| ጅቡቲ በተከላካይነት ጎዳና |
|
|
| Wednesday, 18 June 2008 | |
|
ከሃብታሙ በቀለ
ምንም እንኳ ጦርነቱ ቢቆምም ፍጥጫው እጅግ ባየለበት የጅቡቲና የኤርትራ ወሰን ላይ አሁንም ጥይቶች እንደተቀባበሉ ናቸው፡፡ ጦርነቱ ቢቀዘቅዝም ውጥረቱ ግን እንዳለ መሆኑን ጅቡቲ ተናግራለች፡፡ የጦር ጓደኞቹዋም ጥሪዋን የተቀበሉላት ይመስላሉ፡፡ የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ በበኩላቸው ውጥረቱን በውይይት እንዲፈቱ የመከሩዋቸውን የየመኑን ፕሬዚዳንት “ወግድልኝ” ብለዋቸዋል፡፡ “ኤርትራ ከጅቡቲ ጋር ለመነጋገር አትፈልግም፡፡” የየመኑ ፕሬዚዳንት አሊ አብደላህ ሳላህ፣ የጅቡቲንና የኤርትራን ችግር እንዳሰሙ፣ መሪዎቹ በመካከላቸው የተፈጠረውን የወሰን ግጭት በውይይት እንዲፈቱ መክረው ነበር፡፡ ፕሬዚዳንት ሳላህ ከጅቡቲው አቻቸው እስማኤል ጊሌ ጋር ባደረጉት የስልክ ውይይት፣ በኤርትራና በጅቡቲ መካከል ስላለው ፀብና የጅቡቲን አቋም ተነግሯቸዋል፡፡ ከኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ ጋርም ከጅቡቲ ጋር ስላላቸው የወሰን ፀብ እየተደረገ ስላለው ግጭት በስልክ ጠይቀዋል፡፡ የየመኑ ፕሬዚዳንት፣ የኤርትራው ኢሳይያስ ከጅቡቲ ጋር ያላቸውን ግንኙነት፣ በውይይት በግንዛቤና ማንኛውንም ግጭት ባስወገደ መልኩ ማድረግ እንዳለባቸው ያላቸውን እምነት ገልፀውላቸዋል፡፡ በሁለቱ ሃገሮች መካከል ግጭት መነሳቱ ለሰላማቸውና ለፀጥታቸው መረጋጋት የማይበጅ መሆኑና ለአካባቢው ሃገራት ሰላምም ጠንቅ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ አዥንስ ፍራንስ ፕሬስ ትላንት እንደዘገበው ከሆነ ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ የየመኑን ፕሬዚዳንት ማግባቢያ አልተቀበሉትም፡፡ ከጅቡቲ ጋር በምንም አይነት መንገድ ውይይት አስፈላጊ አይደለም የሚል አቋማቸውን በስልክ ምልልሳቸው ወቅት ነግረዋቸዋል፡፡ “የተፈበረከውን ችግር የባሰ በሚያቀጣጥለው የወቅቱ የዲፕሎማቲክና የመገናኛ ብዙሃን እሰጥ አገባ የመግባት ፍላጎት የለንም”፡፡ ይኸ እንዲህ እንዳለ ጅቡቲ የጦርነት ዝግጅቷን እያደረጃች መሆኑን የተለያዩ ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡ አንድ የጅቡቲ ከፍተኛ ባለሥልጣን በክተት የተሰማራውን የጅቡቲ ጦር ግንባር ድረስ ሄደው ሲጎበኙ በጅቡቲ ቴሌቪዥን ተላልፏል፡፡ የፈረንሳይ ጦር መርከብ ወደ ራስዱሜራ የቀይ ባህር ጠረፍ እየተጠጋ መሆኑን ጅቡቲ መግለጫ ሰጥታለች፡፡ “ፈረንሳይ፣ በሚቀጥሉት ቀናት ሰራዊታችን በተጠንቀቅ ወደቆመበት ራስ ዱሜራ የጦር መርከቦቿን ታስጠጋለች” ሲሉ የጅቡቲው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መሐመድ አሊ የሱፍ ለሪፖርተሮች አረጋግጠዋል፡፡ ፓሪስ ያለው የመከላከያ ሚኒስቴር እንደገለፀው ከሆነ፣ በአካባቢው ሦስት የጦር መርከቦች የሚገኙ ሲሆን ወደጅቡቲ የባህር ጠረፍ የተጠጉት ሁለቱ የጦር መርከቦች ሄሊኮፕተር ተሸካሚዎች ናቸው፡፡ ጅቡቲ ነፃነቷን ካገኘችበት 1970 ጀምሮ ከፈረንሳይ የጋራ መከላከያ ውል ያላት ሲሆን ፈረንሳይም በአካባቢው ታላቅ የሚባል ወታደራዊ ቤዝ ጅቡቲ ውስጥ ሰርታለች፡፡ ጅቡቲ የጦር ጓደኞቿን ትብብር በአንድ በኩል እያረጋገጠች በሌላ በኩል የራሷን ከ11”000 የማይበልጡ ወታደሮች የውጊያ መስመር እያስያዘች መሆኗ ተዘግቧል፡፡ በባህር በኩል በፈረንሳይም ፍፁም መተማመን ያላት ጅቡቲ ነገሩ እየገፋ ከሄደ ፈረንሳይ በምድር ጭምር ወታደሮቿን እንደምታሰልፍ አረጋግጣለች፡፡ ፈረንሳይ እስካሁን በስንቅና ትጥቅ አቅርቦትና መረጃ በመቀበል ተወስና ብትቆይም አስፈላጊ ከሆነ ጦርቱን ለመሳተፍ እንደማትመለስ ገልፃለች፡፡ “ለኤርትራ መንግሥት የላክነው መልዕክት ኤርትራ ለአዲስ ወረራ ከተዘጋጀት ምላሹ ከባድ እንደሚሆን በበቂ ሁኔታ እንድትረዳ ያስችላታል” ይላሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዮሱፍ፡፡ አሜሪካም ሽብርተኝነት ለመዋጋት መንቀሳቀስ ከጀመረች ወዲህ በጅቡቲ የጦር ካምፕ መስርታለች፡፡ የኤርትራው ወረራ ከተሰማ ወዲህ ሚኒፖሊስ ከሚገኘው የጦር ካምፑዋ 200 የባህር ወለድ ወታደሮቿን ወደ ጅቡቲ መላኳን WCCO COM ከሥፍራው ዘግቧል፡፡ የባህር ወለዶቹ ከሰሜን ካሮላይና ከሚገኘው ካምፕ በትላንትናው ዕለት እንደሚነሱም ጨምሮ ዘግቧል፡፡ ወታደሮቹ ለሚቀጥሉት ሰባት ወሮች በጅቡቲ ይቆያሉ፡፡ ሌሎች 100 ወታደሮችም ከሜኔስታ ካምፕ ተነስተው እንደሚቀላቀሉ ተገል”ል፡፡ “ግራ ተጋብቼ ነበር፣ እስከ መጨረሻው ድረስ ወዴት እንደምሄድ አላወቅሁም ነበር” ይላል ማሪን የአስር አለቃ ማቲው ሆልሰን፡፡ “ከአራት አምስት ወራት በፊት ወደ ኢራቅ እንድንሄድ ነበር የተዘጋጀነው፡፡ ግን ሁኔታዎች ተለወጡ፡፡” ይላል ወደ ጅቡቲ ከተላኩት ወታደሮች አንደኛው ሃምሳ አለቃ ቪንሰት ሬይኖልድስ፡፡ እነዚህ ወታደሮች የተላኩት ከኤርትራ የጅቡቲ ወረራ ምክንያት አድርገው መሆኑ ባይገለፅም በድንገት አቅጣጫ እንዲለውጡ መደረጉ አሜሪካ ጅቡቲን ለመርዳት ይሆናል የሚል አስተያየት ተሰጥቶበታል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |