| የመረጃ ቋት ለቅርሶች |
|
|
| Sunday, 13 January 2008 | |
|
ቅርሶች በሀገራዊ ዘላቂ ልማት ውስጥ ትርጉም ያለው ሥራ እንዲኖራቸው ለማድረግ በማዕከልና በክልል ዋና ከተሞች የመረጃ ቋት (ዳታ ቤዝ) የመገንባቱ ሥራ እየተገባደደ መሆኑን የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን አስታወቋት፡፡
በባለ ሥልጣኑ የዓለም አቀፍ ሕዝብ ግንኙነት አስተባባሪ አቶ ካሣሁን አባተ ለሪፖርተር ጋዜጣ እንደገለፁት ከዓለም ባንክ በተገኘ ድጋፍ እየተሠራ ያለው የመረጃ ቋት ዋናው ሰርቨር በአዲስ አበባ ሆኖ በመረጃ መረብ (ኔት ወርክ) ባሕርዳር፣ ጎንደር፣ አክሱም፣ መቀሌና ሐረር ይገናኛል፡፡ ቅርሶቹን በሳይንሳዊ መንገድ የመመዝገብ ሥራው ምልዐት ያለው እንዲሆን ለማስቻል የተሠሩበት ዘመንና ያሉበት ሁኔታ በሚያሳይ መልኩ ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያ በርካታ ቅርሶች በዓይነትም ሆነ በብዛት ቢኖሯትም የተሟላ መረጃ ባለመኖሩ የሚታወቁት ዋናዎቹ እነላሊበላ፣ አክሱም፣ ጎንደር፣ ሶፍ ዑመር ወዘተ. ዓይነቶቹ መሆናቸው ያወሱት አቶ ካሳሁን፣ በአዲሱ የመረጃ ቋት አማካይነት ማንም ስለአገሩ ቅርስ ለማወቅ በቀላሉ መረጃ የሚያገኝበት ሁኔታ እውን እንደሚሆን አስረድተዋል፡፡ እንደ አሰተባባሪው ማብራሪያ መረጃዎቹ የሚጫኑበት ሥርዓት ከተከናወነ በኋላ የሚቀጥለው መረጃዎቹን ተጠቃሚዎች ወደሚያገኙበት ቅርጽ (ፎርማት) መቀየር ነው፡፡ በኢንተርኔት ጉግል ውስጥ ገብቶ መረጃ እንደሚገኘው ሁሉ በአዲስ አበባና በተጠቀሱት የክልል ከተሞች ተጠቃሚዎች የሚፈልጉትን መረጃ ማግኘት ይቻላቸዋል፡፡ በኢትዮጵያ ባህላዊ ቅርሶች ፕሮጀክት አስተባባሪነት እየተመራ ያለው የመረጃ ቋት ተግባር በአዲስ አበባና በባሕርዳር ሥራውን የጀመረ መሆኑን የገለፁት አቶ ካሳሁን ለመረጃው ደህንነት "ዌብ ሴኩሪቲ ፖሊሲ" እንደሚዘጋጅለት ጠቁመዋል፡፡ በየክልል ከተሞች ያሉት የመረጃ ማዕከላት የየአካባቢያቸውን የቅርስ መረጃዎች ሁሉ ይጭናሉ፡፡ በቋቱ ውስጥ ከግዙፍ ቅርሶች ሌላ ወደ ሁለት ሺህ ዓመታት የሚጠጋውን የአገሪቱ የሥነ ጽሑፍና የሥነ ጽሕፈት ሀብት በተለይም ስለብራና መጻሕፍት የሚዘረዝሩ መረጃዎች በጥልቀት እንደሚኖረውና መረጃው ለጥናትና ምርምር በዘርፉ በተለያየ ደረጃ ለሚያጠኑ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚሰጥ አስተባባሪው አውስተዋል፡፡ የመረጃ ቋቱን (ዳታ ቤዝ) ለመሥራት ሲነሳ ተቋሙ መጀመሪያ ያከናወነው የቅርሶችን ነባራዊ ሁኔታ ያሉትን፣ የተቆነፃፀሉትንና የተሰረቁትን በየቦታው ለማየት መሞከሩንም ጠቅሰዋል፡፡ በየገዳማቱና አድባራቱ በርካታ ቅርሶችን በማሰባሰብና በመንከባከብ ለአገሪቱ ቅርስ ባለውለታ የሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅርሶቹን በዘመናዊ ሥርዓት እንዲጠበቁ ለማድረግ ሥልጠና መስጠት አስፈላጊነቱን የገለፁት አስተባባሪው በአማራ ክልል ለቅኝት በተዘዋወሩበት ጊዜ ያጋጠማቸውን አመልክተዋል፡፡ የየገዳማቱ ገበዞች ከቅርስ ቤቱ ሳይወጡ እየጠበቁ መኖራቸው ለጥበቃው የረዳ ቢሆንም በቅርሶቹ ሀብት አለመጠቀማቸው ጎልቶ እንደሚታይ የሚናገሩት አቶ ካሳሁን ከሌባ ለመጠበቅ በአብዛኛው መሬት ውስጥ ቀብሮ የማስቀመጥ ሁኔታ በመኖሩ ቅርሱ እርጥበት እንዲያገኘውና በምስጥም እንዲበላ ምክንያት መፍጠሩንና በዘመናዊ አቅድ በተሠሩ መደርደሪያዎች በማስቀመጥ ቱሪስቶች እንዲያዩት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ጠቁመዋል፡፡ በሔኖክ ያሬድ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |