Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Thursday
Aug 28th
Home arrow Sections arrow ድሬዳዋ እንደ ሰው ከስታለች
ድሬዳዋ እንደ ሰው ከስታለች Print E-mail
Sunday, 13 January 2008

ጌዲዮን ከድሬዳዋ

አንድ መቶ አምስተኛ የልደት በዓሏን የምናከብርላት ድሬዳዋ፣ በተለያዩ የሀገራችን አቀንቃኞች የተዜመላት ድሬዳዋ፣ በአንድ ወቅት ከአዲስ አበባ ቀጥላ፣ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኝ የነበረችው ድሬዳዋ፣ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችና ሃይማኖት ያሏቸው ሕዝቦች ከልብ ተከባብረውና ተፈቃቅረው የሚኖሩባት ድሬዳዋ፣ የሁሉም በመሆኗ ትንሽ ኢትዮጵያ የምትባለዋ ድሬዳዋ፣ በሰው ወዳድነቱና አስተናጋጅነቱ የሚታወቅ ሕዝብ ያላት ድሬዳዋ፣ ቴክኖሎጂዎችንና ስልጣኔዎችን ለመቋደስ ቀደምት የነበረችው ድሬዳዋ፣ ከራሷ አልፋ ለተለያዩ የውጪ ዜጎች ጥገኝነት ከመስጠት ደርሳ የነበረችው ድሬዳዋ "ፊተኛ ኋላ ይሆናሉ እስኪሉ" ድረስ በዕድገት በጣም ወደ ኋላ ቀርታለች፡፡

ድሬዳዋ ለምን ወደ ኋላ ቀረች? ቢያንስ ማደግ ቢያቅታት ባለችበት መቆም ለምን ተሳናት? በድሬዳዋ ብዙ ልብን የሚሰብሩ ጉዳዮችን ለዓመታት ተመልክተናል፡፡ ድሬዳዋ ከቀን ወደ ቀን እንደ ሰው እየከሳች ነው፡፡ ድሬዳዋ ስትከሳ የድሬዳዋ ሕዝብም ይሁን የኢትዮጵያ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን መክሳታቸው አይቀርም፡፡

የድሬዳዋ ማሽቆልቆል መታየት የጀመረው በደርግ የመጨረሻ አመታት ጀምሮ ነው፡፡ በኢሕአዴግም ቢሆን በድሬዳዋ ትርጉም ያለው ነገር አልተሰራም፡፡ ትንሽ ትልቅ፣ ክርስቲያን እስላም፣ የኔ ብሔር የሱ ብሔር ሳንባባል ድሬዳዋን እንወዳለን፣ የምንል ድሬዳዋ በልማት ረገድ ወደ ኋላ መቅረት የሚያንገበግበን ሁሉ ለድሬዳዋ የሚቻለንን ማድረግ አለብን፡፡

ኢሕአዴግ ኢትዮጵያን ከተቆጣጠረበት ከ17 ዓመት ወዲህ እንኳ በድሬዳዋ ያለውን መሽቆልቆል ብናይ በጣም በቂ ነው፡፡ እያወቅንም ሆነ ሳናውቅ ድሬዳዋን በድለናታል በተለይ ሶስታችን፡፡ የድሬዳዋ ጊዜያዊ አስተዳደር ባለሥልጣናት፣ የድሬዳዋ ነዋሪዎች (ተወላጆችና የልብ ወዳጆች) እንዲሁም መንግሥት፡፡ በአሁኑ ወቅት ድሬዳዋ ውስጥ የሚታዩ መልከ ብዙ ችግሮች እንዲከሰቱ የበኩላችንን አስተዋፅኦ አድርገናል ወይም ቢያንስ ስህተቶች ሲከሰቱ በወቅቱ ለማረም አልቻልንም፡፡ በመሆኑም ሁላችንም ድሬዳዋን በድለናታል፡፡ የበደለ ደግሞ ሊክስ ይገባል፡፡ እንዴት ነው ድሬዳዋ የምትካሰው? ስንል ደግሞ እነዚህ ሶስት አካላት ችግር መፍጠር ወይም ችግር ሲከሰት ቆሞ ማየት ብቻ ሳይሆን መፍትሄ ለመስጠትና ድሬዳዋን ለመታደግም አቅም አላቸው፡፡ በመሆኑም ችግራችንን በግልጽ አስቀምጠን ሁሉም ሊያርመው የሚገባውን በማረም አዲሲቷን ድሬዳዋ አብረን ተባብረን የሁላችንም መመኪያና የጥንካሬያችን መግለጫ ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡

በአሁኑ ወቅት ድሬዳዋ ውስጥ አንኳር አንኳር ችግሮች አሉ፡፡ ከምንም በላይ በሶስቱም አካላት በኩል የተሳሳቱ ግንዛቤዎችን መያዝ ትልቅ ችግር ነው፡፡ መንግሥት ስለ ድሬዳዋ ያለው ዋንኛው የተሳሳተ ግንዛቤ የድሬዳዋ ሕዝብ ምንም ስላልተናገረ ከተማዋ ውስጥ ምንም ችግር የለም ብሎ መገንዘቡ ነው፡፡ የድሬዳዋ ነዋሪዎች በተለይም የድሬዳዋ ልጆች ወደ ኢሕአዴግ ለመጠጋት አልቻሉም፤ ወይም አልፈለጉም፤ በሚል የተሳሳተ ግንዘቤ ይመስላል ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ክልሎች በራሳቸው ልጆች ሲተዳደሩ ድሬዳዋ ግን አቅም ያላቸው ነዋሪዎች የሌላት ይመስል ዛሬም በልጆቿ እየተመራች አይደለችም፡፡ በአንድ ወቅት ግን አንድ የውጭ ዜግነት ያለው ጎብኝ እንደፃፈው ኢትዮጵያን ሲጎበኝ ድሬዳዋን ሲያያት በዛ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ በዘመኑ የሰለጠነ የስራ አመራርና አስተዳደር እንደተገነዘበ ነው፡፡ ታዲያ ዛሬ ከ105 ዓመት በኋላ የራሷ የድሬዳዋ ነዋሪዎች እንዴት ራሳቸውን ማስተዳደር ያቅታቸዋል፡፡

የመንግሥት ሌላው የተሳሳተ ግንዛቤ ድሬዳዋ /በሽማግሌዎች ውትወታ ቢሆንም/ በተወላጆች ባይሆንም በአካባቢዋ ልጆች እየተመራች በመሆኑ ችግሯ ተቀርፏል ብሎ ማመን ነው፡፡ በተግባር ግን ሲታይ ከ11 የካቢኔ አባላት ውስጥ የድሬዳዋ ተወላጆች ሶስት ብቻ ናቸው፡፡ /ምክትል ከንቲባ፣ ህዝብ ግንኙነትና ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ማስተባበሪያ/ ይህንን የተወላጆች ስብጥር በጽ/ቤት ኃላፊነት ደረጃ ብንመለከተው ደግሞ የባሰ የሳሳ ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ ድሬዳዋ እየተመራች ያለችው በአስለቃሽ ነው፡፡ የሚያስፈልጋት ግን ከልብ የሚያለቅስ መሪ ነው፡፡ ሐዘን ቤት እንኳን ልብ ብላችሁ እንደሆን አስለቃሽ እኮ አያለቅስም፡፡ ሰውን ሲያስለቅስ ይውላል እንጂ፡፡ በመሆኑም መንግሥት ዕወቀት በተግባር የተገለፀ ልምድ ሀብት ተነሳሽነትና ቅንነት ያላቸውን የድሬዳዋ ተወላጆችና የልብ ወዳጆች ይዞ ቢንቀሳቀስ በአጭር ጊዜ ውስጥ ትርጉም ያለው ለውጥ በማምጣት ድሬዳዋንም ሆነ ሕዝቧ ይክሳል፡፡

በድሬዳዋ ጊዜያዊ አስተዳደር በኩል የተያዙት የተሳሳቱ ግንዛቤዎች ደግሞ ዛሬም ጠባብ ብሔረተኝነትንና ብሎም በዘር ማሰብ በኢሕአዴግ የሚደገፍ አድርጎ መመልከት ነው፡፡ ድሬዳዋ ወደፊት ወይ ለሱማሌ አሊያም ለኦሮሞ ትሰጣለች በሚል የተሳሳተ ግንዛቤ የተለያዩ የጽ/ቤት ኃላፊነት ላይ የድሬዳዋ ነዋሪ ያልሆኑትን ሰዎች ብቻ በመመደብ አጉል ገመድ ጉተታ ውስጥ ገብቷል፡፡ ነገ ሪፍረንደም ቢካሄድ እንኳ የሕዝባችንን ቁጥር እናብዛ በማለት የድሬዳዋ ነዋሪዎች መሬት ሳያገኙ /ከድሬዳዋ ውጭ በአካባቢዋ/ ለሚገኙ ተወላጆች ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ መንገድ እየተሸነሸነ በመሰጠት ላይ ይገኛል፡፡

ይህ በአንዳንድ አክራሪ አቋም ባላቸው የካቢኔ አባላት ጫና የተያዘው የተሳሳተ ግንዛቤ በድሬዳዋ ታይቶ የማይታወቅ የብሄርና የሐይማኖት ችግር እየፈጠረ ከመሆኑም በላይ ከተማዋንና ህዝቦቿን ከመጠን በላይ በመጉዳት ላይ ይገኛል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ይህ የተሳሳተ ግንዛቤያቸው የድሬዳዋ መሪዎቻችን ምን ያህል ከኢሕአዴግ ፕሮግራምና አላማ ጋር የሚቃረን ወይም የሚጋጭ መሆኑን እንኳን ሊረዱ አልቻሉም፡፡

ሌላው የተሳሳተ ግንዛቤ ከልብ የድሬዳዋ ልጆች ወይም ወዳጆች ፍፁም ለሰላም ዓላማ እንኳ ቢደራጁ ነገ ለኛ አደጋ ናቸው የሚል ትልቅ ስጋት ማሳደራቸው ነው፡፡ በጽሞና ቢረዱት ግን ይህ ዓይነቱ ቡድን  ለድሬዳዋና ሕዝቦቿ እንዲሁም ለኢትዮጵያ በአግባቡ ቢያዝ ትልቅ የለውጥ ሃይል ሊሆን እንደሚችል በተረዱ ነበር፡፡ ከዚሁ የማይተናነሰው ሌላው የተሳሳተ ግንዛቤ አንዳንድ የካቢኔ አባላት ራሳቸውን ፍፁም ምትክ የማይገኝላቸው አድርገው ከመቁጠራቸውም በላይ ራሳቸውን ከኢሕአዴግም በላይ ኢሕአዴግ አድርገው መቁጠራቸው ነው፡፡ በጣም በሚያሳፍር መልኩ እነሱ ከሌሉ ድሬዳዋ የምትኖር የማይመስላቸው አንዳንድ ግብዞችም አሉ፡፡፡ አቋማቸውንም አክራሪዎቹ ያደረጉትም እንዳሉ መጠርጠር አስፈላጊ ነው፡፡ በመሆኑም የድሬዳዋ ሕዝብም ይሁን መንግሥት በቃ አቋማችሁን በግልፅ ታውቋል አቅማችሁም ለማስተዳደር አልበቃም ቅንነትም ያንሳችኋል በማለት በግልፅ ሊነግራቸው ይገባል፡፡ ይህ ሊነገራቸው የሚገባው ከወዲሁ ነው፡፡ ምክንያቱም ድሬዳዋ ታማለች፣ ከስታለች እስክትሞት መጠበቅ የለብንም፡፡ ሐኪም ፈልገን ልናድናት ግድ ነው፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በድሬዳዋ ነዋሪዎች /በተለይም በተወላጆችና የልብ ወዳጆች/ በኩል የሚታየው ዋንኛ የተሳሳተ ግንዛቤ ኢሕአዴግ እነሱን ለማቀፍ ፍላጎት ያለው አይመስላቸውም፡፡ በጣም በጥቂቶች ዘንድ ደግሞ የሚታየው አሳፋሪ ግንዛቤ መንግሥት ድሬዳዋን ሆን ብሎ እንዳታድግ የማይሰሩ አመራሮችን ያስቀምጣል፣ ያስቀመጠውንም አመራር በአግባቡ አይከታተልም፣ ከልብ የድሬዳዋ ነዋሪዎችን በተለይም ተወላጆችንና ወዳጆች ምሁራንን ባለሀብትንና የተለያየ የሕብረተሰብ ክፍል ጠርቶ ስለ ፕሮግራሙ ሊያስተዋውቅ ያለመፈለግ ወይም ያለመቻል ዝንባሌ እንደሚያሳይ ነው፡፡

ሌላው የሚታየው የተሳሳተ ግንዛቤ ደግሞ የሚመነጨው ለዓመታት ከተመለከተው ነው፡፡ ይኸውም እኛ እንደ ድሬዳዋ አስተዳደር እነሱን /የድሬዳዋ ነዋሪዎች/ ለመቀበል ዝግጁ የሆንን አንመስላቸው፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ የድሬዳዋ ነዋሪዎች ድሬዳዋን ለመለወጥ ከልብ እንሰራለን፣ በአስተዳደሩ ውስጥ የምናየውም ኢፍትሃዊ ድርጊት በሰላማዊ መንገድ አምርረን እንታገላለን ብለው ቢንቀሳቀሱ ያልተፈለገ መስዋዕትነት ልንከፍል እንችላለን፣ በሚል መሰረት ባለውም ምንም በቂ ምክንያት በሌለውም ሁኔታ ራስን የማሳመን ብሎም ራስን የማግለል አዝማሚያ ይታያል፡፡

የብሄርተኝነት ችግር በድሬዳዋ በጣም እየተስፋፋ ነው፡፡ እገሌ የተባለው ብሐር/ብሔረሰብ ቢኮረኮም መንግሥት ይወዳል፤ ቢያንስ ምንም አይልም፤ በሚል ከመጠን በላይ አጓጉል ቀይ መስመሩን ያለፈ ስሜት ተፈጥሩዋል፡፡ ቀይ መስመሩን እየጣሱት ያሉት ጥቂት ግለሰቦች ብቻ ሳይሆኑ ከተማዋን እንመራለን የሚሉትም አሉበት፡፡ በተለያየ መስሪያ ቤቶች አንዳንድ ወገኖች የድሬዳዋ ነዋሪ ሰራተኞችን በግልፅ እየበደሉ ከተለያየ አካላት ለከንቲባው ቢደርስም በጭራሽ ይህንን ድርጊት ለማስቆም አልቻሉም ወይም ፈቃደኛ አይደሉም፡፡ ይህንን አቋማቸውን በማየት በዳዮችም በደላቸው የድሬዳዋ ነዋሪ ከተማውንና የፌዴራል መንግሥትን አምርሮ እስኪጠላ እየደረሰ ነው፡፡ እንደ ከተማ መሪ ደግሞ ይህንን መግታትና ማስተካከል ካልፈቀዱ ድርጊቱን ደግፈዋል፤ ማለት ነው፡፡

የጠባብነትና የሃይማኖት አክራሪነት ከምንም በላይ የድሬዳዋ ሕዝብ ለዘመናት ይታወቅበት የነበረውን መቻቻልና የመፈቃቀር መንፈስ በጣም በፈጣን ሁኔታ ሊሸረሽር በሚችልበት ሁኔታ ላይ ነው ለማለት ይቻላል፡፡ ልንረዳው የሚገባን መገንባት እንጂ መናድ ቀላልና ጊዜ የማይፈጁ መሆኑን ነው፡፡ አስተዳዳሪዎች ትውልዶች የገነቡትን የመቻቻልና የመከባበር ባህል በታሪክም ተወቃሽ እንዳትሆኑ አትናዱት ወይም ቆማችሁ እያያችሁ አታስንዱት እላለሁ፡፡

ሌላው የድሬዳዋ ችግር መሳሳብ ነው፡፡ አንድ ሃላፊ ስልጣን ላይ ከወጣ የራሱን ዘመድ፣ ብሄር፣ የሃገር ልጆች፣ በሚል ስንከላ አመለካከት ብቃት የሌላቸውን በዙሪያውና በከተማው ውስጥ ማሰባሰብ ነው፡፡ ይህ በሀላፊዎቻችን በኩል የሚታይ ትልቅ ችግር ነው፡፡ የተለያዩ መ/ቤቶች ውስጥ መስራት የሚችሉ ብቃትና ቅንነት ያላቸው የድሬዳዋ ነዋሪዎች የጠፉ ይመስል ባለሥልጣናት የራሳቸውን ብሄር አሊያም የሀገራቸውን ልጆች በብዛት እያስመጡ በድሬዳዋ አስቀጥረዋል፡፡ ይህ መሳሳብ በድሬዳዋ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ሌላውን ነዋሪ ማስከፋት ብቻ ሳይሆን ካቢኔ ውስጥ ያሉ ኦሮሞዎችንና ሶማሌዎችን ጭምር በከፍተኛ ደረጃ እያነታረከ ያለ ጉዳይ ሆኗል፡፡ በላይ ለድሬዳዋ ዕድገት የሚበጁ ሃላፊዎችን ሠራተኞችን በየመስሪያ ቤቱ ከመመደብ ይልቅ የእነሱ ትልቁ ራስ ምታታቸው የየራሳቸውን ሰው ማስገባቱ ላይ መሆኑን የከተማችን ወሬ ከሆነ ሰነበተ፡፡

አሁን ያለውን የድሬዳዋ ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ ብንመለከት ብዙ ችግር ያለበት ነው፡፡ በሶስት ከፋፍሎ ማየት ይቻላል፡፡ ይህም የምሥራቅ ሐረርጌ ቡድን፣ የሶማሌዎች ቡድን እና የድሬዳዋ ተወላጆች በሚል መንፈስ ማየት ይቻላል፡፡ የምሥራቅ ሐረርጌ ቡድን ሌሎች ወገኖቻቸውን ከተለያየ ቦታ በማስመጣት ድሬዳዋ በማስቀጠር አንደኛ ናቸው፡፡ የሶማሌው ግሩፕ እንደ ኦሮሞዎች ሁሉ በሚቻለው ሁሉ ወገኖቻቸውን አስቀጥረዋል፡፡ ምንም መፍጠር ያልቻሉት በካቢኔ ውስጥ ያሉ የድሬዳዋ ተወላጆች ናቸው፡፡ ምክንያቱም የካቢኔውን ስብጥር ብንመለከት በብሄርም በሃይማኖትም ቁጥር ብዛት ተውጠው ይገኛሉ፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ የካቢኑ ቁጥር 11 መሆኑ ብዙ በመሆኑ ካቢኔው በአንድ ጉዳይ ላይ እንኳ ተወያይቶ አቋም ለመውሰድ ብዙ ሲቸግረው ይታያል፡፡

መሪዎቻችን /የካቢኔ አባላት/ እየመሩት ያለው ከተማ ምን አይነት ከተማ እንኳን እንደሆነች አልገባቸውም፡፡ ይህ ነው ትልቁ አደጋ ድሬዳዋንም ቁልቁል እየወሰዳት ያለው፡፡ ድሬዳዋ ልክ እንደ አዲስ አበባ በፌዴራል መንግሥት ስር መሆኗ ግልፅ ሆኖ ሳለና የመንግሥትም አቋም ወደፊት ድሬዳዋን የምሥራቅ ኢትዮጵያ የንግድና ኢኮኖሚ ማዕከል ለማድረግ እንደሆነ በተለያየ ጊዜ በተደጋጋሚ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሳይቀር በግልፅ ቋንቋ ሲነገርም፣ መሪዎቻችን ዛሬም የሚያስቡት ከዚህ አኳያ ሊሆን አልቻለም፡፡ ድሬዳዋ የፌዴራል ከተማ እንደመሆኗ መጠን የክልል ብሄርተኝነትና ተወላጅነትም የግድ ቦታ ሊሰጣቸው አይችልም፡፡ ለድሬዳዋና ለኢትዮጵያ ማደግ ህልም ያለው ማንኛውም የኢትዮጵያ ነዋሪ ሊመራት የሚችል የፌዴራል ከተማ ወይም አስተዳደር መሆኗ ተረስቶ ዛሬም በብሄርና በሃይማኖት አክራሪነት ጎርፍ ውስጥ መንደርደር ትክክል አይደለም፡፡ ጎርፉ ውስጥ ደግሞ እስኪገቡ ድረስ ራሳቸው ዋኝተው መውጣት እንጂ ሌላው አማራጭ በጣም በአሳዛኝ ሁኔታ እስከወዲያኛው ጭልጥ ብሎ በጎርፉ መጥፋት ነው፡፡ 

 
< Prev   Next >