Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Friday
Aug 29th
Home arrow Sections arrow ለትምህርት ጥራት ቅድሚያ
ለትምህርት ጥራት ቅድሚያ Print E-mail
Sunday, 22 June 2008
የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን በተመለከተ በማኀበራዊ ገጽ ሰኔ 8 ቀን 2ዐዐዐ የወጣውን ጽሑፍ ተመልክቼዋለሁ፡፡ የግሉ የትምህርት ተቋማት አሠራራቸውን አስተካክለው ጥራት ያለው ትምህርት ሊሰጡ ይገባል፡፡ በዚህም ሳይወሰኑ ከሰርተፊኬት እስከ ዲግሪ ብሎም እስከ ድህረ ምረቃ አድገው ተወዳዳሪነታቸውን ማስመስከር ይኖርባቸዋል፡፡
በነፃ ገበያው በመወዳደር ነጥሮ መውጣት የሚቻለው ከብዛት ይልቅ ጥራት ላይ ሲተኮር ነው፡፡ ኘሮፌሰር እሸቱ ወንጨቆ እንዳሉትም የትምህርት ጥራትን ለማምጣት ብዙ ካፒታል ይጠይቃል፤ ገንዘቡም በአጭር ጊዜ ላይመለስ ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ በትምህርት ወደ ኋላ ቀርታለች ለምትባለው ኢትዮጵያ የተሻለ ዜጋን ለመፍጠር ሁላችንም ኃላፊነት አለብን፡፡

መንግሥትም በየጊዜው እየጨመረ ከመጣው የሕዝብ ብዛት አንፃር የትምህርት ተቋማት ያላመመጣጠንን የሚያስተካክለው በመጠኑም ቢሆን በግሉ ዘርፍ ሥራዎች እንዲሰሩ ሲያደርግ ነው፡፡ ስለሆነም እጅ ለእጅ ተያይዞ መሥራት ይገባል፡፡

(ዓይናለም ታፈሰ፣ ከቤላ)

ጥያቄዎችን ግልፅ ያደርጋል

በእሑዱ ሪፖርተር ጋዜጣ ቆይታ ገጽ ላይ ከቀድሞ የደርግ ባለሥልጣናት ጠበቆች አንዱን አቶ አበበ ወርቄን በማነጋገር የወጣው ቃለ ምልልስ የባለሥልጣናቱን የክስ ሒደትና የመጨረሻ የፍርድ ውሳኔን በማስመልከት ከሠራችኋቸው ዘገባዎች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አለው፡፡ የክሱን አመሠራረትና የፍርድ ውሳኔውን በሚመለከት ሊነሱ የሚችሉ በርካታ ጥያቄዎችን ግልፅ አድርጎልኛል፡፡

(ቃለአብ አበበ፣ ከሽሮ ሜዳ)

ለሕገ መንግሥቱ ጥበቃ

ባለፈው ሳምንት በወጣው የእሑድ ሪፖርተር ጋዜጣ አንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ በኢምፔሪያል ሆቴል የጠራው ስብሰባ እንዳይካሄድ መከልከሉን አነበብኩ፡፡ በዜናው ላይ የአዲሱ ፓርቲ አደራጅ ኮሚቴዎች ለቤት ውስጥ ስብሰባ ማስፈቀድ እንደማይገባቸው የሰጡትን አስተያየት ተመልክቻለሁ፡፡ የመሰብሰብና የመደራጀት መብት ሕገ መንግሥታዊ ነው፡፡ ገዢው ፓርቲ ሲፈልግ የሚፈቅደው፣ ሳይፈልግ የሚከለክለው እንዳይሆን አስቀድሞ ታስቦ ነው ሕገ መንግሥታዊ ጥበቃ የተሰጠው፡፡ በአደባባይ ለሚደረግ ስብሰባ ማስፈቀድ እንደሚያስፈልግ ታሳቢ ሆኖ በአዲስ አበባ ከተማ ራሱን የቻለ ቢሮ መኖሩ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ለመሰብሰብ ለፀጥታ ሲባል “ማሳወቅ” ካልሆነ በስተቀር “ማስፈቀድ” ኢ ሕገ መንግሥታዊ ነው፡፡ የቤት ውስጥ ስብሰባ ፈቃድ ያስፈልገዋል የተባለውም የሕግ ድጋፍ የለውም፡፡ ስለዚህ በትንሽ በትልቁ ተቃዋሚዎች ስለሆኑ ብቻ እንቅስቃሴያቸው ለማወክ ከመሞከር ይልቅ መደራጀታቸው ይጠቅመኛል በሚል በጎ አስተሳሰብ ቢያዝ ለአገሪቱ ዴሞክራሲ ማበብ የበኩሉን አስተዋፅኦ ያደርጋል፡፡ ገዢው ፓርቲ ሕገ መንግሥቱን አክብሮ ማስከበር ይኖርበታል፡፡

(ሰለሞን አንተነህና በለጠ ይመር፣ ከአዲስ አበባ)

አርሶ አደሩ እንዳይዘነጋ

ኢሕአዴግ ኢትዮጵያን ከተቆጣጠረ ጀምሮ በተደጋጋሚ የሚገልፀው “ለአርሶ አደሩ ቆሜያለሁ” ማለቱን ነው፡፡ ኢሕአዴግ ለአርሶ አደሩ ቆሜያለሁ እንደማለቱ የአርሶ አደሩ ህይወት ተለውጧል ወይ? ሀገሪቱ በኢሕአዴግ አስተዳደር ሥር ከዋለች ወዲህ ከዘንድሮው ጋር ለሁለተኛ ጊዜ በከፍተኛ ድርቅና የምግብ ችግር ተጠቅታለች፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የተለያዩ የኢኮኖሚክስ ተመራማሪዎች የአርሶ አደሩ የመሬት ይዞታ ጥበት እንዲሁም የነፍስ ወከፍ የግብርና ምርት ከእለት እለት እየቀነሰ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ከዚህ አንፃር ብዙ የቤት ሥራዎች አሉበት፡፡ አደገ የሚለው ሪፖርት ሳያዘናጋው የተፈጠሩ ችግሮችን ለማስወገድ መሥራት ጊዜ የማይሰጠው ነው፡፡

(ትህትና አበበ፣ ከቤተል)

ግልጽነት ይጎድለዋል


ሰኔ 1/2ዐዐዐ ዓ.ም. ታትሞ በወጣው ሪፖርተር ጋዜጣ የኘራቬታይዜሽንና የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪውን ዘርፍ በሚመለከት ግልጽ የሆነ መልስ አልሰጡም፡፡

በመግለጫው ላይ ዳይሬክተሩ የድሬዳዋ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ “ማኔጅመንቱ” ወደ “ግል” ከተዛወረ ወዲህ ከቀድሞው በተሻለ ሁኔታ ላይ እንዳለ ገልፀዋል፡፡ ከቀድሞ ሲባል ከየትኛው አነጻጽረውት ነው? ፋብሪካው በ198ዐዎቹ መጀመሪያ አሁን ካለበት የተሻለ ደረጃ ላይ እንደነበር ሳይገነዘቡ የቀሩ አይመስለኝም፡፡ ዛሬ ከጨርቅ አምራችነት ለምን ወደ ኋላ ወደ ክር አምራችነት ሄደ? በሌላ በኩል የአዋሳ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ሐምሌ 1/1997 ወደ ሊዝ ኪራይ ለሦስት ዓመት ሲዛወር በወቅቱ በፋብሪካው ተገኝተው ለሠራተኞች በሰጡት መግለጫ የተከራዩን የሥራ እንቅስቃሴ በየጊዜው እየተገኙ እንደሚከታተሉ ከመጠቆማቸውም በላይ ተከራዩም ፋብሪካውን ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያሳድግ የቦርዱ ሰብሳቢም ገልፀዋል፡፡ ሆኖም ግን ፋብሪካው ውድቀት እያንዣበበት ስለሆነ በፋብሪካው ተገኝተው የሥራ እንቅስቃሴውን ሳይመለከቱ ለምን ይህን ያህል ዓመት ዘገዩ?

የአርባ ምንጭ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ በተሻለ ሁኔታ ላይ እንዳለ ጠቅሰዋል፡፡ ለመሆኑ ቀደም ሲል የሸሚዝና የፖሊስተር ጨርቅ በሙሉ አቅም እያመረተ ዛሬ ግን የሽመና መሳሪያዎች በመለዋወጫ እቃ እጥረት ምክንያት 50 በመቶ ቆመው ቀሪዎቹ አቡጀዲ ስላመረቱ ነው የተሻሻለው? በሊዝ ኪራይ የተሰጡ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች በከፍተኛ ሁኔታ ምርታቸው አሽቆልቁሎ በሥራ ማስኬጃ እጥረት ተቸግረው እያለ የዳይሬክተሩ መግለጫ ለምን ይህንን አድበስብሶት አለፈ?

(ማቲዎስ ሸመሎ፣ ከአዋሣ)

ቀጣና ጠቃሚ ነው

የአዲስ አበባን የትራንስፖርት እጥረት ይቀርፋሉ ተብለው ከውጭ የገቡት 27 መቀመጫ ያላቸው ተሽከርካሪዎች ሙሉ በሙሉ ችግሩን ባይቀርፉም በመጠኑ ተንፈስ እያደረጉት ነው፡፡ ይሁን እንጂ በመነሻና በመድረሻዎች ቆመው የሚጭኑበትና የሚያወርዱበት አጥተው ሲጨናነቁ ይታያል፡፡

መገናኛ ያለው ቦታ ለተወሰኑ መኪኖች የተዘጋጀ ነው፡፡ በዚሁ አካባቢ ግራና ቀኝ ባዶ ሰፊ ቦታ አለ፡፡ ለማስታወቂያ ብረቶች መትከያና ለሕገ ወጥ ንግድ መገልገያ የሆነው ይህን ቦታ የሚመለከተው ክፍል ትኩረት ሊሰጥበት ያስፈልጋል፡፡

ጭንቅንቁ በለገሃር አካባቢም ይስተዋላል፡፡ ይህንንም የአሸዋ መኪኖችን ትርምሱን ለማስወገድና  አገልግሎቱን ለማስተካከል፣ ለባለታክሲዎች ገቢም ሆነ ለተገልጋዩ ሕዝብ ጠቀሜታ ታክሲዎችን በቀጣና ማሠማራት መፍትሄ ነው፡፡ ይህ ከሆነ በመጠኑም ቢሆን ህብረተሰቡ ከግፊያና ከእንግልት ይድናል፡፡ ቀጣና ከዚህ ቀደም ይሰራበት ስለነበር ጠቃሚ እንጂ ጐጂ አይሆንም፡፡

(ቁምላቸው መላኩ፣ ከመገናኛ)

 
< Prev   Next >