| በየዓመቱ 8 መቶ ሺህ የሚደርሱ... |
|
|
| Sunday, 15 June 2008 | |
|
በየዓመቱ 8 መቶ ሺህ የሚደርሱ ሰዎች ህገወጥ ዝውውር ያደርጋሉ
በጋዜጣው ሪፖርተር የሰዎች ህገወጥ ዝውውር በአለማቀፍ ደረጃ ችግር እያስከተለ ሲሆን በየዓመቱም ወደ 8መቶ ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ከቀያቸው ህገወጥ በሆነ መንገድ ይዘዋወራሉ፡፡ በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ በሴኔ መጀመሪያ የተለቀቀውን የ2008 የሰዎች ህገወጥ ዝውውር ሪፖርት ጠቅሶ በሳምንታዊ እትሙ እንደዘገበው ይህ ቁጥር በዛው በትውልድ አገራቸው ሆነው ከቦታ ቦታ በራሳቸውም ሆነ በህገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ከቀያቸው የሚወጡትን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አይጨምርም፡፡ በሪፖርቱ እንደተጠቀሰው ኢትዮጵያ ወንድ፣ ሴትና ህፃናት መንገድ የሚዘዋወሩባት አገር ስትሆን ሰዎቹም ለግዳጅ የጉልበትና ለፆታ ንግድ ሥራ ብዝበዛ የተጋለጡ ናቸው፡፡ ከገጠሪቱ የአገሪቱ ክፍል ህፃናትና ወጣቶች ወደ ከተማ ይዘዋወራሉ፡፡ በአብዛኛውም በቤት ውስጥ ሠራተኝነት ይሰማራሉ፡፡ ብዙ ጊዜም ባይሆን ለሴተኛ አዳሪነት የሚጋለጡም አሉ፡፡ በጎዳና ንግድ፣ በልመና፣ በሽመናና በግብርና ተሠማርተው የሚገኙ መኖራቸውንም ሪፖርቱ አትቷል፡፡ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ለቤት ውስጥ ሠራተኝነት ለማገልገል በመጀመሪያ ደረጃ ወደ ሊባኖስ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ዩናይትድ አረብ ኢምሬትስ፤ በማስከተልም ባህሪን፣ ጅቡቲ፣ ኩዌት፣ ሱዳን፣ ሶሪያና የመን ይዘዋወራሉ፡፡ ከአገራቸው በቤት ውስጥ ሠራተኝነት ስም ከተዘዋወሩት ውስጥም ወደ ሴተኛ አዳሪነት ሥራ የሚሰማሩ አሉ፡፡ በሌላ በኩል ሊባኖስ ከደረሱ በኋላ ወደ ቱርክ፣ ጣሊያንና ግሪክ የመዘዋወር እድል የሚያጋጥማቸውም መኖራቸው በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡ ቁጥራቸው ብዙ ባይሆንም ወንዶችም ወደ ሳዑዲ አረቢያና ባህረሰላጤ አካባቢ አገሮች በዝቅተኛ የጉልበት ሥራዎች ለመሰማራት ይዘዋወራሉ፡፡ እንደ ሪፖርቱ ከሆነ የኢትዮጵያ መንግሥት ዝውውሩን ለመግታት ዝቅተኛውን ደረጃ ያላሟላ ቢሆንም ጥረቶች ግን ይታያሉ፡፡ የህገወጥ ዝውውሩ ሃያላን በሚባሉት አገሮችም ችግር መፍጠሩ በሪፖርቱ የተጠቀሰ ሲሆን በአሜሪካ ብቻ በየዓመቱ ከ14 እሰከ 17 ሺህ 5 መቶ የሚደርሱ ሰዎች በህገወጥ መንገድ ወደ ግዛቲቱ በመግባት የችግሩ ሰለባ ናቸው፡፡ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኮንዶሊዛ ራይስ ሪፖርቱን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ ለህገወጥ ዝውውሩ መስፋፋት ምክንያት የሆነው የርካሽ ጉልበትና የጾታዊ ንግድ ሥራ አገልግሎት ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱ ነው፡፡ ሚኒስትሯ ራይስ በአይነቱ ዘመናዊ ባርነት የሆነውን የሰዎች ህገወጥ ዝውውር ለመግታት "መጀመሪያ መደረግ ያለበት የርካሽ ጉልበት ፍላጎትንና የጾታ ንግድ ሥራን ከመሰረቱ መግታት ነው" ብለዋል፡፡ አብዛኞቹ የአለማችን አገሮች የፆታ ንግድ ሥራን መሠረት አድርጎ የሚኖር ህገወጥ ዝውውርን ለመግታት አዘዋዋሪዎቹን በወንጀል እስከ መቅጣት የደረሱበት ደረጃ ቢኖርም አላግባብ የሰዎችን ጉልበት የሚበዘብዙት ላይ ግን ይሄ ነው የተባለ ርምጃ ሲወሰድ አይታይም፡፡ እንደ ሪፖርቱ ከሆነ የህጎች አለመፈፀም ለችግሩ መስፋፋት አንዱ ጋሬጣ ሲሆን በዘርፉ ዙሪያ የሚሰሩ አካላት ህግ የሚከበርበትን ሁኔታ ማጤን ይኖርባቸዋል፡፡ የግዳጅ ጉልበት ብዝበዛም ከሰዎች ህገወጥ ዝውውር ጋር ተያይዞ በሪፖርቱ የተካተተ ሌላው ጉዳይ ነው፡፡ በህገወጥ መንገድ ተዘዋውረው በፋብሪካ ውስጥ በርካሽ ጉልበት የሚሰሩ ሰዎች እንደ እስረኛ በማያወላዳ የፋብሪካ የአሰራር መዋቅሮች ተተብትበው ይገኛሉ፡፡ ከሰል በሚመረትባቸውና በስኳር ኢንዱስትሪዎች የግዳጅ ጉልበት ብዝበዛ ከሚከናወንባቸው ቦታዎች ተመድበዋል፡፡ በፋብሪካዎች ከሚኖር የግዳጅ ጉልበት ብዝበዛ በተጨማሪ ለቤት ውስጥ ሠራተኝነት በሚል ሰዎችን በህገወጥ መንገድ ማዘዋወርም በሪፖርቱ ተካትቷል፡፡ እንደ ፊሊፒንስ የመሣሠሉ አገራት በህገወጥ መንገድ ለቤት ሠራተኝነት የሚዘዋወሩ ሰዎችን ለመግታት እርምጃ እየወሰዱ ቢሆንም ችግሩ በአብዛኛዎቹ የዓለም ክፍሎች ተንሰራፍቶ ይገኛል፡፡ ችግሩ እንዲንሰራፋ ያደረገው ደግሞ "ሥራ እናስቀጥራለን" በሚል ምክንያት ሰዎችን ከየአገሩ እየመለመሉና ሙሉ ወጪያቸውን እየሸፈኑ ከአገር አገር የሚያዘዋውሩ ሰዎች መኖራቸው ነው፡፡ ይህ አይነቱ አሰራር "ተቀጣሪዎችን" በብድር አስሮ ስለሚይዝ በቀላሉ ለጉልበት ብዝበዛና ችግር ያጋልጣል፡፡ ሰዎችን ካሉበት ሥፍራ አፈናቅሎ በብድር ማሰርና ማሰራት አንዱ የህገወጥ ዝውውር መገለጫ ሲሆን በዚህ መልኩ "የተቀጠሩ" ሰዎችም እዳቸውን ለመክፈል ስለሚያቅታቸው መብታቸው ሳይከበርና ገንዘብ ሳይኖራቸው የግዞት ሕይወት ይኖራሉ፡፡ ሕፃናትን በውትድርና ማሰማራትም ህገወጥ ዝውውር ከሚገለጽባቸው አይነቶች አንዱ ሲሆን እንደ አለማቀፉ የሕፃናት መረጃ ድርጅት መረጃ ከ18 ዓመት በታች የሚገኙ ከ3 መቶ ሺህ ሕፃናት በአለማቀፍ ደረጃ ጦርነት በሚገኝባቸው ከ30 በሚበልጡ አገራት ተሰማርተው ይገኛሉ፡፡ አብዛኞቹ ሕፃናት ወታደሮች ከ15 እስከ 18 ባለው የእድሜ ክልል የሚገኙ ቢሆንም የ7 እና የ8 ዓመት ሕፃናትም በዘርፉ ተሰማርተዋል፡፡ ሕፃናትን ወደ ወታደርነቱ የማስገባቱ ሂደት ኃይልን መሠረት ያደረገ፣ ምልመላና ማታለልን ያካተተ ሲሆን ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች ሕፃናቱን ለወሲብ እስከመጠቀምም የዘለለ ነው፡፡ ሕፃናትን ተዋጊ ለማድረግ ከየአካባቢያቸው መጥለፍና ከተወሰዱም በኋላ በአብሳይነት፣ በስለላ፣ መልዕክት በማስተላለፍና እርስ በርስ እንዲጋቡ በማድረግ ገደብ የለሽ የጉልበት ብዝበዛ ይደረግባቸዋል፡፡ የሕፃናት ውትድርና በብዛት ተንሰራፍቶ የሚገኘውም በአፍሪካና በእሲያ ነው፡፡ ሆኖም በአሜሪካና በመካከለኛው ምስራቅ የሚገኙ ታጣቂዎች ሕፃናትን እንደሚጠቀሙ ሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡ በአለማቀፍ ደረጃ በየዓመቱ ከ2 ሚሊዮን ሕፃናት በላይም ለሴተኛ አዳሪነት ይዳረጋሉ፡፡ አብዛኛውም መሠረት ያደረገው ህገወጥ ዝውውር ላይ ነው፡፡ ፆታዊ ዝውውርና ሴተኛ አዳሪነት፣ የኃይልና የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ በፈቃደኝነት ላይ ያልተመሰረተ የቤት ሠራተኝነት፣ ስደተኞችን ያለፈቃዳቸው ጉልበታቸውን መበዝበዝና የሕፃናት የወሲብ ሽያጭ በአለማቀፍ ደረጃ እየተስፋፉ ያሉ የህገወጥ ዝውውር አይነተኛ መገለጫ ሆነዋል፡፡ የኤምባሲው ሳምንታዊ ሪፖርት እንዳተተው አሜሪካ የሰዎች ህገወጥ ዝውውርን ለመግታት አገራትን፣ አለማቀፍና አገር በቀል ድርጅቶችን በማሳተፍ ትሰራለች፡፡ እ.ኤ. በ2007 የአሜሪካ መንግሥት 79 ሚሊዮን ዶላር በማውጣት 180 ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለማስቆም ለሚሰሩ በ90 አገሮች የሚገኙ ፕሮጀክቶችን ረድቷል፡፡ ከ2001 ጀምሮ ደግሞ በአለማቀፍ ደረጃ 528 ሚሊዮን ዶላር በመመደብ ሲሰራ ቆይቷል፡፡ የሰዎች ህገወጥ ዝውውርን ለማስቀረት ሲቪል ማኅበረሰቡን፣ መንግሥታትንና አለማቀፍ ድርጅቶችን ያቀፈ "ተስፋ ያለው አለማቀፍ እንቅስቃሴ ይኖራል" በማለት የገለፁት ሚኒስትር ራይስ ናቸው፡፡ በ2008 የሰዎች ሕገወጥ ዝውውር ሪፖርት 170 አገራት ችግሩን ለመፍታት ያደረጉትን ጥረት ጨምሮ መደረግ ስላለባቸው እርምጃዎች የተካተተ ሲሆን ዓላማ ያደረገውም ዘመናዊው ባርነት ምን ያህል ችግር እየፈጠረ ለመሆኑ ግንዛቤ ለማስጨበጥና አገራት ችግሩን እንዲችሉ ለማበረታታት ነው፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |