Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Wednesday
Aug 20th
Home arrow Sections arrow ክቡር ሚኒስትር
ክቡር ሚኒስትር Print E-mail
Thursday, 12 June 2008
(የበጀት ዓመት በሰኔ ወር መጨረሻ ላይ ያልቃል፡፡ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ዓመታዊ ሪፖርት አዘጋጅታችሁ አቅርቡ ተብሏል፡፡ ከቀጣይ እቅድ ጋር ክቡር ሚኒስትሩ በዚሁ ዙሪያ ኮሚቴ አቋቁመው እየተዘጋጁበት ነው)

- በአጠቃላይ ደካማና ጠንካራ ጎናችንን እንዴት ዘርዝረን እናስቀምጠው?
- ክቡር ሚኒስትር መዘርዘር የሚያስፈልግ አይመስለኝም፡፡ በአጠቃላይ ብናስቀምጠው ይሻላል፡፡
- ምን ብለን እናጠቃልለው?
- አበረታች ነበር ብለን፡፡
- ባለፈው ዓመት እንደዚያ አስቀምጠን ዝርዝር ነው፤ የሚስፈልገው ብለውን ነበር፡፡ (ሌላ ተናጋሪ) አዎን ክቡር ሚኒስትር ዘርዘር ብናደርገው ነው ጥሩ፡፡
- እኮ እንዴት እንዘርዝረው ነው ነገሩ፡፡ በዚህ ዓመት ሰላሳ ሰባት ጊዜ መደበኛ ስብሰባ አካሄዷል፡፡ መሥሪያ ቤቱ በዚህ ዓመት በሕዝብ ግንኙነት በኩል አስራ ሁለት መጽሄቶችን አሳትሟል፡፡ በሬዲዮና በቴሌቪዥን ዘጠኝ ጊዜ መግለጫ ሰጥቷል፡፡ በተጨባጭ እንደዚህ አድርገን ብንዘረዝረው ነው ጥሩ፡፡
- ጥሩ ሃሳብ ነው፡፡
- (ሌላ ተናጋሪ) እንዴ ክቡር ሚኒስትር፣ ዝርዝር ይቅረብ ሲባልና ስራችንን በሚመለከት ከእቅዱ ምን ተሰራ፣ ምን ሳይሰራ ቀረ ዝርዝር ይቅረብ ማለት ነው እንጂ ወንድሜ እንደሚለው ዓይነት ዝርዝር ማለት አይደለም፡፡
- እስቲ አንተ ዝርዝር የምትለውን ንገረን፡፡ ሌላው በተናገረው ላይ አቃቂር ከምታወጣ እስቲ ያንተን ዝርዝር እንስማ፡፡
- ጥሩ፡፡ ለምሳሌ በዚህ ዓመት ለማጠናቀቅ ያሰብነው አንዱ ትልቁ ሥራ የቢ.ፒ.አር ፕሮግራም ነበር፡፡ እስካሁን ድረስ አልተጠናቀቀም፡፡
- እንዴ ቢ.ፒ.አር አልተጠናቀቀም እንዴ?
- አልተጠናቀቀም፤ ክቡር ሚኒስትር፡፡ ወደ ስልጠናና ተግባራዊነት ከመሄዱ በፊት እርስዎ መፈረም አለብዎት፡፡
- አልፈርምኩም እንዴ?
- አልፈረሙም፤ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ሳልፈርም ስቀር እንዴት ዝም አላችሁ? ለፀሐፊዋ አቅርባችሁ መፈረም ነበረብኝ፡፡
- ለፀሐፊዋ ከቀረበማ አራት ወር ሆነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ታዲያ እንዴት አልፈረምኩም?
- ባለፈው ወደ ደቡብ አፍሪካ ሄዱ፣ ከዚያ ቻይና፣ ከዚያ ለሕክምና እንደገና ደቡብ አፍሪካ ሄዱ፡፡ ለመፈረም በጭራሽ ጊዜ አላገኙም፡፡
- እኔ ስላልፈረምኩ ነገሩ ቆሟል ማለት ነው?
- (ሌላ ተናጋሪ) ለነገሩ ክቡር ሚኒስትር የሚባረሩትን አባረናል፣ የሚሾሙትን ሾመናል፡፡ ቢፈረም የወሰድነው እርምጃ ሕጋዊ ያደርገዋል ማለት ነው፡፡
- እኔ ሳልፈርም እንዴት አባረራችሁ?
- ያባረርናቸው ያው ሁላችንም የምናውቃቸው ሰዎች ናቸው፡፡
- እነ ማን ናቸው?
- አንዱ ያ ነዝናዛ ነው፡፡ ይህ ካልተገመገመ፣ በሚገባ ካልታየ እያለ ይረብሸን የነበረው ሰውዬ፡፡ እንደሱ ዓይነቱን ነው ያባረርነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ሌላስ?
- ሌላው ክቡር ሚኒስትር እርስዎም ያውቁታል፡፡ ኢሕአዴግን ከመጥላቱ የተነሳ ግንቦት ሃያ ሲመጣ እረፍት የሚወስድ አለ፡፡ እሱ ነው፡፡
- ሌላስ?
- ክቡር ሚኒስትር ሌላኛዋ ያቺ የመምሪያ ሃላፊ ሆና አላስፈላጊ መረጃዎችን ለጋዜጦች የሰጠችው ናት፡፡
- አላስታውሰውም፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ግማሽ ዓመት ላይ ደርሰናል፡፡ ነገር ግን ከእቅዳችን ሩቡንም ገና አልሰራንም ብላ መግለጫ ሰጥታ ነበር፡፡
- እህ አስታወስኩ፡፡ ሌላ ጥፋት ነበራት ወይስ ይኸው ብቻ ነው?
- መዓት ጥፋት አለባት እንጂ፣ የማባረር ስራ ስንሰራ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱን ባለሙያ እንዳይኖረው እያደረጋችሁት ነው ብላ አሾፈችብን፡፡
- እሺ፣ እሺ ይህ ከቢ.ፒ.አር ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ሌላ በዝርዝር የሚቀርብ ምን አለ? የፋይናንስ ዘርፉ የሚለው ምን አለ?
- ክቡር ሚኒስትር ዝርዝር ሪፖርት እየሰራን ነው፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ስራዎች ይቀሩናል፡፡
- ምን፣ ታይፒንግ?
- ታይፒንግ አይደለም ክቡር ሚኒስትር፡፡ አሁን የባጀት ዓመቱ እየተጠናቀቀ ስለሆነ ባጀት ከምንመልስ አንዳንድ ነገር እየገዛን ነው፡፡ እሱን ገዝተን ስቶር እስከምናስገባ ለጊዜው ሪፖርቱን አቆይተነዋል፡፡
- ምን እየተገዛ ነው?
- ክቡር ሚኒስትር፣ ለምሳሌ የእርስዎ ኮምፒዩተርና ፕሪንተር እየተቀየረ ነው፡፡ መጋረጃና ምንጣፍ አዲስ ገዝተናል፡፡
- አምና ነበር አዲስ የተገዛው?
- ያኔ በጨረታ እንገዛለን ብለን ዋጋውን ብቻ አይተን ያልሆነ ኳሊቲ ነበር የገዛነው፡፡ የአሁኑ ደረጃውን የጠበቀ ነው፡፡ የመምሪያና የዘርፉ ኃላፊዎች ክፍልም እንደዚሁ በኮምፒዩተር፣ በመጋረጃ፣ በምንጣፍ አጠናክረነዋል፡፡ የድርጅቱ ቴሌቪዥን አስወግደን አሁን ፕላዝማ ገዝተናል፡፡ ግዥው ስላላለቀ ሪፖርቱን ማጠናቀቅ ብቻ ነው፡፡
- ለፕሮጀክቶቹስ?
- ክቡር ሚኒስትር አሁን የነዳጅ ዋጋ ስለጨመረ ወደ ፕሮጀክቶቹ መመላለስ አክሰሪ ስለሚሆን የፕሮጀክቶቹ ነገር አስተላልፈናል፡፡
- (ሌላ ተናጋሪ) ክቡር ሚኒስትር ይህ ያስጠይቀናል፡፡
- ምንድነው የሚያስጠይቀው?
- ምንጣፍና መጋረጃ እየገዛችሁ ፕሮጀክቶቹን ረሳችሁ ያሰኛል፤ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- የነዳጅ ዋጋ ስለናረ ነው ብሎሃል እኮ፡፡
- የመጋረጃውና የምንጣፉ ባጀት ወደ ፕሮጀክቶቹ ነዳጅ ይዛወራል፡፡
- (ሌላ ተናጋሪ) ክቡር ሚኒስትር እኔ ክፍል ኮምዩተር ምንጣፍና መጋረጃ ካልገባ የሌላውም አይገባም፤ የሚሉት የምቀኝነት ኋላ ቀር አስተሳሰብ ቢቀር ጥሩ ይመስለኛል፡፡ ያገር ጉዳይ እያወራን የግል ፍላጎት ማንሳቱ ጥሩ አይመስለኝም፡፡
- አልገባኝም?
- ክቡር ሚኒስትር ለዘርፉና ለመምሪያ ኃላፊዋ ብቻ ነው መጋረጃ፣ ምንጣፍ፣ ኮምፒዩተር፣ ቴሌቬዥን ያስገባነው፡፡ ለዋና ክፍል ሃላፊዎች አልገዛንም፡፡ በቂ ገንዘብ ስላልተረፈ እና ወንድሜ የዋና ክፍል ሃላፊ ስለሆነ አልተገዛለትም፡፡ እቅድ ስለሌለው አይገባም ማለቴ ነው፡፡
- ለመሆኑ ይህ ምንጣፍ፣ መጋረጃ ኮምፒዩተር የሚባለው ለራሳችን እንድናውቀው የቀረበ ነው ወይስ በሪፖርቱ ተፅፎ ይቀርባል፡፡
- እንዴ ክቡር ሚኒስትር ለራሳችን ነው እንጂ የሚዘረዘረው፡፡ በሪፖርቱማ “አቅም ግንባታ” በሚል አጠቃላይ ርዕስ ነው የሚጠቀሰው፡፡ በማቴሪያል ተጠናክረናል በሚል፡፡
- ጎሽ እንዳያዋርደን ብዬ ነው፡፡
- ሁሉም ሚኒስቴር መስሪያ ቤት የሚያደርገው ነውኮ ክቡር ሚኒስትር፡፡ ሁሉም ያደርገዋል፡፡
- በካቢኔ ሲቀርብ ግን ሁሉም አፉን ያሾላል እንጅ እኔም አድርጌዋለሁ ብሎ ዝም አይልም፡፡ መሳቂያ እንዳታደርጉኝ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር፣ መገዛቱ አይደለም መሳቂያ የሚያደርገው ከተገዛው ኮምፒዩተር 75 ከመቶ እንኳን ሳንጠቀምበት ፕሮግራም ሳይጫንበት ዓመት ማለፉ ነው፡፡ የነበሩት ኮምፒዩተሮቻችን ማለቴ ነው፡፡
- እኔ ራሴም ከፍቸው አላውቅም፡፡ እሺ ወደ ሌላ ርዕስ ከመሄዳችን በፊት እዚሁ ፋይናንስ ላይ ይህ የውጭ ጉዞ የሚሉት ጣጣስ?
- አዎን ክቡር ሚኒስትር፣ የውጭ ጉዞ በዘንድሮው ዓመት እጥፍ ጨምሯል፡፡ አንድም ሂሳብ ያወራረደ ግን የለም፡፡
- ለምን?
- ደረሰኝ አምጡ፤ ሲባል የሚያመጣ የለም፡፡ ቀሚስና ሽቶ ሲገዛ ይውልና ደረሰኝ ማቅረብ ይቸግራል፡፡
- በእቅድ ውስጥስ ምን ተካቷል?
- ክቡር ሚኒስትር፣ ያሉን መኪኖች ነዳጅ ስለሚጨርሱ ነዳጅ ብዙ የማይወስዱ አዳዲስ መኪኖች እንዲገዙ ነው በእቅድ የያዝነው፡፡
- ለግል ምቾታችሁ ነው የምታስቡት እንዳይባል መጠንቀቅ አለብን፡፡
- የምቾት ጉዳይ አይደለም፣ ክቡር ሚኒስትር፡፡ ነዳጅ የመቆጠብና አገርን አስፈላጊ ካልሆነ ወጪ የመከላከል እርምጃ ነው፡፡
- ሁሉም ሰው ሲናገር አንቺ እስካሁን ድረስ አንዲት ቃል አልተነፈስሽም፤ እየታዘብሽ ትመስያለሽ፡፡
- አዎን እየታዘብኩ ነው፤ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምንድነው የምትታዘቢው? ታዛቢስ ማን አደረገሽ?
- የተሰጠኝ ሃላፊነት ነው ታዛቢ ያደረገኝ፡፡ ይህ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት የተቋቋመው መጋረጃ ለመግዛት፣ ምንጣፍ ለመቀየር፣ ኮምፒዩተር ቴሌቪዥን ፕላዝማ ለመግዛት፣ መኪና ለመቀያየር አይደለም፡፡ የተቋቋመበት ዓላማ አለው፡፡ በነጋሪት ጋዜጣ የፀደቀ የሚገዛ ዕቃና የሚቀጠረው ሰው የመስሪያ ቤቱን እቅድና ዓላማ ለማስፋፋት ነው፡፡ አሁን ግን ስለመጠየቁ ሥራና ኃላፊነት የተጻፈ ግምገማ የለም፡፡ መሳቂያ የምንሆን ከሆነ ምንጣፍ ገዛችሁ ተብሎ አይደለም፤ ስለተሰጣችሁ ሥራ ሪፖርት ማቅረብ የማትችሉ ናችሁ ተብሎ ነው የሚሳቅብን፡፡
- አልገባኝም፣ በግልፅ አስቀምጭው ምን ሰርተናል?
- ክቡር ሚኒስትር መኪችኮ መከላከያ ሚኒስትርም ይገዛል፣ ጤና ጥበቃ ሚኒስትርም ይገዛል፣ ያቺ መኪና ወታደር ልታመላልስ ትችላለች፣ ያቺ ደግሞ መድኃኒት ልታመላልስ ትችላለች፡፡ መኪና መግዛት ማቆም ሳይሆን በመኪናው ይህን ስራንበት ማለት አለብን፡፡
- እኛ ይህን ስላላልን መሳቂያ እንሆናለን?
- ክቡር ሚኒስትር እዛላይስ ነገሩ የሚያስቅ ብቻ ሳይሆን የሚያስለቅስም ሊሆን ይችላል፡፡
- በምን ምክንያት?
- ክቡር ሚኒስትር እዚህ በእርስዎ ዙሪያ ያሉት ሰዎች ስለ ግል ፍላጎታቸው  ብቻ የሚያስቡ ናቸው፡፡ ስለ አገር የሚያስብ ይህ ሪፖርትና እቅድ አያቀርብም፡፡ የእኛ ሪፖርት የሚቀርብለት አካል ዝም ብሎ አዳምጦ የሚዘጋ አይደለም፡፡ ይጠይቃል? ለምን ይላል? መዓት ጥያቄ ሊነሳልን ይችላል ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እስቲ መዓቱን ተውና ጥቂት ዘርዝሪ፡፡
- ይኸውልዎት ክብር ሚኒስትር፣ የፕሮጀክቱ አካሄድ ካለ ጨረታ የተካሄደና በጓደኝነት ወይም በሌላ ጥቅማ ጥቅም የተሰጠ ነው የሚል ጥያቄን ያስነሳል፡፡
- አንቺ ታነሺ እንደሆነ እንጂ ሌላው ምን የሚያውቀው የውስጥ ጉዳይ አለና፡፡
- የራሳችን ሰራተኛም’ኮ መድረክ አጥቶ ነው እንጂ፣ እየሳቀብን ነው፡፡ ይህ ጥያቄ ሌላ አያነሳውም ማለት የዋህነት ነው፡፡ ይህ ብቻም አይደለም፡፡
-  ሌላስ ምን አለሽ?
- ክቡር ሚኒስትር፣ በሕጉ መሰረት፣ኮ ልንገዛ የምንችለው መኪና ብዛቱ ይታወቃል፡ ከሕግ ውጭኮ መኪኖች ገዝተናል፡፡
- ቁጥር ስንሰጥ የት ነበርሽ?
- መቼ የቁጥር ስህተት ሆነ ክቡር ሚኒስትር፣ ሙስና ነው እንጂ፡፡ ከመኪና ሻጮቹ ጋር በመመሳጠር የጥቅም ግንኙነት ነው፡፡ ሌላም አለ፡፡
- ቀጥይ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር መስሪያ ቤታችን መዓት ብረታ ብረት አያስፈልገኝም ብሎ ለግንባታ አከማችቶት የነበረውን ሸጧል፡፡
- ታዲያ መሸጥ ክልክል ነው፡፡
- በጨረታ አልተሸጠማ፡፡ የእህትዎ ባል እኮ ነው የወሰደው፡፡ በነፃ ቢባል ይሻላል፡፡
- ስለአገር የተቆረቆርሽ መስሎኝ ነበር፤ ለካ የግል ጥላቻ ነው፡፡
- አይደለም ክቡር ሚኒስትር፡፡ አንድ ቅርንጫፍ መስሪያ ቤታችን በፕራይቬታይዜሽን በኩል ለባለቤቶች እንዲመለስ ተወስኖ ነበር፤ አላአግባብ የሰው ሀብት ይዘናል፡፡
- ጉቦ ሰጥተው ተሟገቻቸው ብለውሻል? የእኛ ስላልሆነ ስለእኛ ንብረት አታስቢም?
- ክቡር ሚኒስትር፣ የእኛ ንብረት ለግለሰቦች ተሰጥቶ የነበረው በስህተት ነው ለሚኒስቴሩ ይመለስ ብሎ ፍርድ ቤቱና ፕራይቬታይዜሽን የወሰኑትን ተከታትላችሁ ንብረታችንን ማስመለስ አልቻላችሁም እኮ፡፡
- ለምን?
- የሕግ ክፍላችን በጥቅማ ጥቅም ስለታሰረ ነዋ!
- ሌላስ?
- መሥሪያ ቤታችን ባለሙያ አልባ ሆኗል፡፡
- ለምን?
- በዘመድ አዝማድ ሰው ለመቅጠር ተብሎ ባለሙያ ቦታ እንዲለቅ እየተደረገ ነዋ!
- ለምን ታዲያ አንቺ እንድትለቂ አልተደረገም?
- ተደርጓል፣ኮ ክቡር ሚኒስትር፡፡ እነዚህ ሰዎች አባረውኛል፡፡ እኔም መልቀቂያ አቅርብያለሁ፡፡
- ለማን አቀረብሽ?
- ለእርሶዎ ክቡር ሚኒስትር፡፡ መባረሬንም መልቀቂያዬንም እስኪፈርሙ እኮ እየጠበቅኩ ነው፡፡
- አላየሁትም አልሰማሁምም፡፡
- ችግሩስ እሱ አይደል፡፡
- ምን?
- አለማየትና አለመስማት! 
 
< Prev   Next >