቶ ክቡር፡- የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪዎች እለት ከዕለት ከማደግ እየወረዱ እየቆረቆዙ የመጡበት ሁኔታ አለ፡፡ እድገቱ በጣም ውሱን ነው፡፡ ከአገልግሎትና ከእርሻው አንፃር ስናየው እድገቱ የሚያረካ ባይሆንም ኢንዱስትሪን ለማስፋፋት የሚረዱ ሁኔታዎች እየተመቻቹ ነው፡፡ አሁን ለአገር ውስጥ ፍጆታም ሆነ ውጪ ለመላክ የሚሆን የኢንዱስትሪ ምርት የለንም፡፡

አሁን ያሉት የኢንዱስትሪ አምራቾች የትኞቹ ናቸው? ገበያው የት ነው? ምን ያህል ለገበያ ቀረበ የሚለውን ስናይ ተጨባጭ ለውጥ የለም፡፡ ኢንዱስትሪን ለመገንባት መሠረተ ልማት ለመጣል እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው፡፡ ሆኖም አሁን ባለው ሁኔታ የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ አቅም ተስፋ የሚያሰጥ አይደለም ይህ ምርት ተወዳዳሪ ነው፡፡ ገበያ አለው፣ የለውም ማለት ይከብዳል፡፡

ሪፖርተር፡- ካለው የካፒታል እጥረት አንፃር ምን ዓይነት ኢንዱስትሪዎች የመመስረት አቅም አለ?

አቶ ክቡር፡- ለኢንዱስትሪ ልማት የሚውል የካፒታል ችግር የለም፡፡ ትልቁ ድክመት የሰለጠነ የሰው ኃይል ማስተባበርና ወደ ሥራ እንዲገቡ ማድረግ ላይ ነው፡፡ በካፒታል ምክንያት ወደ ኋላ የቀረ የለም፡፡ መሠረታዊ የሆኑ መሠረተ ልማቶች እየተገነቡ ነው፡፡ በመንግሥት ከፍተኛ ሥራ እየተሠራ ለኢንዱስትሪ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ከግብርና ምርቶች አግሮ ፕሮሰሲንግ ሥራ አንፃራዊ ተጠቃሚነት አለን፡፡

ሪፖርተር፡- የተወዳዳሪ አቅም ለመገንባት ምን ያስፈልጋል?

አቶ ክቡር፡- ከአገር ውጪ በመሸጥና ገበያ ላይ ለመቅረብ የሌሎች ተወዳዳሪዎችን አቅም ስናይ ውድድሩ ኩባንያ ለኩባንያ ነው፡፡ የውጪዎቹ በሰው ኃይል፣ በአደረጃጀት፣ በመንግሥትና በባንክ ድጋፍ የተሻሉ ናቸው፡፡ እዚህ ደረጃ መድረስ የሚያስችል ሁኔታ እስካለ ድረስ መወዳደር ይቻላል፡፡ ይህን ማመቻቸት ይኖርብናል፡፡

ለምሳሌ ቡና ቆልተን ፈጭተን እንላክ ብንል የምንወዳደረውካደጉት አገራት ድርጅቶች ጋር ነው፡፡ እነርሱ ቴክኖሎጂን በማስተካከል፣ ገበያው ምን እንደሚፈልግ ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ እንወዳደር ብንል ገበያው በቀላሉ የሚከፈት አይደለም፡፡ እዚያ ደረጃ ላይ ለመድረስ ብዙ ይቀረናል፡፡

ቴክኖሎጂዎቻችን ከ50 ዓመታት በፊት የነበሩ ናቸው፡፡ ለቴክኖሎጂ የተማረ የሰው ኃይልና ሳይንስ ወሳኝ ነው፡፡ የሳይንስ እድገት መሠረት ያስፈልጋል፡፡ ሳይንስ በኢትዮጵያ በትምህርት ደረጃ ብዙ ተማሪዎች አናይም፡፡ ብዙዎች እንዲሄዱ መርዳት ይኖርብናል፡፡ 

ይህ ብዙ ነገሮችን ያካትታል፡፡ ትምህርትን ስናስብ ሳይንስ ላይ ያተኰረ መሆን አለበት፡፡ ለገበያ በሚመች መልኩ ተደራጅተናል ወይ የሚለውን ማየት አለብን፡፡ አሁን ያሉት ማኅበራት ከጥቂት ቦታዎች ውጪ አልተስፋፉም፡፡ ለማስፋፋት የሚረዱን ምቹ ሁኔታዎች ምን እንደሆኑ አውቀው ማስተካከል አለብን፡፡ ከመንግሥት የሚወጡ ፖሊሲዎች በሕዝቡ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኙ የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ተቀባይነት አግኝተው ሥራ ላይ እንዲውሉ ማድረግ፣ የመንግሥት ድጋፍ፣ በባንከ ገንዘብ አሰጣጥ ላይ ለውጥ ያስፈልጋል፡፡ እውቀት፣ ችሎታና የመሥራት አቅም ኖሯቸው ገንዘብ የሚያገኘት ምን ያህሉ ናቸው የሚለው መታየት ይኖርበታል፡፡

ሪፖርተር፡- የገንዘብ ተቋማት ኢንዱስትሪውን በማገዝ በኩል እያደረጉ ያሉት እንቅስቃሴ አርኪ ነው?

አቶ ክቡር፡- የገንዘብ ተቋማት አትራፊ ናቸው፡፡ ይህ ከመሆኑ የተነሳ ኢንዱስትሪን የመፍጠርና የመለወጥ ሥራ አይታይም፡፡ ገንዘብ ያለው ገንዘቡን ማስቀመጥ፣ የባንክ አክሲዮን መግዛት፣ የራሱን ባንክ ማቋቋም ይፈልጋል፡፡ ባንኮች በራሳቸው ከገንዘብ ዝውውር በበለጠ ማምረት አይችሉም፡፡ ግን ማምረትንም ሆነ መገንባት የሚያስችል ሁኔታ እንዲያስቀምጡ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ባንኮቻችንን ስናይ ግን የራሳቸውን ትርፍ ለማሳደግ እንጂ የአገርን እድገትም ሆነ የባለ ኢንዱስትሪዎችን አቅም የሚገነቡ ሆነው አይታዩም፡፡ ከትርፍ አንፃር ስለሚሽቀዳደሙና ሥራ እንዴት እንደሚሠራ ስለማያውቁ የሚጠበቅባቸውን አይሠሩም፡፡ አትራፊ ስለሚሆኑ በሽርክና ይሠራሉ፡፡ ጀርመንን ስንወስድ ባንኮቹ ትልቅ ደረጃ ቢደርሱ እንኳ ከትልቅ ድርጅቶች ጋር ተባብረው ይሠራሉ፡፡ በየዘርፉ ያሉትን ችግሮች ያውቃሉ፡፡ ለችግሮቹ መፍትሄ ያቀርባሉ፡፡ ለተወሰኑ ባለ ኢንዱስትሪዎች ካልሆነ አገርን ለመገንባት የሚያስችል ባንክ የለም፡፡ ያሉት ባንኮች ገንዘብ ከማስቀመጥ፣ ትንሽ ከማበደርና በተለያየ መልኩ በአገልግሎት ጥያቄ ሲነሳ ገንዘብ ከመስጠት ውጪ ሰፋ ላሉ የልማት እድገት ሁኔታዎች ብዙ ይቀራቸዋል፡፡ 

ሪፖርተር፡- የባንኮች የሥራ ሂደት ምን መሆን አለበት?

አቶ ክቡር፡- ባንኩ ከባለኩባንያው ጋር የኪሳራም ሆነ የትርፍ ተካፋይ ሊሆን ይገባዋል፡፡ የተለየ አስተሳሰብን ይጠይቃል፡፡ ባንኮቻችን በእውነት የአገር ልማትን የሚፈልጉ እውነተኛ ባንኮች ከሆኑ ማሰብ አለባቸው፡፡ በየዓመቱ ትርፉን የሚያስብ ከሆነ ይህን ለውጥ ማምጣት አይቻልም፡፡ በአገራችን ያለውን ሁኔታ ስናይ አንድ ኩባንያ ለመወዳደር አቅቶት ብድሩን መክፈል ካልቻለ የሚወሰደው እርምጃ ድርጅቱን መዝጋት ነው፡፡ ይህ መቀየር አለበት፡፡

በዓለም ላይ በማኅበራት የተደራጁ ባንኮች አሉ፡፡ ከአባላቱ ጋር ቅርበት አላቸው፡፡ የእድገትም ሆነ የኪሣራ ተካፋይ ናቸው፡፡ እዚህ አገር ጥፋት እየተፈፀመ ያለው በባንክ አሠራር ነው፡፡ ድርጅቶች አቅማቸው ሲያድግ በቅጡ ገበያ ውስጥ ሳይገቡ እንዲከፍሉ ይጠየቃሉ፡፡ ይህን ማድረግ ስላልቻሉ እንዲዘጉ ይደረጋል፡፡

ሪፖርተር፡- መንግሥት ምን ማድረግ አለበት?

አቶ ክቡር፡- ባለኢንዱስትሪዎችም ሆኑ፣ የግል ባለሐብቶች አቅም የላቸውም፡፡ በሰው ኃይል፣ በገንዘብ፣ በመሬት፣ በእውቀት፣ በልምድ፣ በተቋም ደረጃ በሁሉም መልኩ አቅም ያለው መንግሥት ጋር ነው፡፡ ማሳደግ ከፈለገ መቀየር ይችላል፡፡ ባለኢንዱስትሪዎቹ ተሰብስበው አንድ ነገር እንዲያደርጉ ይጠበቃል ግን አይቻልም፡፡ አገር ለመለወጥ ወደ ልማት ለማምጣት አቅም ያላቸው ኢንዱስትሪዎች የሉም፡፡ ትልቁ ታክስ ከፋይ መንግሥትንና በመንግሥት እጅ ያሉ ድርጅቶች ናቸው፡፡ ለውጥ ለማምጣት ሙከራዎች ይኖሩ ይሆናል፡፡ መንግሥት ከባለ ኢንዱስትሪዎች ጋር ያለው አካሄድ ግን ግልፅ አይደለም፡፡ የአበባን ምርት ስናይ መንግሥት ግልፅ የሆነ አቋም ነበረው፡፡ መሬት፣ ብድር፣ ፕሮጀክት አጥንቶ የሚፈልጉትን ድጋፍ ሰጠ፡፡ በ10 ዓመታት ውስጥ አሁን ያለበትን ደረጃ ደረሰ፡፡ ይህ የሆነው በግል ባለሐብቱ ጥንካሬ ሳይሆን በመንግሥት ጥንካሬና ሙሉ ተሳታፊነት ነው፡፡ የአበባው ትምህርት ሆኖ በሌሎች ኢንዱስትሪዎችም ላይ እንዲደገም የመንግሥት ተሳትፎና ትኩረትን ይፈልጋል፡፡

ሪፖርተር፡- ከባለሐብቶችስ ምን ይጠበቃል?

አቶ ክቡር፡- እዚህ አገር ባለሐብት የለም፡፡ ባለሐብትን ባለሐብት እያሰኘው ያለው ከባንክ የሚወስደው ብድር ነው፡፡ ከባንክ ገንዘብ ይወስዳል፤ ፕሮጀክቱ በትክክል ባለመካሄዱ ሥራውን ባለመሥራቱ ወደ መዘጋት ደረጃ ይደርሳል፡፡ እንዲህ ዓይነት ባለኢንዱስትሪ ባለሐብት አንለውም፡፡

ሪፖርተር፡- በባለ ኢንዱስትሪዎች ላይስ ያሉ ችግሮችስ ምንድናቸው?

አቶ ክቡር፡- ብዙዎቹ ድርጅቶች ሥራን ደረጃ በደረጃ መጀመር አይፈልጉም፡፡ በጨርቃ ጨርቅ የገበያ እድል አለ ከተባለ ይበደራሉ፣ ትልልቅ ማሽኖችን ይተክላሉ፡፡ ሥራ ይጀምራሉ ሠራተኞቻቸውን አላሰለጠኑም አቅማቸውን በትንሹ አልገነቡም፡፡ ትልቅ ብር አውጥተው ኢንቨስት ስለሚያደርጉ ገበያ ውስጥ ቶሎ አለመግባታቸው ይጎዳቸዋል፡፡ ሚስማር ሳይሠራ መኪና መሥራት አይመጣም፡፡ ባንክም ሆነ መንግሥት የሚሠራና የማይሠራውን መለየት አለባቸው፡፡ በሕዝብ ገንዘብ ላይ የሚቀልዱ በዝተዋል፡፡ በኢንዱስትሪ ደረጃ ጥሩ እየሠራ ያለው ቢራ ነው፡፡ ይህ ከአንዱ ከውጪ ኩባንያ ውጪ አብዛኛዎቹ በመንግሥት እጅ ናቸው፡፡

በዘርፉ አንፃራዊ ተጠቃሚነት አለ የለም የሚለው ታምኖበትና ተረጋግጦ ያለ የሌለውን አቅም መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ አንድ ኩባንያን ወስደን የሰው ኃይል፣ ተወዳዳሪ የመሆን የገበያ ትልቅ ችግር እያለበት ትልቅ ኩባንያ ይሆናል ለማለት ተስፋ የሚያሰጥ አይደለም፡፡ ሆኖም እንደ እድገቱ እያደገ ቢመጣ በልምድ እየታየ ሌሎች እየሳበ የሚያድግበት ሁኔታ አይደለም፡፡ ለወደፊት ተስፋ የሚያሰጡ ፍንጮች አሉ፡፡ ዛሬ ወደ ቻይና የሚሄደው ኢንቨስተር ሌላ አማራጭ ይፈልጋል፡፡ ምክንያቱም የቻይና ሠራተኞች ደመወዝ እየጨመረ መጥቷል፡፡ ግን ተስፋ የሚኖረን የሰው ኃይላችን የሰለጠነ ዲሲፒሊን ያለው ቃል አክባሪ ሲሆን የመንግሥት ድጋፍ ሲኖር ነው፡፡ በሰው ኃይል ልማት፣ በኤሌክትሪክ ኃይል፣ በመሠረተ ልማት እየተደረጉ ያሉት እንቅስቃሴዎች ተጠናክረው መቀጠል ይኖርባቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪዎች የአጎዋ እድሉ አለ፡፡ ከዚህ ለመጠቀም ምን ያስፈልጋል?

አቶ ክቡር፡- ጨርቃ ጨርቅ ለውጪ ገበያ አቅርቡ ተባለ፡፡ ሆኖም ግን በጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ለአገር ውስጥና ለውጪ ገበያ ሰፊ ጥናት ያስፈልጋል፡፡ ከመሃል አገር በመኪና ከጅቡቲ በወደብ ቀርቦ ተዘጋጅቶ ከመሃል አገር ወደ ውጪ በጅቡቲ ልከን ተወዳዳሪ እንሆናለን ይከብዳል፡፡ ይህን ዓይነት ኢንዱስትሪ መገንባት ይቻላል? አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም ቬትናምን ስንወስድ ጥሬ እቃ የጫነው መርከብ ሲመጣ የተዘጋጁትን ይዞ ይሄዳል፡፡ ይህ ለተወዳዳሪነት መሠረት ነው፡፡

በአገር ውስጥ ከሆነ ከውጪ የሚመጣውን እንዴት መገደብ ይቻላል የሚለውን ማየት አለብን፡፡ ለውጪ ገበያ ሲቀርብ ቃል አክባሪነት ያለው የበፊት ልምድ ይጠይቃል፡፡ ይህ እኛ ጋር የለም፡፡ ስለዚህ ያን አቅም እስክንገነባ ብዙ ትርፍ ሳንጠብቅ መላክ ይኖርብናል፡፡ ይህን ለማድረግ የሚያስችል አቅም ግን የለንም፡፡

ሪፖርተር፡- ከአውሮፓ ጋር የነበረን የገበያ ስምምነት መቅረት ምን ዓይነት ተፅዕኖ ይፈጥራል?

አቶ ክቡር፡- አሁን ባለው ሁኔታ ውጪ የምንልከው ዓይነት የኢንዱስትሪ ምርት የለም፡፡ ብዙ ለውጥ አይፈጥርም፡፡ በአገር ውስጥ ጠቅላላ የምናመርተው ጨርቃ ጨርቅ የሌላ አገር አንድ ኩባንያ ሊያመርተው ይችላል፡፡ በአብዛኛው ምርቶቻችን ከእርሻ ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ ፍላጐት እያደገ መጥቷል፡፡ ይህ ለውጥ በአገር ውስጥ የምግብ ምርቶች ላይ እየታየ ነው፡፡ ልንነጋገርበትና ሊጎዳን ይችላል፡፡ እንችላለን የምንለው የወጪ ምርት የለንም፡፡ የግብርና ምርቶችንና ሙሉ በሙሉ በአገር ውስጥ የሚመረቱ ምርቶችን ለመላክ የሚያስችል እድል ስላለ ብዙ ተፅዕኖ አይፈጥርም፡፡

ሪፖርተር፡- መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለመሰለፍ የኢንዱስትሪ ድርሻ ምን መሆን አለበት?

አቶ ክቡር፡- መካከለኛ በሚለው አንድ ቁጥር ላይ መስማማት አለብን፡፡ አሜሪካ መካከለኛ ገቢ አለው የሚባለው በአቅም ኢትዮጵያ ውስጥ ካለው ይለያል በዓለም አቀፍ ደረጃ መለኪያ ቻይናን፣ ብራዚልን፣ ሕንድን ከወሰድን ከ10 ዓመት በላይ ይፈጃል፡፡ ለውጥ ለማምጣት የሕዝቡን ቁርጠኝነት የመንግሥት በሰው ኃይል፣ መሠረተ ልማት ላይ የሚያደርገው ተሳትፎ ውጤት ነው፡፡ ሆኖም በመካከለኛ ገቢ ይህን ያህል መሆን አለበት የሚል ግልፅ ቁጥር የለም፡፡

በቤዛዊት ሥዩም

 
< Prev   Next >