Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version

Friday
Nov 21st
Home arrow Sections arrow የሰብዓዊ መብት ወሬው ቀላል፤ ተግባሩ ግን ከባድ
የሰብዓዊ መብት ወሬው ቀላል፤ ተግባሩ ግን ከባድ E-mail
Sunday, 13 January 2008
ሰብዓዊ መብቶችን የማክበር፣ የማስከበርና የመጠበቅ ሂደት ረጅም ጊዜና ቁርጠኝነትን እንደሚጠይቅ፣ የስኬት መለኪያውም በየጊዜው የሚመዘገበው/ የሚታየው የመሻሻል ሁኔታ መሆኑን አንድ የሕግ አማካሪና ጠበቃ ሲገልፁ፣ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቃቤ ሕግ ደግሞ መንግስታዊ እቅዶች የሕዝቡን ግንዛቤ ለማሳደግ፣ ፍርሃቶቹንና ስጋቶቹን ለመረዳት፣ ተነሳሽነቱን ለማጎልበት በሚያስችል መልኩ ካልተቀረፁ በስተቀር ለሰብዓዊ መብቶች አከባበር ዋስትና የሆነውን የዴሞክራሲ ስርዓት የመገንባቱ ጥረት ውጤታማ እንደማይሆን አስታወቁ፡፡

የሕግ አማካሪው አቶ ገብረአምላክ ገብረጊዮርጊስና አቃቤ ሕጉ አቶ ሽመልስ ከማል ይህንን ያመለከቱት ..ሰብዓዊ መብትን በማክበርና በማስከበር ረገድ የመገናኛ ብዙሃን ሚና.. በሚል ርዕስ ለጋዜጠኞች በአዳማ ከተማ ከታህሳስ 25 ቀን 2000 ጀምሮ ለሁለት ቀናት ያህል በተሰጠው የሥልጠና ፕሮግራም ላይ በየተራ ባቀረቡት የጥናት ጽሁፍ ላይ ነው፡፡

ከጽሁፉ አቅራቢዎች መካከል አቶ ገብረአምላክ እንዳመለከቱት፣ ሰብዓዊ መብቶችን የማክበርና የመጠበቅ ሂደት በአጭር ጉዞ ብዙ መውደቅና መነሳትን ያስከትላል፡፡ ፈታኝና ተስፋ አስቆራጭም ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ሁልጊዜ  የወደፊት ብሩህ ተስፋ እየታየ የሚከናወንና ወደ ተሻለ ደረጃ ለመድረስ የሚደረግ ትግል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የሰብዓዊ መብቶችን በመጠበቅ፣ በማስፋፋትና በማስፈፀም ረገድ የተጣለባቸውን ኃላፊነትና ግዴታ በቅንነት ሊወጡ እንደሚገባ አቶ ገብረአምላክ አሳስበዋል፡፡ በዚህም ሂደት ላይ በፌደራልና በክልል ደረጃ የሚገኙ የሕግ አውጪ፣ ሕግ አስፈፃሚና የዳኝነት አካላት ከጎናቸው ሊሰለፉ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

ገደብ ሊጣልባቸው የሚችሉና ፍፁም የማይነኩና የማይገደቡ ሰብዓዊ መብቶች እንዳሉ መታወቅ ይኖርበታል ያሉት አቶ ገብረአምላክ ገደብ የሚጣልባቸውም የአገር ሉዓላዊነት በአደጋ ወይም በጦርነት ላይ በሚሆንበት ጊዜ በአስቸኳይ ጊዜያዊ አዋጅ አማካይነት ሊገደቡ የሚችሉ ሰብዓዊ መብቶች መሆናቸውን እንዲሁም ምንም አይነት ሰብዓዊና አሰቃቂ አያያዝ (ቶርቸር) ቢኖሩም መገደብ የማይቻልባቸው ደግሞ የብሔር፣ ብሔረሰቦች መብት እስከመገንጠል የሚለው መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሕጎች በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቁትን የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌዎችን አካትቷል ተብሎ በድፍረት መናገር ይቻላል፡፡ ነገር ግን የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌዎች በሕጎች መካተትና በተግባር መፈፀም መካከል ያለውን ልዩነት ማጤንና መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ መብቶቹ በሕግ ውስጥ ተካተዋል ማለት መብቶቹ ሙሉ ለሙሉ በተግባር ውለዋል ማለት እንዳልሆነ መታወቅ ይኖርበታል፡፡

አቶ ሽመልስ በበኩላቸው እንዳብራሩት የጠቅላላው ሕዝብ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊና ማኅበራዊ ሕይወት ያለማቋረጥ የሚሻሻልበት ሁኔታ ሳይፈጠር የግለሰቦችና የቡድኖች ሰብዓዊ መብቶች የተሟላ አፈፃፀም ዋስትና ሊያገኝ አይችልም፡፡

ከዚህ አኳያ ለመገናኛ ብዙሃን ተቋማት የተሰጠው ነፃነት ከሌሎች መሰረታዊ ጥቅሞችና ነፃነቶች ጋር በማይጋጭ መልኩ መተግበር ይገባዋል፡፡ የፕሬስ ነፃነትም ፍፁምና ወሰን አልባ ሳይሆን ሌሎች ሕጋዊ ጥቅሞችንና መብቶችን በማይጋፋ መንገድ ብቻ መተግበር ይኖርበታል፡፡

ወይዘሮ የሺሀረግ ዳምጤ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የሕፃናት፣ የሴቶችና የአካል ጉዳተኞች ኮሚሽነር በበኩላቸው እንዳመለከቱት የመገናኛ ብዙሃን የሰብዓዊ መብት ተከራካሪና ጠበቃ ከሚባሉት ውስጥ ይመደባሉ፡፡ ይህም ኅብረተሰቡ የሰብዓዊ መበት ጥበቃን በተመለከተ ተገቢውን መረጃ እንዲያገኝና ሐሳቡንም እንዲገልጽ ከማድረግ አኳያ ከፍተኛ ሚና ስለሚጫወቱ ነው፡፡

የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ስለፀደቁ ወይም ስለተፈረሙ ብቻ ተፈፃሚ ይሆናሉ ማለት አይደለም፡፡ የመንግስት ቁርጠኝነት የሚገለፀው ስምምነቶችን በማጽደቅ ብቻ ሳይሆን መርሆዎች ተፈፃሚ እንዲሆኑና በሴቶች ላይ የሚደረግ ልዩነትን ለማጥፋት የሚያስችሉ ሕጎችና ፖሊሲዎች አውጥተው መተግበር ሲችሉ፣ እንዲሁም ነባር ሕጎችና ፖሊሲዎችን ከዚህ አኳያ ቃኝተው ማሻሻልና ለአፈፃፀሙ የሚረዳ ተቋማዊ አደረጃጀት ሲኖር ነው፡፡

በኢኮኖሚው፣ በማኅበራዊውና ፖለቲካዊ መስኮች አድሎአዊ ልዩነትን ለማስወገድ ለውጦችን የሚያመጡ ሕጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃዎች መፈፀም እንደሚገባ ኮሚሽነሯ ጠቁመው፣ ምንም እንኳን ለሴቶች ሕጋዊ እኩልነት ቢደረግም ይህ በቀጥታ በተግባር ተተርጉሞ በእኩልነት ይታያሉ ለማለት እንደሚያስቸግርና የተከበሩላቸውን መብቶች በተሟላ ሁኔታ እንዲረጋገጥላቸው እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል፡፡

ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ቢደረግም ቀደም ሲል የነበረውን ክፍተት በተለየ ሁኔታ ማጥበብ ካልተቻለ እኩልነትን ማምጣት ብቻ ሳይሆን እኩልነት የሚያስጠብቅ ሕጎችን በተሟላ ሁኔታ ተግባራዊ ማድረግ አይቻልም፡፡ ስለሆነም የሴቶችን እኩልነት በማኅበረሰብም ሆነ በሥራ ቦታ በተጨባጭ ለማረጋገጥ መንግስታት የተለየ ማካካሻ እርምጃ መውሰድ ይኖርባቸዋል፡፡

አቶ ደመወዜ ማሜ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር የዜጎች ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ በሚደረገው እንቅስቃሴ ከጋዜጠኞችና ከመገናኛ ብዙሃን ቅንነትና ኃላፊነት እንደሚጠበቅ አስገንዝበዋል፡፡ ሰብዓዊ መብቶችን የማክበርና የማስከበር ጉዳይ ሰኬታማ የሚሆነው ከጥላቻ፣ አንድን ወገን ከማጥቃትና ከግላዊ የፖለቲካ ጥቅም በፀዳ መልኩ መንቀሳቀስ ሲቻል መሆኑንም አውስተዋል፡፡

በአዳማ ፓላስ ሆቴል በተካሄደው በዚሁ የሥልጠና ፕሮግራም ላይ ሰብዓዊ መብት በማክበርና በማስከበር ረገድ የመገናኛ ብዙሃን ሚና ከሌሎች አገሮች ተሞክሮ አንፃር፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ዓላማና ተግባር በሚሉና በሌሎች ተዛማጅ ርዕሶች ላይ ያተኮሩ ውይይቶችና ገለፃዎች ተደርገዋል፡፡

በታደሰ ገብርማርያም

 
< Prev   Next >