| ሰላማዊዋ ጅቡቲ በጦርነት ጎዳና |
|
|
| Sunday, 15 June 2008 | |
|
ከጋዜጣው ሪፖርተር
ጅቡቲ በራስ ዱሜራ በኩል በኤርትራ የመወረሩዋ ዜና፣ ኢትዮጵያ በባድመ በኩል በኤርትራ ወረራ በተፈፀመባት ወቅት እንደነበረው ዜና አስደናቂና ያልተገመተ አልነበረም፡፡ ኤርትራ ፍቅራቸው ልክና መጠን አጥቶ በጋራ ምንዛሬ ለመጠቀም ክርክር ካልነበራቸው ኢትዮጵያ ጋር፣ የስልክ ግንኙነትና ገንዘብ ከኢትዮጵያ የሚያሰጥ ፍቅር አስይዛ በነበረበት ወቅት በድንገት የተሰማው ፀብ በርግጥም ለሰማው ሁሉ አስደንቋል፡፡ ከጅቡቲ ጋር ግን በተለያየ ጊዜ የሚያገረሸው ቅራኔያቸው፣ በተለይም ጅቡቲ የሱማልያን እርቅ ማስተናገድ ከጀመረች ወዲህ የነበረው መናቆር በወሰን ደረጃ ኤርትራ መተናኮሷ እንደማይቀር ሳይታለም የተፈታ ነበር፡፡ ባለፈው ማክሰኞ ምሽት ኤርትራን እየከዱ ወደ ጅቡቲ የሚገቡ ወታደሮች ሰበብ ሆነው ተኩስ ሲጀምሩ ጅቡቲ የመጨረሻው የወረራ ምልክት አድርጋ ቆጠረችው፡፡ የጦር ኃይል መምሪያዋ ክተትና ማሳሰቢያ ሲሰጥ፣ ሰራዊቷንም ለግዳጅ አሳለፈች፡፡ ለወዳጅ ሃገሮችና ለተመድ ጉዳዩን ማስታወቅ የማግስቱ ሥራ አድርጋዋለች፡፡ ኘሬዚዳንት አስማኤል ኦማር ጊሌ ራሳቸው ረቡዕ ዕለት ቁስለኞቹን ሊጎበኙና ሊያፅናኑ ለዓለም ሕዝብ በቴሌቪዥን እንደተላለፈ ሆነ፡፡ ነገሩ እየተባባሰ ከሄደ ሰላማዊዋ ጅቡቲ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ጦርነት ትገባለች፡፡ “ኤርትራ ከፈለገችው ታገኛታለች” የሚለውም የቁጣ ማሳሰቢያቸውም የተላለፈው ያን ጊዜ ነው፡፡ በአፍሪካ ቀንድ ትንሿ የምትባለዋ ጅቡቲ የታላላቅ ሃገሮችን ቀልብ ስባለች፡፡ አሜሪካ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የጦር ካምፑዋን ሰርታለች፡፡ ፊረንሳይ በቅኝ ግዛትነት በጅቡቲ ከገባች ጊዜ ጀምሮ አሁንም መከላከያን ጭምር በዋና የጋራ ትብብር ላይ በተመሰረተ ግንኙነት ላይ ነች፡፡ እነዚህ ኃያላን ዓይናቸውን የጣሉበት ጅቡቲ አሁን በኤርትራ ድንበሩዋ መጣሷ ሲሰማ ጉዳዩን በቀላሉ ሊያዩት አይችሉም፡፡ ኢትዮጵያ ዋነኛ የዕቃ ማስወጫና ማስገቢያዋ በመሆኗ የጅቡቲ ሕልውና እንደ እራሷም አድርጋ ታያለች፡፡ የጅቡቲ ሰላም ተናጋ ማለት ከራሱዋም የሰላም መታጣት ጋር ይቆራኝባታል፡፡ በተለይም በድንበር ምክንያት በከፍተኛ ፍጥጫ ላይ ከምትገኘው ኤርትራ በኩል ወረራው ሲመጣ ለብዙ ጥንቃቄ የሚዳርግ ሥጋት ሊያድርባት ይችላል፡፡ የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ለኤርትራ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል፡፡ የአረብ ሃገራት አባል የሆነችው ጅቡቲ የመደፈሩዋን ዜና አብዛኛዎቹ የአረብ ሃገሮች ከጎኑዋ እንዲቆሙ ሲገልፁ ኤርትራም በአስቸኳይ ሰራዊቷን ከጅቡቲ መሬት እንድታወጣ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል፡፡ ሮይተር የጅቡቲን የጦር ዕዝ ፅህፈት ቤት ጠቅሶ እንደዘገበው ጅቡቲ ዘጠኝ ወታደሮቿን አጥታለች፡፡ ከ6ዐ የሚበልጡ ቆስለዋል፡፡ ኤርትራ በበኩሏ ያለፈው ረቡዕ ምሽት ላይ በአጭር መግለጫ፣ የተባለባትን ሁሉ ለማስተባበል ሞክራለች፡፡ የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው ጅቡቲ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለመተናኮስ ብትፈልግም ኤርትራ መልካም ጉርብትናን የሚያጠፋ ትንኮሳ ለማድረግ እንደማትፈልግ ገልጿል፡፡ የሁንና ኤርትራ ካላት ባህርይ አላደረገችም ብሎ የጠረጠረ ያለ አይመስልም፡፡ ይኸም የሚገለፀው በርካታ ሃገሮች ለጅቡቲ ድጋፋቸውን የሰጡት በፍጥነት ነበር፡፡ በተለይም ተመድ አሜሪካና ፈረንሳይ፡፡ ጅቡቲ ከ11,000 በላይ ወታደሮች እንዳሏት ሲገመት አሁን በኤርትራ በኩል ለተቃጣባት ጦርነት ለመከላከል ያህል ጡረታ የወጡ ወታደሮቿን ጭምር እንዲከቱ አዛለች፡፡ ኤርትራ እስከ 2ዐዐ ሺ የሚደርስ ወታደር እንዳላት ይገመታል፡፡ ይሁን እንጂ ከኢትዮጵያ ጋር ባላት ፍጥጫ አብዛኛውን በደቡብና በደቡብ ምስራቅ የሃገሪቷ ክፍል እንዲመሽግ አድርጋለች፡፡ ኤርትራ ጦርነቱን ለምን ፈለገችው? ኤርትራ በጅቡቲ ላይ ጦርነት ለመቀስቀስ ምክንያት የሆናት ከኢትዮጵያ ጋር ያላት የከረረ ፀብ ሳይሆን እንደማይቀር የፖለቲካ አስተያየት ሰጪዎች በመናገር ላይ ናቸው፡፡ በአስተያየት ሰጪዎቹ ግምት በጅቡቲ ላይ ጦርነት መክፈት ወይም ማተራመስ ወይም ማስጋት ሁለት ምክንያቶች ይኖሩታል፡፡ ዋነኛው የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ መስበር አድርጋ ስለምትወስደው ነው፡፡ ኢትዮጵያ ነዳጅም ይሁን የሸቀጥ ኬሚካል፣ እቃዎችን የምታስገባውና የወደብ አገልግሎት የምታገኘው ከጅቡቲ ነው፡፡ የደረቅ ወደብ፣ የመንገድ ግንባታ የተደረገው ከጅቡቲ ጋር ለመገናኘት ነው፡፡ ባለፈው የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅት መቶ በመቶ የጦርነት ቁሳቁሷን ያስገባችው በጅቡቲ በኩል መሆኑ አይዘነጋም፡፡ ከዚያም ወዲህ ሌሎቹንም ሸቀጦች በጅቡቲ በኩል ሲገቡ ቆይተዋል፡፡ ስለዚህ ኤርትራ በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት የምታነሳ ከሆነ ኢኮኖሚያዊ ጥቅሟን መቁረጥ ያስፈልጋታል፡፡ ኢኮኖሚያዊ አቅሟን ለመስበር ደግሞ ጅቡቲን ጦርነት ውስጥ በመክተት ወይም ሰላም በማሳጣት የወደብ አገልግሎትን ጨርሶ ማስቀረት ባይቻል እንኳ ለመቀነስ ፍላጎቷ ነው፡፡ ሌላው ምክንያት ኤርትራ በደቡብና በምስራቅ በኩል ከኢትዮጵያ ጋር የምትገጥም ከሆነ ከጅቡቲ አዲስ አበባ ያለውን መንገድ ለመቁረጥ የጅቡቲ ሰሜናዊ አካባቢዎች መቆጣጠር ሊያስፈልጋት ችሎ ይሆናል፡፡ ይኸ እንግዲህ በኤርትራ በኩል ያለው ግምት እንጂ በኢትዮጵያ በኩል የራሷን ስትራቴጂ እንደምትጠቀም የታወቀ ነው፡፡ በኤርትራና በጅቡቲ መካከል በድንበር ምክንያት በተነሳ ጦርነት፣ ፈረንሳይ ጅቡቲን እየረዳች እንደሆነ ምንጮች ጠቆመዋል፡፡ የፈረንሳይ ወታደራዊ ባለሥልጣን ዱክሬት በጅቡቲ መንግሥት የዜና ወኪል የተናገሩት ዋቢ አድርጎ ቢቢሲ እንደዘገበው “ፀቡ ከተጀመረ ጀምሮ፣ በጅቡቲ የሰፈሩ የፈረንሳይ ኃይሎቻችን በሎጂስቲክና በህክምና እርዳታና በመረጃ የጅቡቲ ወታደሮች እየረዳ ነው” ብለዋል፡፡ የአፍሪካ መንግሥት ስቴት ዲፓርትመንት ኤርትራ የፈፀመችውን ወረራ በማውገዝ ሁለቱም አገሮች ወታደሮቻቸው ከድንበሩ እንዲሰበሰቡና ወደነበሩበት እንዲመለሱ አቅርበዋል፡፡ ኤርትራ በበኩሏ የአሜሪካን ውንጀላ በቁጣ በማስተባበል በቀጠናው እየተፈጠረ ላለለው አለመረጋጋት ወንጅላለች፡፡ ባለፈው ሐሙስ የኤርትራ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ፣ “አሳዛኙና ግልፅ የሆነው ሐቅ በቀጠናው የአሜሪካ የጣልቃ ገብነት ፖሊሲ ግጭቶች እንዲበራከቱና እንዲጋነኑ መንስዔ ነው” ብሏል፡፡ ጅቡቲ ምንም እንኳ አነስተኛ ሃገር ናት ብትባልም በጥቅም ያሰረቻቸው ሃገሮች ብዙ ናቸው፡፡ ስለዚህ ከጀርባዋ የተሰለፉላት ብዙ ናቸው፡፡ አንዳንዶች ምንም እንኳ “ጋሻ መከታዬ” ሃገሮች ቢኖሩም ኩዌት በኢራቅ የተወረረችበትን ሁኔታ በማስታወስ “አንድ ቀን ኤርትራ ከተማ ብትገባስ?” የሚል ጥያቄ ያነሳሉ፡፡ ነገር ግን ኤርትራ ራሷ በውጥረትና በችግር ያለች በመሆኗ እንደተለመደው “ዜና መሠራት” ካልሆነ ከዚያ በላይ ለመድፈር ትችላለች ተብሎ አይገመትም፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን ጅቡቲና ኤርትራ ጦርነት ውስጥ ገብተዋል፡፡ ኘሬዚዳንት ጊሌ “ሁለቱ ሃገሮች በጦርነት ውስጥ ናቸው ማለት ነው?” ተብለው ሲጠየቁ “በእርግጥ አዎ!” ሲሉ የመለሱትም ይኸንኑ ለማረጋገጥ ነው፡፡ የጅቡቲ ችግር የአፍሪካ ቀንድ ችግር ነው የኢጋድ አባል ሃገሮች ችግር ነው፡፡ የአፍሪካ ሕብረትም ችግር ነው፡፡ ስለዚህም ሁሉም የራሳቸውን አፋጣኝ ምላሽ ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |