| ሥነ ጥበብ ፡ እንደ ባህል |
|
|
| Sunday, 13 January 2008 | |
|
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በሚገኘው የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም ራስ መኮንን አዳራሽ በርከት ያሉ እንግዶች ተሰባስበዋል፡፡ የአገር ውስጥና የውጭ ምሁራን፣ ታዋቂ ሰዎች፣ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና ጋዜጠኞች የአንዲት አሜሪካዊት ወ/ሮና የአንድ ሃበሻ ጎልማሳ ከፊት ለፊታቸው ሆነው በቪዲዮ የታገዘ ገለፃቸውን በተመስጦ ይከታተላሉ፡፡ ረቡዕ ታህሳስ 30 ቀን 2000 ዓ.ም፡፡
ከጥር 13 ቀን 1999 ዓ.ም እስከ ህዳር 28 ቀን 2000 ዓ.ም ድረስ በአሜሪካ ፍሎሪዳ ውስጥ "ኮንቲኒዩቲ ኤንድ ቼንጅ፣ ዘ ስሪ ጀኔሬሽንስ ኦፍ ኢትዮጵያን አርቲስትስ" በሚል የኢትዮጵያውያን ሠዓሊዎችን ሥራ ለአሜሪካ ነዋሪዎች ለማስተዋወቅ ኤግዚቢሽን ቀርቦ ነበር፡፡ የኤግዚቢሽኑ አዘጋጆች ከአሜሪካ መጥተው የሰጡት ገለፃ ነበር፣ ዝግጅቱ የተስተናበረው በኢትዮጵያ ጥናት ወዳጆች ማኅበር ነው፡፡ ኤግዚቢሽኑ የተካሄደው በፍሎሪዳ ዩኒቨርሲቲ ሃረን ሙዚየም ኦፍ አርት ውስጥ ሲሆን አዘጋጆቹ (የራስ መኮንን አዳራሹን ገለፃ ያደረጉት) የሙዚየሙ ዳይሬክተር የሆነችው ዶ/ር ርቤካ ናጅ እና በኖርዝ ካሮላይና ሴንትራል ዩኒቨርሲቲ ፕፎፌሰር በሆኑት በአቻምየለህ ደበላ አማካኝነት ነው፡፡ የ23 ኢትዮጵያውያን ሠዓሊያን ሥራዎች የቀረቡበትን ኤግዚቢሽን ለማዘጋጀት የፈለገችበትን ምክንያት ስትናገር እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1998 የእስክንድር ቦጎስያንን ሥራ ካየች በኋላ ነው፡፡ ወዲያውኑ ፕሮፌሰር አቻምየለህን አንድ ዝግጅት ማቅረብ እንዳለባት አስረዳችው፡፡ "የእስክንድር ሥራዎችን ከሱ ተከታይ ሰዓሊያን ጋር ለአሜሪካ ነዋሪዎች ብናሳይ ባህልንም ስነ ጥበብንም እናስተዋውቃለን በሚል ያጋራሁትን ሃሳቤን ደገፈው፡፡ የዕድል ነገር ሆኖ ለሱ ማዋየቴ ጠቅሞኛል፡፡ ምክንያቱም በአዲስ አበባ የሥዕል ትምህርት ቤት ውስጥ ተምሮ የወጣ፣ እዚህም የሚያስተምረው አርት ኢዱኬሽንና ኮምፒዩተር ግራፊክስ መሆኑ ለስራው መቃለል ረድቶኛል" ብላለች፡፡ ፕሮፌሰር አቻምየለህ በበኩላቸው "የእስክንድር ቦጎስያንን ሥራ በሙዚየማቸው ረሃርን ሙዚየም ኦፍ አርትሪ እንዲቀመጥ ገዝተው በእጃቸው ካስገቡ በኋላ ዶ/ር ርቤካ በኢትዮጵያዊያን ሠዓሊያንና ሥራዎች ዙሪያ መሥራት እንዳለብን አዋየችኝ፡፡ የእስክንድር ቦጎስያን አድናቂ በመሆኔና እንደ ኢትዮጵያዊም አንድ ነገር ማድረግ እንዳለብኝ ስላመንኩ ሃሳቡን ተቀበልኩ" ይላሉ፡፡ ብዙ ውይይት ካደረጉ በኋላ ጥናት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አመኑበት፡፡ በ2003 "ኢትዮጵያን አርቲስትስ ኤንድ ዲያስፖራ" በሚል በዚያው አሜሪካ ታላቅ ኤግዚቢሽን ተካሂዶ ነበር፡፡ በኤግዚቢሽኑም ከፈረንሳይ፣ ከስዊድን፣ ከእንግሊዝ፣ ከአሜሪካና ከመሳሰሉት አገሮች የተውጣጡ በውጭ የሚኖሩ አስር ኢትዮጵያውያን ሠዓሊያን ተካፍለዋል፡፡ በዚያ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄደ ስለነበረው ኪነጥበባዊ እንቅስቃሴ ጥናታዊ ጽሁፍ እንዲያቀርቡ በተጋበዙት መሠረት ፕሮፌሰር አቻምየለህ በአምሳ አመት ውስጥ በአዲስ አበባ ያለውን ኪነ-ጥበባዊ እንቅስቃሴ አጥንተው አቅርበዋል፡፡ በዚህ የተነሳም ከዶ/ር ርቤካ ጋር የሚያዘጋጁትን ኤግዚቢሽን በጥናት የተደገፈ ለማድረግ ከ2001 ጀምሮ እንቅስቃሴ ማድረግ ጀመሩ፡፡ ዶ/ር ርቤካ ለጥናት ለስድስት ጊዜ ያህል ወደ ኢትዮጵያ ተመላልሳለች፡፡ በወቅቱ ስለተሰማት ነገር ስታስረዳም "ያ መመላለሴ የበለጠ በአገሪቱ አስገራሚ ታሪክ፣ ባህልና ሥነጥበብ እንድማረክ አደረገኝ" ብላለች፡፡ ለዝግጅታቸው ደፋ ቀና በሚሉበት ወቅት የአዲስ አበባ የሥነጥበብ ት/ቤት በዩኒቨርሲቲው ሥር ለመካተት በእንቅስቃሴ ላይ ነበረና ያ አጋጣሚ ለሁለቱ አዘጋጆች ጥሩ ሆነ፡፡ ፕሮፌሰር አቻምየለህ ካሪኩለም በመንደፍ ለሥዕል ትምህርት ቤቱ እገዛ ያደረጉ ሲሆን ርቤካም በመመላለስ እግረ መንገዳቸውን ጥናት ይሰሩ ነበር፡፡ ከጥናታቸው ዋና ነጥብ አንዱ የኢትዮጵያን የሥነ ጥበብ ዕድገት ማወቅ ሲሆን ለዚህ ፍላጎታቸውም የሥዕል ትምህርት ቤቱ ዕድገት ውጤቶችን ማየት ያስፈልጋል በሚል ስለ ትምህርት ቤቱ አመሰራረት በውስጡ ስለነበሩ ችግሮችና ስለ ተማሪዎቹ አጠኑ፡፡ ኤግዚቢሽን አሳይተው "በግል ይህን ያህል ሰርቼ አምጥቻለሁ እርስዎ ይጨምሩበትና የሥዕል ትምህርት ቤት ይቋቋም ብለው አፄ ኃይለሥላሴን የጠየቁት ሠዓሊ አለ ፈለገ ሠላም በ1951 ዓ.ም ለትምህርት ቤቱ መመስረት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን የጠቆሙት ፕሮፌሰሩ ..እኔም ተምሬ ወጥቼበታለሁ፡፡ ታላላቅ ሠዓሊያንንም አፍርቷል" ብለዋል፡፡ በጥናታቸው ከተካተተው ሌላው ነጥብ ደግሞ "በውጭ ያሉ ሠዓሊያን ሥራዎቻቸውን ለተመልካች ለማቅረብ ብዙ ዕድል አላቸው፡፡ የአገር ውስጥ ሠዓሊያን ግን ዕድላቸው የጠበበ በመሆኑ ለእነሱ እድል እንስጥ" የሚል ነበር፡፡ በአገር ውስጥ ያሉ ሠዓሊያንንም በየቤታቸውና በሚገኙበት ቦታ እየሄዱ ሥራዎቻቸውን አሰባሰቡ፡፡ ውጤታማ የሆነ የአሰራር ዘዴን ተከትለዋል ተብለው የተመረጡ ሥራዎችን ይዘው ሄዱ፡፡ በዚያም መሠረት አገር ውስጥ ያሉ ሃያ የሚደርሱ ሠዓሊያንና በህይወት የሌሉ ሶስት አንጋፋ ሠዓሊያን በድምሩ ሃያ ሶስት ሠዓሊያን በሶስት ዘመን ተከፍለው በፍሎሪዳ የሃርን ሙዚየም በኖርዝ ካሮላይናና በዲግስ ጋለሪ ውስጥ ለዕይታ ቀርቧል፡፡ ፍሎሪዳ ውስጥ ከ36ሺህ በላይ የሥዕል አፍቃሪዎችና በኖርዝ ካሮላይና ደግሞ ከአስራ ስድስቱ ዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙ ተማሪዎች የጎበኙት ይህ ኤግዚቢሽን የአፄ ኃይለስላሴ፣ የደርግና ድህረ ደርግ ዘመን ሠዓሊያን በሚል የተከፋፈለ ነበር፡፡ በዘመን መከፋፈሉ የየወቅቱን የሠዓሊያን አስተሳሰብና አመለካከት አጉልቶ ለማሳየት ያለመ ሲሆን የመጀመሪያው ትውልድ (በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን) የተመደቡት በህይወት የሌሉት አገኘሁ እንግዳ፣ እስኩንድር ቦጎስያንና ገብረ ክርስቶስ ደስታ እንዲሁም በህይወት ያሉት አፈወርቅ ተክሌና አለ ፈለገ ሰላም ሲሆኑ እነዚህ በኢትዮጵያ ዘመናዊ የሥዕል ጥበብ ዕድገት ፈር ቀዳጆች ተብለዋል፡፡ በሁለተኛው ምድብ የተከፈሉት ሠዓሊያን በርከት ያለ ቁጥር ይዘዋል፡፡ በደርግ ዘመን ከፈለቁት ሠዓሊያን መካከል ደስታ ሃጎስ፣ ልዑል ሰገድ ረታ፣ ዮሐንስ ገዳሙ፣ ዘሪሁን የትምጌታ፣ ጥበበ ተርፋ፣ አብዱራህማን ሸሪፍ፣ እሸቱ ጥሩነህ፣ ታደሰ መስፍን፣ ብስራት ሺባባው፣ ጌታ መኮንን፣ በቀለ መኮንን፣ መዝገቡ ተሰማ፣ በሃይሉ በዛብህ፣ አዲሱ ወርቁና ኤልሳቤጥ ሃብተወልድ ተጠቅሰዋል፡፡ በዚህ ምድብ የተቀመጡት በግላቸው የሚስሉና በአዲስ አበባ የሥዕል ት/ቤት መምህር ሆነው እያገለገሉ ያሉ በማለት ይገልጿቸዋል፡፡ በሶስተኛው ምድብ በድህረ ደርግ ዘመን ብቅ ያሉ ሠዓሊያን ተብለው ለኤግዚቢሽኑ የተመረጡት ጥቂት ናቸው፡፡ ኤልያስ ስሜ፣ ገዛኸኝና ተስፋሁን ክብሩ ሲሆኑ በሥዕላቸው ውስጥ ከሁለቱ ዘመን በተሻለ አንፃራዊ ነፃነት ይንፀባረቅበታል ተብሏል፡፡ ከላይ በቀረበው ዝርዝር መሠረት የአንድ ዓመቱ የሥዕል ኤግዚቢሽን በተሳካ ሁኔታ እንደተካሄደ የጠቆሙት አዘጋጆቹ ተመልካቹ ከመደሰቱ ባሻገር ስለ ኢትዮጵያ ያለውን ግንዛቤ እንዲያሰፋም አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ "ሥነጥበብ እንደ ባህል አምባሳደር የሆነበት ኤግዚቢሽን ነበር" ሲሉ ገልፀውታል ፕሮፌሰር አቻምየለህ፡፡ ለኤግዚቢሽኑ ዓላማ መሳካት ትልቁ አስተዋጽኦ ደግሞ በተለያዩ ሰዎች የተለያየ ጥናታዊ ጽሁፍ መቅረቡ ነው፡፡ ፕሮፌሰር አቻምየለህ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን የሥነጥበብ ትምህርት ቤት ዕድገት፣ ዶ/ር ሄራን ሠረቀ ብርሃንና አቶ ሽፈራው በቀለ ከደርግ በፊት የነበረውን የኪነጥበብ እንቅስቃሴ፣ ሠዓሊ ጌታ መኮንን የደርግ ዘመንን የኪነ ጥበብ እሳቦት፣ ዶ/ር ርቤካ ናጅ የአሁኑን ዘመን ኪነ ጥበባዊ እንቅስቃሴ በተለይ በሥዕል ዘርፍ፣ ሊያ ኔደርስታድ ደግሞ የወጣቶቹን የሥዕል ህይወት በጥናታቸው አቅርበዋል፡፡ ይህም ስለ ኢትዮጵያ የሥነ ጥበብ እንቅስቃሴ የተዛባ አመለካከት ያላቸውን ሁሉ እይታቸውን እንዲቀይሩ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ዶ/ር ርቤካ እንደተናገረችው ከሌሎች የአፍሪካ አገራት በተሻለ ለኢትዮጵያውያን ሥራዎች ጥሩ አድናቆት እንዳላቸው የገለፁት በርካታ ተመልካቾች አጋጥሟታል፡፡ "ከየትኛውም ዓለም ያልተናነሰ መስራት የሚችሉ ኢትዮጵያውያን ሠዓሊያንና ቀራፂያን እንዳሉን አሳይተናል" ሲሉ ፕሮፌሰር አቻምየለህ አክለዋል፡፡ ከስዕል ሥራዎችና ከጥናታዊ ጽሁፎች በተጨማሪ በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ሁኔታ በፊልም ኢንዱስትሪው ውስጥ እየተቀላቀሉ ካሉ ጥቂት ጥቁር ሴቶች ቀዳሚውን ሥፍራ የያዘችውና የዋሌሰሌይ ኮሌጅ ፕሮፌሰር የሆነችው ሳሌም መኩሪያ "ኢሜጅንግ ጦቢያ" የተሰኘ የቪዲዮ ሥዕል አንዱ ነበር፡፡ ይህም የኢትዮጵያን መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ፣ የሕዝብ ኑሮና ባህል ለማሳየት ጉልህ ሚና የተጫወተ እንደነበር ፕሮፌሰር አቻምየለህ ገልፀውልናል፡፡ በውጭው ዓለም የኢትዮጵያን ስም ለመለወጥና እንደዚህ ያሉ ኤግዚቢሽኖችን ለማዘጋጀት በአገሪቱ ውስጥ ዘመናዊ የሥዕል ማሳያ ቦታዎች (ጋለሪዎች) ቢስፋፉ፣ የሥዕል መሳያ ቁሳቁሶች ማቅረቢያ ቦታዎች (ሱቆች) ቢበራከቱ፣ ባለሃብቶች የሥዕል ንግድን እንደ ቢዝነስ ቆጥረው ኢንቨስት ቢያደርጉ፣ የሥነጥበብ ትምህርት ቤቱም የመቀበል አቅሙን ቢያሰፋና የግል የሥዕል ትምህርት ቤቶችም ቢጎለብቱ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የኢትዮጵያዊን ሠዓሊያን ሥራዎች ተፈላጊነታቸው ይጨምራል ብለዋል፡፡ በደመቀ ከበደ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |