Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Thursday
Aug 28th
Home arrow Sections arrow የንግድ ም/ቤቶችን እንደገና ለማቋቋም...
የንግድ ም/ቤቶችን እንደገና ለማቋቋም... Print E-mail
Thursday, 12 June 2008
የንግድ ም/ቤቶችን እንደገና ለማቋቋም የወጣው አዋጅ እንዲሻሻል ሊጠየቅ ነው

በዳዊት ታዬ

የንግድ ምክር ቤቶችን እንደገና ለማቋቋም የወጣው አዋጅ ቁጥር 341/95 ለአንዳንድ አሠራሮች አስቸጋሪ የሆኑ አንቀፆች አሉበት በሚል እንዲሻሻል ለማድረግ እንቅስቃሴዎች መጀመራቸው ተገለፀ፡፡

በዘርፍና በንግድ ምክር ቤቶች መካከል ሊኖር ስለሚገባው ግንኙነት የሥራ ኃላፊነትና አወካከል ላይ አዋጁ ክፍተት እንዳለው በመታመኑ ክፍተት አለባቸው የተባሉ የአዋጁ አንቀፆችን በመለየት አዋጁ እንዲሻሻል ለማድረግ በብሔራዊ ምክር ቤት ደረጃ ውሣኔ ላይ መደረሱን የኢትዮጵያ ንግድ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የቦርድ አባላት ለሪፖርተር ጋዜጣ አስረድተዋል፡፡

በውሣኔውም መሠረት እስካሁን ባሉ አሠራሮች አዋጁ ግልፅ ያላደረጋቸውና አስቸጋሪ በተባሉ ጉዳዮች ላይ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች ተወያይተው የደረሱበትን ስምምነትና ግልፅ አይደለም የተባለውን የአዋጁን አንቀፅ በምን መልክ እንዲስተካከል እንደሚፈልጉ የሚያሳይ መረጃ ለብሔራዊ ምክር ቤቱ እንደሚያቀርቡም እንደሚደረግ ተጠቁሟል፡፡

ያነጋገርናቸው የቦርድ አባላት እንደገለፁት ከሆነ ለአሠራር እንቅፋት ሆነዋል የተባሉት የአዋጁ አንቀፆች ላይ ጉዳዩ የሚመለከተው የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ኤክስፐርቶች ማብራሪያ እንዲሰጡበት የተደረገ ቢሆንም ችግሩ እንዳልተቀረፈ ግንዛቤ ላይ በመደረሱ ብሔራዊ ምክር ቤቱ በጉዳዩ ላይ አባላት ተወያይተው መፍትሔ እንዲያቀርቡ እንዲወስን አድርጐታል፡፡

የቦርድ አባላቱ ጨምረው እንዳስረዱት፣ አዋጁ ውስጥ ለአሠራር አመቺ ያልሆኑ አንቀፆች እንዲሻሻሉ ለማድረግ በመጀመሪያ ደረጃ እንደመፍትሔ የተወሰደው የአባላት አስተያየት ነው፡፡ ጐን ለጐንም በአሠራር ሂደት የገጠሙ ችግሮችም እንዲቀርቡ የሚደረግ መሆኑንም ይገልፃሉ፡፡

በአዋጁ ውስጥ ለአሠራር አመቺ ያልሆኑ ተብለው በታመነባቸው የተወሰኑ አንቀፆች ውስጥ በዘርፍና በንግድ ምክር ቤቶች መካከል ያለው አሠራር አንዱ እንደሆነና በሁለቱ ም/ቤቶች መካከል ያለ የአሠራር ሂደትና የኃላፊነት ደረጃ ግልፅ አለመሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡

ንግድ ምክር ቤቶችም ሆኑ የዘርፍ ማህበራት አደረጃጀት ከከተማና ከወረዳ የሚነሱ ሲሆን በክልልና በብሔራዊ ደረጃ ተጣምረው እንደገና እንዲሠሩ በመጨረሻ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራትን የሚመሠርቱ በመሆኑ በዚህ የአደረጃጀት ሂደት ውስጥ ሁለቱም ወገኖች ለየብቻ እንዲንቀሳቀሱ የሚያደርግ እድል ስለሚሰጥ የሥራ ግጭትም እየተፈጠረ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡  

የዘርፍ ማህበራት ከወረዳ እስከ ብሔራዊው ምክር ቤት ባለፈው አደረጃጀት ውስጥ የሚታቀፉ መሆናቸው ሌላው ቢቀር ዓመታዊ መዋጯቸውን ለየትኛው አካል ይክፈሉ የሚለውን ጥያቄ እንኳን ለመመለስ ያላስቻለ ክፍተት በአዋጅ ውስጥ ይንፀባረቃል፡፡

የንግድም ሆነ የዘርፍ ማህበራት ላይ ብቻ የሚንቀሳቀሱበት አሠራር በመኖሩም ሁለቱም ወገኖች ተመሳሳይ የሆነ አጀንዳና ፕሮግራም ይዘው ለአንድ አካል በሚቀርቡበት ጊዜ ጥያቄው የቀረበለት አካል ጥያቄውን ለመመለስ እየተቸገረ ከመምጣቱም በላይ በብሔራዊ ደረጃ በአንድ ምክር ቤት ሥር ያሉት ሁለቱ ተቋማት ለየብቻ በሚንቀሳቀሱበት ጊዜ ተመሳሳይ ጥያቄ ለተመሳሳይ አካል እንዲያቀርቡ የሚያደርግ በመሆኑ አዋጁ ግልፅ መሆን አለበት ተብሏል፡፡

የየራሳቸው ስልጣን አለን የሚሉ በመሆኑና በተለያዩ የጥቅም ጉዳዮችም ሁለቱም የተለያየ ጥያቄ እያነሱ መሆናቸው እስካሁን ባለው አሠራር እየታየ በመሆኑ አዋጁ ድጋሚ እንዲታይ ማድረጉ አግባብ እንዲሆንና ይህ አሠራር ቶሎ ካልተስተካከለ ለመሥራት የታቀዱ ሥራዎች ላይ ችግር ሊፈጥር ይችላል የሚል ሥጋት እንዳላቸው አመልክተዋል፡፡

ከሁሉም ወገን የሚሰበሰበው መረጃ ለብሔራዊ ምክር ቤቱ ቀርቦ ምክር ቤቱ ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት እንደሚያቀርብ የተጠቆመ ሲሆን ከዚሁ ጋር በተያያዘም ከመጪው ሣምንት ጀምሮ በወረዳ ደረጃ ያሉ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ውይይት እንደሚጀምሩም ለማወቅ ተችሏል፡፡
 
< Prev   Next >