| ኢፍዴኃግ በአገሪቱ ወቅታዊ ችግሮች... |
|
|
| Wednesday, 18 June 2008 | |
![]() የግንባሩ ሊቀመንበር አቶ ግርማይ ሃደራ በየማነ ናግሽ የኢትዮጵያ ፍትህና ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች ግንባር (ኢፍዴኃግ) በኢትዮ-ሱዳን ድንበር፣ በኑሮ ውድነትና በረሃብ መባባስና በግጭቶች መስፋፋት አስመልክቶ ባለፈው እሁድ በፅህፈት ቤቱ በሰጠው መግለጫ ኢህአዴግን ተቸ፡፡ በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል ያለውን ድንበር መካለል በማስመልከት ጠቅላይ ሚኒስትር ለተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡት ሪፖርትና የአካባቢው ተወካዮች የተገለፀው የተራራቀ ሆነው መገኘት አሳሳቢ እንደሆነ የግንባሩ መግለጫ ያስረዳል፡፡ በአካባቢው ከድንበሩ ጋር በተያያዘ 17 ሰዎች እንደተገደሉ፣ ከ8ዐ በላይ የደረሱበት እንደማይታወቅ፣ 28ቶቹ እንደታሰሩና 26ዐዐ ገበሬዎች ከመሬታቸው እንደተፈናቀሉ የአካባቢው ሕዝብ ተወካዮች መግለጫ እንደሚያስረዳ የግንባሩ ሊቀመንበር አቶ ግርማይ ሃደራ ተናግረዋል፡፡ የዜጐችን ብሔራዊ መብትና ደህንነት በማስከበር ረገድ በመንግሥት በበላይ ባለሥልጣን በኩል የተሰጠው የማስተባበያ ምላሽ አግባብ እንዳልሆነ ተገልጿል፡፡ ከኢትዮጵያም ሆነ ከሱዳን ድንበር አልፈው መሬት የያዙ ነዋሪዎች ምንም ዓይነት መፈናቀል አያጋጥማቸውም ተብሎ የተገለጸው ሌላው አነጋጋሪ ጉዳይ ሆኖ ተገኝቷል ብለዋል፡፡ የሱዳን መሬት ገብተው ቦታ ያዙ የተባሉት ኢትዮጵያውያን ዜግነታቸው የማን ሆኖ ነው በያዙት ሥፍራ ላይ የሚረጉት፣ እስከ መቼስ በዚህ ዓይነት ሁኔታ ሊቀጥሉ ይችላሉ በማለት ግልፅነት የጎደለው የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር ተችተዋል፡፡ “ኢትዮጵያ በታሪኳ ከራስዋ መሬት ቅንጣት ያህል ለሌላ አሳልፋ የማትሰጥ፣ የሌላውንም እንደማትፈልግ አጐራባች አገሮችም ጠንቅቀው የሚረዱት ነው፡፡ በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል የሚካሄድ የድንበር ማካለል ሥራም ይህንኑ ፈለግ ተከትሎ የሚፈጸም መሆን ይገባል” ይላይ የግንባሩ መግለጫ፡፡ በስደት በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ላይ የሚፈፀም በደልን አስመልክቶ መግለጫው እንዳመለከተው በአፍሪካም በመካከለኛው ምስራቅ አገሮች ውስጥ ኢትዮጵያውያን ላይ አስከፊ የሆነ በደልና እንግልት እየደረሰባቸው መሆኑ በልዩ ልዩ የዜና ማሰራጫዎች እየተገለፀ ቢሆንም በመንግሥት በኩል የዜጐችን ደህንነትና ብሔራዊ መብት በማስጠበቅ ረገድ የተወሰደ እርምጃ እንደሌለ ድርጅቱ ተችቷል፡፡ “የኑሮ ውድነትና አስከፊው የድርቅ ሁኔታ እጅጉን እየገዘፈ በመምጣት ላይ ስለሆነ ሁሉም አካላትና የአገሪቱ ዜጐች በየተሰለፍንበት መስክ ተረባርበን ሂደቱን የመግታት ኃላፊነት ይኖርብናል” የሚለው የድርጅቱ መግለጫ፣ ጉዳዩ የመልካም አስተዳደር እጦት የአየር መዛባት ካስከተለው ድርቅ ጋር ተዳምሮ በሕዝብ ላይ ያንዣበበውን አደገኛ ችግር ለመቋቋም በጋራ መነሳሳት እንደሚገባ ጠይቀዋል፡፡ የእርስ በእርስ ግጭቶችና ያስከተሉትን ጉዳት በተመለከተም ሰላም፤ የውስጥ ሰላምን መገንባት ከምንም በላይ ከፍተኛ ግምት ሊሰጠው የሚገባ አብይ ተግባር እንደሆነ ይገልፃል፡፡ “አንዱ ብሔር ከሌላው፣ አንዱ ጐሳ ከሌላኛው ጋር በየወቅቱ የማያባራ ግጭት የሚፈጥር ከሆነ የሰላሞች ሁሉ መሰረት የሆነ የውስጥ ሰላም ክፉኛ ሊጐዳ እንደሚችል መታመን አለበት”፡፡ እንደነዚህ ያሉ ችግሮች የሚዘወተርባቸው አካባቢዎችን ባህሪያቸውንም እያጠና በቂ የሰላም መጠበቂያ ቅድመ ዝግጅቶችን ማድረግ እንደሚያስፈልግ የግንባሩ ሊቀመንበር አቶ ግርማይ ሃደራ ተናግረዋል፡፡ “በተለይም በደቡብ ኢትዮጵያ የውስጥ ግጭት በተከሰተ ጊዜ ብቻ እሳት የማጥፋት እርምጃ ለመውሰድ ከመሞከር ይልቅ ችግሩ እንዳይፈጠር የማድረግ ዝግጅት ማድረግ በጣም ወሳኝነት ይኖረዋል”፡፡ በሕዝቦች መካከል መቼ፣ እንዴት እና በምን ምክንያት ወይም ሁኔታ ላይ ተመርኩዞ ግጭት ሊነሳ እንደሚችል በላቀ ጥንቃቄ እየተጣራ የግጭቶችን ምንጭ መጥፋት የየክልል መንግሥታት ኃላፊነት መሆኑንም አመላክቷል፡፡ እንደ የግንባሩ መግለጫ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ በቦረና እና በኮንሶ ብሔረሰቦች መካከል በቅርቡ በተከሰተው ብጥብጥ 42 ሰዎች ሕይወታቸውን ሲያጡ 7400 የሚሆኑ ደግሞ ከኑሮአቸው ተፈናቅለዋል፡፡ በምዕራብ ወለጋም አንገር 4 እና አንገር 8 በተባሉ ቀበሌዎች ነዋሪ በሆኑ የሕብረተሰብ አባላት መካከል በተቀሰቀሰው አለመግባባት የብዙዎች ሕይወት እንደጠፋ የመፈናቀልና ንብረትንም የመዝረፍ ችግር እንዳጋጠማቸው ይገልፃል፡፡ ከግንቦት 9 እስከ ግንቦት 22 2ዐዐዐ ዓ.ም. ድረስ በመሬት ይገባኛል ጥያቄ ምክንያት በቤንሻንጉል ጉምዝና በወለጋ ሕዝቦች መካከል በ1ዐ ቀበሌዎች በተነሳው አለመግባባት በመቶዎች የሚቆጠሩ እንደሞቱ፣ በርካቶች እንደቆሰሉ ከኑሮአቸው እንደተፈናቀሉ፣ ቤቶች እና የእህል ጐተራዎች እንደተቃጠሉ እንዲሁም በርካታ ከብቶች እንደሞቱ ከመግለጫው ለማወቅ ተችሏል፡፡ ችግሩን የመፍታት ኃላፊነት የተጣለባቸው አንዱን ወገን ጠቅመው ሌላውን የመጉዳት ድብቅ ፍላጐት ያላቸው መሆኑና “በዚህ አስነዋሪ አስተሳሰብ የተበከሉ ግለሰቦች እየቀበሩት የሚያቆዩት የግጭት ፈንጂ እየፈነዳ ሕዝቦችን ክፉኛ እየጐዳ የሚሄድ መሆኑ” የሚታይበት ሁኔታ እንዳለ ከመግለጫው መረዳት ተችሏል፡፡ አገሪቱን ወደ ከፋ ሁኔታ እየከተተ ያለው የኑሮ ውድነት፣ ንረት ከጀመረ ዓመታት ያስቆጠረ ቢሆንም ሁልጊዜ ስለ እድገት እየተወራ፣ ህዝብን እያሰቃየ ስላለው ችግር ብዙ ትኩረት አለማግኘቱ አግባብነት የለውም ሲሉ የድርጅቱ ሊቀመንበር መንግሥትን ተችተዋል፡፡ የምግብ እህል እጥረት የዋጋ ንረቱና የነዳጅ ዋጋ መጨመር ያስከተሉዋቸው ችግሮች የብር የመግዛት አቅም ማሽቆልቆልና ያስከተለውን የገበያ ቀውስ ለማረጋጋት የተወሰደው እርምጃ አመርቂ አለመሆኑ በመግለጫው ተገልፀዋል፡፡ በመንግሥት “ተወሰዱ የተባሉ” እርምጃዎችም ዘለቄታ ያላቸው መፍትሄ ባለመሆናቸው በድርጅቱ ተቀባይነት የላቸውም፡፡ መንግሥት በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ለተከሰተው የድርቅ ሁኔታ በቂ ትኩረት አለማድረጉንም በማስመልከት ግንባሩ ወቅሷል፡፡ “የተከሰተውን የረሃብ ሁኔታና ችግር አምኖ ከመቀበል እና ተገቢ መፍትሄ ከማፈላለግ ይልቅ ለመሸፋፈን ጥረት ሲያደርግ ይታያል” ይላል መግለጫው፡፡ ግንባሩ በሰጠው መግለጫው ላይ ከጋዜጠኞች ለቀረቡለት ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ኢትዮ-ሱዳንን በተመለከተ የመረጃቸው ተአማኒነት ላይ ጥያቄ ቀርቦላቸው፣ የመረጃቸው ምንጭ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች፣ የአካባቢው ተወላጆች፣ በተለይ ደግሞ የፓርላማ አባላት በአካባቢው የተፈጠረው ወረራና መፈናቀል ማረጋገጣቸው የግንባሩ ሊቀመንበር አቶ ግርማይ አስረድተዋል፡፡ የግንባሩ ዋና ፀሐፊ አቶ ገረሱ ገሳ በበኩላቸው ከሱዳን ድንበር ወደ ኢትዮጵያ 5 ኪ.ሜ ገባ ብሎ ደላሎ በሚባል አካባቢ የእስራኤል ዜግነት ላላቸው ሦስት ኢንቨስተሮች መሬት ተሰጥቷቸው ወደ ሥራ ከተሰማሩ በኋላ መነሳታቸውና ከ3 ማሊዮን ብር በላይ መክሰራቸው፣ ኘላን ኮፒም በእጃቸው ጭምር እንዳለ ለሪፖርተር ጋዜጣ ተናግረዋል፡፡ እንዲሁም ዘመድ የታሰረባቸውና የተፈናቀሉ ሰዎችን በአካል አግኝተው ማናገራቸውን አቶ ገረሱ አብራርተዋል፡፡ እስከ 2 ሚሊዮን የሱዳን ፓውንድ ተቀጥተው “ወገን እርዳን” የሚሉ ዜጎች እንዳሉ ከአካባቢው ተወላጆች (የፓርላማ አባላት) ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል፡፡ “የዚህ መንግሥት አሰራር ድብቅ ነው” የሚሉት አቶ ገረሱ፣ ጉዳዩ በሚዲያዎች ባይወጣና እንደዛ አልቆ ቢሆን ኖሮ ምን ይሆን እንደነበር በምሬት ጠይቀዋል፡፡ “ይሄ መንግሥት የአገር ሉአላዊነት በብቃት መጠበቅ አልቻለም፡፡ በአገር ጉዳይ የሚሰራው ሁሉ ለህዝብ ማሳወቅና መጠየቅ አለበት” ብለዋል፡፡ አቶ ግርማይ የወቅቱ ሁኔታዎች አስመልክተው፣ “ሁሉም ነገር ድብብቆሽ ሆኗል፣ ሳናድግ አደግን ይባላል፣ ሚዲያው የሚያወራው የኢህአዴግ ዕድገት ብቻ ነው፣ ነገ መውደቂያችን የት ላይ እንደሚሆን አይታወቅም” በማለት ኢትዮጵያ ያለችበት የመንግሥት ሚዲያዎች ከሚያቀርቡት መረጃ በተቃራኒ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ያለንበት ሁኔታ “አምስት ሰዎች ሰክረው፣ አምስት ሚሊዮን ህዝብ እራት የማይበላበት ነው” ብለዋል፡፡ በውጭ የሚኖሩ ዜጎች በተመለከተም፣ “በተለያዩ አገራት ያሉት የመንግሥት ዲኘሎማቶች ብር መሰብሰብና የፖለቲካ ሥራ መስራት እንጂ ለዜጎች ደህንነት ግድ የላቸውም” በማለት መንግሥት በዜጎቹ ላይ ያለውን ግድ የለሽነት ወቅሰዋል፡፡ ለኑሮ ውድነቱ አማራጭ መፍትሄ ካላቸው ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፣ የምግብ እህል አቅርቦት መጨመር ተከታታይነት እንዲኖረው፣ በየአካባቢው እንደባህሉና የአኗኗሩ ዘዴ ተጠንቶ ለችግሩ አፋጣኝና ዘላቂ መፍትሄ እንደሚያስፈልግ የግንባሩ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ተክሌ ቦረና ገልፀዋል፡፡ እንደ ግንባሩ ከሆነ መንግሥት የሀገርን የውስጥና የውጭ ደህንነት የማስጠበቅ፣ የሀገርና የሕዝብ ሉአላዊነት የማስከበርና በሕዝብ ላይ የሚደርሱ ልዩ ልዩ ችግሮችን የመከላከልና የማስወገድ ኃላፊነትና ግዴታ ያለበት አካል ቢሆንም ችግሩን እንዳላየና እንዳልሰማ ሆኖ ማለፍ ከአንድ ለአገርና ለሕዝብ ክብርና ሉአላዊነት ቆሜለሁ ከሚል መንግሥት የሚጠበቅ አይደለም፡፡ መንግሥት ከሕዝብ ጋር በመሆን ለችግሮች አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስድ፣ በሱዳን በኩል በድንበር አከላለል ምክንያት የተፈናቀሉና የተሰደዱ ዜጐች በአስቸኳይ ወደ ቀድሞ ቦታቸው እንዲመለሱ፣ በሱዳን መንግሥት የታሰሩ የኢትዮጵያ ዜጎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በነፃ እንዲለቀቁ፣ የደረሱበት ሳይታወቅ የቀሩ ዜጎችም ጉዳይ ተጣርቶ ትክክለኛው መረጃ ለሕዝብ እንዲገለፅ በመጠየቅ በሁለቱ ሀገሮች መካከል ያለው የድንበር አከላለልም እንግሊዝ ሱዳንን ከመያዟ በፊት የነበረውን የድንበር ሁኔታንም ከግንዛቤ ያስገባ ጥልቅ ጥናት ተደርጎ እንዲከናወን የሳስበዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የተፈጠረውን የኑሮ ውድነትና የምግብ ሸቀጦች የዋጋ ንረት ለማረጋጋት መንግሥት በተለይም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኘው ሕዝብ ችግር ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ አስቸኳይ መፍትሔ እንዲፈልግና ለጉዳዩ ልዩ ክብደት እንዲሰጥ፣ በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰተውን የርሃብ ችግር ከመሸፋፈን ይልቅ አፋጣኝ የሆነ መፍትሔ እንዲፈልግና ሕዝቡን ከጉዳት እንዲታደግ፣ በተለያየ ምክንያት ወደ ውጪ ሀገራት የሚሄዱ ዜጎች በየሄዱበት ቦታ አደጋና ችግር ሲያጋጥማቸው መንግሥት ከጎናቸው እንዲቆምና እንዲደርስ መግለጫው ጠይቋል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |