| በቋንቋ ምክንያት የተገደቡ መረጃዎች |
|
|
| Sunday, 13 January 2008 | |
|
አዝጋሚ ቢሆኑም አዳዲስ አገልግሎቶችን እየተገበሩ ካሉት መንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶች መካከል የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽንና የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽን ተጠቃሾች ናቸው፡፡
እነዚህ ሁለት መሥሪያ ቤቶች በአራቱም አቅጣጫ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ደንበኞች አሏቸው፡፡ የሚሰጡት አገልግሎት ከኀብረተሰቡ የእለት ተእለት እንቅስቃሴ ጋር የሚጣመር ነው፡፡ ከሁሉም የኀብረተሰብ ክፍል ጋር የጠበቀ ግንኙነት አላቸው፡፡ ወደፊትም ከእነዚህ ተቋማት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ደንበኞች አገልግሎታቸውን ይሻሉ፡፡ በሌላ አነጋገር ሰፊ ገበያ አላቸው ማለት ይቻላል፡፡ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያሉና አገልግሎቱን በሞኖፖል የያዙ ናቸው፡፡ ተወዳዳሪ የላቸውም፡፡ እነዚህ ትላልቅ ተቋማት የሚሰጡት አገልግሎት ለምን የግል ባለሃብቶች እንዲገቡ አልፈቀደም? መሥሪያ ቤቶቹ ሥራውን (ዘርፉን) በሞኖፖል በመያዛቸው አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በተፈለገው ፍጥነት ማስገባት አልተቻለም፡፡ ደንበኞችም በምርጫ ሊስተናገዱ አልቻሉም፡፡ ሞኖፖሊ የሚፈጥረው ችግር ከዚህም ያለፈ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ቴለኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽን ሞባይልን ኢትዮጵያ ውስጥ ለማስገባት የፈጀበትን ጊዜ እናስታውሳለን፡፡ ከዚያ ወዲህም አዳዲስ አገልግሎቶችን ለመተግበር የሚወስድበትን እየታዘብን ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ የ3ጂ አገልግሎት ጀምሬያለሁ ካለ ወራት አሳልፏል፡፡ ሌላም ሌላም ማቅረብ ይቻላል፡፡ ተወዳዳሪ ቢኖረው ይህ ሁሉ መጓተት እንደማይፈጠር እንገነዘባለን፡፡ ዘግይተውም ቢሆን ሁለቱ መሥሪያ ቤቶች አዳዲስ አገልግሎቶቹን እያስገቡልን ነው፡፡ ከአገልግሎቶቱ መካከል የቅድመ ክፍያ የሞባይል አገልግሎት ይጠቀሳል፡፡ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽንም በኩል በካርድ የሚሠራ ቆጣሪ አገልግሎት ጀምሯል፡፡ ቢዘገይም እንዲህ ዓይነት አገልግሎቶች መምጣታቸው አይጠላም፡፡ በተለይ ለቅድመ ክፍያ የማያገለግለው ካርድ አሁን በከተማችን በተለይ አዳዲስ በተገነቡት የኮንዶሚኒየም ቤቶች ውስጥ አገልግሎት እየሰጠ ነው፡፡ የካርዶቹ አጠቃቀም ግን ጥያቄን ያስነሳል፡፡ በየካርዶቹ ላይ ያሉት መረጃዎች የተፃፉት በእንግሊዝኛ ቋንቋ ነው፡፡ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተፃፉትን መረጃዎች ተረድቶ ሊጠቀም ከሚችለው የኀብረተሰብ ክፍል ቁጥር አንፃር ሲታይ ተቋማቱ ሊያስተካክሉ የሚገባቸው ጉዳይ እንዳለ ይጠቁመናል፡፡ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይም እንዲህ ያለው ነገር ገጥሞኛል፡፡ ኮንዶሚኒየም ቤት የደረሰው ሰው የሚጠቀምበትን የኤሌክትሪክ ካርድ ይዞ ከካርዱ ጀርባ ላይ ያለውን ፅሁፍ ለመረዳት አቅቶት ሰው ሲያስተረጉም ተመልክቻለሁ፡፡ እንዴት ማስሞላት እንዳለበት ጭምር መረጃ የተቀበለው ከሌሎች ሰዎች ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ክስተት ተቋማቱ የሚሰጡትን አዳዲስ አገልግሎቶች ጐደሎ ማድረጉን ይጠቁመናል፡፡ ኀብረተሰቡ በሚገባው ቋንቋ ካርዶቹ ላይ መግለፁ ለምን አልተፈለገም፡፡ ወይስ አገልግሉቱ የታሰበው ለእንግሊዝኛ ተናጋሪዎች ነው? የሁለቱን ተቋማት አሠራር በምሳሌነት አነሳን እንጂ ሌሎች ለሸማቾች በሚቀርቡ ምርቶች ላይም ተመሳሳይ ችግር አለ፡፡ በእርግጥ በአንዳንድ ምርቶች ላይ አገራዊ በሆኑ ቋንቋዎች ሲጠቀሙ እናያለን፡፡ ነገር ግን የተፈለገውን ያህል አይደለም፡፡ ስለሆነም ትኩረት የሚያሻው ጉዳይ ነው፡፡ መድኃኒት የመሳሰሉ ምርቶች ጥንቃቄ ያስፈልጋቸዋል፡፡ በአገር ውስጥ የሚመረቱ መድኃኒቶች ስለአጠቃቀማቸው ስለመድኃኒቱ ይዘትና የመሳሰሉትን መረጃዎች በእንግሊዝኛ ብቻ መፃፉ ተገቢ አይደለም፡፡ ደንበኛዬ ማነው ብሎ መመልከት ያስፈልጋል፡፡ አንዳንዶቹ ምርቶች እንዲያውም ለውጭ ዜጐች ሊቀርቡ የማይችሉ መሆናቸው እየታወቀ ፅሐፎች በእንግሊዝኛ ብቻ መደረጋቸው አስገራሚ ነው፡፡ ማንበብና መፃፍ የሚችለው የኀብረተሰብ ክፍል በሚገባው ቋንቋ ቢፃፍለት ተመራጭ ነው፡፡ ለእንዲህ ዓይነቱ አሠራር አስገዳጅ ሕግ ሊኖርም ይገባል፡፡ ከዚህ ቀደም የጥራትና ደረጃዎች ባለሥልጣን ከውጭ የሚገቡ ምርቶች ቢያንስ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተፃፈ መረጃ ሊኖራቸው እንደሚገባ አስገዳጅ እርምጃ ሲወለድ እንደነበር ይታወሳል፡፡ በአገር ውስጥ ምርቶች ላይ እንዲሁም ወደ አገር ውስጥ ያስገነባናቸው የተለያዩ አገልግሎት የሚውሉ ካርዶችና ዶክመንቶች ላይ ከእንግሊዝኛ ቋንቋ በተጨማሪ በሌሎች የአገሪቱ ጭምር ቋንቋዎችም መረጃ ማስቀመጡ ጠቃሚ ነው፡፡ በናታን ዳዊት |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |