Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
Jul 20th
Home arrow Sections arrow የአሹራ በዓል...
የአሹራ በዓል... Print E-mail
Sunday, 13 January 2008

የአሹራ በዓል በነጃሽ ይከበራል

የሙስሊሞች የዘመን መለወጫ በገባ በአስረኛው ቀን የሚከበረው አሹራ በነጃሽ ከተማ እንደሚከበር በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጽ/ቤት የኢትዮጵያ ሚሌኒየም በዓል አከባበር ኮሚቴ አስታውቋል፡፡

ኮሚቴው በብሔራዊ ሚሌኒየም በዓል አከባበር ጽ/ቤት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቀው በሒጅራ አቆጣጠር ዘንድሮ 1429ኛው ዓመት ሲሆን ዓመቱ በባተ በአስረኛው ቀን የሚከበረው አሹራ የፊታችን ጥር ዘጠኝ ቀን በነጃሽ እንዲከበር ተወስኗል፡፡

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ምክትል ሊቀ መንበር ሼህ ኤልያስ ሬድዋን እንደተናገሩት ነቢዩ መሀመድ በሃዲስ በሰጡት ቃል መሠረት በየጊዜው በዓሉን የእስልምና እምነት ተከታዮች መውሊድ በመደገስ፣ በፆም፣ ከሰዎች ጋር በመረዳዳትና በተለያየ ሁኔታ ያከብሩታል፡፡

ወትሮም ቢሆን በነጃሽ ከተማ ለብዙ ዓመት ይከበር የነበረው በመውሊድ በመሆኑ ይህንን በመንተራስ በፌዴራል ደረጃ በዓሉን ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ሚሌኒየም በዓል አከባበር ጽ/ቤት፣ ከትግራይ እስልምና ጉዳዮች ጽ/ቤትና ከትግራይ ሚሌኒየም አከባበር ጽ/ቤት ጋር በመተባበር የነጃሽ ግንባታ ኮሚቴ ተቋቁሟል ያሉት ሼህ ኤልያስ እስልምና ለ1400 ዓመት ኢትዮጵያ ውስጥ በቆየበት ወቅት ትቶት ያለፈውን የታሪክ አሻራ ለማስተዋወቅ ይረዳል ብለዋል፡፡

ምክትል ሊቀ መንበሩ አክለውም ቁራይሾች ሙስሊሞችን ባሰቃዩበት ወቅት ነቢዩ መሀመድ ወደ አበሻ ምድር ሂዱ ባሏቸው መሠረት ወደ ኢትዮጵያ ምድር መጥተው በነጃሽ መልካም አቀባበል ተደርጐላቸዋል፡፡ በመሆኑም ቦታው በአፍሪካ ብሎም በመላው ዓለም ለሚገኙ ሙስሊሞች ትልቅ ሥፍራ አለው ብለዋል፡፡ እንደ ምክትል ሊቀመንበሩ ገለፃ ሃበሻ እንጅ ኢትዮጵያ በሚለው ቃል ውስጥ የነጃሽን ታሪክ አማኞች ስለማያውቁት የአሹራ በዓል በነጃሽ መከበር መላው ዓለም እንዲያውቀው ይረዳል፡፡ ለበዓሉ ድምቀት ከተለያዩ አገራት የሚመጡ እንግዶችን ለመቀበል አስፈላጊውን ዝግጅት እንዳደረጉም ጠቁመዋል፡፡

በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት የሚሌኒየም በዓል አከባበር ጽ/ቤት ሰብሳቢ ሃጅ ሙጅብ ሰይድ በበኩላቸው ኢትዮጵያና ነጃሽ  በሙስሊሙ ዓለም በየዕለቱ የሚወሱ መሆናቸውን ጠቁመው ነጃሽ የኢትዮጵያ ቅርስ በመሆኑ ሙስሊሙ ብቻ ሳይሆን ሌላው ኅብረተሰብም ቀና ትብብር እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የሚሌኒየም በዓል አከባበር አብይ ኮሚቴ ሰብሳቢ መሃመድ አህመድ የነጃሽ መስጊድን በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ አስፈላጊው ጥረት እየተካሄደ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በከተማውም የህክምና ማዕከላት፣ ሆቴሎችና ኮሌጆችን ለማቋቋም ታስቧል፡፡

በበዓል አከባበሩ ሥነ ሥርዓት ከተለያዩ አገራት አማኞች እንደሚመጡ የሚጠበቅ ሲሆን ከሱዳን የናይል ቴሌቪዥን ጋዜጠኞች እንደሚገኙም ታውቋል፡፡

በደመቀ ከበደ

 
< Prev   Next >