| ከቤት ለቤት ደረቅ ቆሻሻ ሰብሳቢዎች... |
|
| Sunday, 13 January 2008 | |
|
ከቤት ለቤት ደረቅ ቆሻሻ ሰብሳቢዎች መካከል አብዛኞቹ ወንዶች ናቸው አዲስ አበባ ውስጥ በሶስት ክፍለ ከተሞች ከሚገኙ 15ሺ የቤት ለቤት ደረቅ ቆሻሻ ሰብሳቢዎች መካከል 65 ከመቶ ያህሉ ወንዶች ሲሆን 77.1 ከመቶ የሚሆኑት ደግሞ ዕድሜያቸው ከ35 ዓመት በታች ዕድሜ ላይ የሚገኙ ሴቶች እንደሚኖሩበት አንድ ጥናት አስታወቀ፡፡ በአዲስ ከተማ፣ በቂርቆስና በቦሌ ክፍለ ከተሞች በሚገኙ የቤት ለቤት ደረቅ ቆሻሻ ሰብሳቢዎች ላይ በዚህ ዓመት የተካሄደው ጥናት እንዳመለከተው 14.5 ከመቶ ያህሉ መሃይማን ሲሆኑ አብዛኞቹ ግን የመደበኛ ትምህርት ተከታትለዋል፡፡ ይህም ሁኔታ የሥራ ላይ ደህንነትና ጤንነት ሁኔታዎችን ለማሻሻል በሚካሄደው እንቅስቃሴ ላይ የጎላ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ጥናቱ አስታውቋል፡፡ ከዚህም ሌላ 53 በመቶ ያህሉ ያላገቡ፣ 28 ከመቶ ያገቡ፣ 16 ከመቶ የሚሆኑት ደግሞ አግብተው የፈቱ መሆናቸውን ጥናቱ ጠቁሞ 74.4 ከመቶ የሚሆኑት ደግሞ መጠለያ ቢጤ እንዳላቸው 25.6 ከመቶ የሚሆኑት ደግሞ ቤት አልባ መሆናቸውን አስረድቷል፡፡ እንዲሁም 56.6 ከመቶ የሚሆኑት በደረቅ ቆሻሻ አሰባሰብ ላይ ከመሰማራታቸው በፊት ምንም አይነት ሥራ ይዘው እንደማያውቁ፣ 90 ከመቶ የሚሆኑትም በደረቅ ቆሻሻ ሥራ ላይ ከተሰማሩ ሦስት ዓመት እንደሞላቸው ጥናቱ አመልክቷል፡፡ ጥናቱ በተከናወነበት ወቅት 54 ከመቶ ያህሉ ጊዜያዊ ቅጥር ሠራተኞች እንደነበሩ፣ ይህም ሁኔታ ቀጣሪዎች በአንድ አጋጣሚ ያለማስጠንቀቂያ ከሥራ ሊያባርሯቸው እንደሚችሉ፣ ከዚህም ሌላ 64 በመቶ ያህል የአገሪቱን የደመወዝ ክፍያ አስመልክቶ በሕግ ከተደነገገው በታች 150 ብር በየወሩ ደመወዝ እንደሚከፈላቸው፣ ከእነዚህም መካከል 63 ከመቶ የሚሆኑት ደረቅ ቆሻሻን እርስ በርስ በመሸጥ ኑሯቸውን እንደሚደጉሙ ታውቋል፡፡ አንድ ደረቅ ቆሻሻ ሰብሳቢ በቀን ውስጥ የ32 ደምበኞች ደረቅ ቆሻሻ ይሰበስባል፡፡ ይህም እንደ የቀበሌው ሁኔታ ይለያያል፡፡ ሰዎቹ ደረቅ ቆሻሻ የሚሰበስቡት ከመኖሪያ ቤቶች ከሬስቶራንቶች፣ ከውበት ሳሎኖች፣ ከፀጉር ማስተካከያ ቤቶች፣ ከፎቶ ስቱዲዮዎች፣ ከተሽከርካሪ ጋራዦችና ክሊኒኮች ነው፡፡ ለአገልግሎታቸው በየወሩ የሚያስከፍሉትም በድርድር ከአንድ እስከ አሥር ብር ሲሆን ደህና ገቢ ያላቸው ቤተሰቦች ከፍተኛውን ሲከፍሉ ንግድ ተቋማት ደግሞ በወር እስከ 55 ብር ያሰከፍላሉ፡፡ የግል ንጽህናን በተመለከተ 37 ከመቶ የሚሆኑት ደረቅ ቆሻሻ በሚሰበስቡበት ወቅት እንደሚታጠቡ፣ የእነዚህ እኩሌታዎች ደግሞ ሥራቸውን ካጠናቀቁ በኋላ እጃቸውንና ፊታቸውን በውሃና በሳሙና እንደሚታጠቡ፣ 24 ከመቶ የሚሆት በየሁለት ወራት ወደ ሕክምና ተቋም እየሄዱ አስፈላጊውን ሕክምና እንደሚያገኙ፣ ከፍተኛው ሕመም ጉንፋንና ሳል፣ ተቅማጥና የሆድ ቁርጠት፣ የቆዳ መቆጣት፣ የቁስል መቆረጥ፣ መሆናቸውን ጥናቱ ያሳያል፡፡ ይህንኑ ጥናት የዓለም የሥራ ድርጅት የምስራቃዊ አፍሪካ ክፍለ አህጉራዊ ጽህፈት ቤት በኢትዮጵያና በአዲስ አበባ አስተዳደር የጽዳት፡ ውበትና መናፈሻ ልማት ኤጀንሲ ናቸው፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |